ክቡር ሆይ፣ እንግዲህ ችግራችንን ዘርዝሬ ላልጨርሰው በዚህ ይብቃኝ፡፡ እርስዎንም ከጭንቀት ያውጣዎ! ከስኳርና ከግፊት፣ ከኩላሊትና ከመሳሰሉት አምላክ ይጠብቅዎ! አደራ የምልዎት ግን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትም መልእክቴን ያድርሱልኝ፡፡ በተለይ ለመከላከያ ሚኒስትሩ አጠንክረው ይንገሩልኝ!

አንቱዬ፣ በሕይወት ያለነውምኮ በእርሱ ቸርነት ብቻ ነው!

ክቡር ሆይ፣ ባለፈው ሳምንት በአንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግርና አስደንጋጭ የጤና መረጃ አደመጥሁት፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ የጤና ባለሙያ ስላልሆንሁ ማኅበረሰባችን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ በእርግጠኝነት አላውቅም ነበር፡፡ ምን አለፋዎት ኧረ የእኔንም ጤና በሚገባ አላውቅም፡፡ ያው አንድ ቀን ስኳር ወይ ኩላሊት ሲጥለኝ ወደጤና ተቋም እሄድና ቁርጤን ይነግሩኛል፡፡

ክቡር ሆይ፣ እንደሰማሁዎት በሀገራችን ከተላላፊ በሽታዎች ይልቅ ተላላፊ ያልሆኑት በይበልጥ እየጎዱን ይገኛሉ፡፡ ተላላፊዎችንማ ተባብረን ድል ነስተናቸው ነበር፡፡ ያለልቻልናቸው ተላላፊ ያልሆኑትን ነው፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ ወራሪን (ወረርሽኝን) የማጥፋት ችግር የለብንም፡፡ ሳንነቃ የምንጠቃው ግን ወረርሽኝ ባልሆኑት ነው፡፡ እርስዎ እንዳሉት በተለይ የኩላሊትና የስኳር ሕመሞች ለማኅበረሰባችን ዋነኛ ጠንቆች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ያስገረመኝ ግን መንሥኤ ብለው የጠቀሱት ነገር ነው፡፡ በንግግርዎ ለበሽታዎቹ ዋና መንሥኤ ጭንቀት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም ትክክል ነዎት፡፡

ፕሮፍ፣ እንዳሉት ያለነው በጭንቀት ላይ ስለሆነ የጠቀሷቸው በሽታዎች ቢበዙ አያስገርምም፡፡ እስኪ ያስቡትማ! ስለምንበላው እናስባለን፤ ስለምንለብሰው እናስባለን፡፡ ስለመኖሪያችን እናስባለን፤ ስለልጆቻችን ትምህርት እናስባለን፡፡ ማሰብባ ተገቢ ነው፤ እንጨነቃለን! ከሁሉም በላይ ስለደኅንነታችን እንጨነቃለን፡፡ ዛሬ ዛሬ ሰው ለአንድ ጉዳይ ከቤቱ ወጥቶ በሰላም መመለሱን መተማመን አቅቶታል፡፡ ይህ ቢሆን አይደል ባለፈው ጊዜ “ሀገር ሰላም ነው” ብለው የተቀመጡ ወገኖቻችን “በስህተት በተተኮሰ” ጥይት ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ታዲያ እንዴት ብለን ከጭንቀት እንወጣለን? እነዚያ የጠቀሷቸው በሽታዎችስ እንዴት ብለው ሊጠፉ ይችላሉ? በዚህ ሁኔታስ ለደኅንነታችን ከለላ ይሆናል ያልነው መንግሥት ራሱ የጭንቀት መንሥኤ ሲሆን አያስጨንቅም?

ክቡር ሆይ፣ አሁንም እባክዎ ያስቡበት! በፓርላማ ስትሰበሰቡ ተነጋገሩበት፡፡ እርስዎ እንደጠቀሱት መፍትሔው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናው መፍትሔ የአእምሮ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፡፡ በጎ ማሰብ፤ በጎ ነገርን ተስፋ ማድረግ፤ በጎ መሥራት! ይህ በሌለበት ከባቢ እየኖሩ የአካል እንቅስቃሴን እንደመፍትሔ መስጠት ነባራዊውን ሁኔታ አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ የምር!

ክቡር ሆይ፣ እርስዎ ባሉበት አዲስ አበባ ለዚህ የአካላዊ እንቅስቃሴ አመቺ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንዶች ለራሳቸው ይህን የአካል እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ድርጅት ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ሰፊ የመኖሪያ ግቢ ማግኘትምኮ አንድ ነገር ነው፡፡ እኛ ግን ከጭንቀታችን ለማገገም የአካል እንቅስቃሴ እናድርግ ብንል እንኳ ከዚያው ከተፈጥሮ ሜዳ ውጭ አማራጭ የለንም፡፡ ያውም ከሊዝ ሽያጭ የተረፈ ቦታ ቢገኝ ነው! በዚያም በተረፈው መሬት እንቅስቃሴ ለማድረግ ስንወጣ ማን አብሮን እንደሚወጣ ስለማናውቅ እንጨነቃለን፡፡ “በስህተት” ሌላ አካልም አብሮን ቢወጣስ?

ክቡር ሆይ፣ እባክዎ! ስኳር፣ ግፊት፣ ኩላሊት፣ ወዘተርፈ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዲቀንሱ የኑሮ ጫና ይቀንስልን! ይህን ማድረግ ደግሞ በዋናነት የመንግሥት ኃላፊዎች ሥራ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች ነጋዴ በሆኑበት እንደኛ ባለ ሀገር ጭንቀት ወለድ በሽታዎች ቢበዙ ሊደንቀን አይገባም፡፡ በሕይወት ያለነውምኮ በአምላክ ቸርነት ብቻ ነው! እንጂማ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ሠራተኞች (ኃላፊዎችን ጨምሮ) ሌላ የጭንቀት መንሥኤዎች ሆነውብናል፡፡ እኛ ሥርዓት ባለው መንገድ ለመገልገል ተሰልፈን የሥጋ ዘመዶቻቸው በጓሮ በር ይገባሉ፡፡ “ተዉ!” ብለን ስንሟገት ደግሞ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አሸባሪ፣ ነገረኛ፣ አካባጅ፣ ያልገባው፣ ወዘተ ይሉናል፡፡ እንደዜጋ መብትን መጠየቅ ይህን ስም የሚያሰጥ ከሆነ ጭንቀት እንዴት ይቀራል? ስኳርና ደም ግፊትስ እንዴት ይጠፋሉ? በየትኛውም ደረጃ ለሰላም መስፈን መፍትሔው ዜጋው ወንጀል እንዳይሠራ ማስተማር እንጂ ዘመናዊ እስር ቤቶችን መገንባት አይደለም፡፡

ክቡር ሆይ፣ ይገርምዎታል! በቀድሞ ዘመናት የተጨነቀ ሰው ረፍት የሚያገኘው አምልኮ ወደሚፈጽምባቸው የሃይማኖት ተቋማት በመሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን እንርሱም ያው ሆነዋል፡፡ አሁን አሁን ወደእነርሱ መሄድ ከመጥበሻው ወደእሳቱ (From the frying pan into the fire) መግባት መስሏል፡፡ እነርሱም ያው ሆኑ፡፡ ጭንቀት ያሽላሉ የተባሉት ሌላ የጭንቀት መንሥኤዎች ሆነው አረፉት፡፡ “ልዝብ ቀንበር፣ ቀላል ሸክም” አላቸው የተባሉት ዛዝላ የሚያሸክሙ ሆነው አረፉት፡፡ አንቱዬ፣ ምን ይሻላል? ለማንኛውም እርስዎን ብቻ ወቀሳ አበዛሁብዎት መሰለኝ፡፡ ይቅርታ! ከጭንቀቴ የተነሣ ነው፡፡ እንዲያው በዚያ ስብሰባ ምክንያት ተናግረው አናገሩኝ፡፡

ክቡር ሆይ፣ እንዲያው ፈረድህ አይበሉኝ እንጂ ሕዝቡምኮ ሕዝብ አይደለም፡፡ በእናንተ የተበላሸ አስተዳደር እያመካኘ በየደረጃው ግፍ የሚሠራውኮ ሌላ የጭንቀት ምንጭ ነው፡፡ ነጋዴ የሚባለው ክፍል እናንተ የምትፈጥሩትን አለመረጋጋት ምክንያት ያደርግና በመቶ ብር የገዛውን ዕቃ አንዳች እሴት ሳይጨምርበት በሁለትና ሦስት እጥፍ አሳድጎ ይሸጠዋል፡፡ “ለምን?” ብለው ሲጠይቁ ደግሞ “ከፈለግህ ግዛ፤ ካልፈለግህ አትጨቅጭቀኝ! ያስገደደህ ስለሌለ መተው ትችላለህ!” ይልዎታል፡፡ አሁን ይህ መልስ የሀገር ወዳድ ዜጋ መልስ ነው? አሁን ይህ የሃይማኖተኛ ሰው መልስ ነው? እስኪ በሞቴ ያስቡት! ያ ሰው ያለው ቤተሰብስ በቤቱ የሚያተዳድራቸው ብቻ ናቸው? እኅት፣ ወንድም፣ አክስት፣ አጎት፣ ሌላም ወገኔ የሚለው በሌላ ቦታ የለውም? እርሱ ባደረገው ክፉ መንገድ እነዚያም እንደሚደረግባቸው ማሰብ ለምን ተሳነው? አንቱ፣ ይገርምዎታል! ለምን ሰው ሲታመም ብቻ ለመርዳት ገንዘብ እናዋጣለን? ለምን መጀመሪያ እንዳይታመም ማድረግ አልቻልንም?

ክቡር ሆይ፣ እንግዲህ ችግራችንን ዘርዝሬ ላልጨርሰው በዚህ ይብቃኝ፡፡ እርስዎንም ከጭንቀት ያውጣዎ! ከስኳርና ከግፊት፣ ከኩላሊትና ከመሳሰሉት አምላክ ይጠብቅዎ! አደራ የምልዎት ግን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትም መልእክቴን ያድርሱልኝ፡፡ በተለይ ለመከላከያ ሚኒስትሩ አጠንክረው ይንገሩልኝ!

ስጋትና ጭንቀት ምክንያት ሆነው ካላስተኙን ደግመን በሌላ ደብዳቤ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቀጣዩ ደብዳቤዬ ግን የምስጋና እንደሚሆንም አምናለሁ፡፡ ደኅና ይሁኑ፤ እኛም ደኅና እንሁን! ደግ ደጉን ያስመልክተን፤ አሜን!

መጋቢት 10/2010 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *