“Our true nationality is mankind.”H.G.

"በለው እያሉ ሲገድሉ ነበር፤ አስር አስከሬን አይቻለሁ፤ ይህ በስህተት ነው? "

ስሜቷን መቆጣጠር ያቃታት ሴት ትናገራለች። ” በለው” እያሉ ሲገሉ እንደነበር ምስክርነቷን ተሰጣለች። እሷ ባለችው መልኩ አስር ሰዎች ተገለው አይታለች። ” በስህተት” ግድያው መፈጸሙ አስመልክታ ስትናገር እየተጣሩ መግደላቸውን፣ ያልሞተውን ወድቆም እያለ በጥይት በተደጋጋሚ መምታታቸውን በመግለጽ የማይሆን ምክንያት መሆኑንን ተናገራለች። ይህች ሴት ከሞያሌ ተሰዳ የወጣች ናት። ድምጿን ከተያያዘው ፍያል ያድምጡ። ሙሉውን የቢቢሲ ዘገባ የሚከተከው ነው።

ባለፉት ሁለት ቀናት ከኢትዮጵያ ሸሽተው በኬንያ ደምበላ ፈቻና እና ሶመሬ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ቢቢሲ ቃኝቷል፤ በርካታ ስደተኞችንም አነጋግረናል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የህክምና ባለሙያዎች ”እድለኛ” ብለው የሚጠሩት ጉዮ ጃርሶ ነው። ጉዮ በሞያሌ ከተማ የተሽከርካሪ ጎማ የመጠገን ሥራ ላይ ነበር የተሰማራው።

”ሰዎች የተገደሉ ቀን እንደተለመደው ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የተሽከርካሪ ጎማ የመጠገን ሥራ ላይ ነበርን። ምንም ሳናጠፋ በስራችን ላይ እያለን ተኩስ ከፈቱብን። እኔ በሁለት ጥይት ተመታሁ። ከሶስቱ ጓደኞቼ ሁለቱ የዛን ቀን ሲገደሉ አንዱ ደግሞ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል” ሲል በምሬት ይናገራል።

ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ሁለቱም ጥይቶች ሰውነቱን በስተው ነው ያለፉት። የመጀመሪያው ቀኝ እጁን ሁለተኛው ጥይት ደግሞ ከሆዱ በላይ ጎኑን በስቶት አልፏል።

በስደተኛ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ የቀይ መስቀል ማሕበር የጤና ባለሙያዎች የጎዮ ህይወት መትረፍ አስደናቂ እንደሆነ፤ ምናልባትም ከሁለቱ ጥይቶች አንዱ ጥቂት ወደ ግራ የሰውነቱ ክፍል ቢጠጋ ኖሮ ህይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችል እንደነበር ይናገራሉ።

ጉዮ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች አምቡላንስ ጠርተው ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል እንደወሰዱት ይናገራል፤ ከትናንት በስትያ ከሆስፒታል አንደወጣ በቀጥታ ወደ ሶመሬ ስደተኞች ጣቢያ ነበር ያመራው።

ጉዮ ጃርሶ

ከሃገር ሸሽተው ከወጡት ዜጎች መካከል ሌላኛዋ ወ/ሮ ከድጃ መሃመድ ነች። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ከድጃ ሞያሌ ከተማ በሚገኘው አነስተኛ መደብሯ ውስጥ የተለያዩ ሸቀጦችን ትነግድ ነበር። ወ/ሮ ከድጃ በሞያሌ የነበረው ግድያ ”ለእኔ እና ለልጆቼ ስጋት ስለሆነብኝ ሸሽቼ ወጣሁ” ትላለች።

ወ/ሮ ከድጃ ”እኔ ተከራይቼ የምኖርበት ግቢ ውስጥ ፊት ለፊቴ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። በሬን ከፍቼ ስወጣ እኔም ላይ ተተኮሰብኝ። አላህ ጠብቆኝ ህይወቴ ተረፈች። ከዛም በሬን ዘግቼ እስኪያልፉ ጠብቄ ልጆቼን ይዤ በፍጥነት ከከተማው ሸሽቼ ወጣሁ” በማለት የነበረውን ክስተት ታስታውሳለች።

የእርሷ እንዲሁም የጎረቤቴ ናቸው ያለቻቸውን ልጆች ጨምሮ በርካታ ህጻናት ከድጃ በሰራችው የላስቲክ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ተመልክተናል።

ራሄል የአክስቷን ልጅ አቅፋአጭር የምስል መግለጫራሄል የአክስቷን ልጅ አቅፋ

ከህጻናቱ መካከል በወላጆቻቸው ፍቃድ የ15 ዓመት ዕድሜ ያላት ራሄልን እና የ10 ዓመቷ ኢቅራን አነጋግራናል። የአክስቷን ልጅ አቅፋ ያገኘናት ራሄል ”የጦርነቱ ቀን በጣም ብዙ ደም አየን። እኛንም ይገድሉናል ብለን ሸሽተን ወደ እዚህ መጣን። እዚህ ከመጣን ጀምሮ የበቆሎ ገንፎ ነው የምንበላው” ትላለች። ራሄል የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደ ትምህር ቤት መመለስ ብትፈልግም ከፍተኛ ፍራቻ እንዳደረባት ግን አልደበቀችንም።

”ልጆች ሲገደሉ አይቻለሁ። ትምህርት ቤት ሄጄ መማር እፈልጋለው ግን ወደዛ መመለስ እፈራለው” ያለችን ደግሞ ልክ እንደ ራሄል ሁሉ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ኢቅራ ናት።

መንግሥት ከቀናት በፊት በሞያሌ የተፈጸመው ግድያው ‘በስህተት የተፈፀመ ነው’ ማለቱ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ወ/ሮ ከድጃን ጨምሮ በጣቢያዎቹ ውስጥ ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች በዚህ የሚስማሙ አይመስሉም።

ድንበር ተሻግረው ኬንያ ከገቡ የሞያሌ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች ”እኔ በስህተት ነው ብዬ አላምንም። ‘ሸሚዝ የለበሰውን ምታው’ እያሉ እየተኮሱ በስህተት ነው ማለት አይቻልም። ሆነ ብለው ወጣቶችን ነበር ኢላማ ሲያደርጉ የነበረው። ከዛም በኋላ የ10 ዓመት ልጅ አባረው ነው የገደሉት ይህም በስህተት ነው?” ስትል በምሬት ትጠይቃለች።

አውዲዮውን ለመስማት ይጫኑት

ባሳለፍነው ቅዳሜ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጂኔራል አሰፋ አብዩ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዲና ሙፈቲም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተመሳሳይ ነገር ነግረውናል።

አምባሳደሩ ይህን ይበሉ እንጂ በኬንያ እና ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የታዘብነው አሁንም በርካቶች ድንበር አቋርጠው ወደ ስደተኛ ጣቢያዎች ሲተሙ ነው። አልፎም ካነጋገርናቸው ተፈናቃዮች መካከል በርካቶች ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጎት የላቸውም።

ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ ከአራት በላይ በሆኑ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር አስር ሺህ ይገመታል። ከወርልድ ቪዝን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየን ደግሞ ከስደተኞቹ መካከል ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው።

ሶመሬ ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ከ3500 በላይ ሰዎች ይገኛሉ። በጣቢያው በአንድ አነስተኛ ከላስቲክ በተሰራ ቤት ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ይዞ ይገኛል።

በጣቢያው በርካታ ሰዎች በጠባብ ቦታዎች ላይ ተፋፍገው ስለሚገኙ እንዲሁም የመጸዳጃ እና በቂ የሆነ የህክምና አገልግሎት ባለመኖሩ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በጣቢያው የወርልድ ቪዥን ተወካይ የሆኑት ደንከን ኦዳዎ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

በጣቢያው ውስጥ በርካታ ህጻናት እና ነብሰ ጡር ሴቶች ስለሚገኙ የበሽታ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወስ የተቅማጥ በሽታ ምልክቶች መታየታቸውንም ድንከን ኦዳዎ ነግረውናል። ጨምረውም በኢትዮጵያ መረጋጋት ሰፍኖ የስደተኞች ቁጥር ካልቀነሰ በቀር ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።

ኬንያውያን ልብስ ሲያድሉ

የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለስደተኞቹ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በርካታ የኬንያ ዜጎች ሃገር ጥለው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አስጠግተው እያኖሯቸው እንደሆነም ቢቢሲ ተገንዝቧል። ከዚህ በተጨማሪም በግል መኪኖቻቸው ልብስ እና ምግብ ጭነው ሲያድሉም ተመልክተናል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Egypt and Ethiopia meet in Russia over mega dam dispute
0Shares
0