“Our true nationality is mankind.”H.G.

የባለሀብቶች የባንክ ብድር ማወራረጃ ህንፃዎች

ለአንድ ወር አንድ ሚሊዮን 156 ሺ 909 ብር ለህንፃ ኪራይ ይከፍላል፡፡ 13 ሚሊዮን 882 ሺ 908 ብር በዓመት ወጪ ያደርጋል የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር፡፡

ይሄ መስሪያ ቤት ህንፃውን ለረጅም ዓመታት ተከራይቶ ቢቆይ የሚያወጣው የመንግስት ገንዘብ ሌላ ህንፃ ሊያስገነባ እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላለበት የቢሮ ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ይሆናል። ሌሎችም በርካታ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች በተመሳሳይ የባለሀብቶች የባንክ ብድር ማወራረጃ መሆናቸው ይሰማል።
የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ቀደም በላው ጊዜ በቦሌ አካባቢ ቢሮ ተከራይቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም በቢሮ ጥበት ምክንያት በተደራጀ መንገድ ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ ችግሩን በመፍታት አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግም ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም ጀምሮ አራት ኪሎ አካባቢ ሁለት ህንፃዎችን ከግለሰብ ላይ በመከራይት ሥራ ይሰራል፡፡ ለህንፃው በሁለት ዓመት ውስጥ ከ27 ሚሊዮን 765ሺ ብር በላይ ለኪራይ ወጪ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህንጻውን የሚያከራየው ግለሰብ የኪራይ ዋጋ ካልጨመራችሁ በማለት ከመስሪያ ቤቱ ጋር እየተደራደረ ይገኛል፡፡ መስሪያ ቤቱ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለህንፃ ኪራይ ገንዘብ እየከፈለ የሚቀጥል ከሆነ በአስር ዓመት ውስጥ ከ138 ሚሊዮን 829 ሺ ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ይገደዳል፡፡ ይህ ገንዘብ ብቻ ወጪ የሚሆነው ዛሬ ላይ ለህንፃ ኪራዩ እየተከፈለ ያለው ዋጋ ባለበት የማይቀጥል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ እና ኪራዩ የሚጨምር ከሆነ መስሪያ ቤቱ ከዚህ በላይ ወጪ ለማውጣት የማይገደድበት ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም መስሪያ ቤቱ ተልዕኮውን ለመወጣት የግድ መስሪያ ቦታ ያስፈልገዋል፡፡ የዚህን መንግስታዊ ተቋም የህንፃ ኪራይ የገንዘብ መጠን ለአብነት ያህል አነሳን ኢንጂ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለቢሮ ኪራይ የሚያወጡት ገንዘብ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ወጪ መንግስት ለሌላ የልማት ሥራ ሊያውል የሚገባውን ለኪራይ ወጪ እያዋለ እንደሚገኝ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት ለኪራይ የሚከፍለውን ገንዘብ ለተወሰነ ዓመት ያህል ቢጠራቀም የራሱን ህንፃ ሊያስገነባው የሚችል መሆንም በየአመቱ የሚከፍሉት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አመላካች ነው፡፡ ይህ ቢሆንም ግን መንግስት ለመስሪያ ቤቶች የቢሮ ኪራይ የሚያወጣውን ገንዘብ ለማስቀረት ከሰኔ 1999 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ህንፃ መገንባት ጀምሯል፡፡ በዚህም እስካሁን ድረስ 22 ህንፃዎችን በአንድ ቢሊዮን 265 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ የነዚህ ህንፃዎች መገንባት ለመስሪያ ቤቶች ያላቸው ፋይዳ ቀላል የሚባል ባይሆንም ለቢሮ ኪራይ ገንዘባቸውን እየገፈገፉ ካሉ መስሪያ ቤቶች አንጻር ብዙ መስራት ይቀራል፡፡ 
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመንግስት ፕሮጀክት ህንጻዎች ግንባታ ከተሰሩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ መስሪያ ቤቱ ቀደም ብሎ ህንፃ ተከራይቶ ሥራውን ያከናውን ነበር ፡፡ በወቅቱም በየሦስት ወሩ 489ሺ 150 ብር ለቢሮ ኪራይ ከፍሏል፡፡ በ2006 አዲስ ወደ አስገነባው ህንጻ በመግባቱም በአራት ዓመት ውስጥ 7 ሚሊዮን 826 ሺ 400 ለኪራይ የሚወጣን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ 
የድርጅቱ የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ ድንበሬ እንደሚሉት የህንፃው መገንባት ቀድሞ ሁለት ቦታ ላይ ተበታትኖ የነበረውን የድርጅቱን ሰራተኞች ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ይህም መረጃን በተደራጀ መልኩ እንዲያዝ አስችሏል፡፡ ለህብረተሰቡም በአንድ ቦታ ላይ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በትራንስፖት ዙሪያ ይባክን የነበረውን የነዳጅ ወጪ አስቀርቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ በየሦስት ወሩ ለቢሮ ኪራይ ያወጣ የነበረውን ገንዘብ በማስቀረት ለሌላ የልማት ሥራ እንዲውል አድርጓል ብለዋል፡፡ 
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚኒስቴሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ብርቅነሽ ተስፉ እንደሚሉት ፅህፈት ቤቱ ካለው የሰው ሀይል እና አደረጃጀት አንፃር በቂ ቢሮ የለውም፡፡ በዚህም ጽህፈት ቤቱ አገራዊ መግባባትን በመፍጠር በኩል ያለውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ ጎትቶታል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ጽህፈት ቤቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ያለበትን ተልዕኮ ለመወጣት በ 9 ሚሊዮን ብር የአመት ክፍያ ለቢሮ የሚውል ህንጻ ተከራይቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህን ህንፃ መከራየቱ ግን በተደራጀና በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጎታል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የራሱን ህንጻ እያስገነባ ነው፡፡ የህንፃው ግንባታ መጠናቀቅም ጽህፈት ቤቱ አሁን ያለበትን የቢሮ ጥበት በተገቢው ሁኔታ የሚያስቀር ይሆናል፡፡ የተደራጀ መረጃ እንዲኖርም ያግዛል፡፡ ከዚህም ባሻገር በየዓመቱ ለኪራይ የሚወጣውን ወጪ ለሌላ ሥራ እንዲውል ያደርጋል ብለዋል፡፡ 
ጽህፈት ቤቱ አዲሱን ህንጻ አራት ኪሎ ባልቻ ወልዴ ችሎት አካባቢ እያስገነባ እንደሚገኝ የሚናገሩት ወይዘሮ ብርቄ የህንፃው የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው የተጀመረው ታህሣስ 2009 ዓ.ም ነው፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የህንፃው የግንባታ ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አካካቢ ነው ፡፡
‹‹የህንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ ጽህፈት ቤቱ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የፓናል ውይይቶች እና ፕሬስ ኮንፍረንስ የሚካሄድበት አዳራሽ ስለሚኖረው በተለያዩ ሆቴሎች እና አዳራሾች የሚወጣውን ወጪ እንዲቆጠብ ያደርጋል፡፡ ይሄም ከህብረተሰቡ ጋር በየጊዜው መረጃ ልውውጥ እንዲኖር ያግዛል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ህንጻው ላይ ዘመናዊ የስቲዲዮ ግንባታ ይደረግበታል›› ያሉት ወይዘሮ ብርቅነሽ ይሄም ጽህፈት ቤቱ የተደራጀ መረጃ እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከቢሮ ጥበት አንጻር ጠንካራ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ከመስራት አኳያ የነበረበትን ችግር ይፈታል ነው ያሉት፡፡ 
የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለፃድቅ ተክለአረጋ በበኩላቸው፤ መንግስት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ የግለሰብ ህንጻዎችን ተከራይቶ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡
በህንፃና በቢሮ ኪራይ መንግስት ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ነው፡፡ ይሄን ወጪ ለማስቀረት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ህንፃ እያስገነባ ይገኛል፡፡ በዚህም እስካሁን ድረስ 23 ህንፃዎች በአንድ ቢሊዮን 265 ሺ ብር ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የህንጻዎቹ መገንባት መንግስት ለኪራይ ያወጣ የነበረውን ወጪ በተወሰነ መልኩ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ በ 5ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ደግሞ 13 ህንጻዎች በግንባታ ላይ እንዳሉ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ህንፃዎቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ መስሪያ ቤቶቹ ያለባቸውን የቢሮ ጥበት ችግር በመፍታት ቀልጣፋ እና የተሳለጠ አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ የኪራይ ወጪን በማስቀረት ገንዘቡ ለሌላ ልማት እንዲውል ያግዛል፡፡ ‹‹ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩና ገና በመገንባት ላይ ያሉ ህንጻዎች የግንባታ ወጪያቸው እንደ ህንጻው ርዝመትና ስፋት ይለያል›› ያሉት አቶ ተክለጻድቅ በአጠቃላይ ለህንጻዎቹ ግንባታ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ስምንት ዓመት ውስጥም የህንፃና የቢሮ ኪራይን ለማስቀረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የራሱ ህንፃ እንዲገነባለት ጠይቆ ወረፋ በመጠበቅ ላይ ይገኛል አሁን እየተገነቡ ካሉ 13 ህንጻዎች ውስጥ ባለመሆኑም በቀጣይም የህንፃ ኪራይ ወጪ ተዳርጓል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ መንግስት ለህንፃ እና ለቢሮ ኪራይ ከሚከፍል ህንጻ እያስገነባ ቢሰጥ ትርፉ የተሻለ ነውና የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በጀትን በቁጠባ ፤ለታለመለት አላማ እናውል የሚለውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መመሪያም መስራት ያለበት ለአነስተኛ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን የቢሮ ኪራዮችንም የሚመለከት ይሁን።

ENA

Related stories   መንግስት ከግብርናው ዘርፍ ስኬት ቆንጥሮ በዳታ የተደገፈ መረጃ ይፋ አደረገ - አቡካዶ ቀጣዩ ወርቅ !

ሰብስቤ ኃይሉ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0