ዓለም አቀፍ ህግ ሁላችንም አናውቅም። እስኪ አጥኑ እና የጥናታችሁን ውጤት አምጡ የሚል የለም። ‹‹አሰብ የእኛ ናት›› የሚሉ በሙሉ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ጦርነት ናፋቂ ናቸው ብለን ከመጀመሪያው ነው የደመደምነው። እብሪት ያልኩህ እሱ ነው። ጥናቴ ላይ የጻፍኩትም ድንቁርና እና እብሪት ተደባልቋል የሚል ነው።

… ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየቀጨጨ ሲሄድ ህዝቡ መብቶቹ እየተረገጡ ሄዱ። ይህ የመብት ጥሰት ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ነው የበደለው ተለይቶ ተጠቃሚ የሆነ ብሔር የለም። ለምሳሌ በትግራይ ክልል ያለው አፈና እና የመብት ጥሰት ከሌላው ብሔር ይልቅ የከፋ ነው። ከሞላ ጎደል በትግራይ ክልል ያለው አገዛዝ የኤርትራ አይነት ነው ማለት ይቻላል። እኔ ያልኩት ችግሩ 2007 ዓ.ም መጣ ሳይሆን የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ሲሄድ ሰው ስጋት ውስጥ ገባ እና በ2007 ዓ.ም ችግሩ ፈነዳ። አሁን ያለው ችግር እየመጣ መሆኑን የገዥው ፓርቲ ሰዎች እየተነገራቸው ቀለል አድርገው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ብለው ሊያልፉት ፈለጉ። በ2009 ዓ.ም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ አዋጁን ሊሰሩበት ሲገባ ተደበቁበት።

“የኢህአዴግ የፖለቲካ ማዕከል ህወሓት መሆኑ ከቀረ ቆይቷል” ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት የቀድሞ አየር ኃይል አዛዥ

በይርጋ አበበ – ሰንደቅ ጋዜጣ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቀድሞ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት በ1993 ዓ.ም ከመንግስት የስራ ኃላፊነት ከተለዩ በኋላ በመምህርነት አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። እኒህ የቀድሞ ታጋይ በተለያዩ ጊዜያት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው ማብራሪያ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን ሃሳባቸውን ወደ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በህትመት ሚዲያው በኩል ለህዝብ በማድረስ ተጠቃሽ ናቸው። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሁፍ የባህር በር ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗ ከሚያስቆጫቸው ኢትጵያዊያን መካከል አንዱ ናቸው። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ሊኖር ስለሚችለው ግንኙነት፣ ስለ ዶክተር አብይ አሕመድ ካቢኔ፣ ስለ ህወሓት እና የተለያዩ ጉዳዮች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል እነሆ!!

ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳይ እንጀምረው። በኢትዮጵያ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ከሂደቱ ጀምሮ እስከ ርክክቡ እንዴት አዩት?

ጄኔራል አበበ፡- ኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋት ነበር። አጠቃላይ የነበረው የሰላም ማጣት ሁኔታ ለውጥ፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን እና የህግ የበላይነት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው። ተፈጥሮ የነበረው ሁኔታ ጸረ ዴሞክራሲ የተስፋፋበት፣ የህግ የበላይነት የማይከበርበት፣ ፍትህ የታጣበት ስለነበር ለውጥ ያስፈልግ ነበር። ለውጡ ከየት ይምጣ እና በማን ይነሳ የሚለው ነገር የአገሪቱ ሁኔታ እና ታሪካዊ ሁኔታ ይወስነዋል። በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ አንመራም እያሉ ቢሆንም በዋናነት የተነሳው ግን ኦሮሚያ አካባቢ ነው። በመሰረታዊነት የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ወጣት አጠቃላይ ያደረገው እንቅስቃሴ አልገዛም ባይነት ያሳየበት ሁኔታ ነበር፤ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ። በእርግጥ እዚህ ላይ አንዳንድ ወንጀለኞች ከለውጡ ጋር ተደባልቀው ብሔር ተኮር ጥቃት የታየበት፣ ንብረት የወደመበትና በአጠቃላይ ብዙ ጥፋት የተፈጸመበት ቢሆንም በዋናነት ግን የኦሮሞ ወጣት እንቅስቃሴ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ለውጥ ያስፈልግ ስለነበርና የለውጡ ማዕከል ደግሞ ኦሮሚያ በመሆኑ የለውጥ መሪ ከየት ይመጣል የሚለውን ብዙ ጥያቄ እናነሳ ለነበረው ጥያቄ መሪዎች ከኦሮሚያ እየመጡ መሆኑን ማየት ጀመርን። የለማ ቡድን የምንለው መምጣት ጀመረ። ከዚያም ምናልባት ኢትዮጵያን የሚያድናት እና መምራት የሚችል ከዚህ ይመጣል ብዬ ማሰብ ስለጀመርኩ መከታተል ጀመርኩ። ስለዚህ በአንድ በኩል ከነበረው የኢህአዴግ ጸረ ዴሞክራሲ ስርዓት ብዙ ንክኪ ያልነበራቸው፣ በአንጻራዊነት ጎልማሳ የምንላቸው እና የተማሩም ናቸው። ስለዚህ አሁን የሚመጣው ለውጥ ዋናዎቹ መሪዎች ከኦህዴድ ይመጣል ብዬ ሳነሳ ነበር። አሁን ሲታይም የለውጡ መሪዎች እነሱ ናቸው የሆኑት።

ህወሓት እና ብአዴን በነበሩበት ላይ ነው የቆሙት። እነሱ ግን (ኦህዴድ) ተቀይረው ፌዴራሊዝምን እና ኢትጵያዊነትን አንድ ላይ አድርገው የኢትዮጵያ አንድነትን አጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህ በተለይ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ሲጀመር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያየ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳውን ስራ (Campaign) በደንብ ሰርተውታል። ይህ ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዛ መሆን አለበት። እኔም ጓደኞቼም በእነሱ ላይ (የለማ ቡድን) ተስፋ ስናደርግ ነበር። እሳቸው በመመረጣቸውም በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ተገቢም ነው ብዬ አምናለሁ። በእሳቸው መመረጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረናል። በኢትዮጵያ ሁኔታ የሰላም አየር ከለውጥ ውጭ ሊሆን አይችልም።

ሁለተኛ በፓርቲያቸው ግምገማ የነበራቸው ጥንካሬ ለወጣቱም ትልቅ አርአያ ነው የሚሆኑት። ከሁሉም በላይ የኢህአዴግ ዋና በሽታ የሆነውን አግላይነት ሁሉን አቀፍ በሆነ አስተሳሰብ እየቀየሩት ነው። በተለይ ከተመረጡ በኋላ ያደረጓቸው ንግግሮች (ጎንደር እና ባህር ዳር ላይ ተገኝተው ንግግር ከማድረጋቸው በፊት የተደረገ ቃለ ምልልስ ነው) ድሃውን፣ ሴቶችን፣ ወጣቱን ማዕከል የሚደርግ እና የለውጥ አቅጣጫ የሚያሳይ ንግግር ነበር ሲያደርጉ የነበሩት። እንዳጋጣሚ ይህ መጽሐፍ የእሳቸው ነው (ለሁለተኛ ጊዜ እያነበቡት የነበረውን እርካብና መንበር መጽሐፍ እያመለከቱ) አሁን በቴሌቪዥን የሚናገሩት እዚህ መጽሃፋ ላይ ያለውን ነው። ስለዚህ የሚናገሩት ድንገት የመጣላቸውን ሳይሆን ያሰቡበትን እና የራሳቸውን አስተያየት ይዘው ይህችን አገር ለመለወጥ የመጡ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይም ሆኑ አጠቃላይ የለማ ቡድን የሚባለው ቡድን እናንተ አዲስ አበባን ስትይዙ ገና ታዳጊ የነበሩ ልጆች ናቸው። እድገታቸው በኢህአዴግ ቤት ውስጥ በመሆኑና የኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና የውስጥ ግምገማ አልፈው ሂስና ግለሂስ እያወረዱ የመጡ ስለሆነ ከእነዚህ ሰዎች ለውጥ መጠበቅ የዋህነት ነው ሲሉ የሚናገሩ አሉ። እርሰዎ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- ጥያቄው ተገቢ ነው። ኢህአዴግን የምንቃወምበት ምክንያት ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ስላላዳረገ እና ጸረ ዴሞክራሲያዊ አየር በመፍጠሩ ነው። የለማ ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ ህገ መንግስቱን የማክበር፣ ፌዴራሊዝሙን የማክበር ነገር እና ኢትየጵያዊነትን የማክበር ነገር ነበራቸው። ስለዚህ ከኢህአዴግ ውስጥ አዲስ ኃይል እየተፈጠረ ነው፤ ሊፈጠርም ይችላል። በሌሎች አገሮችም የሚታዩት እንኳን እንደ ኢህአዴግ ከፊል ዴሞክራሲያዊ የሆነ ድርጅት ጭፍን የሆነ ጸረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ገዥ መደቦች ውስጥም ቢሆን ከእነሱ የሚወጣ ለውጥ ፈላጊ ሊኖር ይችላል። የኢህአዴግ ፕሮግራም ከሞላ ጎደል ዴሞክራሲያዊ ነው። እነሱም ህገ መንግስቱን አክብረው ፌዴራሊዝሙ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ አለበት ብለው ነው የተነሱት። በዚህ ሌሎቹም የኢህአዴግ ድርጅቶች ለውጥ ያስፈልጋል የሚለውን የተሟላ ነገር ሳይዙ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ነው የመጡት። የምርጫ ሂደቱን ስታየው ራሱ የኢህአዴግን ኋላቀር የሆነ ነገር በጣጥሰው ነው የመጡት። ለምሳሌ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለያየ መንገድ ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ራሳቸውም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ሌሎች ሊያደርጉት ይችላሉ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለይ ሶሻል ሚዲያውን ተጠቅመውበታል።

የኢህአዴግ አመራረጥ ግን ፊውዳል አትለው ምን አትለው በጣም ኋላ ቀር ሲሆን እሳቸው ግን ይህን እየበጣጠሱ ነው እዚህ የደረሱት። ከተመረጡም በኋላ ቢሆን የተለየ ራዕይ እና አስተሳሰብ ያላቸው መሆናቸውን ነው ያሳዩት። በእርግጥ በተግባር ብዙ የሚታይ ነገር ይኖረዋል። እስካሁን ያለው አቅጣጫ ግን የሚያስደስትና እኛም ሁላችንም ደግፈን ለውጡን ማቀላጠፍ ያለብን ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ህወሓት በነበረበት ቆሟል ብለዋል። ፓርቲውም ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሰዎች ታጋዮች ናቸው። ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ከዚህ በተለየ መንገድ ነው የሚጓዙት። ይህን በማንሳትም ፖለቲከኞች ህወሓት መውለድ አይችልም (ተተኪ አያፈራም) ሲሉ ይናገራሉ። ህወሓት ለውጥ ያላመጣበት ችግሩ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

Related stories   አቡነ ማቲያስ መነጋገሪያ ሆነዋል - ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻው እንዲከር ጥሪ አቅርበዋል

ጄኔራል አበበ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው ህወሓት በ1993 ዓ.ም ቆስሎ ነበር። አሁን ያ ቁስል አመርቅዞ የማይድን ቁስል (ጋንግሪን) ሆኗል። ህወሓት ድሮ መማር የሚወድና በመማር የሚያምን ድርጅት ነበር፤ አሁን ግን እንደዛ አይደለም። ስልጣን የተጠሙ ሰዎች የተሰባሰቡበት ስለሆነ የተማረውን ወጣት ክፍል እንዳይቀላቀላቸው የመከልከልና የማራቅ ስራ ይሰራሉ። ምክንያቱም የተማረው ወጣት ወደእነሱ ከገባ ይገዳደርና የእነሱንም ቦታ ይነጥቃል። የህወሓትን ስራ አስፈጻሚ ስትመለከት ከሁለት አባላት በስተቀር ሁሉም ታጋዮች መሆናቸው ይህን ይነግርሃል።

አሁን በአንድ በኩል የእነ ዶክተር ደብረጽዮን የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድንን ከእነ ለማ ቡድን ጋር ታነጻጽራለህ። እነ ለማ አሸንፈው ሲወጡ እነዚህ (ህወሓቶችን) መስራች ነን በሚሉ ሰዎች ታፍነዋል አልወጡም። ስለዚህ ህወሓት ጋንግሪን ያለው ነገር ነው። ጋንግሪን ደግሞ ወይ ተቆርጦ ይወጣና የለውጥ ሀይል ይሆናል አለዚያ ደግሞ ጋንግሪኑ ሌላውን እየበላ የሚሞት ድርጅት ነው ህወሓት።

ሰንደቅ፡- ህወሓት 17 ዓመት በትግል እና 27 ዓመት በስልጣን ላይ ተቀምጦ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት የሚለውን ስሙን አለመቀየሩን በተመለከተ አሁንም ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ድርጅት ነው። እናንተስ ከድርጅቱ የለቀቃችሁ የቀድሞ ታጋዮች በዚህ ዙሪያ የታዘባችሁት ነገር አለ? የስያሜውን ተገቢነት በተመለከተ እርስዎን ጨምሮ አንጋፋ ምሁራንና ታጋዮች ምን ትላላችሁ?

ጄኔራል አበበ፡- ነጻነት ማለት መገንጠል ማለት አይደለም (Liberation is not Independent)። ከብዙ ጭቆና እና ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ነጻ መውጣት ማለት ነው። ስለዚህ ስሙን መቀየሩም ሆነ በስሙ መቀጠሉ የሚለው ጉዳይ ብዙም ለውጥ የለውም። በእርግጥ እስካሁን በዚህ ዙሪያ ውይይትም ሆነ ጥያቄ ገጥሞኝ አያወቅም። ነጻ አውጭ ማለት መገንጠል ሊመስል ይችላል እንጂ ዋናው ፍሬ ነገር (Essence) ግን ገና ሲጀመር ለመገንጠል ሳይሆን እንደነገርኩህ ከሁሉም ጭቆና እና ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ትግራይንም ኢትዮጵያንም ነጻ ለማውጣት ነው።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዙ በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ካደረጉት ንግግር መካከል ‹‹በርካታ የለውጥ አጋጣሚዎችን አግኝተን በወጉ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል›› ብለው ነበር። ብዙ ሰዎች በተለይ በኢህአዴግ ጊዜ ከተፈጠሩ አጋጣሚዎች መካከል የ1983 ዓ.ም ለውጥ፣ የ1993፣ የ1997 ምርጫ ወዘተ… እያሉ ይቀጥላሉ። በእርስዎ እይታ እነዛ መልካም አጋጣሚዎች የተባሉት የትኞቹ ናቸው?

ጄኔራል አበበ፡- ከኤርትራ ጦርነት በኋላ አንድ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ለጦርነት ተንቀሳቅሷል። ለጦርነት እየተንቀሳቀሰን ህዝብ ለዴሞክራሲ እና ለልማት አስተባብሮ ለማነሳሳት በጣም የተመቻቸ ነበር። ስለዚህ ለአገሩ ፍቅር መስዋዕት በመክፈል ያረጋገጠን ህዝብ እንደነገርኩህ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት የተዘጋጀ ህዝብ ነበር። ነገር ግን ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የውስጥ ቀውስ ይህን ሁኔታ በሚገባ ሳንጠቀምበት ቀርተናል። ያ አንድ ዕድል ነበር። በ1993 ዓ.ም የተፈጠረው የፖለቲካ ቅራኔ በሰላማዊ መንገድ ቢፈታ ኖሮ አንድ እርምጃ ወደፊት ይወስደን ነበር።

1997 ዓ.ም ምርጫን እኔ የምገልጸው ወርቃማ (Golden Period) ጊዜ ነበር በማለት ነው። ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ድል ቢቀበል እና ተቃዋሚዎችም ያገኙትን ድል ተቀብለው ፓርላማ ቢገቡ ኖሮ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴያችን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ይሸጋገር ነበር። ከምርጫው በፊት ይካሄዱ የነበሩ ክርክሮች ዴሞክራሲያችንን ወዴት ሊያመራ እንደሚችል እና ሊያብብ እንደሚችል ያሳየ ነበር። ነገር ግን መንግስትም ተደናገጠ ኢህአዴግ ተደናገጠ። ኢህአዴግ ያስብ የነበረው ለፖለቲካ ፍጆታው ያለምንም እንከን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ አደረኩ ለማለት ነበር። ስላልተዘጋጀበት አላወቀበትም። ያ ዕድልም አመለጠን።

ከአስር ዓመት በኋላ ደግሞ ሌላ ምርጫ መጣ። መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል አደገኛ መሆኑን መረዳት ያልቻለ ድርጅት ነው። ግን ደግሞ መቶ በመቶ መረጠኝ የሚለው ህዝብ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ተነሳበት። ስለዚህ 1993፣ 1997 እና 2007 የነበሩ እድሎች አመለጡን ብዬ ነው የማምነው። ግን አሁንም ይህችን አገር ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ዕድል ከፊታችን አለ። ይህን ዕድል እንጠቀምበታለን ወይስ አሁንም እንደ ቀደሙት ሁሉ እናበላሸዋለን? የሚለው ነገር ነው ዋናው ቁም ነገር። አጀማመሩ ጥሩ ነው ተስፋ አለው። እስከምን ድረስ ይሄዳል የሚለውን ግን እያየን መሄድ አለብን። ግን የማይካደው ነገር አንድ ጥሩ ነገር ተፈጥሯል እሱም ዴሞክራሲያዊ አካባቢ መፍጠር የሚያስችል ነገር ነው የተፈጠረው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጸረ ዴሞክራያዊ በሆነ አገዛዝ አንገዛም ብሏል። ስለዚህ አመራሩ ጥሩ ከመራ ወደፊት እንራመዳለን። ያ ከሆነ ከልማቱም ከጸጥታውም ከሰላሙም ተጠቃሚ እንሆናለን።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ሌላው ትኩረት ሳቢ ንግግር ያደረጉት አገራዊ እርቅ እና መግባባት ያስፈልገናል የሚለው ነው። ኢትዮጵያ ሰፊ ምድር እና ብዙ ብሔር ብሔረሰብ ያላት አገር ስትሆን በመካከላችን ግጭቶች መስፈናቸው ታይቷል። የአንድ ብሔር በተለይም የትግራይ የበላይነት አለ ሌሎቹ ተጨቁነዋልም ይባላል። ለመሆኑ ይህ አስተያየት እውነት ከሆነ እና ግጭቶቹም ወደከፋ ደረጃ ሳይሸጋገሩ ተቀርፈው አገሪቱ ወደነበረችበት ሰላም የምትመለሰው እንዴት ነው?

ጄኔራል አበበ፡- ለዚህ ጥያቄ ወደኋላ ተመልሰን ከ2007 ዓ.ም በፊት የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ከ1983 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት 24 ዓመታት ምንም እንኳን አንዳንድ ቦታዎች መጠነኛ ግጭቶች ቢኖርም አገሪቱ ውስጥ ግን ሰላም ነበረ። ይህ ሰላም እንዴት መጣ ብለን ስንጠይቅ በጣም ዘመናዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገ መንግስት ስላለን እና ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ማድረግ ስለጀመርን ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቋሙ፣ ሁሉም በቋንቋው መማር ጀመረ፣ በምርጫ አስተዳዳሪውን መምረጥ ጀመረ፣ ፌዴራል መንግስት እና የክልል መንግስታት ተቋቋሙ፣ እንዲሁም ፕሬሱ ተስፋፋ። እነዚህ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ከባቢ አየር መፍጠር ጀመረ። ስለዚህ ሰው ተስፋ ማድረግ ቻለ።

ከዚያ በኋላ ግን ይህ ዴሞክራሲያ ምህዳሩ እየሰፋ መሄድ ሲኖርበት እየቀጨጨ የሄደበት ሁኔታ ተፈጠረ። ስለዚህ ለሰላሙ መጥፋት እና በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፈጠር ምክንያት የሆነው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ባለመኖሩ ነው። የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገ መንግስት መያዝ ስንጀምር የተሻለ ሰላም ተገኘ፤ ያ ህገ መንግስት ሲጣስ ደግሞ ችግሩ ተፈጠረ። ያን ህገ መንግስት ጥሰት የፈጠረው ደግሞ ኢህአዴግ ነው። ህዝቡ መሬቱን ሲነጠቅና ያለምንም ካሳ ሲቀማ፣ ማዳበሪያም በግድ ውሰድ የሚባልበት ሁኔታ ነበረ፣ በአጠቃላይ ብዙ ግፍ ነው ህዝቡ ውስጥ የደረሰው። ይህ በመሆኑ ደግሞ በህዝቦች መካከል ግጨትን ፈጠረ። ከዚያ በፊት እኮ አንዳንድ አካባቢ የአማራ ተወላጆችን የማፈናቀል ነገር ነበረ እንጂ በሶማሌ እና በኦሮሚያ መካከል እንደተደረገው አይነት ግጭት አልነበረም።

ለምሳሌ የትግራይ የበላይነት አለ ይባላል። ይህ ውይይት አይደረግበትም። በሚዲያ ውይይት ቢደረግበት ችግሩ ካለ ይስተካከላል ችግሩ ከሌለ ደግሞ የለም ይባላል። በእኔ እምነት የትግራይ የበላይነት የሚባል ነገር አልነበረም በዚህ ስርዓት ሊኖርም አይችልም። በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያዊነት እንዳሁኑ አድጎ አያውቅም። በደርግ ጊዜ ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ነጻ አውጭ ድርጅት ነበር። ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ቢነግርም ህዝቡ ግን ይገደል ነበር። ህዝቡ እየተገደለ ኢትዮጵያዊነትን ማሳደግ አይቻልም። አሁን ለምሳሌ ጋምቤላው ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለት የሱን ማንነት የሚያውቅ የራሱ አስተዳዳሪ አለው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት በጣም ነው ያደገው። ነገር ግን ዴሞክራሲው እየቀጨጨ ሲሄድ ኢትዮጵያዊነትን እየተፈታተነው መጣ። ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ከባቢ አየር ቢኖር ብሔር ብሔረሰቦች በመካከላቸው ልዩነት ቢኖር እንኳን ችግሩ ለዚህ ሳይደርስ በውይይት መፍታት ይቻል ነበር። እስከ 2007 ዓ.ም ያልነበረ ነገር ነው እኮ አሁን የተፈጠረው ነገር።

ሰንደቅ፡- እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ሰላም ከነበረ በአንድ ጀምበር ተነስቶ እዚህ ደረጃ ደርሶ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል እና ለበርካች ሞት እንዴት ሊበቃ ቻለ? የዞረ ድር ውጤት ነው ብለን መውሰድ አንችልም?

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

ጄኔራል አበበ፡- እሱ እኮ ነው ያልኩህ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየቀጨጨ ሲሄድ ህዝቡ መብቶቹ እየተረገጡ ሄዱ። ይህ የመብት ጥሰት ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ነው የበደለው ተለይቶ ተጠቃሚ የሆነ ብሔር የለም። ለምሳሌ በትግራይ ክልል ያለው አፈና እና የመብት ጥሰት ከሌላው ብሔር ይልቅ የከፋ ነው። ከሞላ ጎደል በትግራይ ክልል ያለው አገዛዝ የኤርትራ አይነት ነው ማለት ይቻላል። እኔ ያልኩት ችግሩ 2007 ዓ.ም መጣ ሳይሆን የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ሲሄድ ሰው ስጋት ውስጥ ገባ እና በ2007 ዓ.ም ችግሩ ፈነዳ። አሁን ያለው ችግር እየመጣ መሆኑን የገዥው ፓርቲ ሰዎች እየተነገራቸው ቀለል አድርገው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ብለው ሊያልፉት ፈለጉ። በ2009 ዓ.ም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ አዋጁን ሊሰሩበት ሲገባ ተደበቁበት።

ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ መሰረታዊ ችግሩ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እጥረት ስላለ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከብዙ ሺህ እና መቶ ዓመታት አብሮ የኖረ ህዝብ ችግሮች እንኳን ቢኖሩበት በውይይት ችግሮቹን በመፍታት እንደቀደመው አብሮ ይኖር ነበር። ለምሳሌ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል የተፈጠረው ችግር እዛ አካባቢ ያሉ መሪዎች በሙስና የተዘፈቁ ስለሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉት ሰላም እንዳይኖር ነው የሚፈልጉት። ምክንያቱም ሰላም ካለ የእነሱ ሙስና እና ወንጀል ይጋለጥባቸዋል። ይህ ደግሞ የመንግስት ችግር በተለይ ህገ መንግስቱ ላይ ኢህአዴግ ስላመጸ ህገ መንግሰቱን ስላላስከበረው እንጂ ህዝቡ በሰላም አብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊትም ሆነ ከዚያ በፊት የአማራ ተወላጆች ከኦሮሚያ እና ሌሎች አካባቢዎች ሲፈናቀሉ ምንም አልተደረገም። ችግሩን ማነው ያጠፋው ለምን አጠፋው? ተብሎ በህገ መንስቱ መሰረት ማጣራትና ምርመራ አልተደረገም። ዝም ብሎ እነዚህ ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ ናቸው ወዘተ ተብሎ በዝምታ ታለፈ፡ ያ ችግር ዝም ሲባል አሁን ከደረሰበት ደረጃ ደረሰ።

ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ጥሩ መስመር እንዲመጣ ለኤርትራው መንግስት ዶክተር አብይ በአደባባይ ጥሪ አቅርበዋል። በኤርትራ በኩል ደግሞ የሚነሳው ቅሬታ ‹‹መጀመሪያ ኢትዮጵያ በወረራ የያዘችብንን ባድሜን ትመልስልን›› የሚል ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ከሁለት ወራት በፊት ተናግረው ነበር። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንደተሳተፈ የጦር አዛዥ በባድሜ እና በአሰብ ጉዳይ ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ይስጡን እስቲ፤

ጄኔራል አበበ፡- ፕሬዝደንት ኢሳያስ እንኳን የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝቦች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግ ቀርቶ ኤርትራዊያንንም ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ ነው በጭቆና ስር እና ሙሉ በሙሉ በፖሊስ አስተዳደር ነው እየገዟት ያለው። ስለዚህ ለሁለቱ ህዝቦች መገናኘት የሰላም አምባሳደር ሊሆኑ አይችሉም። ነገር ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ዘንባባ ይዘው መምጣታቸው ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ኢሳያስን ብቻ አይደለም የምናየው፤ የኤርትራ ህዝብን ነው። ስለዚህ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በሰላም ከመጡ ጥሩ ካልመጡ ደግሞ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ጥሩ ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ ጥሩ ይመስለኛል።

የባድመም ሆነ የአሰብ ጉዳዮች ቁጭ ብሎ በውይይት መፈታት ይኖርበታል። ቀደም ብሎ የተፈረደው ፍርድ አለ ያን ፍርድ የሚተገበርበትን መንገድ በራሱ መወያየት ያስፈልጋል። ነገሩ ግን ከዚያ በላይ ነው። በተለይ ትግራይ እና አፋር አካባቢ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሰላምም ጦርነትም የሌለበት መሆን ህዝቡን ብዙ ጎድቷል። ምክንያቱም በአካባቢው ኢንቨስትመንት ማካሄድ ያስቸግራል፤ ገበሬዎቹም በየቀኑ ዘብ መውጣት አለባቸው፤ ስለዚህ ያ ነገር መፈታት አለበት። ችግሩ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰዷ ጥሩ ነው። ነገር ግን እዛ በሰላም የማይኖር ህዝብ አለ። ስለዚህ በአጭር ጊዜ ከኤርትራ መንግስት የምንጠብቀው ምላሽ ‹እምቢ›› ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ዶክተር ያዕቆብ ኃለማሪያም “አሰብ የማናት?” በሚለው መጽሃፋቸው ዓለም አቀፍ ህጎችን ተጠቅመን የባህር በር ሊኖረን የሚያስችል መብት አለን ሲሉ ጽፈው ነበር። በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ግንኙነት ሲፈጠር ወደቡን የመጠቀም እድል ለኢትዮጵያ መብት ይሰጣል ወይስ ቀድሞም ወደቡ ለኢትዮጵያ ይገባት ነበር ብለው ነው የሚያምኑት? 

ጄኔራል አበበ፡- የማስትሬት ዲግሪ መመረቂያ የጥናት ጽሁፍ የሰራሁት “Ethiopian Soveriegn Right Access to the Sea” በሚል ርዕስ ነበር። መጀመሪያ በዚህ ርዕስ ለማጥናት ከመጀመሬ በፊት በፖለቲካ የማምንበት የነበረው አሰብ የኤርትራ ነው ስለዚህ እኛ ኤርትራን መውረር የለብንም የሚል እምነት ነበረ፣ ስልጣን ላይ እያለሁ። የማስትሬት ትምህርቴን ስጀምር ግን “የባህር በር አልባ ሆነን ምንድን ነው መብታችን?” የሚለውን ለማወቅ ነበር ጥናቱን የጀመርኩት። ምክንያቱም በጦርነቱ ጊዜ ከአሰብ ወደ ጅቡቲ ስንዞር ብዙ ንብረት ነበር የወሰዱብን። እንዲሁም ብዙ ውጣ ውረድ ስለነበረ በጣም ነበር የተናደድኩት። የባህር በር ባይኖረንም መብት አይኖረንም ወይ የሚል ነበር ህግ ትምህርት ቤት ያጠናሁት።

መጀመሪያ የባህር በር ባይኖረንም የምናገኘው መብት ምንድን ነው? የሚለውን ርዕስ እየቆየሁ በሂደት ርዕሱን ቀየርኩትና የባህር በር የማግኘት መብት (Access to the Sea) ቀየርኩት። ዓለም አቀፉ ህግም ይፈቅድልናል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፌዴሬሽን በነበሩበት ወቅት የነበረው ውሳኔ (ያ ውሳኔ) ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ስትቀላቀል አንደኛውና ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዲኖራት የሚያደርግ ነው። ኤርትራ ስትገነጠልም ያ መብት ለኢትዮጵያ ይቀርላታል ማለት ነው። ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መብቷ የማይገረሰስ (Sovereign Right) ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ህግ ሳናጠና እና እውቀቱ ያለው ሰውም ሳናማክር አስቀድመን በነበረው ፖለቲካ ነው የወሰነው።

ሰንደቅ፡- እዚህ ላይ ግን ዓለም አቀፍ ህጉን ሳናጠና ወይም ባለሙያ እንዲያማክረን ሳናደርግ በፖለቲካ አቋም ብቻ ነው የወሰነው ይበሉን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ምሁራን (ዶክተር ያዕቆብን ጨምሮ) በወቅቱ ለአቶ መለስም ሆነ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ለነበሩት ኮፊ አናን ውሳኔው ኢትዮጵያን ተጎጂ እንዳያደርጋት ደብዳቤ በመጻፍ ጭምር ጠይቀው ነበር። በወቅቱ አቶ መለስም የአሰብን ወደብ የሻዕቢያ መንግስት ‹‹ግመል ያጠጣበት›› ብለው እስከመመለስ ደርሰው ነበር በፓርላማ። አሁን ደግሞ እርስዎ ባለማወቅ የተወሰነ መሆኑን እየነገሩን ነው። በትክክል ግን ባለማወቅ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ጄኔራል አበበ፡- በጥናቴ ላይ የተረዳሁት ሁለት ነገሮች ድንቁርና ወይም አለማወቅ እና እብሪት (Ignorance and arrogance) መደባለቃቸውን ነው። አሸናፊ ስትሆን ሁሉንም ነገር የምታውቅ ይመስልሃል ሳታውቀው። አቶ መለስም ቢሆን የኢትዮጵያን መብት አሳልፈው ለመስጠት ፈልገው አይደለም እኔም አመለካከቴ እንደዛ ነው። የኤርትራ ከሆነ እና ኤርትራ የምትባል አገር ካለች የሌላ አገር መሬት መውሰድ የለብንም የሚል አቋም ነው የነበረኝ። ግን ዓለም አቀፍ ህግ ሁላችንም አናውቅም። እስኪ አጥኑ እና የጥናታችሁን ውጤት አምጡ የሚል የለም። ‹‹አሰብ የእኛ ናት›› የሚሉ በሙሉ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ጦርነት ናፋቂ ናቸው ብለን ከመጀመሪያው ነው የደመደምነው። እብሪት ያልኩህ እሱ ነው። ጥናቴ ላይ የጻፍኩትም ድንቁርና እና እብሪት ተደባልቋል የሚል ነው።

ሰንደቅ፡- ከኤርትራ መገንጠል ጋር ተያይዞ የአሰብ ወደብን ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠ ውሳኔ በመወሰኑ ወደቡን ለኢትዮጵያ በጎ የማያስቡ አገራት በቁጥጥር ስር አውለውታል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አደጋ አለው ሲሉ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። እውን አደጋው ምን ያህል ያሰጋል? መፍትሔውስ ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- አሁን አደጋው የባህር በር አልባ (Land locked) መሆናችን ብቻ አይደለም፤ ችግሩ ከዚያ በላይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ አንድ ያጠናሁት ጥናት ነበረ። ብሔራዊ የደህንነት ፖሊሲ ላይ የሚጠና አንድም ተቋም የለንም። መከላከያ የራሱን ያጠናል ያም የራሱን ያጠናል። አጠቃላይ አገሪቱን የሚመለከት የደህንነት ፖሊሲ አጥንቶ ስትራቴጂ ተቀርጾ በእሱ የምንሄድበት ሁኔታ የለም። ተቋም አለመኖሩ ነው ትልቁ ስጋት። ኤርትራ ውስጥ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ቡድን ማስቀመጥ አልነበረብንም። እኔ በኤርትራ ነጻነት አምናለሁ፤ ምክንያቱም ህዝቡ ፈልጎታል፤ መብታቸውን ማክበር አለብን። ግን የእኛ መብት ደግሞ መረጋገጥ አለበት። በኤርትራ ያለው ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ነው። እኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦታ ብሆን በኤርትራ ያለው ነገር እንዲቀጥል አልፈቅድለትም፤ የራሳቸውን ስራ ይስሩ በእኛ ጉዳይ ግን ጣልቃ እንዲገቡ አልፈልግም፤ በየጊዜው ሰው እየላኩ የማተራመስ ስራ አልፈቅድላቸውም። አሁን ችግሩ በኤርትራ ያለው በተግባር ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ኃይል ዝም ብለነዋል። በዚህ ደግሞ ዋናው ስጋት ኤርትራ ሳትሆን የባህር በር የሌለን መሆኑን ተከትሎ ኤርትራ ውስጥ የጦር እንቅስቃሴ ይታያል፤ የግብጽም የገልፍ አገራትም። ኤርትራ የምትባለው አገር ሰላማዊ ሆና እስከቀጠለች ድረስ የባህር በር የማግኘት መብታችንን እንጠይቃለን። በህጋዊ መንገድ ማግኘት ይኖርብናል። ግን ህግ ደግሞ ሁልጊዜ ከኃይል ውጭ በህግ የሚባል ነገር የለም። በዓለም አቀፍ ህግ ኃይል እና ህግ ተሳስረው ነው የሚታዩት። ስለዚህ ያን መብታችንን ማረጋገጥ አለብን።

Related stories   በአቡነ ማቲያስ መልዕክት ሳቢያ - ሲኖዶስ በመቆጣቱ አስቸኳይ ስብሰባ ተደርጎ የተግሳጽና የማስተካከያ መግለጫ ሊሰጥ ነው

የአትዮጵያ መንግስት ደግሞ በኤርትራ በኩልም ሆነ በደቡብ ሱዳን የተቀናጀ ስትራቴጂ እና ፖሊሲ ያለው አይመስለኝም። አካባቢያችንን በደንብ አውቀን ደህንነታችንን የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማውጣት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የሚችል ተቋም የሌለን መሆኑ ደግሞ ትልቁ ፈተና ነው።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ፖሊሲ እየቀረጸ መሆኑን ከዓመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር። እስካሁን ግን የፖሊሲው ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተገለጸ ነገር የለም። እርስዎን ጨምሮ በርካታ ምሁራን እና ፖለቲከኞች የኤርትራ ጉዳይ ለኢትዮጵያ በጣም አሳሳቢ እና አስጊ መሆኑን እየገለጻችሁ ነው። በዚህ ሁኔታ የፖሊሲው ጉዳይ መዘግየቱን እንዴት ያዩታል?

ጄኔራል አበበ፡- በ1994 ዓ.ም የወጣ የውጭ ጉዳይ እና ግንኙነት ፖሊሲ አለ። ያ ፖሊሲ ከሞላ ጎደል ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉት። ግን ደግሞ ብዙ ችግሮችም አሉበት። አሁን ያለነው 2010 ዓ.ም ነው፤ ፖሊሲው ከወጣ 16 ዓመቱ ነው፤ እስካሁንም አልተሻሻለም። ሌላው ፖሊሲው ሲቀረጽ ባለሙያዎች የሰሩት ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ እና በአካባቢው ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን ሰብስቦ ያደረገውን ጨዋታ ነው ፖሊሲ አወጣን የሚሉት። በመጀመሪያ ደረጃ የአገር ፖሊሲ ሲወጣ በመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ፓርላማው ቢሆንም ሁሉን አሳታፊ የሆነ ለምሳሌ ምሁራንን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና ራሱ ኢህአዴግ ያሉበት ሆኖ የሁሉም ድምጽ ሊሰማ ይገባዋል። ያም ሆኖ እየተቀረጸ ነው የተባለውም አጀማመሩ ጥሩ ስላልሆነ አሁን የት እንደገባም አይታወቅም።

ሰንደቅ፡- ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀት አለበት የሚለውን በርካቶች የሚስማሙበት ነጥብ ነው። ነገር ግን ‹‹ኢህአዴግ በተለይም የኢህአዴግ አስኳል የሆነው ህወሓት በባህሪው አግላይነት የተጠናወተው ስለሆነ አብሮ መስራት አይታሰብም›› ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- በመሰረታዊነት አግላይ ባህሪ የህወሓት ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ባህሪ ነው። አሁን ግን አዲስ አመራር ከኦህዴድ እየመጣ ነው፤ ተስፋ እየጣልንበትም ነው። ይህ አመራር ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች እያነጋገረ እና ቃል የሚገቡትን ነገሮች እየፈጸመ ከሄደ ህወሓት የግድ ይቀየራል። ህወሓት የኢህአዴግ አስኳል መሆኑን ካቋረጠ ቆየ እኮ። ተቃዋሚውም ሆነ ራሱ ህወሓት አልገባቸውም እንጂ የኢህአዴግ የፖለቲካ ማዕከል ህወሓት መሆኑ ከቀረ ቆይቷል። ህወሓት እንደ ድርጅት ጠንካራ መሆኑን ካጣ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ደጋግሜ በትግርኛ የምጽፈውም ህወሓት እየሞተ መሆኑን ነው።

ሰንደቅ፡- የህወሓት መዳከምም ሆነ እየሞተ መሄድ የጀመረው እናንተ ከወጣችሁ በኋላ ነው ወይስ አቶ መለስ ካለፉ በኋላ?

ጄኔራል አበበ፡- እኛ ስንወጣም ትንሽ ችግር ነበረው። በእርግጥ እኛ ከዛ ፖለቲካ ውስጥ አልነበርንም (እሳቸውና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ በጡረታ የተገለሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ነበሩ)። ዋናው ግን እሱ ሳይሆን ከዛ በኋላ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ከባቢ እና ተቋማት እየተፈጠሩ አለመሆኑ ነው። አቶ መለስ ይህችን አገር ለመቀየር የተቻላቸውን ነገር አድርገዋል፤ በተለይ ከልማትና ከድህነት ቅነሳ አኳያ። ዴሞክራሲን በመገንባት በኩል ግን እየታፈነ እየታፈነ ነው የሄደው። ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ እኮ ህወሓት ጽሁፍ የሚጽፍ አንድም ሰው እንኳን የላቸውም። ህወሓት በእሳቸው ቃል ብቻ የምትኖር ድርጅት ነበረች የሚል ነገር ነበር። በእርግጥ አገሪቱም ወደዛ የመሄድ ነገር ነበረ። ስለዚህ የ1993 ዓ.ም ክፍፍሉ አንድ አስደንጋጭ ተሞክሮ (trauma) ነበር። ግን ሊታረም የሚችል ነገር ነበር። ከዛ በኋላ የተማረውን ወጣት በሙሉ አገሪቱን በመገንባቱ ሂደት ቢሳተፍ ኖሮ ተቋማት ስራቸውን ቢሰሩ ለምሳሌ አቶ መለስ በገመገሙት 1992 ዓ.ም ፓርላማው አቅመ ቢስ (Rubber Stamp) ሆኗል የሚል ነበር። በዚያ ጊዜ የነበረው ፓርላማ ጥቂትም ቢሆን ተቃዋሚዎች የነበሩበት ስለነበረ ይሻል ነበር። ከዚያ በኋላ ያሉት የፓርላማው እንቅስቃሴ (2002 እና 2007 በተደረጉ ምርጫዎች የተመሠረተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) በ1992 ዓ.ም ከነበረው የባሰበት ሆነ። ፓርቲዎችም ተቋማትም እየተዳከሙ ነው የሄዱት።

ህወሓት ብቻ ሳይሆን ብአዴንም የአማራውን የተማረ ወጣት በማደራጀት አልተጠናከረም እየተዳከመ ነው የሄደው። ኦህዴድም እንዲሁ በአንጻራዊነት ደኢህዴን ይሻሻላል። ህወሓትም ሆነ ብአዴን የተዳከሙት ከእነሱ ውስጥ ያሉት ሰዎች መጥፎ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም መተካካት አለመኖር ነው።

ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አድርገን እንጨርስ። ዶክተር አብይ ትናንት ያዋቀሩትን ካቢኔ (ቃለ ምልልሱ የተካሄደው ዐርብ ዕለት ነበር) እንዴት አዩት?

ጄኔራል አበበ፡- በጣም አስበው እና አቅደውበት እንዳደረጉት ይገባኛል። ለውጥ ለማካሄድ እንቅፋት ይሆኑብኛል ያሏቸውን አካባቢዎች ለይተው አስበው እንደሰሩት ያሳያል። በአቶ ኃይለማሪያም ጊዜ የጠፋ አንድ አደረጃጀት ነበር። የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኦፊስ የሚባል አቶ አባዱላ የተመደቡበት። እሱ መደራጀቱ ራሱ በጣም ጠቃሚ ነው። ግን ደግሞ ከጠበኩት በታች ሆኖ ነው ያገኘሁት። በተለይ ተፎካካሪነትን በሚመለከት ወደ ፖለቲካ ታማኝነትና የፖለቲካ አጋርነት ያዘነበለ ምደባ ነው ያካሄዱት። ስለዚህ እዛ ላይ ትንሽ ቅሬታ አለኝ። ሰዎቹን ስለማውቃቸው ሳይሆን ከዚህም እዚያም የነበሩ ሰዎች ናቸው አሁንም ወደ ሌላ ስራ የተመደቡት። ለምሳሌ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ወደ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መመደብ አልገባኝም። አጠቃላይ ሲታይ ጥሩ ቢመስልም ከተፎካካሪነት አኳያ ሲታይ ክፍተት አለበት።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት ወቅት የተናገሩት “የችሎታ ክፍተት ቢኖር ለመማር ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ በመማማር መሙላት ስለሚቻል እሱን እናደርጋለን” የሚል ሀረግ ተጠቅመዋል። የአቅም ችግር እንዳለ እያመኑ ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ግለሰቡን መመደብ አሁንም ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለንም የሚሉ ምሁራን አሉ። እርስዎ ይህን እንዴት ገመገሙት?

ጄኔራል አበበ፡- የአቅም ችግር ያለበትን ሰው ከመጀመሪያው ለምን ወደ ስልጣን ማምጣት አስፈለገ? የኔ የመጀመሪያው ጥያቄም ይህ ነው። አቅም ያለው ሲባልም መቶ በመቶ ብቁ የሆነ ሰው የለም፤ ስለዚህ መደጋገፉ አይከፋም። ነገር ግን የአቅም ጉድለት ቢኖርም ብለው ሲናገሩ ግን መጀመሪያ አቅም አለው ብለው ያቀረቡት በመሆኑ ነው ጥያቄዬ። ሁሉንም ባይሆን አንዳንዶቹ አቅም እንደሌላቸው እኛም እናውቃቸዋለን። ለምሳሌ መከላከያ ሚኒስትር የተመደቡት ስለ ሴኩሪቲ ምን ያህል ያውቃሉ? ብለን እናነሳለን። ግን መማር የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በነገራችን ላይ እየተናገርኩ ያለሁት ስለ አንድ ግለሰብ አይደለም። አጠቃላይ ግን ብቃትን ማዕከል ያደረገ ሰው ይመጣል ብዬ ነበር ስጠብቅ የነበረው። በአንድ በኩል ጊዜው አጭር በመሆኑ አሁን የተዋቀረው ካቢኔ የእሳቸው ካቢኔ ሳይሆን የሽግግር ካቢኔ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ፖለቲካውን ለማረጋጋት የፖለቲካ አጋርነትን (political alliance) ፈልገው ይሆናል እንጂ ከብቃት (Compitenecy) አንጻር የዶክተር አብይ ካቢኔ ይህ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *