ከትግራይና ከአማራ ህዝቦች ትስስር አንጻርና ህወሓት ከፍ ያለ ወታደራዊ ሀይል የነበረው በመሆኑ፤ በሚገባ መጠን ለአማራ ወንድሞቹ ከለላ መከታ አልሆነም የሚል ወቀሳ ሊቀርብ ይችላል።

ማንንም ህዝብ ሳልወክል ይህን አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ።

በ1980ዎቹ በደቡባዊና ደቡብ ምዕራብ የሀገራችን ክፍሎች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሱ ጥቃቶች እንደነበሩ ስንሰማ ስናነብ ኖረናል። የጉዳቶቹ ስፋት ምን ያህል ነበር? አማራ ላይ ብቻ ነበር የደረሰው? ማን በምን ሁኔታ ፈጸመው? ማንስ ምን ሊያደርግ ሲገባው ቸል አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ከፖለቲካ ፍጆታ የጸዳ ጥናት ያስፈልጋል።

ነገር ግን ባመዛኙ አማራ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንደደረሰ የሚያከራክር አይመስለኝም። ተያይዞም ከትግራይና ከአማራ ህዝቦች ትስስር አንጻርና ህወሓት ከፍ ያለ ወታደራዊ ሀይል የነበረው በመሆኑ፤ በሚገባ መጠን ለአማራ ወንድሞቹ ከለላ መከታ አልሆነም የሚል ወቀሳ ሊቀርብ ይችላል።

ይሄ ወቀሳ ከተራ ወቀሳ አልፎ በሁለቱ ህዝቦች መሀል ካለው ጥልቅ ትስስር አንጻር እንደ”መከዳት” ተደርጎ ቢወሰድ አይገርምም። አንዳንዴ የቅሬታው ጥልቀት የቅርበቱን መጠን እንደሚያመለክት አድርጎ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ትግራዮችም ባለፈው ዓመት ጎንደር የደረሰው በተለይ የሚያበሳጫቸው በዚሁ መንፈስ እያዩት ነው ብሎ መረዳት ይቻላል።

ዳን ኤል

ልክ እህትማማቾች ወይም ወንድማማቾች በሆነ ነገር ሲጣሉ “ልጆች እያለን ጀምሮ እንዳስቸገረችኝ ነው፣ ድሮንም’ኮ እሷ….” ብለው ጸቡን ጥግ ድረስ እንደሚወስዱት ሁሉ፤ ተመሳሳይ ስሜታዊ ጡዘትና የከረረ ብስጭት በህዝቦች ደረጃ ሊንጸባረቅ ይችላል የሚል መላምት አለኝ።

ዋናው ችግር የሚመጣው ፖለቲከኞችም በዚሁ ትራክ መጋለብ ሲፈልጉ ነው። ሀላፊነት የጎደላቸው የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች ተጨባጭ ቅሬታዎችን በግልጽነትና በአውድ በአውድ ማቅረብ ሲገባቸው፤ በተቃራኒው የስሜት ጡዘቱን “ሳይንሳዊ” ለማድረግ የተለጠጠ የታሪክ፣ የኮንስፒሬሲ፣ ምናምን ቅርጽ ይሰጡታል። ወይም እንዲያ ዓይነት ትርክቶች እንዲፋፉ ያመቻቻሉ።

የተነሳሁበትን ጉዳይ አልሳትኩትም። በ1983 በኋላ በአማራ ላይ ስለደረሱ ጥቃቶች እያወራሁ ነው። እስኪ የፖለቲካውን ዳራ ለማስቀመጥ የሚረዱኝ ሁለት ቁንጽል ወጎች ላቅርብ።

1) ድሬዳዋ የማውቃት ጎረቤቴ ስለአያቷ እንዳወጋችኝ፤ አያቷ ሀረርጌ አካባቢ ባላባት ነበሩ። ድሬዳዋ ይኖሩ ነበር።
በንጉሱ ዘመን ሰውየው ገጠር እየሄዱ ጭሰኞቹም ቤታቸው ድረስ እየመጡ ብዙ አገልግሎት ይሰጧቸው ነበር።
ደርግ ከመጣና መሬት ከተወረሰ በኋላ የድሮ ጭሰኞቹ በየጊዜው እየመጡ ለሰውየው እህልና ወተት ይሸጡላቸው የነበረ ቢሆንም፤ “ድሮኮ እንዲህ ታደርጉን ነበርኮ” እያሉ በወቀሳ መልክ ያወሯቸው ነበር።
“ከ1983 በኋላ ግን እሳቸውም ወደገጠር አይሄዱም እነሱም አይመጡም” አለችኝ።

2) ባለፉት ወራት በጅማ፣ በኢሉአባቦራ፣ ወዘተ ከሚኖሩ በደርግ የሰፈራ ፕሮግራም የሄዱ ትግራዮች ጋር በተደጋጋሚ የማውራት እድል አግኝቼ ነበር። በአንዳንድ የሰፈራ ጣቢያዎች የነዋሪዎቹ ቁጥር ከ1990ዎቹ ወዲህ በቀጥታ ወይም በአንጻራዊ መጠን እንደቀነሰ (in absolute or relative decrease) እንዳሳየ ተገንዝቤያለሁ። የአባወራዎችን ስምና ብዛት እየጠቀሱ ወደድሮ መንደራቸው እንደተመለሱ አውግተውኛል።

እነዚህን ሁለት ማሳያዎች በመመርኮዝ የምንገነዘበው ነገር፤ የብሔር መስተጋብሮች ላይ ያለው መሸረሸር ከግዜ ግዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣ እንጂ ድንገት 1983 ላይ እንዳልተከሰተ፤ እንዲሁም “ትግሬ አማራ ላይ ያቀነባበረው ዘመቻ” ብሎ ለማስቀመጥ እንደማይቻል ነው።

አቶ አሰፋ ጫቦ በ1990ዎቹ በጻፈው ጽሑፍ ላይ – በትክክል ካስታወስኩ – የእድገት በህብረት ዘማች የነበሩ ዘማች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጋሞ አካባቢ “ነፍጠኞችን” ሰብስበው አስረው እንዳገኛቸው ሆኖም ከመሀላቸው የግማሾቹ የአያት ስም የደቡብ መሆኑን እንዳየና ለተማሪዎቹም እርማት እንደሰጣቸው የተረከውን አስታውሳለሁ። ገና በ1960ዎቹ ማለት ነው። በመሰረቱ የደርግ የፕሮፓጋንዳ ድርሳናት ላይ “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል በብዛት ይገኛል።

በመሰረቱ ህወሓት ከብሄርተኝነቱ ይልቅ የፖለቲካ ዶግማቲዝም (dogmatism) የሚያይልበት፣ ድርጅታዊ ህልውናውንና ጥቅሙን ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት የሚሄድ ድርጅት መሆኑን ብዙ ግዜ የታየ በመሆኑ ህወሓት የፈጸማቸውን ወይም ያልፈጸማቸውን ነገሮች ሁሉ ከትግራይ ጥቅም አንጻር ተሰልተው የተሰሩ ታላላቅ ሴራዎች (grand conspiracy) አድርጎ መውሰድ አሳሳች ነው።

ብዙ ዝርዝር ሳንገባ ህወሓት በሻዕቢያና በኤርትራ ጉዳዮች ላይ የወሰዳቸው አቋሞች ከርዕዮተ-ዓለም ዶግማቲዝምና ከአመራር ድክመት ወይስ የትግራይ ህዝብን ጥቅሞችና ስሜቶች ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ? መልሱ ሁለተኛው ነው ለማለት በጣም የተለጠጠ የሴራ ንድፈ ሀሳብ መስራት ይጠይቃል።

እንግዲያ የተለያዩ የሻዕቢያ አመራሮች ሰው ከማስገደል ጀምሮ ሌላም ሌላም ሲባልጉ “እስኪ ይታለፍ ወዳጅነታችን ይበልጣል” ያለ ድርጅት፤ አንድ የሀገሪቱ ጥግ ላይ ያለ ካድሬ ህዝቦችን ሲበድል ከመርህ ተነስቶ አስፈላጊውን የፖለቲካ ዋጋ ከፍሎ ባያስቆም ባህርያዊ ነው። ለነገሩ ፖለቲከኞች ባመዛኙ እንዲያ ናቸው።

እዚህ ጋር “አስፈላጊውን ፖለቲካዊ ዋጋ ከፍሎ” የሚለው ነጥብ ይሰመርበት። አዎ! መሪ አስፈላጊውን ዋጋ ከፍሎ መርህን ማስከበር አለበት። ፖለቲከኞች ገበያውን እያዩ ይንቀሳቀሳሉ ማለት እንዲያ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ያ የፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ደካማ ገጽታ እንጂ ቅቡል ባህርይ ነው ማለት አይደለም።

ይህንን አውድ ይዘን፤ ህወሓት ምን ማድረግ ይችል ነበር? ምንስ አድርጓል? ምን ላይ ወድቋል? ሌሎቹ ድርጅቶችስ ምን ሚና ነበራቸው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። ችግሩ ከርዕዮተ-ዓለም ነው ሊባል ይችላል፣ ወይም በርዕዮተ-ዓለምና በፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ያለ ልክ ዶግማቲክ ከመሆን ሊመነጭ ይችላል፣ ወይም ከድርጅታዊ ፖለቲካ ገበያ ስሌት የሚመነጭ ኦፕሬሽናል ድክመት ሊሆን ይችላል፣ ወይም ነባራዊ ሁኔታው በቀላሉ ሊስተካከል የማይችል ውስብስብ ፈጥሮ ነበር ሊባል ይችላል፣ ወዘተ። ይህንን በሰከነ የታሪክና የፖለቲካ ትንተና መመለስ ይገባል።

ይህም ሆኖ ግን አንድ አማራ አክቲቪስት ወይም ሽማግሌ በደምሳሳው “የትግራዮች ድርጅት የሆነው ህወሓት መከታ አልሆነንም” የሚል ወቀሳ ቢያቀርብ፤ ወቀሳው በራሱ ስህተት አይሆንም። መማማሪያም መተራረሚያም የወዳጅነትን ክሮችን ማደሻ ገንቢ ውይይት ነው። እውነተኛ የቤተዘመድ ምክክር በሽፍንፍን አይሆንምና።

ነገር ግን አንድ የመሪነት ሚናን ወስጃለሁ የሚል ግለሰብ ወይም ድርጅት:- በትክክል የደረሰውን ጉዳት ለይቶ፣ መንስዔና አውድ አስቀምጦ፣ የተለያዩ አካላትን ድርሻ ለይቶ መተንተንና ህዝብን ማሳወቅ እንጂ በህዝብ ውስጥ ያሉ የተዛቡ ግንዛቤዎችን እና ቤተዘመዳዊ ቅሬታዎችን በማራገብ መጠቀሚያ ሊያደርጋቸው መሞከር አይገባውም።

በዚያ መልኩ ለጥቂቶች የፖለቲካና የቢዝነስ ትርፎችን ለማስገኘት ቢቻልም ብዙ ርቀት አይወስድም። የማታ የማታ ከህዝብና ከታሪክ ተጠያቂነትም አያድንም። ህዝብንም ከተወሰነ ግዜ በላይ ማደናገር አይቻልም።

ከህወሓትና ከብአዴን ፖለቲካዊ መፈክሮችና ድርጅታዊ ውስብስቦች ነጻ የሆነ እውነተኛ ቤተዘመዳዊ ውይይት በሁለቱ ህዝቦች ኤሊቶች መሀል ማድረግ የሚቻልበት ቀን ሲመጣ ያንን ውይይት ማድረግ ይገባል።

(ይሄ ጽሑፍ እንደወረደ የተጻፈ ስለሆነ ቃላት ስንጠቃ ሳይገባ ዋና ሀሳቡን ብቻ ወስደን እንወያይ)

ዳንኤል ብርሃኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *