ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በተስፋ የሚቆዩበት ዘመን አልፏል!

ታሪኩ አባዳማ – በዚህ የፋሲካ ሰሞን ከወደ ህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ወጥ ቤት የሚመጣው ሽታ የዶሮ ውጥ ይሁን የአሞራ ስጋ መለየት ቸግሮኛል። ገበታው ላይ ቀርቦ ለማየትም ለመለየትም ብዙሀን እንደጓጉ መታዘብ ይቻላል። የምናነባቸው እና የምንሰማቸው አስተያየቶች እና ግምቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ብዙሀኑ የተደገሰው ዶሮ ከሆነ ሊያጣጥሙት አሞራ ከሆነም አውጥተው ወደ ቆሻሻ ገንዳ ሊደፉት የተዘጋጁ ይመስላል። ሽታው ግን በርግጥም አፍንጫን ያውዳል… በጉጉት እንዲጠብቁ ይጋብዛል።

እንደተለመደው ወያኔ ፋታ ለመግዛት ሲል የፈጠረው የቆረጣ ማፈግፈግ ይሁን ሌላ ሁላችንም አብረን የምናየው ነው። አሁን ግን በደረሰበት ህዝባዊ እምቢተኝነት ተገፍቶ ተፈጥሮው ሳይሆን አቅሙ የፈቀደለትን ያህል በመጓዝ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ መሀንዲስ ይዤ ቀርቤያለሁ ብሏል። ለዚህ ክፉ ቀን ይሆነኛል ያለውን አዲስ መሪ ሰይሟል።

በሌላ በኩል ‘ስልጣን ከአገር በላይ አይደለም’ (ድርጅት ከአገር በላይ አይደለም በሚል ብናሰፋው) የሚሉ ወጣት ፖለቲከኞች አንዳንዶቻችን ይመጣል ብለን ካልጠበቅነው አቅጣጫ ተከስቷል። አገራዊ ራዕይ ሰንቆ የተከሰተው መንገድ የመጣበት አቅጣጫ ከቶውንም የማይጠበቅ ባይሆንም ኢትዮጵያን በፍፁም ነብሱ የሚታደጋት ዜጋ በዘር ግንድ ከታነፀ ቡድን ይመነጫል ብለን መጠበቅ እንደሌለብን ተደርጎ የዘር ጉንጉን ሲፈተል መቆየቱ እውነት ነው።

ቄሮ ተከሰተ!

… ኢትዮጵያዊነት ‘ሱስ’ ሆኖ ተከሰተ።

ኦፒዲኦ ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ከሚሉ ደካማ መሪዎች መዳፍ ውስጥ ተፈልቅቆ መውጣቱንም እያበሰረ ነው። የጦር ምርኮኞቹ እነ አስር አለቃ አባዱላ ገመዳ (ምናሴ) በወያኔ ሞግዚትነት የመሰረቱት ድርጅት ከመንገድ መሪነት ፣ ጉዳይ አስፈፃሚነት እና ዘረፋ ተባባሪነት ወደ አገር ታዳጊነት እየተሸጋገረ ይመስላል። እንኳንም ተማረካችሁ ፣ እንኳንም ኦፒዲኦን መሰረታችሁ የሚያሰኝ ዘመን እየመጣ ነው። እናንተ ተማርካችሁ ወያኔ ብብት ስር ባትቆዩ ፣ ውስጡን መርምራችሁ አስፀያፊ ደባውን ክፋቱን ከውስጥ ባታስተውሉ ፣ አካሄዱ የማያምር አገር አጥፊ መሆኑን ባትረዱ ኖሮ ዛሬ የምናሸተውን ለውጥ መቼ እናይ ነበር የሚሉ አልጠፉም።

የአባይ ፀሀዬ ‘ልክ እናስገባለን’ ድንፋታ ያልበገረው ቄሮ “ኢትዮጵያዊ” መታወቂያችን ከአፈሯ ጋር የተወሀደ ማንም ሊፍቀው የማይችል መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም አረጋገጠ።

ኢትዮጵያዊው እንግልት ዜጋ ትዕግሰቱ እና ተስፋው በፈተና ውስጥ ቢወድቅም እየተፈፀመበት ያለውን ሰቆቃ ችሎ ወያኔ በብረት ውግርግር ከገነባው ረጅሙ ጨለማ ሸለቆ መውጫ በር ከሩቅ የምታበራውን ጭላንጭል ብርሀን ተከትሎ ለማለፍ ወገቡን አጥብቋል። ተስፋው እውን መሆኑን በተግባር ማረጋገጫው ታሪካዊ ዘመን አሁን ነው።

መጨረሻው ካላማረ ግን ኦሮሞ በብሂሉ እንደሚገልፀው “ኢንታኣ ጄናን ሀሬ ቀሌ ፣ ኢንታኡ ጄናን ባስኔ ገኔ” የሚለው ይከተላል ወይንም በአማርኛው ‘ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለያ ድንጋይ ብለው ይጥሉሀል’ ነው ጉዳዩ።

በወያኔ ዘመን ተንሰራፍቶ የቆየው የጥቂቶች ‘ዘርፎ መብላት’ ተግባር ወይንም ባንድ ጀንበር ከባዶ እጅ ወደ ሚሊየነርነት የሚለውጠው ህገ-ወጥ አካሄድ መሰረቱን የጣለው በወያኔ የፖለቲካ ስልጣን መከታ በተፈቀደ ልዩ ጥበቃ እና ማበረታቻ መሆኑን የምንስተው አይመስለኝም። በሙስና እና ከዚህ ጋር ተቆራኝቶ ከቆየው የሰቆቃ ስርዓት እንዲህ በቀላሉ ያውም በዚያው በጥልቅ ከበሰበሰው ስርዓት መልካም ፈቃድ መገላገል ይቻላል? ከኢኮኖሚ ሙስና በፊት የፖለቲካ ሙስናው በፅኑ መሰረት ላይ ተገንብቶ በቆየባት አገር ምን አይነት ለውጥ ይጠበቃል?

ለመሆኑን የፖለቲካ ሙስና ምንድነው?

በአጭር አገላለፅ የፖለቲካ ሙስና ይፋ በተደነገገ ህገ-መንግስት የማይገዛ የፖለቲካ ስርዓት ማለት ነው። የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ደግሞ “… the abuse of political power by government leaders to extract and accumulate for private enrichment and to use politically corrupt means to maintain their hold on power…”  ሲሉ ይገልፁታል።

የአንድ ግለሰብ ወይንም ቡድን ፈቃድ ለራሱ ወይንም ለቡድን ፍላጎት እና ጥቅም ማረጋገጫ ሆኖ ሲገኝ የፖለቲካ ሙስና ነው። በጥልቅ ‘በሰበሰ’ የተባለው ህወሃት/ኢህአዴግ በገዛ አገራችን ባዕድ ሆነን የህይወት ዋስትና እንድናጣ አድርጎናል። ማን ሰላማዊ ማን አሸባሪ ፣ ማን ‘ምሁር’ አዋቂ እና ማይም እንደሆነ ሁሉ ደረጃ አውጥቷል። የህዝብ አገልግሎት ተቋማት ላንድ ጠባብ የብድን ፍላጎት እና ጥቅም ሲባል ተቀርፀው የማይወጡበት ውስብስብ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ሆኗል- ትምህርት ተቋማት ፣ መገናኛው ፣ ፍርድ ቤት ፣ ሰራዊቱን ፣ ደህንነቱን ፣ ወህኒውን… ሌላው ቀርቶ የሰብአዊ መብት ተቋማትን በራሱ አላማ እና ግብ አኳያ ቀርፆ አስቀምጧል… to use politically corrupt means to maintain their hold on power…።

በፊውዳል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት የቆየችው አገራችን በ66 አብዮት በተነሳ ህዝባዊ ጥያቄ የግል ንብረት ባለቤትነት ተወግዶ እንደ መሬት እና ቤት ያለ ሀብት ባብዛኛው በማዕከላዊ መንግስት ይዞታ ስር ነበር። ወያኔ ይህን ባለቤት የሌለው የሚመስል የአገር ሀብት መረን በለቀቀ የስግብግብነት ባህሪ ተቀራምቶታል። አልፎ ተርፎ ለም መሬት በተገኘበት ሁሉ እየሰሰ ለአባላቱ እና ለወዳጆቹ በረከት ሆኗል። እነኛ የአገር ሀብት ተብለው የተከበሩ ማዕድናት እና የተፈጥሮ ደኖቻችን እጅግ ሀላፊነት በጎደለው የስግብግብነት (የደመኛ ጠላትነት ስሜት ብንለው ይቀላል) ዘረፋ እና ብዝበዛ ተፈፅሞባቸዋል።

የአገር ሀብት ካንድ ጎጥ ተጠራርተው በተነሱ የጦር አበጋዞች እጅ መፈንጪያ ሆኖ ቆይቷል።

ባለፉት 27 የወያኔ አገዛዝ ዘመናት የፖሊተካ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ህወሃት ካድሬዎቹን ሲሻው ከምንም አንስቶ ጄኔራል ፣ ሚኒስትር ፣ ዳይሬክተር እና አምባሳደር እያለ ሲመድብ እንደቆየ ይህንንም በወቅቱ የነበረው መሪያቸው ‘ለኢህአዴግ (ህወሃት) ታማኝ እስከሆነ ድረስ ማይም ቢሆን እንኳ ሚኒስትር መሆን ይችላል’ ማለቱን ማስታወስ ይበቃል። ይህ የሆነው ግን ዝም ብሎ በነሲብ አልነበረም – ሁዋላ ላይ የተከተለው አይን ያወጣ የኢኮኖሚ ዘረፋ እና መሬት ወረራ ህጋዊ ሽፋን እንዲያገኝ በፊት የፖለቲካው ሙስና መሰረቱን አደላድሎ ለሚቀጥለው እርምጃ ምቹ መሰረት ለመጣል ነበር። በመለስ ዜናዊ አመራር ህጋዊ ስርዓትን ተከትሎ አገርን መምራት ፣ ህዝብን ማገልገል በሁሉም መስክ ማለት ይቻላል ተኮላሽቷል።

አዲሱ ጠ/ሚኒስትር እንደጠቆመው ‘አንዱ ዘርፎ የሚበላበት የሚከብርበት ሌላው የበይ ተመልካች የሆነበት’ ላለፉት 27 ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየው ስርዓት ኢትዮጵያን ገሀድ እግር ተወርች አስሮ አሽመድምዷታል። ማንስ አይን ባወጣ ዘረፋ እንደተሰማራ ማንስ ለፍቶ ቁልቁል እንደወረደ እንኳን እኛ በባዕድ አገር ያሉ የወያኔ ቅምጥ ኮረዳወች የሚስቱት ጉዳይ አይደለም።

በወያኔ ዘመን የደረሱ ልማቶች እና ጥፋቶች ጭብጥ በሆነ የሰነድ ክምር ተሰትረው ተቀምጠዋል። በልማት ስም ኢትዮጵያ እስከ መቼውም ከፍላ የማትወጣው ዕዳ ውስጥ እንድትዘፈቅ መደረጉን ከነኝህ ሰነዶች አሀዝ እየጠቀሱ መተንተን ይቻላል።

ወያኔ በቀየሰው ‘የልማት’ አቅጣጫ ዕድገት በሚል ሰበብ እጅግ ሰፋፊ ለም መሬቶች ለባዕዳን ‘በነፃ’ መታደላቸውን ፣ በሙስና ለተካኑ የወያኔ ባለሟሎች እና ወዳጆች እንዲሁ በከተማም በገጠርም ነፃ መሬት እና በአሰርት እና መቶ ሚሊየን የሚሰላ የማይከፈል ብር ሲመዘበር መቆየቱን ፤ አንዳችም ጥናት ሳይደረግ በወያኔ ሹማምንት ምናብ ውስጥ የተፈጠሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በመቀየስ አሁንም በቢልየኖች የሚቆጠር ገንዘብ መዘረፉን ከአስረጂ ሰነድ ጋር አያይዞ ይፋ ማድረግ ተችሏል።

ለዘረፋ ሲባል ሆን ተብሎ የተቀየሱት የወያኔ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ያለ በቂ ጥናት እና የአፈፃፀም ብቃት እንዲወጠኑ ለምን ተደረጉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሩቅ መጓዝ አያስፈልግም። አሁን አሁን እነሱም ጭምር ዘረፋው በ‘ኔትወርክ’ ተጠናክሮ እየተቀላጠፈ ነው ብለዋል። አንዳችም ህጋዊ ተጠያቂነት ፣ አንዳችም ግልፅነት የሌለው የዘረፋ ስርዓት።

የ‘ኔትወርክ’ ነገር ሲነሳ መራራ ፈገግታ ያሳደረብኝን አንድ የዚህ ሰሞን ዜና ልጥቀስ – የወያኔ ኮንትሮባንዲስቶች ከባድ ጭነት ይዘው ከጂቡቲ ወደብ እስከ አዲስ አበባ ያሉትን የፍተሻ እና የጉምሩክ ጣቢያዎች እንዴት በስልት እንደሚያልፉ የቀረበውን ሪፖርት ይመለከታል። በዚህም በያንዳንዱ ጣቢያ ላይ ተመርጠው የተሾሙ የወያኔ ታጋዮች ሀላፊዎች እና እነሱ የመለመሏቸው የበታች ሰራተኞች የትኛው የጭነት መኪና መፈተሽ እንደሌለበት ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተለይ ደግሞ የሚገርመው መኪኖቹ ካንድ ጣቢያ ሲደርሱ ሆን ተብሎ የኤሌክትሪክ ስርጭት እንዲቋረጥ እና የቀረጥ ሂሳብ ደረሰኝ ማዘጋጃ ማሽኖች አገልግሎት እንዲቆም የሚደረግ መሆኑ ነው። መብራት ሀይል በኔት ወርክ ውስጥ ድርሻ ተሰጥቶት መብራት አጥፋ ሲባል ያንድን ከተማ ነዋሪ አገልግሎት ድርግም አድርጎ ይዘጋል። ይህ በተመሳሳይ ቀን ተደጋጋሚ የመብራት መቋረጥ እስከሚፈጥር ድረስ ይፈፀማል… ምህረት የለሽ ኔትወርክ።

ካች አምና ሀይለማርያም ደሳለኝ ያቋቋመው አንድ ‘መርማሪ’ ቡድን እዚያው ወያኔ ፓርላማ ፊት ቀርቦ እንደተናገረው ‘ኢትዮጵያ በዚህ መንግስት ወታደራዊ እና ሲቪል ሹማምንት በቁሟ የተጋጠች አገር ናት’ ብሏል። እንዲህ አይነቱ ጥፋታዊ ልማት እንደ ግስጋሴ ተቆጥሮ በፈጣን ዕድገት ውስጥ የምትገኝ አገር እየተባለ ነጋሪት ሲጎሰም መቆየቱም እንግዳ አይደለም።

የወያኔን የማይጠረቃ የዘረፋ አፒታይት ለማርካት ሲባል አርሶ አደሮች ከአፅመ ርስታቸው ካለ አንዳች የህይወት ዋስትና ተነቅለዋል። በድህነት ሲማቅቅ ዕድሜውን የገፋው የአዲስ አበባ ነዋሪ ጎስቋላ መሆኑ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በየዱሩ ፣ በየጎዳናው እና በየእዳሪው እንዲወድቅ ተደርጓል ፣ በቆሻሻ ክምር ናዳ ተቀብሮ እንዲቀር መደረጉንም አለም ታዝቧል።

ለወያኔ የብዙ ቢሊየን ዶላር ባዶ ፕሮጀክቶች ሲባል ዜጎች በገመድ እንደ እንሰሳ እየተጎተቱ ሳይቀር ተግዘዋል ፣ ገዳማት እና ታሪካዊ ቅርሶች በዶዘር ታርሰዋል ፣ ለምን ብለው የጠየቁ መነኮሳት እና ምእመናን ወህኒ ታጉረዋል ፣ ንፁሀን ዜጎች በጥይት ተደብድበዋል ፤ አሰርት ሺህዎች በከረፉ ወህኒዎች እንዲማቅቁ ተደርጓል።

እነ አባይ ፀሀዬ ያቀነባበሩት የስኳር ፕሮጀክት እነ ጀነራል ማንትስ በሚያስተዳድሩት ፋብሪካ አቅራቢነት ፣ እነ ታጋይ ማንትስ በፈጠሩት ኤፈርት የጥሬ እቃ አቅራቢነት እና አጓጓዢነት በሁለት አመት ፣ በሶስት አመት ይህን ያህል ቶን ስኳር ወደ ውጪ ይላካል ተብሎ አንዲት ማንኪያ ስኳር ላረረበት ህዝብ ተሰሰብኳል። ከሁለት ሶስት አመታት በሁዋላ ግን በአሰርታት ቢሊየን የሚቆጠር ሀብት ውሀ በላው የሚል መርዶ ከ100% ፓርላማው ደጃፍ ይሰማል። ወያኔ ይቺን ድሀ አገር እንዲህ ባለ ጭካኔ ራቁት ያስቀረ የፖለቲካ ድርጅት ነው።

ሰቆቃውን በጥቅሉ መግለፅ ምን ያህል አጥጋቢ እንደሆነ ባላውቅም ግን ከያንዳንዱ ዘረፋ ፣ ማፈናቀል ፣ ሙስና እና መሬት ወረራ ጀርባ ቁጥር ስፍር የሌለው ዜጋ እና ቤተሰብ የደም እምባ መርጨቱን ፣ በዚች አገር ምድር ላይ መፈጠር መርገሙን ማስተባበል የሚችል የለም። የወያኔ እርምጃ በያንዳንዱ ቤተሰብ እና ግለሰብ ላይ ከሚያደርሰው ፅኑ የአይምሮ መታወክ አልፎ በኢትዮጵያዊነት ስሜት የተገነባውን ማህበራዊ ህይወት ከስሩ ነቅሎ የማጥፋት ግብ ላይ ያነጣጠረ ነው።

አቢይ አህመድ ይህን እቀይራለሁ ነው የሚለው… “… አትዮጵያችን አንዱ ሰርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናድርግ… መንግስት የህዝብ አገልጋይ ነው…” በማለት ከህግ የበላይነት ውጪ በህልውና መዝለቅ እንደማይቻል ሲያሳስብ ‘… ህግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት…” ብሏል።

በህግ የበላይነት ለመኖር መወሰን ጤናማ አቅጣጫ ነው – ሆኖ መገኘት ወይንም መኖር ደግሞ በሞራል ልዕልና ታላቅነት ነው። ህወሃት ጫካ አርቅቆ ያመጣውቸውን ፀረ አገር እና ፀረ ሰብአዊ መብት አንቀፆች እና ድንጋጌዎችን ይዞ ግን የህግ የበላይነት እንዴት እንደሚረጋገጥ ማሰብ ይቸግራል።

ይሁንና በህግ የበላይነት ስልጣን ላይ የሚወጣ እና የሚወርድ እንዲሁም ግልፅነት እና ተጠያቂነት በህግ ፊት የሚረጋገጡበት መንግስታዊ ስርዓት መስርቶ ለማለፍ እንዲችል ታሪክ ለዚህ መሪ ወርቃማ ዕድል ሰጥታለች። ከራሱ እና ከድርጅቱ በላይ ለህግ የበላይነት መስፈን ከቆመ መላው ዜጋ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ጥርጥር የለውም።

አሁንም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሲናገር ‘… ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል መንግስት’ ሊኖረን ይገባል አሰዘወአ~ቸአብሏል። ከወያኔ ተፈጥሮ አንፃር ሲታይ ይህን መፈፀም በውነቱ ከባድ ይመስለናል። ለምሳሌ ስሙን እንጂ ማንነቱን የማናውቀው የወያኔ ደህንነት ሚኒስትር ጌታቸው አሰፋ ህዝብ አለቃው ሲሆን ከተደበቀበት መጋረጃ ወጥቶ ለአለቃው ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለስራ አፈፃፀሙ ሪፖርት ሊያደርግ ግድ ነው።

የደህንነት ሹም ብቃት የሚለካው ንፁሀን ዜጎችን ቀን ተሌት እያሳደዱ በማጥቃት ፣ መግደል እና ወህኒ ማጎር አለመሆኑንም በተቋም ደረጃ ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ይሆን? መልኩን እንኳ የማናየው እና የማናውቀው ሰው እንዴት አድርጎ ለደህንነታችን ዋስትና ይሆናል? የዚህ አይነቱ ድብቅ ሚኒስትር በየትኛው አገር ታይቶ ያውቃል?…

የቤተ-መንግስት በግ እየተባለ ሲንጓጠጥ የቆየው ሀይለማርያም ቢያየው ቢያየው ከወያኔ ጋር ተጉዞ ሁሉም መንገድ ወደ ሲኦል የሚያደርስ መሆኑ ሲገለፅለት ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል ወንበራቸውን መልሶ አስርክቧቸዋል። ላለፉት 6 ዓመታት ወያኔዎቹ እሱን ከፊት ጎልተው ላፈሰሱት የንፁሀን ደም ፣ ለበተኑት ቤተሰብ ፣ አካለ ጎደሎ ላደረጉት ዜጋ ፣ በየወህኒው ለዘለዘሉት የሰው ስጋ ፣ ዝርፊያ እና ጭፍጨፋ ተጠያቂ ከመሆን የሚድነው እሱ በለቀቀው ወንበር ላይ የተተካው ሰው እውነትም ህዝብ የሚጠይቀውን ፍትሀዊ ስርዓት ማስፈን ሲችል ብቻ ይመስለኛል። ሀይለማርያም ወንበር መልቀቁ እሱ እንዳለው እውነትም ለፍትህ መባት ምክንያት ሆኖ ከተገኘ ቢያንስ በሂደቱ ሚና ተጫውቷል ያሰኛል። አለበለዚያ ጉልቻ ብቻ ቀያይሮ አሁንም የሚቀርብልን የአሞራ ስጋ ከሆነ የረከሰውን መአድ ከመድፋት ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

በባዶ ተስፋ መቀጠል አይቻልም።

አሁን እንደሚታየው በሲቪል አገልግሎቱ ዘርፍ ህወሃት እንደ ቀድሞው እንዳሻው የሚያዝ የሚፈነጭበት ሁኔታ የተዳከመ ይመስላል – ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ህወሃት ገንኖ ሲወጣ ሁሉም ነገር ፀረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ይሆናል። ዘረፋ ገሀድ ይወጣል ፣ በማን አለብኝነት እብሪት የተወጠሩ ካድሬዎቹ ባልተፃፈ ህግ በያቅጣጫው ሲፈነጩ እናያለን ። ከቀሪዎቹ ሶስቱ ድርጅቶች አንዱ ወይንም ሁለቱ ጠንክረው መቆማቸውን የምናውቀው ደግሞ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በፖለቲካው መድረክ ጎልተው ሲነሱ ነው።

ይህ በተጨባጭ የሚያመለክተው ህወሃት የለየለት ፀረ-ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለከት የሌለው ሙሰኛ የስግብግብ እና ልክስክስ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን ነው። በውነቱ የትግራይ ህዝብ የተለየ ጥቅም አለኝ ብሎ በፖለቲካ ድርጅት መወከል ካለበት ታሪኩን ፣ ጨዋነቱን ፣ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ቡድን ሊመሰረት ይገባዋል – ህወሃት አይመጥነውም።

በወያኔ አገዛዝ ፍትህ እና ርትዕ ተጓደለ ፣ ሰብአዊ ክብር ተዋረደ ፣ ድህነት ተንሰራፋ ፣ ስደት ተባባሰ ፣ ሰው በሥራው እና በብቃቱ ሣይሆን በዘር ግንዱ እና በወላጆቹ ፣ በአያት ፣ ቅድመ-አያቶቹ የቋንቋ አይነት ተፈረጀ። ሃሳብ እና አመለካከት የሚመዘነው የሰውን ልጅ የአገርን ዕድገት ከማፋጠኑ ወይንም ማጓተቱ አኳያ ፣ ወይም የአገርን ዘላቂ ጥቅም ከማስከበሩ አንፃር ሳይሆን የማንኛው ዘር ፣ የየትኛው ቄየ አቋም ነው በሚል መለኪያ ሆነ። የበቃ – የተባ ጥበብ ያካበቱ አገር እና ወገን ወዳድ ዜጎች እንደ አልባሌ ዕቃ ተጥለው ለሰብአዊ ክብር ቅንጣት ደንታ የሌላቸው ጥራዝ ነጠቅ ካድሬዎች የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል እንዲወስኑ ተደረገ።

በቄሮ መራራ ተጋድሎ ውስጥ አርበኝነት ጎልቶ ይታየኛል። አርበኝነት (Patriotism) ያገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ወይም አገር ጠላት እጅ መውደቋ ሲታወቅ ወይንም በወገን ላይ ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት የሚቀሰቀስ አገርን ከውርደት ፣ ወገንን ከጥቃት ለማዳን የሚደረግ በዜጎች ህሊና ውስጥ ሰርፆ ያለ ፍፁም እራስን አሳልፎ የመስጠት ታላቅ የመስዋዕትነት ስሜት ነው። ከምንም ነገር (ከቤተሰብ፣ ንብረት፣ ሀብት … ወዘተ) በላይ የአገርን ህልውና እና የወገንን ክብር ያስቀደመ እስከ ሞት ድረስ ሊመጣ የሚችለውን መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ተገንዘቦ እና ፈቅዶ የሚሰለፉበት ቆራጥነት የተላበሰ አቋም ነው።

በእርግጥም በየትኛውም አለም እንደታየው የማንነት መሠረት ሲናጋ ፣ ዜጋ ባገሩ በቄየው ሲዋረድ – ላገር ህልውና ፣ ለታሪክ ክብር እና ለወገን ፍቅር ሲባል አገርን ከጠላት ለመታደግ የሚደረግ የአርበኝነት ተጋድሎ ክቡር ነው። በአገራችንም ቢሆን

ዘመድ አዝማድ ቢሞት ባገር ይለቀሳል

አገር የሞተ ‘ንደሁ ወዴት ይደረሳል

በሚል ጥልቅ ምሬት ላይ ተገንብቶ የቆየ በታሪክ ዘንድ የክብር ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ሳልደብቅ ልናገር – መታወቂያችንን መልሶ “ኢትዮጵያዊ” ያደረገው ቄሮ ውስጤ ነው!