ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የምርት ገበያውም የሠራተኛ ገበያውም፣ የካፒታል ገበያውም የመሬት ገበያውም መዛባታቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ አውቋል፡፡ የምርት ገበያው ዋጋ ሰው አስመርሯል፡፡ በሠራተኛ ገበያው ውጥንቅት ወጣቱ ትውልድ ሥራ አጥቷል፣ ለራስህ ሥራ ፍጠር፤ አለበለዚያ መሞት ወይም መሰደድ ትችላለህ ተብሏል፡፡


cheating

ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ  ዕቅድ ባለሙያ)

ብዙ ሰው መንግሥት ስለ ኢኮኖሚው ዕድገት የሚያቀርበው መረጃ እውነት ነውን? ለምንስ ሁልጊዜ በዐሥራ አንድ በመቶ ያድጋል? የሚል ጥያቄ በጭንቅላቱ ውስጥ ይመላለሳል፡፡ ዐሥራ ሦስት ዓመታት ድርቅ ሲኖርም ሳይኖርም፣ የውጭ ምንዛሪ እየተሟጠጠም፣ ሥራ አጥነት እየበረከተም፣ ኢኮኖሚው በዐሥራ አንድ በመቶ አደገ ይባላል፡፡ ይኽ የሕዝብ እንቆቅልሽ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ራስ ለራስ ምስክር መሆን አይከብድም፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የዓለምን አምስት እጥፍ የአፍሪካን ሁለት እጥፍ በሆነ የዕድገት መጣኝ በየዓመቱ እያሳደግን ለዐሥራ ሦስት ዓመታት ያህል ዘልቀናል፤ ከሚሉት የራስ ለራስ ምስክርነት የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ መረጃዎች ተነስተን፣ ከገበያው ሁኔታ ጋር አነጻጽረን የተደበቀውን እውነት ከተሸፈነበት መጠቅለያ በመግፈፍ እርቃኑን እናያለን፡፡

ዓይን ራሱ በቀጥታ አይቶ ስለሚለካና ስለሚገምት እንደ ጆሮ ከሌላ ሰው በሰማው አይታለልም፡፡ ራሱ ባዘጋጀው ስታቲስቲክስ ከራሱ ከመንግሥት ባለሟል አፍና በሁለት ቀን ቆይታው የተነገረውን መልሶ ከሚነግር የውጭ እንግዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልታለልም ካለ ቆይቷል፡፡ ቀባጣሪዎች ብዙ ቀባጥረው ስለ ኢኮኖሚው የተባለው ሁሉ ውሸት ሆኖ ራሳቸውን ሊቆጫቸውም አየጀመረ ነው፡፡

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢኮኖሚው ከ2003 እስከ 2007 ለአምስት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ አድጓል ተባለ፡፡ ዓመታዊ አማካይ የነፍስ-ወከፍ ገቢ በ2002 ከነበረበት 377 የአሜሪካን ዶላር በ2007 መጨረሻ ወደ 691 የአሜሪካን ዶላር አድጓል፤ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የማሰለፍ አገራዊ ራዕይ ተይዟል ተባለ፡፡ እነ ጂቡቲ፣ እነ የመንና እነ አፍጋኒስታን ኢትዮጵያን ቀድመው መካከለኛ ገቢ ውስጥ ይገባሉ ስለተባለ መካከለኛ የከፍተኛና የዝቅተኛ መሃል ቤት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ስትገባ የዝቅተኛ ገቢ አገር ስለማይኖር መካከለኛ የሚባለው ነገር ትርጉም አይኖረውም፡፡

በ1997 የበጀት ዓመት 38.7 በመቶ የነበረ የድህነት መጣኔ በ2003 ዓመት ወደ 29.6 በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻም ወደ 23.4 በመቶ ገደማ ዝቅ ብሏል፡፡ በዓለም ዓቀፍ የገቢ ክፍፍል ፍትሐዊነት መለኪያ በ ‹Gini Coefficient› አመልካች ከአንድ በታች ሆኖ ወደ ዜሮ የተጠጋ ዝቅተኛ ክፍልፋይ ቁጥር መሆን ደርግ ንብረትን ከሀብታሞች ወርሶ የሕዝብ በማድረጉ የመጣ ውጤት ቢሆንም፣ የኢሕአዴግ ስኬት በማስመሰል በ1997ም በ2003ም 0.3 ሆኖ እኩልነት ተረጋግጧል ተባለ፡፡

ይኽ ከዚህ በላይ የቀረበውን የመንግሥት የኢኮኖሚ ስኬት ስታቲስቲክስ ዘወትር የምንሰማው፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች ሲሆን ማረጋገጫው ራሳቸው ለራሳቸው ምስክር በመሆን የራሳቸው የባለሙያዎቹ ዕቅድና የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶችና መረጃ እና መረጃውን ከነርሱ ያገኙት ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ናቸው፡፡

ዘወትር በአገር ዐቀፍ ደረጃ ስለ ኢኮኖሚው ዕድገት ወሬ እና የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊነት ዲስኩር ተዓማኒ አለመሆን በግለሰብ ደረጃ ተቃራኒ በመረጃ አቅርቦ ማፍረስ ባይቻልም እንኳ፣ በገበያ ውስጥ መገለጫ አረጋግጦ ሊሞግት የቻለ ባለሙያ ባለመኖሩ፣ ሁኔታው ራሱ ገፍቶ መጥቶ የሕዝቡን አመጽ ቀስቅሷል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የምርት ገበያውም የሠራተኛ ገበያውም፣ የካፒታል ገበያውም የመሬት ገበያውም መዛባታቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ አውቋል፡፡ የምርት ገበያው ዋጋ ሰው አስመርሯል፡፡ በሠራተኛ ገበያው ውጥንቅት ወጣቱ ትውልድ ሥራ አጥቷል፣ ለራስህ ሥራ ፍጠር፤ አለበለዚያ መሞት ወይም መሰደድ ትችላለህ ተብሏል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በዝቶ የሸቀጦችን ዋጋ አንሯል የውጭ ምንዛሪ መጣኙን አዛብቶታል፡፡ በዓለም ታላላቅ ከተሞች እንኳ ባልታየ ዓይነት በአዲስ አበባ የአንድ ካሬ ሜትር መሬት ዋጋ ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት ሺሕ ብር ደርሷል፡፡ በእነኚህ ሁሉ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምጽ ሆኖ ሁላችንንም ሁሌም ማታለል አይቻልም ብሏል፡፡

የወጣቱ ሥራ አጥነት ለአገር ህልውና የሚያሰጋ ኹከት ቀስቅሶ የከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ መቆየቱን እናስታውሳለን፡፡ በውጭ ምንዛሪና በካፒታል እጥረት ምክንያት ብዙ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች ተጓትተዋል መዋዕለንዋይ ማፍሰስም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የከተማና የገጠር መሬት ሽሚያው ሕዝብ ከሕዝብ ከማጋጨቱም በላይ ለፀጥታ አስከባሪዎችም ፈታኝ ጊዜ ሆኖ ከርሟል፡፡

ናይጄሪያዊው ቁጥር አንድ ከበርቴ የሆኑትን የዳንጎቴን ሲሚንቶ ፋብሪካ ሊያዘጋ የደረሰ የመዋዕለንዋይ አፍሳሽ መብት ያልተጠበቀበት ሁኔታ ተፈጥሮ ግጭቱ በውይይት ተፈቷል፡፡ እያንዳንዱ ክልል የክልሉ መሬትና የክልሉ ማዕድናት ለክልሉ ወጣት ብቻ እያለ ወጣቱን በቋጥኝ ፍንቀላ ሥራ አሰማርቷል፡፡ ለምን ያህል ጊዜ እንዲህ በተፈጥሮ ላይ ብቻ ተመርኩዞ መኖር እንደሚቻል ማወቅ አይቻልም፡፡

እህል በጆንያ እየለኩ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራትም ነፍሶባቸዋል፤ ‹ብሪክስ› የተባሉትና በቅርቡ በፍጥነት ስለማደጋቸው የተመሰከረላቸው ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካም አርጅተዋል፤ አሁን ዓለም እያወራ ያለው ስለ እኛ ዕድገት ነው ብለው፣ እስከ ዐሥራ አንደኛው ሰዓት አውርተው የነበሩ የመንግሥት ባለሟሎችና ጋዜጠኞች በዐሥራ ኹለተኛው ሰዓት ላይ የዋጋ ንረቱን አመኑ፡፡ ሁከት የቀሰቀሰው የወጣቱ ሥራ አጥነት ነው አሉ፣ የብራችሁን ዋጋ አርክሱ ላሉ የዓለም ባንክ ሰዎች ከጆንያ ምርት ውጪ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ሸቀጥ ሳይኖረን ለምን ብራችንን እናረክሳለን አሉ፡፡

የኢኮኖሚ ሊቆች፣ “በመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንዳንድ ሰዎችን ሁሌም ማታለል ይቻላል፤ ሁሉንም ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ማታለልም ይቻላል፤ ሁሉንም ሰዎች ሁሌም ማታለል ግን አይቻልም፤” የሚል የአብርሐም ሊንከንን ንግግር ጠቅሰው ደካማ ፖሊሲ በስተመጨረሻ አግጦና አፍጥጦ በአደባባይ ተገልጦ በሕዝብ እንደሚታወቅ ይናገራሉ፡፡

የእኛ ኢኮኖሚስቶች በሙያቸው የተረዱትን ቀድመው ባይናገሩም ሁሉንም ሰዎች ማታለል አይቻልም የሚባልበት ደረጃ ተደርሶ ሕዝቡ እየተናገረ ነው፡፡ ሕዝቡ የመንግሥት ኢኮኖሚ ባለሟሎችን እየሞገታቸው ነው፤ ኑሯችን የምትሉትን አይመስልም እያለ ነው፤ አደገ የምትሉትን በወረቀት ላይ ራሳችሁ ጽፋችሁ ራሳችሁ ከምትነግሩን በአካል አምጡና በገበያ ውስጥ ዘርግፉትና በዓይናችን አሳዩን አለ፡፡ ከመንግሥት አገልግሎት ውጪ የሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችስ እንዴት ለሕዝቡ እውነቱን ማስረዳት አቃታቸው፡፡ ሙያቸውን እንዴት ሕዝቡ ቀድሟቸው አወቀ፡፡

በፍጥነት አደገ የተባለው ኢኮኖሚ ራሱን ኢሕአዴግን እየፈተነው ነው፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ራሱን ያዘጋጀው የግብርና ኢኮኖሚን ለማስተዳደርና ለመምራት ብቻ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ የበለጸገች የግሎባላይዜሽን ዘመን አገር መሪ ለመሆን ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ከፍተኛ የገንዘብ አስተዳደር ችሎታንና ኢኮኖሚን በመጠን ሳይሆን በአመልካቾች (indices) የመለካት ችሎታን ይጠይቃል፡፡ የአቅም ማነስ ምልክቶቹ አሁን መታየት ጀምረዋል፡፡

በሦስት መቶና በአራት መቶ ዶላር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በሸቀጦች ዋጋ ሰማይ መንካት ከአውሮፓና ከአሜሪካ ተስተካክለናል፡፡ እንደነርሱ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን ሠላሳ ሺሕና አርባ ሺሕ ዶላር ሲደርስ የሸቀጦቻችን ዋጋ የት ሊደርስ ነው፡፡ የዋጋ ንረትና ግሽበትን አሁን ካለበትም በላይ እንዳይሆን መንግሥት በቁጥጥርና በራሽን ለወደፊት እየገፋውና እያስተላለፈው ነው እንጂ እየቀረፈው አይደለም፡፡

ባለሟል ኢኮኖሚስቶች የሚበልጡና የሚያንሱ ቁጥሮች መፈብረክ ላይ ችግር የለባቸውም ችግሩ ቁጥሩን መተርጎሙ ላይ ነው፡፡ ቁጥርን መተርጎም ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ኢኮኖሚክሱ ተጠቃሎ ማሳረጊያው ይበልጣል ያንሳል ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሟሎች ክህሎትና ችሎታ ይበልጣል ያንሳል ብቻ ሆኗል፡፡ ይበልጣል ያንሳል ለማለት ከሐምሳ ዓመት በፊት የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢኮኖሚና ከሠላሳ ዓመት በፊት የነበረውን የደርግ ዘመን ኢኮኖሚ ካለበት ቦታ ቆፍረው ያመጣሉ፡፡

መሠረታዊ ሁኔታዎች ተሟልተውለት እንደ ሰው ለመኖር የሚፈልገው ሕዝብ እና በይበልጣል ያንሳል ትንታኔ ቁጥር ቆልለው እንደ ቻይና ለማደግ የሚፈልጉት የኢኮኖሚ ባለሟሎች የኢኮኖሚ ቁጥሩን በመተርጎም ላይ አልተግባቡም፡፡ ፍጆታ ለዛሬ፣ መዋዕለንዋይ ለነገ ነው፡፡ ዛሬ ሙትና ነገ ትኖራለህ የተባለ ሕዝብ ነገ ለመኖር ዛሬ መሞትን አልመረጠም፡፡ ዛሬን ሳይሞት ነገ መኖር የሚችልበት መንገድ ባለሟሎቹና መንግሥታቸው አላወቁትም እንጂ ዛሬን ሳይሞት ነገንም መኖር ይቻላል፡፡

የዛሬ ኑሮ ፍጆታና የነገ ዕድገት መዋዕለንዋይ ሀብት የሚሻሙ ተጻራሪ ሁኔታዎች ሳይሆኑ የሚደጋገፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን መደጋገፋቸው ችሎታ ባለው ባለሙያ መገራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግርም ከይበልጣል ያንሳል ትንታኔ ወጥቶ፣ የፍጆታን እና መወዕለንዋይን መደጋገፍ የሚፈጥር ባለሙያ ባለመኖሩ፣ እየኖሩ ማደግ ሲቻል እየሞቱ ማደግ እንደ አማራጭ መወሰዱ ነው፡፡

ለድህነት መቀነስም ሆነ ለሌሎች የሰብዓዊ ልማት መለኪያዎች መሠረቱ የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ስለሆነ ስለ አለካኩ በጥቂቱም ቢሆን ማወቅ ይጠቅማል፡፡

የአገር ውስጥ ምርት መጠን ዕድገት የሚጋነንበት ሦስት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዱ የተባበሩት መንግሥታት የብሔራዊ ገቢ አለካክ ሥርዓት ለውጥ ሲያደርግ ሲሆን፣ ሁለተኛው አገራት የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መለኪያ ዋጋቸውን ሲከልሱ ነው፡፡ ሦስተኛው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የሚለካው በሙያዊ ግምት ስለሆነ የፖለቲካ ሰዎች በባለሙያው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በሦስቱም መንገዶች ዕድገቱ ተጋኖ ቀርቧል፡፡

የብሔራዊ ኢኮኖሚ ገቢ ሒሳብ መለካት ከተጀመረበት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 1947 ጀምሮ የአለካክ ዘዴው በ1956፣ በ1968፣ በ1993፣ አና በ2008 ተከልሷል፡፡ በክለሳዎቹ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት ወደ ገበያ የገቡ አዳዲስ ምርቶች፤ ከክለሳው በፊት በኢ-መደበኛነት ተመድበው ሳይለኩ የቆዩ ሥራዎች፣ የቤት እመቤቶች እቤት ውስጥ የሚሠሩት ሥራዎች፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተሠሩ የሚባሉትና ጥቂት ሳይቆዩ የሚደርቁ ችግኞችና የሚደፈኑ ጉድጓዶች ተገምተው በቆጠራው ተካተዋል፡፡

በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መለኪያ ዋጋ መከለስ ምክንያትም ኢትዮጵያ የጥቅል አገር ውስጥ መለኪያ ዋጋዋን ከ1992 ወደ 2003 ስትከልስ ኢኮኖሚዋ በቅጽበት ሦስት እጥፍ እንዳደገ የመንግሥት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በፖለቲካ ተጽዕኖ ግምቱን ከፍ አድርግልኝ ማስረጃ የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም፡፡

በወረቀት ላይ በእነዚህ ሦስት ምክንያቶች ስታቲስቲክሱ ያድጋል፡፡ አገሮች በዕድገት ደረጃ ይነጻጸራሉ፤ በኑሮ ደረጃ ግን ምንም የተለወጠ ነገር ስለሌለ የሕዝቡ ኑሮ አይሻሻልም፡፡ እቤት ውስጥ ለግል ፍጆታ ይመረት የነበረው ገበያ ስለወጣ ወይም መለኪያ ዋጋው ስለተቀየረ ወይም በፖለቲካ ጫና ግምቱ በመዛባቱ ኢኮኖሚው ያድጋል ኑሮ ያው ነው፡፡ በወረቀት ላይ በእነዚህ ሦስት ምክንያቶች ስታቲስቲክሱ ያድጋል፤ አገሮች በዕድገት ደረጃ ይነጻጸራሉ ደረጃቸውም ይገለባበጣል በኑሮ ደረጃ ግን ምንም የተለወጠ ነገር ስለሌለ የሕዝቡ ኑሮ አይሻሻልም፡፡

ይኽ ስታቲስቲካዊ አሃዝ አርተፊሻል ቁጥር እንጂ በሕዝብ የኑሮ ደረጃ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ2013 ናይጄሪያ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርቷን የምትለካበትን የአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር 1990 ወደ 2010 ከልሳ በቀድሞው ዋጋ ሁለት መቶ ሰባ ቢልዮን ዶላር የነበረውን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ወደ አምስት መቶ ዐሥር ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር አሳድጋ፣ ቀደሞ በሦስት መቶ ሰባ አምስት ቢልዮን ዶላር ከአሕጉሪቱ በአንደኝነት ደረጃ ስትመራ የነበረችውን ደቡብ አፍሪካን በልጣ ከአፍሪካ ቁጥር አንድ እና ከዓለም ሃያ ስድስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ እንደተባለችና ናይጄሪያ በዋጋ ክለሳው ምክንያት በቅጽበት የጨመረችው ሁለት መቶ አርባ ቢልዮን ዶላር ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ብቻ እንኳን የኢትዮጵያን የዓመት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሰባ ቢልዮን ዶላር ሦስት እጥፍ ያህል እንደሆነ ከዚህ ቀደም እንደ ምሳሌ አንስተናል፡፡ በባለሙያዎቹ ስሌት ቁጥር ቢቆለልም የሕዝብን ኑሮ አይለውጥም፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያዎች በአገራችንም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ማከራከራቸውም አልቀረም፡፡ የኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግሊዝ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስቲና ላጋርድን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም ዐቀፍ ምሁራን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሁነኛ የዕድገት መለኪያ አለመሆኑን ይገምታሉ፡፡ ኢኮኖሚው ምን ያህል አድጓል ከሚለው ክርክር ጋር አብሮ የሚነሳው ጉዳይ በምንም ያህል ይደግ ለሕዝቦች ፍትሐዊ ክፍፍልስ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ስለ ሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት የተለያዩ ሥርዓተ ኢኮኖሚዎች ተፎካክረዋል፡፡

ፍትሐዊ ሥርዓት ተብሎ ለሰባ ዓመታት ስሙ ገኖ በነበረው በሶሻሊዝምም ጥቂቶች የአገሬውን ሀብት ወደ መንግስት ይዞታነት አዙረው እንደፈለጋቸው ሲያዙበት ለራሳቸው መዝናኛ ሥፍራዎችን ሲገነቡ የአብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ከካፒታሊስት አገራትም አንሶ ሥርዓቱ ደጋፊ አጥቶ ለመክሰም በቃ፡፡

ልማታዊ መንግሥታትም ከሶሻሊዝምና ከካፒታሊዝም የሚለዩት በደረጃ ብቻ ነው፡፡ የግል ኢኮኖሚን እና የመንግሥት ኢኮኖሚን በመቀየጥ ደረጃ ከገበያ ኢኮኖሚውም ከሶሻሊስት ኢኮኖሚውም ቢለዩም ወይም የሁለቱን ዲቃላ ቅይጥ ቢመስሉም ውድድር በጎደለው የዋጋ ንረት በገበያ ነጋዴዎች ብዝበዛ እና ራሳቸው ሳይለሙ ሌላውን አልሚ በሆኑ በአፋቸው ብቻ እንጂ በእጃቸው የማይሠሩ ሹመኞች ሕዝቡ ለድርብ ብዝበዛ ተጋልጧል፡፡

ምን ይሻላል?

መወያየት መልካም ነው፡፡ እስኪ እንወያይ …

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *