የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ፤ በሚቀጥለው ቀን ጠቅላይ ሚንስትሩ ያልሰበሰበው የሚንስትሮች ምክር ቤት እንደተሰበሰበ በማድረግ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ። ከዚህ አዋጅ ጀርባ የነበሩት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ የመከላከያ ሚንስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ እና ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ጌታቸው አምባዬ ነበሩ። አዋጁን ካወጡ በኋላ ህጋዊ እውቅና ለመስጠት በሚል፤ ጉዳዩ ወደ ምክር ቤት እንዲሄድ አደረጉት።


abye4

ይኸው አዋጅ በምክር ቤቱ ለመጽደቅ 2/3ኛ ድምጽ የሚያስፈልገው ቢሆንም በተጭበረበረ ድምጽ፤ በአፈ ጉባኤው አባ ዱላ ገመዳ መሪነት፤ አዋጁ እንዲጸድቅ ተደረገ። ይህ አዋጅ ተጭበርብሮም ቢሆን ጸድቋል። የአዋጁ አስፈጻሚዎች ሆነው እንዲሰሩ የተመደቡትም የመከላከያ ሚንስትሩ እና ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ነበሩ። ከነሱ ጀርባ ደግሞ እነደብረጽዮን አስፈላጊውን ሁሉ እያደረጉ፤ እንደእንዝርት ሲያሽከረክሯቸው ቆይተዋል።

አሁን ይሄ ሁሉ ነገር አለፈና የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መሪ ተዋናዮች እንደጉም ብን ብለው ጠፍተዋል። መከላከያ ሚንስትር በመሆን፤ የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ሆኖ ይሰራ የነበረው ሲራጅ ፈርጌሳ ከስልጣኑ ተነስቶ ትራንስፖርት ሃላፊ ሆኗል። ህጉን እያወጣና እያስተገበረ፤ ህግን ከለላ አድርጎ ህዝብ ሲያስርና ሲያስገድል የነበረው ጌታቸው አምባዬ ከጠቅላይ አቃቤነቱ ተነስቶ ወደ ውጪ ተወርውሯል። ዶ/ር ደብረጽዮን በትግራይ ህዝብ ጭምር ተጠልቶ፤ የህወሃት ሊቀመንበር እንደሆነ አሁንም አለ። ከዚያ ውጪ ግን ዶ/ር አብይ አህመድ -ለደብረጽዮን የሚሆን ምንም ስራ አልሰጠውም።

አዲሱ መከላከያ ሚንስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ በቀላሉ ለህወሃት የሚንበረከኩ ሰው አይደሉም። ከኦሮሚያ ምክትል ፕሬዘዳንትነት ተነስተው፤ የገቢዎችና ጉምሩክ ሃላፊ የሆኑት ኡመር ሁሴን ሙስናን የሚቃወሙ፤ የህወሃትን የዘር አድልዎ የሚጸየፉ፤ በተደጋጋሚ የህወሃት ሰዎች በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ ሊያሳልፉ የነበረውን ስኳርን ጨምሮ ሌሎች የሃገር ሃብቶችን “በህገ ወጥ መንገድ አናስወጣም።” ከማለት አልፈው የህወሃት ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጉ ናቸው። አሁን በፌዴራል ደረጃ የተሰጣቸው የጉምሩክ ሃላፊነት ደግሞ፤ በኮማንድ ፖስት ሰበብ የተጀመሩትን የኮንትሮባንድ ሰንሰለቶች የሚሰብር፤ የህወሃት ጥቅመኞችን አንገት የሚያስቀብር ጉዳይ ነው የሆነው።

ለብዙ አመታት የህወሃት ታዛዥ ሆኖ በመስራት የሚታወቀው አባዱላ ገመዳም፤ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነት ተነስቶ በምትኩ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ስልጣኑን ተረክባለች። በየደረጃው ያሉ የህወሃት ታዛዦች በዚህ አይነት አንድ በአንድ የመንግስት ስልጣናቸውን እየለቀቁ ናቸው። በምትካቸው ኃላፊ ሆነው የሚቀመጡት ሰዎች ደግሞ፤ ህወሃት እንደልቡ የሚያሽከረክራቸው ሰዎች አይደሉም። ይህ አዲስ የአሰራር ሂደት ማንኛውም ሰው በእውቀት እና በችሎታ እንጂ፤ በብሄር ተዋጽኦ ሰበብ የሚንስትርነት ማዕረግ ይዞ ህዝብን እየዘረፉ፣ እየበደሉ እና እያስለቀሱ መቀጠል እንደማይቻል ጥሩ አመላካች ነው።

በአጠቃላይ አዲሱ የካቢኔ ምልመላ በኮማንድ ፖስት ስም ሲዋቀሩ የነበሩትን አፋኞች የሚያኮስስ፤ የዶ/ር አብይ አህመድን ቡድን ደግሞ የሚያገዝፍ ነው። ከዚህ በኋላ ዶ/ር አብይን የሚጠብቃቸው አዲስ ስራ… በህጉ መሰረት ነባር እና አዲስ ሚንስትሮቻቸውን ሰብስበው በህዝብ ላይ የተጫነውን የይስሙላ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ በህጋዊ መንገድ መቀልበስ አለባቸው። አሁን ባለቤት የሌለውን ኮማንድ ፖስት በራሱ ግዜ መበተኑ የማይቀር ቢሆንም፤ በኮማንድ ፖስቱ ስም በየከተማው የተሰማራው ገዳይ ሃይል በዝምታ ሊታለፍ አይገባውም። ለሌሎች ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ገዳይ እና አስገዳዮች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚያ በተረፈ መከላከያው ድንበር ወደማስከበር ስራው እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመከላከያ ውስጥ በላይኛው እርከን ላይ የሚገኙ፤ ያለአግባብ የተሾሙ ሰዎችን ጉዳይ መከለስ አስፈላጊ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ… ቀስ በቀስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊጸየፈው የሚገባውን የዘረኝነት በሽታ እንዲታከም ካደረጉ፤ የቀረውን ህክምና ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችንም በማሳተፍ ከሰሩ፤ ታላቂቱን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪቃንም ወደአንድ የማምጣት መሰረቱ አሁን ላይ ሊጣል ይችላል። ከዚህ ባለፈ ግን… የህዝብ ጩኸት በበዛ ቁጥር ህዝብን ለመጨፍጨፍ የሚታወጅ “አስቸኳይ ግዜ አዋጅ” ለማንም አይበጅም። ታላቅ መሆን የሚቻለው በኢህአዴግ ፈረስ ላይ ብቻ በመጋለብ መሆን የለበትም። ከአድልዎ የነጻና ፍጹም ህጋዊ ምርጫ ተካሂዶ ስልጣንን ለህዝብ ማጋራት ወይም ማስረከብ ቀጣዩ የኢትዮጵያዊነት አዲስ ምዕራፍ ሊሆን ይገባዋል።

ዳዊት ከበደ ወየሳ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አቡነ ማቲያስ መነጋገሪያ ሆነዋል - ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻው እንዲከር ጥሪ አቅርበዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *