“Our true nationality is mankind.”H.G.

መንታ ሃሳብ ያዘለው የዶናልድ ትራምፕ ከሶርያ እንውጣ ጥያቄ

ባለፉት 17 ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ 7 ትሪሊዮን ዶላር ማውጣቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአሁኑ አወዛጋቢ የልዕለ ኃያሏ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ እስካሁን ይህ ሁሉ ወጪ ብታደርግም የሰው ህይወት ከመቅጠፍና ሀብትና ንብረት ከማውደም በስተቀር ምንም ያስገኘው ትርፍ የለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

መንታ ሃሳብ ያዘለው የዶናልድ ትራምፕ ከሶርያ እንውጣ ጥያቄ

 

በሶርያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ እንሆ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በጦርነቱ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህወታቸውን ሲያጡ፤ ብዙዎች ተሰደዋል፡፡ 
ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳትና ቁሳዊ ውድመት በስተጀርባም የተለያዩ አገራት እጅ የሚገኝበት ሲሆን፣ በተለይ ሩሲያ፣ አሜሪካ ፣ ኢራን፣ ቱርክና ሳውዲ አረቢያ በጦርነቱ በመሳትፍ የየራሳቸውን አጀንዳ እያራመዱ ናቸው፡፡ 
ልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካም በሶርያ የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛውን አይ ኤስ አይ ኤስን ለመደምሰስ ካላት ፅኑ ፍላጎት በመነጨ የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊ ሆናለች፡፡ መቋጫ ባጣው በዚህ ጦርነት አሜሪካ በአይ ኤስ ላይ በርካታ ድሎችን ብትጎናፀፍም አሁንም ተጨማሪ የቤት ሥራ እንደሚቀራት ተንታኞች እየገለፁ ቢሆንም አገሪቱ ከአካባቢው ለመውጣት ሀሳቡ እንዳለት እያመለከተች ትገኛለች፡፡
ሰሞኑን ሮይተርስ ይዞት የወጣ መረጃ እንዳመለከ ተው፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ባስቸኳይ ከሶርያ ምድር ለቃ መውጣት አለባት›› ሲሉ በሰጡት ጋዜጣዊ ምግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው የጊዜ ገደብ ባያስቀምጡም አገራቸው ባአስቸኳይ ከሶሪያ መውጣት እንዳለባት ግን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከሶርያ ለቃ እንድትወጣ በንግግራቸው የገለፁ ቢሆንም ‹‹አይ ኤስ ከሶርያ እስካልጠፋ ድረስ አሜሪካ እንቅልፍ አይኖራትም፤ ይሁን እንጂ ድሉ እየተቃረበ በመምጣቱ ጦራችንን ከሶርያ ምድር ማንቀሳቀስ ይኖርብናል›› ሲሉ መንታ ሐሳብ ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 
ይህ የትራምፕ ንግግር መንታ ሃሳብ ያዘለ ነው በሚል ብዙዎች እየተወያዩበት ይገኛሉ፡፡ የአሜሪካ ጥምር ኃይል ልዩ መልዕክተኛና የትራምፕ አማካሪ በሬት ማጉርክ እስላማዊው ፅንፈኛ ቡድን ሙሉ በሙሉ እስካልተደመሰሰና ከቡድኑ ነፃ የሆኑ አካባቢዎች ላይ መረጋጋት አስካልተፈጠረ ድረስ አሜሪካ ከሶርያ ለቃ መውጣት የለባትም ሲሉ የፕሬዚዳነቱን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡ 
ፔንታገንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩላቸው ፅንፈኛውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳያንሰራራ አድርጎ ለማሸነፍ የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ጥረት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ በርግጥም የአሜሪካ ጦር ከሶርያ መውጣት እንዳለበት በውሳኔያቸው መፅናታቸውን ከዘጋቢዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ጊዜው አሁን ነው፤ በፅንፈኛው ቡድን ላይ በወሰድናቸው ርምጃዎች ስኬታማ ነበርን፡፡ በወታደራዊ እርምጃችን በማናቸውም ላይ ስኬታማ መሆን እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳዴ ወደ አገር መለስ ብሎ ጉዳዩን በጥልቀት መመርምር አስፈላጊ ነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡፡ 
ከሮይተርስ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አሜሪካ በሶሪያ ላይ በየዕለቱ የአየር ላይ ጥቃቶችን እየሰነዘረች ስትሆን፤ የአሜሪካ ልዩ ኃይልን ጨምሮ ሁለት ሺ የሚጠጉ የምድር ላይ ተዋጊዎችንም በማሰማራት ከኩርድ ሚሊሻዎችና ሌሎች የአሜሪካ ደጋፊ ተዋጊዎች ጋር በመሆን በርካታ ግዛቶችን ከፅንፈኛው ቡድን ማስለቀቅ ተችሏል፡፡ 
የአሜሪካ የጦር ጄነራል ጆሴፍ ቮቴል ባስቀመጡት ግምት መሰረት ከ2014 ጀምሮ በሶርያ ፅንፈኛው ቡድን ከ90 በመቶ በላይ ተይዞ የነበረው ግዛት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዶናልድ ትራምፕ በኢራቅና በሶርያ በፅንፈኛው ቡድን ተይዞ የነበረው ግዛት ሙሉ በሙሉ ተመልሷል በማለት አስቀምጠዋል፡፡ ከአሜሪካ በይፋ የወጡ አሃዞች እንዳመለከቱት ደግሞ ከፅንፈኛው ቡድን ነፃ የሆነው ግዛት 98 በመቶ ደርሷል፡፡ መረጃው ይህን ያካተተ ይሁን እንጂ ምን ያህል ተጨማራ ሥራዎች በሶርያ እንደቀሩ ያመለከተው የለም፡፡ 
አሜሪካ በሶርያ አይ ኤስን ለመውጋት የምታደርገውን ጥረት ያዘገየው አንዱ ምክንያት በአሜሪካ የሚደገፈው የኩርድ ተዋጊዎች ፅንፈኛውን ቡድን ከመውጋት ይልቅ ትኩረቱን ወደ ቱርክ መራሹ የኩርድ ህብረት በማዞሩ ነው ሲል የሮይተርስ ዘገባ ይጠቁማል፡፡ 
የጥምር ኃይሉ ልዩ መልዕክተኛና የትራምፕ አማካሪ በሬት ማጉርክ በሶሪያ ምድር የተገኘነው አይ ኤስን ለመውጋት ነው፡፡ ተልዕኳችንም ይሄው ነው፡፡ ይህ ተልዕኳችን ገና አላበቃም፡፡ ስለዚህ ተልዕኳችንን እስካላጠናቀቅን ድረስ ከሶርያ ምድር መውጣት የለብንም›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ 
ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ከሶሪያ የመውጣት ሃሳብ ተንታኞቹ በሁለት መንገድ ከፍለው እያዩትም ነው፡፡ የአሜሪካ ስትራቴጂና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ባለሙያ ጆን አለተርማን የአሜሪካ ከሶርያ መውጣት የሶርያን ጦርነት ለማቆም የሚደረገውን ውይይት ያዳክመዋል ሲል ይናገራል፡፡ አሜሪካ በሶርያ የምታሳድረው ትንሽ ተፅእኖ በቀጣይ የሶርያ መፃኢ ዕድል ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም በመግለፅ የቆይታዋን አስፈላጊነት ያመለክታል ፡፡ 
በተመሳሳይ ሌሎች ተንታኞችም የአሜሪካ ከሶርያ ድንገት የመውጣት ውሳኔ የአሜሪካ ተቀናቃኝ የሆኑት ሩስያና ኢራን በሶርያ ተፅእኗቸውን ለመፈፀም ጥሩ ዕድል እንዲያገኙ ያደርጋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ 
ይህን የሰሙት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ በሶርያ በቆየች ቁጥር ወጪ ማውጣቷ አይቀርም፤ ወጪውን ደግሞ እናንተው ትከፍሏታላችሁ›› ሲሉ ለባለሞያዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር የኢራን ታጣቂውን ኃይል ድጋፍ ሳይሰጥ ከኢራቅ ለቆ መውጣቱን ተክትሎ ታጣቂ ኃይሉ በፅንፈኛው ቡድን እጅ በመውደቁ የቀድሞወን የአሜሪካ ፕሬዚዳናት ባራክ ኦባማን ይወቅሳሉ፡፡ 
ከሶርያ ጦርነት ማብቂያ በኋላ አሜሪካ በሶርያ ሊኖራት የሚችለው ሚና ምን ሊመስል እንደሚችል ዶናልድ ትራምፕ ያላቸውን ራዕይ በግልፅ እስካሁን ባይታወቅም፤ ሶርያን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሚውለውን የ200 ሚለዮን ዶላር ፈንድ ለመቀነስ የደረሱበት ውሳኔ አሜሪካ ከምታደረጋቸው ዘረፈ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች ጋር የሚፃረር ነው ሲሉ ተንታኞች ገልፀዋል፡፡ 
የአሜሪካ የጦር ጄነራል ቮቴል ለሶርያ መረጋጋት የአሜሪካ ጦር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ በተለይም ፅንፈኛው ቡድን የለቀቃቸውን አካባቢዎች ማረጋጋት፣ ማጠናከርና ሰዎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራ በዋናነት መከናወን እንደሚኖርበትም ያመለክታሉ፡፡ 
ዓመታት በፈጀው የሶርያ ጦርነት አሜሪካ ፅንፈኛውን አይ ኤስን ለመውጋት በርካታ የአየርና የምድርላይ ጥቃቶችን ስትፈፅም ቆይታለች፡፡ በዘመቻዋም በርካታ የፅንፈኛው ቡድን ከፍተኛ አመራሮችን ስትገድል የቡድኑን ጠንካራ ይዞታዎችን ማስለቀቅ ችላለች፡፡ 
አሜሪካ በዓለም ግዙፍ በሆነው የፔንታግ የንግድ ማዕከል ላይ በመስከረም 11 ቀን 2001 በአልቃይዳ የደረሰባትን አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ተከትሎ አፍጋኒስታንና ኢራቅን ከወረረችብት ጊዜ አንስቶ ለዚሁ ዘመቻዋ ባለፉት 17 ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ 7 ትሪሊዮን ዶላር ማውጣቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአሁኑ አወዛጋቢ የልዕለ ኃያሏ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ እስካሁን ይህ ሁሉ ወጪ ብታደርግም የሰው ህይወት ከመቅጠፍና ሀብትና ንብረት ከማውደም በስተቀር ምንም ያስገኘው ትርፍ የለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ አሜሪካ ከሶርያ ባስቸኳይ መውጣት አለባት ያሉበት ዋነኛው ምክንያትም ይህ ሳይሆን እንዳልቀረ ብዙዎች ይግምታሉ፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው
0Shares
0