ደ/ረ አቢይ አህመድ ለአንድ ፖለቲከኛ ከሚያስፈልገውም በላይ የንግግር ችሎታ እንዳላቸው እያየን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እውቀት የመቃረም ከሀሳቦች ጋር በግልም ሆነ በአደባባይ ለመፋተግ የመድፈር ፍላጎታቸው ግልጽ ነው፡፡ በአነዚህ ፍለጎቶቻቸው እና ከጠቅላ ሚኒስቴርነት ስራቸው በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትርፍ ጊዜ መምህርነትን / Visiting Professor/ ቢያክሉ ለአገር መምራት ስራቸውም፤ ለቀጣይ ትውልድም፤ ለቀጣይ ሕይወታቸውም ይጠቅማል ባይ ነኝ፡፡

ስራ አይበዛም?

ይሄን ሀሳብ መጀመሪያ የሚቀርብበት ተግዳሮት ጠ/ሚው ካላቸው የስራ ብዛት አንጻር በዩኒቨርሲቲ ማስተማርን ማከል ስራ መደራረብ አይሆንም ወይ የመሪነት ስራቸው አይበደልም ወይ የሚል ጠንካራ መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ቋሚ ፕሮፌሰር ከመሆን የቪዚቲንግ ፕሮፌሰርነት ለስራ ባሕሪያቸው የሚመቸው፡፡ በዓለም ላይ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት እና የትላልቅ ኮርፖሬሽን መሪዎች የቪዚቲንግ ፕሮፉሰርነትን የሚመርጡበት ዋነኛ ምክንያትም በስራ ለተጨናነቀው ውሎአቸው ስለሚመች ነው፡፡ ለምሳሌ የኢራን ውጭጉዳይ ሚኒስቴር የሆኑት ሙሀመድ ጃቫድ ዛሪፍ የተጨበጨበላቸው የውጭ ጉዳው ፕሮፌሰር ናቸው፡፡

ደ/ር አብይ ከፈለጉ በዓመት አንድ ሴሚስተር ብቻ ያውም ተማሪዎቹ አዛው የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እየመጡ ሌክቸር እንዲወስዱ ማድረግ ይችላሉ ይህን አይነት አሬንጅመንት ስራ ለማቅለልም ሆነ ለፕሮቶኮል ወይንም በሰበብ አስባቡ ከሚያኮርፈው የዩኒቭርሲቲ ተማሪ ዞር ብሎ ለማስተማርም ይመቻል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የ/ር አቢይ የተማሪዎችን ጽሁፍ ለማረምም በደ/ር አብይ ተሰጠው ሌክቸር ላይ ከክፍል በኋላ ውይይት ለማድረግ የሚያግዜ አንድ ሁለት የዶክትሬት ተማሪዎች መቅጠር በጣም ስራ ያቀላል፡፡

ሌላው ስራ ማቅለየያ መንገድ ደ/ር አብይ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የፈለጉትን ፕሮፌሰር በመጋበዝ ተከታታይ ሌክቸር ለክፍላቸው እንዲሰጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንደ አገር መሪነታቸውም የእሳቸውን የሌክቸር ግብዣ በበርካታ ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በክፍሉ ውስጥም እሳቸው በዋነኛነት የፕሮፌሰሩን ሀሳብ በመሞገትም ሆነ በማብራራት ከተማሪዎቹ የሚነሳውንም ጥያቄ እና ሙግት በመካፈል በሴሚናር መልክ ክፍሉን በመምራት የሌክቸር ስራvውንም ሊያቀሉት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፤ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እና ሌሎችንም ምሁራንን በዚህ መልኩ በመጋበዝ ክፍላቸውን ተወዳጅም ጠንካራም ማድረግ ይችላሉ።

ማስተማር ለስራቸው ምን ይጠቅማል?

ማስተማር ለጠሚው መጀመሪያ የሚጠቅማቸው ዋነኛ ስራቸው ከሚፈጥርባቸው ማህበራዊ እና የሀሳብ አጥር buble ውጪ እንዲንቀሳቀሱ ለተለያዩ ሀሳቦች፣ትችቶች ክርክሮች ፖለቲከኛ ብቻ ላልሆኑም ሰዎች እንዲጋፈጡ ያደርጋቸዋል። ሀሳቦች ለሀሳብ ብቻ ብለው በሚፋጩበት የዩኒቨርስቲ ክፍሎች ውስ ደ/ር አቢይ ከካቢኔአቸው ወይንም ከአማካሪዎቻቸው ከሚቀርብላቸው ሀሳብ ላይ ተጨማሪ እና አጋዥ የመፍትሄ ሀሳቦች፣ ተረኮች፣ተጨማሪ መፍትሄ ለማግኘት ጥያቄ መቅረጫ Problematization መድረክ ያገኛሉ።

ይሄ ግን በሚገባው ተግባራዊ እና እውን የሚሆነው ደ/ር አብይ ለክፍላቸው ተማሪም ሆነ ፕሮፌሰር ሲመርጡ ካድሬ ብቻ፣ የሚስማማቸውን ብቻ እንደማይመርጡ ታሳቢ በማድረግ ነው። ያለበለዚያ የደ/ር አቢይ ክፍል ሲቪል ሰርቪስ part 2 ከመሆን አይድንም።

ሁለተኛ ደ/ር የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ መሆን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዳይ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያሉአቸውን ሀሳቦች በደንብ እንዲያብራሩ በዘርፍ ዘርፉ እንዲያስቀምጡ የራሳቸው የሆኑ ቀኖናወችም እንዲነድፉ ሀሳቦቻቸውን እና ምርምሮቻቸውንም በጠንካራ መልኩ እንዲፅፉ ሰፊ እድል ይሰጣቸዋል። ይሄ ደግሞ በቀጥታ በስልጣን ከሚኖራቸው ተፅእኖ ባሻገር በሀሳብም ተፅእኖ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በሃሳብ ተፅእኖ መፍጠር መቻል ደግሞ ከስልጣን ዘመናቸው በኋላም (ቢያንስ ቃል እንደገቡት ከ2 ተርም በላይ አይቆዩም በማለት ) በሃሳብም በአገሪቷ ፖለቲካ እና መዋቅር ላይ ተፅኖ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።

ሶስተኛ በዮኒቨርስቲ ማስተማር በአገሪቷ የቀጣይ ትውልድ በተለያየ ዘርፍ መሪ የሚሆኑትን ወጣቶች በግል ለማወቅ ለመቅረፅ ለመኮትኮት ይረዳቸዋል። ይሄ ደግሞ በሃሳብ ከሚኖራቸው ተፅእኖ ባሻገር ሰፊ የግል ኔትወርክ እነወዲኖራቸው ያስችላቸዋል። ለምሳሌ ከሚቀጥለው አመት ጀምረው ማስተማር ቢጀምሩ ከዚህ በኋላ 11 አመት መስልጣን ላይ ቢቆዩ በአንድ አመት ውስጥ ደግሞ 30 ተማሪዎች ይኖሩአቸዋል ብንል የሚያቋርጠው ትምህርት የሚያቋርጠው ምናምን ተጨማምሮ ስለወጣናቸው ሲያበቃ 300 ምናምን ተማሪዎች ይኖራቸዋል። ይሄ ቀላል ተፅእኖ አይደለም። በዚህ መንገድም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚተኳቸውን ወይንም ሊተኳቸው ብቁ የሆኑ ሰዎችንም ያፈሩበታል።

ከአሁኑ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ስራ የመጀመር አራተኛው ጥቅም ከስልጣን ባሻገር ያላቸውን ሕይወት ከአሁኑ እንዲቀርፁ / Exit Strategy/ ስለሚሆናቸው ነው። በትርፍ ጊዜ 10 ዓመት በላይ የማስተማር ልምድ ከአገር መሪነት ጋር ሲታከልበት በ52 ዓመታቸው በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኝ ዪኒቨርሲቲ ተፈላጊ እና የበቁ ዓለም አቀፍ መምህር መሆን ይችላሉ። አይ ሙሉ ለሙሉ መምህር መሆን አልፈልግ ካሉ ደግሞ የ10+ ዓመት የትርፍ ጊዜ ፕሮፌሰርነት ከአገር መሪነት ያውም ኢትዮጵያን የመሰለ ውጥንቅጣም አገር የመምራት ልምዳቸው ጋር ከክራይስስ ግሩፕ እስከ ጉግል ላለ ለየትኛውም የዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የንግድ ተቋም ዳይሬክተር ፣ትረስቲ፣ ቦርድ ዳይሬክተር ለመሆን የሚያበቃ የልምድ እና ቲየሪ ማደሰበሪያ መድረክ ይሆናቸዋል።

#Ethiopia #AbiyAhmed

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *