የዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣትና የመጡበት ሂደት የህውሃትን መዳከም ያሳያል እንጂ የወያኔ-ኢህአዴግን ህዳሴ አያሳይም። እንደ እኔ እምነት ወያኔ-ኢህአዴግ የሚታደስም ድርጅት አይመስለኝም። ዶ/ር አብይ ይህን ዘመንኑ የጨረስ ሥርዓት ፍጻሜው ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን እና ኢትዮጵያንም ያፋፋማት የለውጥ ምጥ የቀለለ እንዲሆን ያደርጉልን ይሆናል እንጂ ከዛ ያለፈም ተአምር ሊሰሩ የሚችሉ አይመስለኝም


ያሬድ ኃይለማርያም
abye 123

የጠ/ሚ ሹመታቸውን ከያዙ ወር እንኳ ያልሞላቸው ዶ/ር አብይ አስገራሚ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ ባገኙ ማግስት በተደጋጋሚ፤ በተለይም በመቀሌ ባደርጉት ንግግር ተቃውሞን እያስተናገዱ ነው። በፓርላማ ባደረጉት ንግግር እጅግ ደስ ከተሰኙትና ተስፋም ከሰነቁት ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ። ደስታዮ አሁንም እንዳለ ነው። የሰነቅኩትም ተስፋ እንዳለ ነው። የተወሰኑ ጥያቄዎችም ተመልሰውልኛል። ቀሪዎቹም በሂደት ይመለሳሉ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ። ዋናው ቁምነገር ለምን በሳቸው ላይ ተስፋ አደረግን? ከእኚህ ሰው ምን ነበር የጠበቅነው? ተስፋ ያደረግናቸውስ ነገሮች ምን ምን ነበሩ? በምን ያህል ጊዜ ውስጥስ ተስፋችን እውን ይሆናል ብለን ገምተን ነበር? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን እያነሱ መወያየቱ ተገቢ ነው። ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ማግኘት አሁን የሚታየውን ብስጭትና ግለስቡን በዚህ ቅጽፈት የማጣጣሉ ችግር ምንስዔው ከወዴት እንደሆነ ለማየትም ያስችለናል። ችግሩ አንድም ከተስፋ አድራጊዎቹ አልያም ተስፋ ከተጣለበት ሰው መሆኑን በቅጡ እንድናይ ይረዳናል።

ለመሆኑ ተስፋ ያደረግነው፤ ወያኔ የተባለውን እኩይ ድርጅት ከምድረ ገጽ ያጠፉልናል ብለን ነው? ወይስ በአንዳች ተአምር ወያኔን በዲሞክራሲ የታነጸ፣ ለሕግ ተገዢና ሰብአዊ መብቶችን አክባሪ አድርገው እንዲቀይሩልን ነው? ወይስ እንደ አበደ ውሻ ግራ ቀኙን የሚናከሰውን ሥርዓት አፉን ለጉመው ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ ለሚታገሉ ኃይሎች መፈናፈኛ መድረክ ይፈጥራሉ በለን ነው? ወይስ የታሰሩ ወገኖቻችንን ነጻ እንዲወጡ አድርገው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጃቸውን አሽቀንጥረው ጥለው፣ ከተራ የፍቅርና የሰላም ፕሮፓጋንዳ ወጥተው አገራዊ መግባባትና እውነተኛ እርቅ የሚፈጠርበትን መድረክ ያመቻቻሉ ብለን ነው? ወይስ የወያኔ ሥርዓት ለ26 ዓመታት በጎነጎነው ጥላቻና የዘር ልዩነት ላይ የተጠነጠነ ፖለቲካ በአገር ላይ ያስከተለውን አደጋ ሊቀለብሱና በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ዘር ተኮር ግጭቶችን ያሳቆማሉ ከሚል ተስፋ ነው?

ለማንኛውም መነሻችን ምንም ይሁን ምን የሰውየው መልካምነት፣ አዋቂነትና ብቃት እንዳለ ሆኖ መዘንጋት የሌለብት ነገር ዶ/ር አብይ የወያኔ ተሿሚ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምጹ የመረጣቸው ሰው አለመሆናቸውን ነው። ወያኔ እኚህን ሰው ለመምረጥ ከገፉት ምክንያቶች መካከል አንዱ በአገሪቱ የታየው ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞዎች ቢሆንም የወያኔ ዕራዒ አስፈጻሚ መሆናቸው ግን መዘንጋት የለበትም። እኩይ ከሆነውና ለ26 ዓመታት በሕዝብ ስም ሲነግድ ከነበረው የወያኔ ሥርዓት ጉያ የወጡ ነገር ግን ደግሞ ቅን አሳቢ፣ አንድነትን ሰባኪ፣ ፍቅርን አንጋሽ ሰው ሆነው ስላገኘናቸው ነው። ዶ/ር አብይ በፓርላማ ውስጥ ያደረጉት ስሜት የሚነካ ንግግር አስደማሚና የብዙዎችን ቀልብ የሳበው እኮ የወያኔን ጡጦ እየጠባ አድጎ፣ በወጣትነቱ የነመለስ ዜናዊን ዲስኩር እየተጋተና እሱኑ እየተገበረ ከጎለመሰ ሰው ስለሰማነው ነው። እሳቸው የተናገሩትን ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አብሮነታችን ጥቅም፣ ስለ ፍቅር፣ ሙስና ስላሚያስከትለው አደጋ፣ ስለ አያቶቻችን አኩሪ ታሪክ፣ ወዘተ… ከወያኔ አጥር ውጭ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሲናገሩ፣ ሲያስተምሩ፣ ሲሰብኩን እና በተግባርም እየተሰው ሲያሳዩን እኮ ቆይተዋል። እነዚህ ስሜት ቀስቃሽና በሕዝብ መካከል ልዩነትን ሳይሆን ፍቅርን የሚዘሩ ንግግሮች ባለፉት 26 ዓመታት ከወያኔ መሪዎችም ሆነ ጭፍሮች ሳንሰማ በመቆየታችን፤ እንደውም በተቃራኒው ጥላቻና ክፍፍልን የሚያነግሱ፣ ታሪክን የሚያጠለሹና ኢትዮጵያዊነትን የሚያደቨዝዙ ንግግሮች በመንግስት ሚዲያዎች ጭምር ሲሰበክባት በመቆየቱ ነው።

የዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣትና የመጡበት ሂደት የህውሃትን መዳከም ያሳያል እንጂ የወያኔ-ኢህአዴግን ህዳሴ አያሳይም። እንደ እኔ እምነት ወያኔ-ኢህአዴግ የሚታደስም ድርጅት አይመስለኝም። ዶ/ር አብይ ይህን ዘመንኑ የጨረስ ሥርዓት ፍጻሜው ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን እና ኢትዮጵያንም ያፋፋማት የለውጥ ምጥ የቀለለ እንዲሆን ያደርጉልን ይሆናል እንጂ ከዛ ያለፈም ተአምር ሊሰሩ የሚችሉ አይመስለኝም። የለውጡ ኃይል  ዶ/ር አብይን ከወያኔ ፖሊሲዎች ሙሉ በሙሉ ነጥሎ፣ ነጻና ያሻቸውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሰው አድርጎ የሚያያቸው ከሆን ችግሩ ያለው ከወዲህ ነው።

በእኔ እምነት የሚሻለው የሰውየውን እርምጃዎችና በየመንደሩ የሚያደርጉትን ንግግር እየተከተሉና እሱን እያብሰለሰሉ እሳቸውን ከፍ ዝቅ ማድረግ አይመስለኝም። ተቃዋሚው ኃይል የተፈጠሩትን ክፍተቶችና አጋጣሚዎች በመጠቀም የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ላይ ጊዜውን ቢያጠፋ የተሻለና ለአገርም የሚበጅ ይሆናል። ለዚህም የሕዝባዊ ንቅናቄው መሪዎች በጋራ በመሆን ለዶ/ር አብይ አስተዳደር በጊዜ የተገደበና በቅደም ተከተል የተቀመጠ የእርምጃ ጥሪ ቢያደጉላቸው። ለተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ ሕዝባዊ አመጹ ሊቀጥል የሚችል መሆኑን ቢገለጽ። የንቅናቄ ኃይሉ ሊወሰድ የሚችላቸውን እርምጃዎችን አብሮ በጥሪው ላይ በዝርዝር መግለጽ። ከወዲሁም የተጠቀሱትን እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችሉ ዝግጅቶችንም ማከናውን ይበጃል።

ቸር እንሰንብት -ያሬድ ኃይለማርያም

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ምርጫውን ለማደናቀፍ ያሴሩ አካላት ህልማቸው አይሳካም – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *