ቦታው ሰሜን ጎንደር በለሳ ወረዳ ነው። ከአፄ ሲስኒዮስ ቤተመንግስት ባሻገር ይገኛል። በልጅነታችን ከምንፈራው ቦታ መካከል አንዱ ነው። ባለቤትነቱን ማን ለሰይጣን እንደሰጠው ግልፅ አይደለም። የጠየኳቸው ሰዎች ሁሉ ሊያስረዱኝ አልቻሉም። ምንጩን ስለማያውቁት ይመስላል፣ የሰይጣን መንገድ ብለውታል። ተፈጥሮው ትንግርት ሆኖባቸው ይመስለኛል።

ይህ ከዋናው የመሬት ገፅታ ጉብ ብሎ የሚታይ የድንጋይ ክምር “የሰይጣን መንገድ” ተብሎ ይጠራል። ግራኝ አህመድ ከቆሰለበት ግራኝ በር የሚባል ቁልፍ ቦታ በለሳን ተሻግሮ እስከ ወገራ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር የሚያቋርጥ እንደሆነ ይነገራል። በትንሹ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚያቋርጥ ማረጋገጥ ችያለሁ።

የ”ሰይጣኑን መንገድ” ሰይጣን የሚንሸራሸርበት ይመስለን ስለነበር አንቀርብም፣ ብንቀርበው እንኳ ለረዥም ጊዜ አንቆይበትም። ስናድግ፣ ከመልመድም ላዩ እየወጣን ጅራፍ እናጮህበት ነበር። ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ ጅራፍ ለማጮህ ስለሚመቸን ነበር።

የ”ሰይጣኑ መንገድ” ከዛንተራው የሲስኒዮስ ቤተ መንግስት ተሻግሮ ከበለሳ እስከ ወገራ የሚያቋርጥ የመሬት ገፅታ ነው። የበለሳን ዝቅታ ተሻግሮ የእምባጫራን እና የወገራን ከፍታዎች ያገናኛል።

የዛንተራ ቤተ መንግስት ደንቀዝ ላይ ይገኛል። ከስሩ ያለው ገደል ከበለሳ ይለየዋል። ይህ ዝንጀሮ ካልሆነ በስተቀር የሰው ልጅ የማይዘልቀው ረዥም ገደል ለቤተ መንግስቱ የተፈጥሮ ምሽግ ነው።

ሆኖም ከገደሉ ማዶ ያለው የበለሳ መሬት ከወሎ፣ ለትግራይ እና ከሌሎችም አካባቢዎች ጥቃት የሚሰነዘርበት ነው። ለምሳሌ አህመድ ግራኝ ይህን አካባቢ የ”ሰይጣኑ መንገድ” ወደሚያገናኘው እምባጫራ ለመውጣት እንደተጠቀመበት ይነገራል።

የ”ሰይጣኑ መንገድ” አስገራሚ የሚሬት አቀማመጥ አለው። ከከፍታው ባሻገር ስትራቴጅያዊ ቦታዎች ላይ የተሰራ ነው። አብዛኛዎቹ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከዛንተራው ቤተ መንግስት ወይንም ወደ ቤተ መንግስቱ መውጫ በሮችን መቆጣጠር የሚያስችል ነው። ከዛንተራው ቤተ መንግስት ባሻገር ያለውን ቦታ ለመቆጣጠር የሚያስችል በተለይም ቆላውን የበለሳ ክፍል ጠላትን ለመቆጣጠር ከሚታስችለው ሁለቱ ደጋማ ቦታ ጋር የሚያገናኝ ነው።

የ”ሰይጣኑ መንገድ” በጠንካራ ድንጋይ የተማሰ ከጥንካሬው አንፃርም ተፈጥሯዊ የሚመስል የመሬት ገፅታ አለው። ሁለቱን ደጋዎች ያገናኛል የተባለው እና እኔም እስከ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ያለውን እንደታዘብኩት ወጥ ስራ ነው።

ተራራማው ክፍል ላይ ያለው የመንገዱ ክፍል አሁንም ድረስ በግልፅ የሚታይ ሲሆን የሚታረሱ መሬቶች ላይ ያለው ፈራርሷል። ተራራው ላይ ያለውም ለመለየት ከሚያስችለው ውጭ ባለፈው 10 አመት ከነበረው እንኳ አብዛኛው ፈራርሷል። ሆኖም የሚታረሱ መሬቶች ላይም ቢሆን ከመንገዱ የወጣ በርከት ያለ የድንጋይ ክምር ያለባቸው ቦታዎች ይስተዋላሉ። ይህን ለተመለከተ የ”ሰይጣኑ መንገድ” ከተፈጥሯዊነቱ ይልቅ ሰው ሰራሽ ነው ብሎ ለመገመት ያስደፍራል።

ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ ወጥ የሆነ እና ሁለት ደጋዎችን የሚያገናኘው ይህ የ”ሰይጣን መንገድ” ወጥነቱ፣ ስትራቴጅያዊ አቀማመጡ፣ እና ቤተ መንግስቱን ጠላት ከሚያዘወትሩባቸው አካባቢዎች የሚከልል መሆኑ ምን አልባትም ኢትዮጵያውያን እንደ ቻይና ሁሉ የራሳቸውን ታላቅ ግንብ ሰርተው ነበር ወደሚል መላ ምት ይወስዳል።

ይህ መላ ምት እውነት አይደለም ከተባለ እንኳ ይህ ወጥ የመሬት ገፅታ በተፈጥሮ የተገኘ ሆኖ ግን እንዴት የሚለው ምርምር የሚያሻው ይሆናል። ሁሉንም መላ ምት ስለ መሬት ተፈጥሮ፣ ቅርስና ታሪክ የሚያጠኑ ቢጎበኙት አንድ የተለየ ነገር ያገኛሉ የሚል ግምት አለኝ! እኔ ምርምሩን ባልችልም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ!

እንደ አለመታደል ሆኖ የአፄ ሲስንዮስ ቤተ መንግስትንም ዞር ብሎ የሚያየው አልተገኘም። ለቤተ መንግስቱ ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ የዚህን አስገራሚ ተፈጥሮ (የሰይጣኑ መንገድ) ሚስጥርም እስካሁን ባወቅን ነበር።

ጌታቸው ሺፈራው

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *