በእስር ላይ የሚገኙት የኬኬ ድርጅት ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ አረም ለማስወገድ የ20 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ሰጡ።

አቶ ከተማ ከበደ፣ ዕርዳታውን ያደረጉት በወኪላቸውና በድርጅታቸው  ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በአቶ ቦጋለ ማሞ አማካይነት ነው፡፡

የኬኬ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት አቶ ከተማ ከበደ ዕርዳታውን ያደረጉት በሁለት መንገዶች ነው፡፡ —  በጥሬ ገንዘብና ማሽን በመግዛት፡፡Bilderesultat for አቶ ከተማ ከበደ

ስጦታው የተበረከተውም ለአማራ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢና ደን ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በላይነህ አየለ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ይሄው እርዳታም በጥሬ ገንዘብ 15 ሚሊዮን ብርና አምስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ማሽን መሆኑን አቶ ቦጋለ ተናግረዋል፡፡

አቶ ከተማ ‹‹የእኔና የድርጅቴ መኖር ደስ የሚለውና ውጤታማ የሚሆነው ከአገሬ ጋር ነው፤›› ሲሉ እስር ቤት ሆነው ዕርዳታው እንዲደርስላቸው መልእክት መላካቸው ተነግሯል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በጥሬ ገንዘብ ከተሰጠው አስራ አምስት ሚሊዮን ብር አሥር ሚሊዮኑ ሰባት የአረም ማስወገጃ ማሽን ሊገዛ ይችላል፡፡

የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በላይነህ አየለ ዕርዳታውን አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ አንድ ማሽን ተገዝቶ አረሙን የማስወገድ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ማሽኑ አረሙን ከሰበሰበ በኋላ ወደ ውጭ መጣል ስለሚያስፈልግ፣ ይኼንን ችግርና በአጠቃላይ እምቦጭ አረምን ለማስወገድ፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት ያደረጉት ዕርዳታ ጥሩ ድጋፍ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ከማሽን ጋር በተያያዘ የነበረውን ችግር ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እንደሚፈታላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ከተማ በለገሱት ገንዘብ የሚገዙት ማሽኖችም ሆኑ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ገዝቶ በዕርዳታ የሰጠውን ማሽን፣ ወደ ሐይቁ ለማስገባት መንገድ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እስካሁን በሌሎች ግለሰቦችና ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከገዛው ማሽን ጋር ሦስት ማሽኖች እንዳሉ ዶክተር በላይነህ ገልጸዋል።

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 1/2010)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *