“Our true nationality is mankind.”H.G.

እንደ ገና ዳቦ እሳት ሊነድበት – ዶ/ር አብይ ወጣ ከሰገነት

ይገረም አለሙደ/ር አብይ እንደ ግለሰብ የለማ ቡድን የሚባለው እንደ ስብስብ ብሎም ኦህዴድ እንደ ድርጅት ወደ ምንይልክ ቤተ መንግሥት የመጡበት ወቅት እጅግ ከባድ ነው፡፡በተለይ ደግሞ ከሰገነቱ የሚታየው ለሁሉም ነገር ቀድሞ ስሙ የሚነሳውና ኃላፊነቱም የሆነው በጠቅላዩ ቦታ የሚቀመጠው ሰው እንደመሆኑ የሚገጥመውን ተግዳሮት ለመገመት ብዙ የሚከብድ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እንደ ገና ዳቦ እሳት ሊነድበት ለማለት የደፈርኩት፡፡

የጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ንግግር ያዳመጥኩት በቀጥታ ስርጭት ሳይሆን  ለዘመኑ ተክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና በአመቸኝ ሰአት ወደ ዩ ቲዩብ ጎራ ብዬ ነው፡፡ ስሜቴ እየተናወጠ አንዳንዴም አይኔ እየረጠበ ነው ያዳመጥኩት፡፡የኢትዮጵያ የዘመናት የነጻነት ታሪክ ህመም የሆነባቸው፣ ሰንደቅ ዓላማችንን ሲያዩ እንደባለዛር የሚያስጓራቸው፣ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለመጥራት የሚያቅለሸልሻቸው ወዘተ ከተሰበሰቡበት መንደር የወጣ ሰው እንዲያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አንድነት አንድነት አያለ ሲናገር መስማት  እንደምን አያስለቅስ፡፡

“የወንዝን ውኃ ምን ያጮኸዋል ከውስጡ ያለው ድንጋይ” እንደሚባለው የሚያስለቅሰን የውስጥ ህመማችን፣ ብሶታችን፣ ቁስላችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ተብለው ተቀምጠው ኢትዮጵያውያን ለማለት ተጠይፈው የሀገራችን ህዝቦች ሲሉን አመታት ላስቆጠርን ሰዎች ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን የሚል፣ በየጎሳችሁ ተበታተኑና፣ በየመንደራችሁ ተሰባሰቡና ከዛ በኋላ በመፈቃቀድ ኢትዮጵያን እንመሰርታለን እያሉ ልዩነት ሲሰብኩን ብቻ አይደለም ያማለያያ ድር ሲያደሩልን ይህን አልፈን ሴራቸውን አክሽፈን አንድ ነን ስንል ደግሞ እብሪታቸው ማስተዋልን ነፍገዋቸው በአደባባይ እሳትና ውኃ እሳትና ጭድ፤ እንዴት አብሮ ይሆናል ሲሉን የነበርን ሰዎች ክነርሱው መካከል የወጣ ሰው ያውም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መድረክ ላይ አንድነታችን ላይለያይ የተሰናሰነነ ነው ሲል መስማት ስሜቱን የማይነካው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፡፡

የጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይን ንግግር እያዳመጥኩ ይህ ሰው እዚህ ለመድረስ ስንት ነገር አልፎ ይሆን፣እንዲህ በንጹህ ሰዋዊነት ከውስጥ በመነጨ ልባዊ ስሜት የሚነግረንን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ሊገጥመው የሚችለውን ተግዳሮት ከምንም በላይ ብዙ መልካም አጋጣሚዎች እንደ ዋዛ ማሳለፋችንን በማስታወስ ይህን መልካም አጋጣሚ እንጠቀምበት ወይንስ እንደቀደሞቹ እናመክነው ይሆን ወዘተ እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ከአቶ ኃይለማሪያም ጋር እርክክብ ከሚያደርጉበት ከአንደኛው ክፍል ሆኖ ከጋዘጠኛ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ደግሞ ሌላ ስሜት የሚነካ ያልተለመደ ይህ ሰው በርግጥም ለትንሳኤ የመጣ ሳይሆን አይቀርም እድል ያረገኝ ሆነ፡፡ (አንቱታ ያደረብኝን የፍቅር የአክብሮትን የወገናዊነት ስሜት የሚያሳንስብኝ ሆኖ ስለታየኝ ነው አንተ ማለቴና ይቅርታችሁን)

ከእምዬ ምንይልክ እስከ አቶ ኃይለማሪያም የነበሩትን መሪዎች ከኋላ ወደ ፊት በቅደም ተከተል እያነሳ ስለሁሉም በጎ ተግባር ነው የገለጸው፡፡በእኛ ዘንድ ያልተለመደ ግን እጽብ ድንቅ የሆነ ተግባር ነው፡፡ግለሰብም ይሁን ቡድን የቱንም ያህል አንባገነን ቢሆን ትንሽም ብትሆን መልካም ነገር ትኖረዋለች፡፡ሀያ ሰባት አመት ስንሰማ የኖርነው ግን የቀደሙ መሪዎች ሲወገዙ፣ የሀገሪቱ ታሪክ የደብተራ ተረት ተረት ሲባል ነው፡፡ እናም በሁልተናዊ መልኩ ከደደቢቶቹም ሆነ መሀል ከተማ ተቀላቅለው ከጳጳሱ ቁሱ አይነት ሆነው ሲያውኩን ከነበሩት የወያኔ ገባሪዎች በተለየ ሁኔታ ከዛው ከመካከላቸው እንዲህ አይነት የለውጥ ሀዋሪያ የሆነ ሰው ብቅ ሲል የሚገጥመው ፈተና ከባድና ባለ ብዙ ዘርፍ በመሆኑ ነው እንደገና ዳቦ እሳት ሊነድበት ማለቴ፡፡ በግልጽ መገመት ከሚቻሉት አበይት ተግዳሮቶች፤

የህዝቡ የለውጥ ጥያቄ፤ በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀር በማንም በምንም ሁኔታ ከደደቢት ትልማችን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን ፈቀቅ አንልም፣ ስልጣን ከእጃችን በማውጣት የዮሀንስን ስህተት አንደግምም፣ እያሉ የሚፎክሩትንና ለሀያ ሰባት ዓመታታ ተግባራዊ ማድረግም የቻሉትን ደደቢቶች አንበርክኮ በምንም ይሁን አንዴት ዶ/ር አብይን ወደዚህ ወንበር ለመምጣት ያበቃው ገና ቁጥሩ በውል ያልተረጋገጠ ወገን መስዋዕትነት የከፈለበት የህዝብ  ትግል ነው፡፡ የትግሉ ዋንኛ ጥያቄ ደግሞ ኃይለማሪያምን በአብይ ህውኃትን በኦህዴድ መቀየር ሳይሆን ደደቢታዊውን አገዛዝ በህገ መንግሥታዊ አስተዳደር መቀየር ነው፡፡

ይህ ደግሞ ዙሪያ ገባ መሰናክል ተደርድሮ፣እንዲህ ተለያይቶ ሆድና ጀርባ ተኩኖ (ኢህዴጎች መለያየታቸው በግልጽ ይታያል)  ቀርቶ በተስተካከለ መንገድ በአንድ መንፈስ እንኳን ከባድ ስራ እልህ አስጨራሽ ትግል የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ለዘመናት እየተሳከረ መጥቶ  ውሉ የጠፋውን የፖለቲካ ሂደት በአንድ ጀንበር ማስተካከል እንደማይቻል እሙን ሆኖ  የሺህ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ርምጃ ይጀመራል እንዲሉ ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ ለመድረስ ጉዞ መጀመሩን የሚያሳዩ ድርጊቶች ደረጃ በደረጃ መከወን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጨው ለራስህ ብለህ ጣፋጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉህል እንደሚባለው በትግሉ ለውጥ ማምጣት አንደሚችል በተግበር ያየው ህዝብ ማእበል ፈጥሮ አብይንም ቡድኑንም ሊጠራርጋቸው ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በጥለቅ መታሰብና ከዛም በላይ መተግበር ያለበት ለውጥ መጠበቅ የሚጠብቁት ለውጥ አልታይ ሲል ተቃውሞ ማሰማት ሳይሆን ከመነሻው ትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ላይ መግባት እንዲቻል፣ ከዛም የለውጡ ባቡር መስመሩን ሳይስት ፍጥነቱን እየጨመረ መጓዝ እንዲችል ሁሉም በሚችለው መርዳት መተባበር ይኖርበታል፡፡ይህን የማይችል ወይንም ፈቃደኝነቱ የሌለው ደግሞ ከአደናቃፊ ተግባር መቆጠብ፡፡ በመሆኑም ለውጥ ናፋቂውና  አያሌ መስዋዕትነት የከፈለው ህዝብ አብይንና በእርሱ የሚመራውን መንግስት መርዳትንና አደናቃፈዎችን ከመንገዱ ላይ ማጽዳትን ስራው ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

የደደቢቶች እጅ አንሰጥም ባይነት፡፡ በዶ/ር አብይ ጠቅላይ ምኒስትር መሆን ወያኔዎች ደስተኛ አለመሆናቸውን እያየንም እየሰማንም ነው፡፡ የተሸነፍን ስሜታቸው ከካሜራ ፊት መሆናቸውን እንኳን ለማሰብ አላስችላቸው ብሎ  ፓርላማ ውስጥ የነበራቸውን ሁኔታ አይተናል፡፡ አንዳንዶችም መመረጡን በይፋ ሲቃወሙ ከመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል፡፡ ይህን ሽንፈታቸውን ተቀብለው አሜን ብለው ይቀመጣሉ ማለት ከወያኔዎች ባህርይ አንጻር የማይታሰብ ነው፡፡ በርግጥ አብይም ሆኑ ለማ ከደደቢቶች ጋር በቅርብ የሰሩ እንደመሆኑ በህጋዊ መንገድም ሆነ በህገ ወጥ፣ መርህን ተከትለውም ይሁን በመርህ አልባ ግንኙነት ወያኔዎቹ የሚያሴሩትንም ሆነ የሚሰሩትን ስለሚያውቁ ለዚህ ዝግጅት አድርገዋል ብሎ  መገመት ይቻላል፡፡

በተለይ በዚህ ወቅት ለለውጡ ሂደት አስቸጋሪ የሚሆኑት ወያኔ ከየ- ብሄረሰቡ እየመለመለ በፍርፋሪ ያሳደጋቸው  ናቸው፡፡እንዲህ አይነት ሰዎች ኦህዴድም ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በተለይ ከወያኔ ተጠግተው አለአግባብ የከበሩና በማይመጥኑት ወንበር ላይ የተቀመጡ ለውጡ ባሉበት ወንበርና በያዙት ሀብት እንደማያስቀጥላቸው ስጋት ሲገባቸው፣ ከዚህ ባለፈም የህግ ተጠያቂነት ሊከተል ይቻላል ብለው ሲያስቡ በሚችሉት አቅምና መንገድ የለውጡን ባቡር ማስቆም እንኳን ባይችሉ ፍጥነቱን ለመገደብ መንደፋደፋቸው አይቀርም፡፡

የተቀዋሚው አይነተ ብዙነት፡፡ ዶ/ር አብይ ተቀዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ ናችሁ አላቸው፡፡ ተገቢ አገላለጽ ግን ለፖለቲከኞቹ ፈተና ነው፡፡ፖለቲከኛ ነን ባዮቹ በውስጥም በውጪም ያሉቱ አይነቴ ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በወያኔ የጡት አባትነት በምርጫ ቦርድ ክርስትና ተነስተው ፓርቲ ለመባል የሚያባቃውን መስፈርት እንኳን ሳያሟሉ ፓርቲ ተብለው ያሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ፓርቲ የሚባሉት እነርሱና እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች፣፣

ተቀዋሚነት ቀላል ነው መናገር የቻለ ሁሉ መሆን የሚችለው፡፡ ተፎካካሪነት ግን ከባድ ነው፣ ትጋት ጥረት የሚጠይቅ ስራ ያስፍለገዋል፡፡መግለጫ በመጻፍና ዲስኩር በማሰማት ብቻ ተፎካካሪ መሆን አይቻልም፡፡ ስለሆነም እነዚህ እየተቃወሙ ወይንም ተቀዋሚ እየተባሉ የኖሩና ወደ ተፎካካሪነት ለማደግ አቅሙ የሌላቸው ደግሞ ከፖለቲካው መድረክ መጥፋት የማይፈልጉ ለለውጡ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ለምን ሆነ እንጂ እንዲህ ይሁን አይሉም፤ስህተት ሲፈልጉ እንጂ ለማገዝ ሲተጉ አይታዩም ፡፡ እነዚህ ተቀዋሚ እንጂ ተፎካካሪ ለመሆን አቅሙ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮውም የሌላቸው ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ በትክክለኛ መንገድ ይዋቀር ሲሉ የእነርሱንም ህልውና እንደሚመለከት የተገነዘቡ አይመስሉም፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                               ካለበላሁት ጭሬ ላፍሰው አመለካከት፣ ኢትዮጵያን ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ አድርጎ ካኖራት ችግር አንዱ ለለውጥ እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ለውጡ እኛ በምንለው መንገድ ብቻ የሚሉና ከዚህ አልፎም እነርሱን ለሥልጣን የሚያበቃ እንዲሆን የሚፈልጉ መሆናቸው ነው፡፡በንጉሡ የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ የለውጥ ትልም ይዘው ብቅ ያሉ ሰዎች ትንሽ ፋታ ስጡን ሲሉ እነርሱን ተጠቅሞ ሂደቱን ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ ለመውሰድ ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ቀጥሎ ስለመሆነው አይደለም ዝግጅት ውጥን ሳይኖር ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ማለት ነው የተመረጠው፡፡ይህም ሂደቱን በወታደሮች አእጅ አስገባው፡፡

ደርጎቹም ቢሆኑ ለሥልጣን የተዘጋጁ አልነበሩምና ግራ ገብቶአቸው አግዙን ብለው የጠሩዋቸው ምሁራን  እያገዙ ሂደቱን ወደሚፈለገው አቅጣጫ ለማስኬድ ከመሞከር ይልቅ ህዝባዊ መንግሥት አሁን የሚል ሱሪ ባንገት አይነት ጥያቄ አንስተው ሥልጣንን የያዘውን ደርግ ትተው ርስ ከመቀዋወም እስከ መተላለቅ ደርሰው ወርቃማውን የለውጥ ግዜ አመከኑት፡፡

አሁንም በአንዳንዶች ዘንድ ገና ከአሁኑ ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፡፡ ብዕረኛው ሀይሉ ገብረ ዮሀንስ (ገሞራው)ለሽልማትም ለእስራትም ባበቃው በረከተ መርገም በተሸኘው ግጥሙ ውስጥ ያሰብከው ምኞትህ አልሆን ብሎ ሲከሸፍ ሁኔታው ሲጠጥር፤ ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር ይላል፡፡ አንድ መንገድና የትግል ስልት ብቻ አይደለም ወደ ዴሞክራሲ የሚያደርሰን፡፡ በመሆኑም እኛ የተያያዝነው  መንገድ የማያደርሰን ከሆነ መሻታችን ራስን ለሥልጣን ለማብቃት ሳይሆን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያው ሥርዓት ከሆነ በሌላኛው መንገድ ላይ ያሉትን ማገዝ ካልሆነም ከማደናቀፍ መታቀብ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከዶ/ር አብይ ንግግር በኋላ የሚሰሙ አንዳንድ አስተያየቶች ይህን ስሜት ያንጸባርቃሉ፡፡ አንዳንዶች ጽንፍ ሄደው የሽግግር መንግስት ይላሉ፤ህዝባዊ መንግስት አሁን እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች ቃል ሰልችቶናል ተግባር ይላሉ፡ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ነው የሚባለው !! አንዳንዶች በግልጽ የሚታየውን መቀበል ተስኖአቸው አብይን ወያኔ ነው ያስቀመጠው እስከማለት ይደፍራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የውስጡ ፍልሚያ አንደተጠበቀ ሆኖ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ምኒስትር ለመሆን የበቁት በኢህአዴግ መሆኑን ይዘነጉና ንግግሩ ፍጹም ከኢህአዴግ አመለካከት ውጪ መሆን እንደነበረበት አይነት አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

የሚበጀው፡ ዶ/ር አብይ አይደለም በወያኔ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያልተለመደ ነገር አሳይቶናል፡፡ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነት ብቻ አይደለም ቁርጠኝነትም ንግግሩም ስሜቱም ያሳያል፡፡ የሚበጀው ይህን ሰው በሁሉም ዘርፍ በማገዝና በመደገፍ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኣዋላጅ ማድረግ ነው፡፡ ማን ያውቃል የኢትዮጵያ ጎርባቾቭ ቢሆን ?

አብይ ትልምህን ከግብ ለማድረስ እግዚአብሄር ይርዳህ፡፡

እሱ ካለ ደግሞ ማንም በምንም ሁኔታ ሊያስቆመው አይችልም፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “…ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ” አብይ አህመድ
0Shares
0