በግሎባላይዜሽን ፍልስፍና በገበያ ትስስር ዓለምን አንድ የገበያ መንደር አድርገው ድሃውን በሀብታሙ ለማስበዝበዝ በመጣር ደፋ ቀና የሚሉት ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅቶች ፍልስፍናቸው እየሠራ ለመሆኑ ራሳቸው የራሳቸው ምስክር ለመሆን አፍሪካም እያደገች ነው

ጌታቸው አስፋው – የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ – የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ግቦችና ዓላማዎች እንደ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ግቦችና ዓላማዎች በጽንሰ-ሐሳቦች ትንታኔና ጥናት ላይ ተመርኩዘው በባለሙያዎች ብቻ የሚነደፉ አይደሉም፡፡ በሐሳብና በአስተያየት ላይ ስለሚመሠረቱ የፖሊሲ መሣሪያዎቹ በተቻለ መጠን የብዙ ሰዎችን፣ በተለይም የተጠቃሚዎችን በቂ ተሳትፎ ይፈልጋሉ፤ አንድ ወጥም አይደሉም፡፡ ስለሆነም የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች በአብዛኛው የሐሳብ ማስፈጸሚያ የጉዞ ካርታ ከሆኑ ስትራቴጂዎች ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው፡፡

የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ግቦችና ዓላማዎች መሠረተልማትን መገንባት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ፤ ድህነትን መቅረፍ፣ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ ገበያው ሊያቀርባቸው ያልቻሉ ምርቶችን በቀጥታ በመንግሥት ድርጅቶች ማምረት የመሳሰሉ ናቸው፡፡ የእነኚህ ግቦችና ዓላማዎች የፖሊሲ መሣሪያዎች ስትራቴጂዎች በዝርዝር የተዘጋጁ የአምስት ሦስትና ሁለት ዓመታት ብሔራዊ ዕቅዶች ይባላሉ፡፡ የልማት ቅንብሮቹ እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያዩ እንጂ ወጥ የሆነ ዓለም ዐቀፋዊ ጽንሰ-ሐሳብ የላቸውም፡፡

ፖሊሲ ዓላማን፣ የተፈጻሚነት ጊዜና ቦታን፣ አስፈጻሚው አካል ማን እንደሆነ ጠቅሶና ሥልጣን ባለው ከፍተኛ የአመራር አካል ተደንግጎ በኦፊሴላዊ ዶኩሜንት የሚወጣ ሕግ ሲሆን፣ ስትራቴጂ ግን የተመረጠ የልማት ግብ ላይ ለመድረስ በከፍተኛ ወይም በመካከለኛ ባለሥልጣን ውሳኔ፣ የሰውና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም የሚደለደልበት የጉዞ ካርታ ወይም ዕቅድ ነው፡፡

ስትራቴጂዎች እንደ ፖሊሲዎች በበላይ አካል ተነድፈው እንዲተገበሩ ለበታች አካላት እንደ ሕግ የሚሰጡ ትዕዛዞች ሳይሆኑ የፈጻሚው የቅርብ አለቃና ፈጻሚው ከብዙ አማራጮች ውስጥ ሥራችንን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን ይረዱናል ብለው የሚመርጧቸው ከሌሎች አማራጮች የሚሻሉ ናቸው የሚሏቸው መንገዶች ናቸው፡፡ አማራጮቹን መርጠው ለማስጸደቅ ለበላይ አካል ያቀርባሉ እንጂ በበላይ አካል ተቀርጸው ወደ ታች አይንቆረቆሩም፡፡

በታዳጊ አገራት የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪ ፖለቲኞችና የኢኮኖሚ ልማት ውሳኔ ሰጪ በባለሙያዎች ወይም በምሁራን መካከል ያለው አለመግባባትም የሚመነጨው፣ የልማት ስትራቴጂ አመንጪ ምሁራን ከፖለቲካ ባለሥልጣኑ በላይ ኃይልና አቅም አለን ብለው ስለሚያስቡ፣ ለፖለቲካው ያላቸው ታማኝነት ላይ ላዩን ብቻ ሲሆን፣ ፖለቲከኛውም ባለማወቁ እየፈራ ባለሙያውን እየተሸማቀቀ ስለሚያዝ ነው፡፡

ይኽ የሁለቱ ግጭትና መናናቅ አንዳንዴ በኢሕአዴግ አስተዳደር ውስጥ ጎልቶ እንደሚታየው ፖለቲከኛውን ፈሪ ተናካሽ አረመኔ አውሬ ሲያደርገው፣ ባለሙያውን መስሎ አዳሪ፣ በሁለት ቢላ፣ የሚበላ የአለቃውን ውድቀት የሚናፍቅና በሥራው ላይ ቸልተኛ ውስጥ ውስጡን ከተቃዋሚ ጋር ልብ ለልብ የሚናበብ ያደርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂዎችን ቀይሳ ተግባራዊ ማድረጓን በሚታዩት ሕንፃዎችና መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎች መሠረተልማቶች በቂ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳላት አድርገው የሚገምቱና ፖሊሲን እና ስትራቴጂን የሚያምታቱ ሰዎች አሉ፡፡ ይኽ እውነት ቢሆን ኖሮ የ2008፣ 2009 እና 2010 ዓ.ም. ሁከቶችና ብጥብጦች ባልተነሱ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ኒዮ-ሊብራሎች የምትላቸው ሳይቀሩ ያላቸውን የሠራተኛ ገበያውን የምትቆጣጠርበት ዝቅተኛው የሠራተኛ የሥራ ሰዓት ክፍያ ዋጋ ተመን ፖሊሲ የላትም፤ የሥራ አጥ ችግር መፍትሔ ፖሊሲ የላትም፤ የዋጋ ንረት መቆጣጠሪያ ፖሊሲ የላትም፤ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን ብሔራዊ ባንኩ በውስጥ ፖሊሲው ወይም በሕግ አስፈጻሚው ትዕዛዝ እንደፈለገው ይጨምራል ይቀንሳል እንጂ ከሕግ አውጪው የተሰጠውና የሚመራበት ቋሚ ፖሊሲ የለም፤ የገንዘብና የካፒታል ገበያ ፖሊሲዎች የሏትም፡፡

የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቋሚና የብዙ ጊዜ ሕግ ሲሆን፣ ስትራቴጂ ጊዜያዊና የአጭር ጊዜ ችግርን ለመቅረፍ የሚነደፍ የዕቅድ ማስፈጸሚያ ሥልት ሊሆንም ይችላል፡፡ በዚህም መሠረት የልማት ኢኮኖሚ አመለካከትን ለማሳካት የድህነት ቅነሳ ስትራተጂዎች፣ የምዕተ ዓመት ግብ ማሳኪያ ስትራቴጂዎች ተነድፈው ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የድሆች ጉዳይ እኛንም ያገባናል የሚሉ እርዳታ ሰጪና አበዳሪ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችም በእነዚህ ስትራቴጂዎች አነዳደፍ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ፤ አፈጻጸምን ይከታተላሉ፡፡

በብሔራዊ የልማት አቅጣጫ አመላካች ስትራቴጂዎች ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ያልሆኑ በርካታ ፖሊሲዎች ሊታቀፉም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ፣ በምዕተ ዓመት ግብ ማሳኪያ ስትራቴጂ፣ በግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ስትራቴጂ፣ በክፍለ ኢኮኖሚ ደረጃ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ፖሊሲ፣ የንግድ ፖሊሲ፣ የጤና ፖሊሲ፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ በፕሮግራም ደረጃም የምግብ ድጋፍ ፖሊሲ፣ የማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲ በመባል በርካታ ፖሊሲዎች ሊነደፉ ይችላሉ፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የልማት ኢኮኖሚ ስትራቴጂ አራምባና ቆቦ ሊሆኑም ሲችሉ እንዲያው በጥቅሉ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ፖሊሲና የልማት ስትራቴጂ ልዩነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመደበኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ቋሚና በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይለወጥ ሕግ ደንብና መመሪያ ሲሆን፣ የልማት ስትራቴጂ ግን በየጊዜው የሚለዋወጥ የጊዜያዊ ችግር መፍቻ አማራጭ መንገድና ስልት ነው፤
2. ፖሊሲ አስገዳጅ ሕግ ነው፤ ስትራቴጂ በፈቃደኝነት የሚወሰድ አማራጭ ነው፤
3. የኢኮኖሚ ፖሊሲ የከፍተኛ አመራር ሰጪዎች ውሳኔ ሲሆን፣ የልማት ስትራቴጂ ግን የከፍተኛም የመካከለኛም አመራር ውሳኔ ሊሆን ይችላል፤
4. የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአመለካከትና የሐሳብ መተግበሪያ መርህና መመሪያ ነው፤ የልማት ስትራቴጂ ግን የድርጊት መርሐ-ግብር ነው፤

እንደ የኢኮኖሚው ሥርዓት፣ የመንግስት ቅርጽና የዕድገት ደረጃ የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይነደፋሉ፡፡ ሶሻሊስቶች የሶሻሊዝም ኢኮኖሚ ፖሊሲ ይነድፉ ነበር፡፡ የበለጸጉ ካፒታሊስት አገራት የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ይነድፋሉ፤ ታዳጊ አገራት የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ይነድፋሉ፡፡ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በግብርና የሚተዳደሩ አገራት የግብርና ፖሊሲ ላይ ያተኩራሉ፣ ወደ ውጭ ንግድ የሚያዘነብሉ አገራት የውጭ ንግድ ፖሊሲ ይነድፋሉ፤ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ለመተካት አገራት የአገር ውስጥ ምርት እድገት ፖሊሲ ይነድፋሉ፡፡

ደርግ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም የአመለካቱ መመሪያ እንደሆነና ፖሊሲዎች የሚቀረጹትም ከጽንሰ-ሐሳቡና ከተጨባጭ ሁኔታዎች አመለካከቱ ተነስቶ እንደሆነ ለሕዝብ ነግሯል፤ የውይይት ክበብ በየመሥሪያ ቤቱ አቋቁሞ የፖለቲካው አባላትም አባላት ያልሆኑም ተወያይተውበታል፡፡ ሕፃን ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ፣ ገጠሬ ከተሜ፣ የፓርቲ አባል የሆነ፣ አባል ያልሆነ፣ ሳይባል ሁሉም እንዲያጠናው ተደርጓል፡፡ አንድ የውይይት ክበብ ስብሰባ ላይ አንድ አዛውንት ሌኒን እንዳለው ብለው ያልተባለ ነገር ሲናገሩ ‹ሰብሳቢው መቼ ነው ደግሞ ጓድ ሌኒን እንደዚህ ያለው?› ብሎ ቢጠይቃቸው፣ ‹እርሱ ያላለው ነገር የለም ብዬ ነው› ብለው ተሰብሳቢውን አስቀዋል ይባላል፡፡

ሶሻሊስት ፖሊሲ ተሳትፏዊ ስለሆነ ፖሊሲውን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የፓርቲ አባልም አባል ያልሆነም ሊያወቀው ይገባ ነበር፡፡ የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ልማታዊ መንግሥታት መንግሥታትም የአገራቸውን እና የመንግሥታቸውን ፖሊሲ ጠንቅቀው ያውቀሉ ያምኑበታልም ለማስፈጸምም እስከ የደም ጠብታ ድረስ ይቆሙለታልም፡፡

ኢሕአዴግ የሚከተለው የፖለቲካ አመለካከት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ይባላል፣ ልማታዊ ዲሞክራሲ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን እነኚህ አመለካከቶችና ጽንሰ-ሐሳቦች ወደ ሕዝቡ መስረጻቸው ፖሊሲዎች ከአመለካቶቹና ጽንሰ-ሐሳቦቹ ምን ያህል የተገናዘቡ መሆናቸውም አይታይም፤ አይታወቅም፤ አይታመንም፡፡ ልማታዊ መንግሥት ነን የሚለው የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ እስያውያን የኢኮኖሚ አስተዳደር ዘይቤን እንከተላለን ቢባልም፣ እነርሱን እንመስላለን ከሚለው በላይ ልማታዊ መንግሥት ምን ምን እንደሚሠራ፣ ልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴሉ በትክክል ምን እንደሆነ ለሕዝብ ቀርቶ ለአብሳሪዎቹም ግልጽ አይደለም፡፡

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በማዕከል በድርጅቱ ተሰብስበው እናደርገዋለን ብለው ያሉትን የተስማሙበትን በክልል ድርጅቶቻቸው ለየብቻ ተሰብስበው ከክልላቸው አንጻር ሲመለከቱት፣ በማዕከል ያመኑትን አፍርሰው ክልላዊ አቋም ይይዛሉ፡፡ ይኽ እንግዲህ ልማታዊ መንግሥት የሚለው በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ ያልተተነተነና ግራ የሚጋባ ከመሆንም በላይ በጎሳ ፌዴራሊዝም ውስጥ እንዴት ይተገበራል የሚለውም ተጨማሪ ራስ ምታት ነው፡፡

የኢሕአዴግ ተቃዋሚ የትግራይ ምሁራን ትግራይ ከሌሎቹ ቀድማ ልታድግ የቻለችው በትግራይ የተለየ የማስፈጸም አቅም ስለተገነባ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ትክክል ይመስሉኛል፡፡ ምክንያቱም በማዕከል ያሉ የሕውሓት አባሎችም ከኢሕአዴግ ብሔራዊና አገራዊ አጀንዳ ይልቅ የክልላቸውን አጀንዳ ያስቀድማሉ፡፡ ኦሕዴድ ብአዴን ደኢሕዴንም እንደዚሁ ነው፡፡

ይኽ የክልላቸውን አጀንዳ ማስቀደም የልማታዊ መንግሥት አገራዊ አጀንዳን እንደሚጻረር ግን በግልጽ አይናገሩም፡፡ ሰው ሁለት ተቃራኒዎች በአንድ ጊዜ አያገለግልም፡፡ ኬኩን በአንድ ጊዜ የጥቂቶች አድርገን በተመሳሳይ ሁኔታ የሁሉም ማድረግ አይቻልም፡፡ ወይ ለጥቂቱ ብቻ ወይ ደግሞ ለሁሉም መሆን አለበት፡፡

ለታዳጊ አገራት በልክ የተሰፋ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ
ምዕራባውያን የበለፀጉ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ገና ጨቅላ በነበረበት ወቅት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ካፒታሊዝም ሥርዓት እንደተጀመረ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎቻቸውን በገበያ ተጨባጭ ሁኔታ በማጥናትና በመተርጎም የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከቶችና ጽንሰ-ሐሳቦች ነድፈው ኢኮኖሚያቸውን መርተዋል ከአመለካከቶችና ጽንሰ-ሐሳቦች ተነስተውም የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ቀርጸዋል ዕቅዶችንም አዘጋጅተው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ 
የዛሬ ታዳጊ አገራት የኢኮኖሚያቸውን ተጨባጭ ሁኔታ በገበያ ኢኮኖሚ አመለካከቶችና ጽንሰ-ሐሳቦች ሳያጠኑና ሳይመረምሩ የአብዛኛው ሕዝባቸው የኑሮ ደረጃ ከመሬት ንቅንቅ ሳይል ሕዝቡ እንደ አዋቂ ተገበያይ ሸቀጦቹን በውድድር ላይ ተመስርቶ መነጋገድ ሳይችል በፊት በልማት ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ አትኩረው ጥሬ ገንዘብ እንደልባቸው ገበያ ውስጥ በመርጨት ከውጭ በሚገኝ ብድርና እርዳታ ተመክተው የሕዝባቸውን ፍጆታ ከኢኮኖሚው የማምረት አቅም አስበልጠው ላይ ላዩን እየጋለቡ ነው፡፡

ታዳጊ አገራት ሁለቱን የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከት ምዕራፎች ማለትም የሊብራል ገበያ ኢኮኖሚን እና በፖሊሲ የሚመራ የገበያ ኢኮኖሚን ጥበብ በወጉ ሳያውቁ ሦስተኛ ደረጃ የልማት ኢኮኖሚ አስተዳደርን ደርበው በኢኮኖሚ ልማት ካድሬዎች መሪነት በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋት ባልተደገፈ አካሄድ መጓዝና በምኞት መጋለብ ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ኢኮኖሚያቸውን የነቶሎቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ አደረጉት፡፡

ይኽ የሆነበት ምክንያትም ፖለቲከኞች የአገርን ሀብት በእጃቸው አድርገው የኢኮኖሚ አቅማቸውን ካልገነቡ አገር የመምራት ፖለቲካዊ ሥልጣን ከእጃቸው እንደሚወጣ አድርገው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ሰዎች በነጻ ገበያ በውድድር ሀብት እንዳያገኙ ካድሬዎች ኢኮኖሚስቶችን ተክተው ስለልማት እንዲሰብኩ በማድረግ ሕዝብ ስለ ልማት እንጂ ስለ የገበያ ኢኮኖሚው እንዳያውቅ ማድረግ ዋና ዓላማቸውና ቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡

ስለኢኮኖሚ ጥበብ ምንም የማያውቁ ጋዜጠኞች ከኢኮኖሚ መጽሔቶች እየቃረሙ ትንታኔ እንሰጣለን በሚሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ውስጥ ስለ ገበያ ኢኮኖሚ ሕዝብ የሚያውቀው ነገር አይኖርም፡፡ የቢዝነስ ዘገባ፣ ሚዲያ ዳሰሳ፣ ኑሮና ቢዝነስ፣ ወዘተ. እያሉ የተለያዩ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ቀርጸው የማያውቁትን ሲቀባጥሩ የሚታዘብ ሰው ያለ አይመስላቸውም፡፡

እንደ ቢቢሲን፣ አልጀዚራን፣ ሲኤንኤንን በመሳሰሉ ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በሰነዶች ዋጋ መለኪያ አመልካቾች መውጣትና መውረድ፤ ስለ ጠቅላላው ኢኮኖሚ ሲተነትኑ ሰምተው የአማኑኤል ገበያ ጆንያ ጤፍ ዋጋ፣ የአትክልት ተራ ኪሎ ድንች ዋጋ ብለው የቢዝነስ ትንታኔ ሰጠን ይላሉ፡፡

ታዳጊ አገራት የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን እንዳያውቁ ምክንያት የሆኑት የድሆች ጉዳይ እኛንም ያገባናል የሚሉ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እና የታዳጊ አገራትን ጥሬ ዕቃ ከመበዝበዝ አንጻር ብቻ የሚመለከቱ የበለፀጉ አገራት የብድርና የዕርዳታ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ በዚህ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የልማታዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብም የቀድሞዎቹ የዘመናዊነት ኢኮኖሚ ልማት እና የጥገኝነት ኢኮኖሚ ልማት አመለካከቶች በሰፊው ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡

የውጭ ድርጅቶችና ውጭ አገሮች በልማት ድጋፍ ፖሊሲያቸው በሚሰጡት ብድርና እርዳታ ታዳጊ አገራት የኢኮኖሚያቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይመረምሩ በዝርዝር ሳያጠኑና ሳይለኩ በፊት እነርሱ በሩቁ በናሙና አጥንተው በሚነግሯቸው የአገራት ማነጻጸሪያ መረጃዎቻቸው አማካኝነት በግምታዊ የኢኮኖሚ መረጃዎችና የልማት ውጤቶች ብቻ የግልቢያ የልማት ስትራቴጂዎች እንዲነድፉ አደረጓቸው፡፡ የድህነት ቅነሳ፣ የምእተዓመት የልማት ግብ ወዘተ. እያሉም የታዳጊ አገራት ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀያሾች እነርሱ ሆኑ፡፡ እነርሱ ያሉትን ያልሰማ እርዳታም ሆነ ብድር አያገኝም፡፡

የብድሩም ሆነ የዕርዳታው ገንዘብ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጣዊ ኃይሎች በሆኑት የገበያ ኢኮኖሚ ጽንሰ-ሐሳቦች ሕጎችና ደንቦች መሠረት ካልተጠናው ኢኮኖሚ ጋር መዋሐድ ተሳነው፡፡ ምርት ቢያድግም እንኳ በአደጉት አገራት በገበያዎች ውስጥ በውድድር አማካኝነት የሚከፋፈለው የሀብትና የገቢ ሥርጭት በታዳጊ አገራት ውስጥ በመንግሥት ሰጪነትና ነሺነት ክፍፍል ተዘበራርቆ መላቅጡ ጠፋ ጥቂቶች ከበሩ ብዙዎች ደኸዩ፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱን በልማት ስትራቴጂዎች ወይም ከገበያ ውጪ በሆኑ ኃይሎች ለማገዝና ለመደገፍ በተደረገው ሙከራ ሀብት የገበያ ኢኮኖሚን በማያውቁ ሰዎች እጅ ገብቶ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንሳፈፍ ነገር በዛ፡፡ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ሌላም ሀብት ሁሉም ነገር ተንሳፋፊ ሆነ፡፡ በድህነት በምትታወቅ አገር ውስጥ ረኀብ የብዙዎችን ሕይወት በሚቀስፍበት አገር ውስጥ ሀብቱን የሚጥልበት ቦታ ያጣ ያለረዳት ገንዘቡን መቁጠር መደመርና መቀነስ እንኳ የማይችል ከበርቴ ተፈጠረ፡፡ የመሃይም ሚልየነሮች ቁጥር በፍጥነት አደገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢልየነሮችም ተፈጠሩ፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጣዊ ኃይሎችን መርምሮ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ባለቤቶች የሚያሰራ ተስማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ መንደፍ ተዘንግቶ በመንግሥት በራሱ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችና ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦች አስተዳደር ላይ ማትኮር መረባረብ የኢኮኖሚ ልማትን ከገበያ ኢኮኖሚ ውጪ ማሰብ ሆነ፡፡

አንዴ የእነ ዓለም ባንክን የገበያ ኢኮኖሚ መዋቅር ማሸሻያ ፕሮግራም መቀበል ሌላ ጊዜ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ብሎ ቻይናን ለመቅዳት መሞከር፣ ጥቂት ቆይቶ ያለ የውጭ ቀጥታ መዋዕለንዋይ ልናድግ አንችልም ግሎባላይዜሽን ወይንም ሞት ብሎ ወላዋይ አቋም መያዝ ኢትዮጵያን እዚህም መጥተሸ በላሽ እዚያም ሄደሽ በላሸ ሰው ታዘበሽ እንጂ ሆድሽን አልሞላሽ አደረጋት፡፡

ልማታዊ ኢኮኖሚ ለሰው ልጅ በጎ አመለካከት ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ሀብትንና ብልጽግናን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ የተተለመ ጽንሰ-ሐሳብ ነው፡፡ ሆኖም በቂ ሀብት የሌላቸው ታዳጊ አገሮች ራሳቸው ያፈሩትንም በእርዳታና በብድር ያገኙትንም በካድሬዎች በተነደፈ አድሎአዊ ሞዴል ለማከፋፈል ሲሞክሩ፣ ጥቂቶች ሀብቱን ሁሉ ይዘው ለእኛ የሚለው የልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍና ለእኔ በሚል ስግብግብነት በመተካት ሽሚያ ስርቆት ብዝበዛ ሙስና ይሰፍናል፡፡

በሁለንተናዊ ልማት መስፈርቶች የታዳጊ አገራትን ሕዝቦች ሁኔታ ብንለካ፣ ለሰው ልጆች መልማት ምልክቶች ዋናዎቹ በሆኑት የድህነት መቀነስ፣ የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ፣ የገቢና የሀብት ይዞታ መራራቅ መቀነስ፣ የሰዎች ምርጫ መስፋት፣ የሌላው አቀንቃኝ ከመሆን በራስ ለመተማመን መቻል፣ መለኪያዎች ወደኋላ እንጂ ወደፊት እየሄዱ አይደለም፡፡ ይኽም ማለት የልማት ኢኮኖሚው ፍልስፍና ለሁለንተናዊ ልማቱ በቂ አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት ነው፡፡

የአንዳዶቹ ድህነት የቁሳዊ ዕቃዎች አጦት ሲሆን የሌሎቹ ድህነት የቁሳዊ ዕቃዎች ማጣት ሳይሆን ቁሳዊ ዕቃዎችን ለማግኘት ሲሉ ኅሊናቸውን ሽጠው ራሳቸውን ከሌላ ሰው ዝቅ አድርገው አቀንቅኖና አጎብድዶ መኖር ነው፡፡ በቁሳዊ ሀብት ትርጉሙ ድሆች ሀብት የሌላቸው ቢሆኑም በሥነልቦናዊው የልማት ትርጉም ባለጸጎች የሚመስሉ ድሆች ድሆችም የሚመስሉ ባለጸጎች ናቸው፡፡ የተማሩ የሚመስሉ በሰው ትዕዛዝ የሚኖሩ አላዋቂዎች፣ ያልተማሩ የሚመስሉም በኅሊናቸው ትዕዛዝ የሚኖሩ አዋቂዎች ናቸው፡፡

የታዳጊ አገራት የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ባደረጉት የብዙ ዐሥርት ዓመታት ጉዞ በተጠቀሱት ሁለንተናዊ የመልማት ምልክቶች ሕዝቦቻቸው በተለይም በራስ ኅሊናና በራስ ውሳኔ አለመኖር፣ ወደኋላ እንጂ ወደ ፊት አልተራመዱም፡፡

የልማት ኢኮኖሚ ካድሬዎች ስብከት ለሕዝቡ ‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ› ሆኗል፡፡ የሚናገሩት ስለ ዛሬ ሳይሆን ስለ ነገ ነው፤ ዛሬን ተርቦ ነገ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ስለ መግባት ነው፡፡ ሆኖም ግን ከገበያ ሁኔታ ያወቅነው ዛሬን ተርበን ነገንም የባሰ እንደምንራብ እንጂ ነገ እንደምንጠግብ የሚያሳዩ ምልክቶችን አናይም፡፡ የተሳፈርንበት መዣ አይሮፕላንም ሆነ ባቡር ወይም ጋሪ ከመካከለኛ ገቢ በፊት ወደ መካከለኛ ቀውስ እየወሰደን ነው፡፡

የገበያ ኢኮኖሚና የልማት ኢኮኖሚ በብልሀት ከተያዙ ይደጋገፋሉ በሞኝነት ከተያዙ ይጠላለፋሉ፤ ይጋጫሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት እየተደጋገፉም እየተጠላለፉም እዚህ ደርሰዋል፡፡ ቀን በገፋ ቁጥር ከመደጋገፉ ይልቅ መጠላለፉ እየበዛ ለመሆኑ የዋጋ ውጥንቅጡና የሕዝብ በመንግሥት አገልግሎት አለመርካቱ ማስረጃ ነው፡፡ አገሪቱ የተስተካከለ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ ይቅርና የተሟላ የገበያ ኢኮኖሚ መረጃም የላትም፡፡ ስለልማት ኢኮኖሚ እንጂ ስለገበያ ኢኮኖሚ መናገር አልተቻለም፡፡

በግሎባላይዜሽን ፍልስፍና በገበያ ትስስር ዓለምን አንድ የገበያ መንደር አድርገው ድሃውን በሀብታሙ ለማስበዝበዝ በመጣር ደፋ ቀና የሚሉት ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅቶች ፍልስፍናቸው እየሠራ ለመሆኑ ራሳቸው የራሳቸው ምስክር ለመሆን አፍሪካም እያደገች ነው ቢሉም፣ ኢኮኖሚያቸው ሕዝባቸውን ሊሸከም እንዳልቻለ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ባሕርና በረሃ አቋርጠው ወደ አውሮፓ የሚፈልሱ ወጣቶች ሁኔታ በቂ ማስረጃና ምስክር ነው፡፡

The Black Lion

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *