የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በተደጋጋሚ ጊዜ ቢራዘምለትም ሊያጠናቅቅ ያልቻላቸውን አንድ የስኳርና አንድ የአፈር ማዳበሪያ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፣ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ መቅረቡ ተገለጸ፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ግርማ አመነቴ (ዶ/ር) ሐሙስ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፣ የጣና በለስ ቁጥር ሁለት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ከሜቴክ ተነጥቆ በአዲስ ኮንትራክተር ሥራውን ለማስቀጠል እየተመከረ ነው፡፡

የኦሞ ኩራዝ አንድ የስኳር ፕሮጀክትና የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎችን ሜቴክ ባሉበት ደረጃ ላለፉት ሦስት ዓመታት ፈቀቅ ባለማድረጉ፣ መንግሥት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት መጠየቁን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ኬሚካል ኮርፖሬሽን ለፕሮጀክቱ ለወሰደው ብድር እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ 1.8 ቢሊዮን ብር ወለድ ለባንክ የተከፈለ መሆኑን፣ ፕሮጀክቱ ከዚህ በኋላ አዋጭ ስለመሆኑ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ሥጋት እንዳለው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሌሎቹ የስኳር ፕሮጀክቶች ተንዳሆ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ከሰምና ኦሞ ኩራዝ ሁለት ስኳር ፕሮጀክቶች ማምረት የጀመሩ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ወደ ሙሉ አቅማቸው አለመሸጋገራቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች 33.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 24 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የልማት ድርጅቶቹ ካለባቸው የአገር ውስጥ ብድር 24.5 ቢሊዮን ብር ለመመለስ ታቅዶ 18.9 ቢሊዮን ብር መከፈሉን ጠቁመዋል፡፡

የፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚኒስቴሩ በስኳር ፕሮጀክቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች በአስቸኳይ እንዲፈታ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ 

ሪፖርተር አማርኛ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *