“Our true nationality is mankind.”H.G.

ይህ መንገድ ከሙርሲ አካሄድ ጋር ሊገናኝ ይችል ይሆን?

ዶ/ር ደረጀ ገረፋ በዚህ ሰሞን ፅፎ በለጠፈው ፅሁፉ ጠ/ሚኒስትሩን መተቸት ወይም መንቀፍ እንደ ግብፆቹ የፕረዝዴንት ሙርሲ አብዮት የወታደሩ ኃይል ወደ ስልጣን በመምጣት ጉዞውን የማሰናከልና የመቀልበስ/counter revolution/ አደጋ ሊኖር እንደሚችል ፍርሃት እንደገባው ሲገልፅ ነበር፡፡
ነገር ግን እንደነው ዕድሜ ያደላችሁ እንደምታስታውሱት የግብፆቹን አብዮትና ከዚያም ተከትሎ ስለተከሰቱ አንኳር አንኳር ጉዳዮች እተከታተልኩ በተለያዩ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ከስር ከስር ትንታኔ ስሰጥ እንደነበረ እንደማትዘነጉት አምናለሁ፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ አሁና ሰዓት ድረስ በሚገባ የማውቀው ጉዳይ መሆኑ ደግሞ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ በመንተራስ ተመሳሳይ ውድቀት /counter revolution/ የኛን አብዮት እንዳይገጥመው በጅጉ ስለፋና ስደክም እንደነበርኩ ማስታወስ ግድ ይለኛል፤ በተለይ በወረሃ ጥቅምትና ህዳር 2010 የነበሩ የህዝብ ጩኸቶች መለስ ብሎ መፈተሸ መልካምነት ይመስለኛል፡፡
አሁን ካለንበትና ከደረስንበት ስብዕና በመነሳት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን የፕረዝዴንት ሞሀመድ ሙርሲ ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው ይችል ይሆን?ማሟረት አይሁንብኝና መልሱ ሳያሻማ አዎ! ይሆናል፡ ነገር ግን ሊከሰት የሚችለው አሁን እየተባለ ባለው “በመተቸትና በመንቀፍ” ሳይሁን ጠ/ሚኒስትር አብይ በሚሰራው የራሱ የተሳሳተ አሰራርና አካሄድ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡አንባቢዎች ሊረዱት ስለሚገባ ለአስረጂነት አንዳንድ የፕረዝዴንት ሞሀመድ ሙርሲ ስህተቶች ለወታደራዊው ሀይል እንዴት መንገድ ሊከግት እንደቻለ መጠቃቀስ ተገቢና አስፈላጊም ጭምር ይሆናል፡፡ እንደሚከተለው ይሆናል፡
የፕረዝዴንት ሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ የገረሰሰው ህዝባዊው ተቃውሞ ነው፡፡ ይህ ማለት ሞሀመድ ሙርሲ ወደ ስልጣን ሲመጡ ልክ አሁን በሀገረ ኢትዮጵያ እንዳለው ተቃውሞና የሀይል ጎራ ሁለት ተመጣጣኝ ሊባልለት የሚችል ሀይል ነበረ፡፡ የመከላከያውና የደህንነቱ ክፍል ባንድ ጎራ ሲሆኑ የተቃውሞ ህዝባዊው ሀይል ደግሞ በሌላኛው ጎራ ነበሩ፡፡ እንግዲህ ፕሬዚዴንቱ አስቀድሞ ከነዚህ ሁለቱ ካምፕ የትኛው የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችለው በማነፃፀር ማወቅና ለየረቶ መያዝ መቻል ነበረበት፡ አልሆነም፡፡ ስህተት አንድ ከዚህ ይጀምራል፡፡
እንደት? ብሎ መጠየቅ የጤና ነው፡፡ ሀገሪቱ የነበረችው በአምባገነናዊው ስርዓት ስር ስለነበረ በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በስርዓቱ የተደቆሱና አቅም ያጡ መናኞች ነበሩ፡፡ ከነሱ መካከል በመጠኑ የድርጅት ስብዕና የነበረው ሕቡዕ ፓርቲው ሙስሊም ወንድማማቾች (የፍትህና ነፃነት ፓርቲ) የተሻለ ነበረ፡፡ ይህን አስቀድሞ ግንዛቤ የነበረው የወታደራዊው ኃይል የነበሩቱ ሳይጠናከሩ፡ ሳይወያዩና በጠቃሚ ነጥቦች ዙሪያ መግባባት ላይ ሳይደርሱ ወደ ምርጫ ሂደት ውስጥ እንዲገቡ ግፍትና ጫና ሲያደርጉ ነበር፡፡ ሙስሊም ወንድማማቾች ከሌሎች ፓርቲዎች በወቅቱ የተሻለ ሊባልለት በሚያስችል አቋም ላይ እንደነበሩ እራሳቸውን በመገመታቸው ብቻ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት አሳዩ፡፡ በነሱና (ሙስሊም ወንድማማቾች) በሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ሊኖር ስለሚገባ የምርጫ አካሄድና የስልጣን ክፍፍል ምንም ውይይት ሳያካሂዱና ሳይጋብዙ ወደ ምርጫው ገቡ፡ አሸነፉ፡፡ ከምርጫውም በኋላ ለተቀሩቱ ተፎካካሪዎች ምንም ሳያስቀሩ ስልጣኑን ተቆጣጠሩት፡፡ ሙስሊም ወንድማማቾች ከሌሎች ፓርቲዎች አንፃር ሲታይ ግን አብላጫውን የሀገሪቱ ህዝብ ድጋፍ ነበረው ሲባል ሙሉ በሙሉ ነበር ማለት ግን እንዳይደለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሙስሊም ወንድማማቾች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 47% ሲይዝ ሙርሲ ደግሞ 52% ማሸነፍ በመቻላቸው ነው፡፡ የተቀረው ሰፊው የህዝብ ክፍል በአብዮቱ ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ መስዋዕት ቢከፍልም ውክልና በማጣቱ ብቻ አኩራፊ ሆኖ ተገኘ፡፡
ሙስሊም ወንድማማቾች ወደ መነበረ ስልጣኑ ከመጣ በኋላም ቢሆን ተመልሶ ስህተትን ከማረም ይልቅ በተያያዘው ጎዳና በመቀጠል ምሁራኑንና ተፎካካሪ ፓርቲዎቹን በመጋበዝ በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ከመነጋገርና ከመመካከር በዘለለ ከማሰተፍ ጨርሶ ብቻውን ወደ ማይወጣበት አዘቅጥ እየገባም ለመተግበር መዳከሩን ተያያዘው፡፡ ወዲያው የተቃውሞ ድምፆች ተመልሰው ወደ ጎዳና መውጣታቸው ቀጠለ፡ ለመቆጣጠር ይበጀኛል ወዳለው እርምጃም ተሸጋገረ፡፡ ከላይ ከመከላከያ ጀኔራሎቹ ጀምሮ በደረጃ ተቋሙ ለአገዛዙ ታማኝ ናቸው ተብለው በሚገመቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት በመተካት ብቻ ስራው የተጠናቀቀ መስሎት እንዳለ ተወው፡፡ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ባልሆነው ከፋፋይ ፖሊሲው የመተግበር ሂደት ቅሬታዎችና ቅዋሜዎች ተበራከቱ፡ የራሱ ደጋፊ የነበሩት ሳይቀር መንሸራተትና መንጠባጠብ ጀመሩ፡፡ የሀገሪቱ አብላጫ ህዝብና በፕረዝዴንት ሞሀመድ ሙርሲ መካከል መለያየትና መራራቅ እየሰፋ በመሄዱ ቀድሞም የለውጡ ዋነኛ አካል ላልነበረው ወታደራዊው ኃይልና ደህንነቱ ክንፍ እድሎችና አጋጣሚዎች እየሰፉና እየተመቻቹ መጡ፡፡ ስልጣን በተቆናጠጠው የለውጥ ኃይልና ከስልጣን በተገፋው ቡድን መካከል የተፈጠረው ልዩነትና መካረር የራሱ የሆነ ሚና አገኘ፡፡ የሀገሪቱ ሁነኛ የኢኮኖሚ አውታሮች በወታደራዊው ኃይል እጅ ስለነበረ አቅርቦትን በመቀነስ እጥረት እንዲባባስ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ተፅዕኖ ማድረግ ጀመሩ፡፡ የሀገሪቱንና የህዝብን ደህንነት ከመጠበቅ በመታቀብ ውንብድና (hooliganism) የወንጀል ስራዎች እንዲስፋፉ አደረጉ፡፡ ባንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ወታደራዊው ኃይል በመሀሙድ ሞርሲና በፖሊሲው ላይ የሚደረጉ ተቃዎሞዎችን በኃይል ለመጨፍለቅ ሲጥሩ መታየት ተጀመረ፡፡ ትላንት ከቀድሞ አምባገነን መሪ እጅ ተላቅቆ አዲስ ተስፋ ሰንቆ ብሩህ የነፃነት ቀን ሲናፍቀው ለነበረው የግብፅ ህዝብ ሰላም፡ ፍትህ ነጻነትና ልማት ከመጣጣም ይልቅ መና ከሰማይ የመጠበቅ ያህል ሆነባቸው፡፡ ብጥብጥ፡ ሁከት፡ የኢኮኖሚው አለመረጋጋት በላይ በላዩ ከችግረ አልፎ ዕለታዊ ህይወቱ ለሆነው ህዝብ ከሁሉም በላይ “ሰላምን እንሻለን”እንዲያስብለው ሆነ፡፡ መሻት ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ተመልሶ በተቃዉሞ ውስጥ በመሳተፍ የሙርስን ስርዓት ገና በቅጡ ሳይደራጅ ይንጠው፡ ይነቀንቀው ጀመር፡፡ በራሱ በፕረዝዳንት ሙርሲ ሰላምና ፀጥታ አስገኛለሁ ተሸሞ የነበረው ጀኔራል የመንግሰት ስልጣን ግልበጣ በማካሄድ ወደ ስልጣን ብቅ አለ፡፡
የመሀሙድ ሞርሲ ስህተትና ክህደት ሁለት ዓበይት ጉዳዮች መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡ ሀገሪቱ ሁለት ተነጻጻሪ ኃይሎች እንዳሏት ቀደም ብለን አንስተናል፡፡ ለሙርሲ አጋሩ ሰፊው ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝባዊ ኃይል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ አንዳንድ እርምጃዎችን በተለይም የቀድሞውን አምባገነን መንግስት ያንኮታኮተውን የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎችና ፍላጎት ባግባቡ ምላሽ በመስጠት መንከባከብ፡ ተፎካካሪዎችን በመሳብ ማጠናከር ሲገባ በተቃራኒው በመጓዝ ፈቀቅ ማለት አለመቻሉ ነው፡፡ እንደዚሁ የመከላከያ ኃይሉን በማዳከም ከላይ እስከ ታች ያለውን መዋቅር ባዲሱ የለውጥ አስተሳሰብ በታነፁ ኃይላት በፍጥነት መተካት ሲገባው አንዳንድ አመራሮችን ብቻ በማንሳት ሌላው ላይ እምነት በማሳደር መተው በመምረጡ ጭምር ነበር፡፡ በሂደት የራሱ የመሀሙድ ሞርሲ ደጋፊዎች በመዳከም በቆይታው ወደ ራሱ በመዞር ተቃዋሚውን ጎራ መቀላቀል መረጡ፡፡ መሀሙድ ሞርሲ እጅግ አደገኛ ጠላቶቹን ማዳከም ሲገባው ባሉበት በመተው ስላቆያቸው እሱን በመገልበጥ ስልጣኑን ለመቆጣጠር መቋመጥ ጀመሩ፡፡ ከመጠን ያለፈው ደግሞ ለህዝባዊው ድጋፍ መስጠት የነበረበት ትኩረት ሳያደርገው በመቅረቱ ለወታደራዊው ኃይል ከፍተኛ ድጋፍን አስገኘለት፡፡ ያ አምባገነኑን የሆስኒ ሙባረክን የአገዛዝ መንግስት በህዝባዊ ትግሉ የገረሰሰው ኃይል ተመልሶ አውራ መንገዶቹን በማጥለቀልቅና በማጨናነቅ መልሶ በዲሞክራሲያዊ ሂደት የመረጠውን የመሀሙድ ሞርሲ መንግስት ግባተ መሬት አፋጠነው፡፡
ለግብፆች አብዮት መጨናገፍ ትልቁን ድርሻ የያዘውና ሚና የተጫወተው ሙርሲና ፓርቲው ናቸው፡፡ ይህን ማለት ግን የፖለቲካው አክቲቪስቶች፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ስህተቶች አልነበሩባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ከስህተቱ የሚጋሩት ድርሻ አላቸው፡፡ ቀዳሚው ስህተት የቀድሞ አምባገነኑ የሆስኒ ሙባረክ መንግስት ከመገርሰስ ውጭ ካብዮቱ በኋላ ምን ሊመጣ እንደሚችል አስቀድሞ በመተንበይ በመፍትሄው ላይ አቅጣጫን ያመላከተ ወሳኝ ስራ የሰራ አልነበረም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አክቲቪስቶቹ የቀድሞ አምባገነኑ የሆስኒ ሙባረክ መንግስት በመገርሰሱ በመደሰታቸው ወደ ደስታና ጭፈራ በመሰማራታቸው ቀጥሎ እየተከሰተ ላለውና ሊከሰት ላለው ትኩረት መንፈጋቸው ሌላው ስህተት ነበረ፡፡ የልፋትና ድካማቸው ውጤት ምርትና ገለባውን ከመለየት ከውድማው ላይ ሳለ በዝናብ እንዲበሰብስ ፈቀዱ፡፡ብዙኃኑ አብዮቱ ከግብ እንደደረሰ ከማሰብ ባለፈ ፈፅሞ ሊቀለበስ እንደሚችል ግንዛቤው አልነበራቸውም፡፡ይህን ድላቸውን ለተለያዩ ሚዲያዎች ለመግለፅ ሲባዘኑ ማየትና መስማት ልምምዳቸው ሆነ፡፡ በሌላም ወገን ለሚደግፉትና ስልጣን መያዝ አለበት ብለው ለገመቱትና ለፈቀዱት ቡድንና እምነት ጎራ በመያዝ ለተሰለፉበት ጎራ ማቀንቀን ቀጠሉ፡፡በዘሁ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ነበር ሌላው ከፍተኛ ስህተት የተፈጸመው፡፡ ይኸውም የቀድሞ አምባገነኑ ሆስኒ ሙባረክ የለቀቀውን ስልጣን የወታደራዊው ኃይል ካውንስል (armed force councel) እንዲረከበው መተው አልነበረበትም፡፡ ማድረግ የነበረባቸው ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ከሲቪሉ ማህበረሰብና ገለልተኛ አካላት የተውጣጣ የሽግግር መንግስት እንዲከሰት መግፋትና የወታደራዊ ኃይል ሚና እንዲገደብ ህዝባዊውን ተቃውሞ ማጠናከርና መምራታቸውን መቀጠል ነበረባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸውና የማይገባ ኃላፊነት ለጀኔራሎቹ በመተው የሽግግሩ ሂደት ከመደናቀፉ ባሻገር ለነሱ አመቺ ሁኔታን ማመቻቸት ሆነና አረፈው፡፡ ሶስተኛው ስህተታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በወጉ ሳይሰደሩና ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ እምር ብለው ወደ ምርጫው ሂደት የመጣደፋቸው ነገር ነበር፡፡ ምርጫውንም በተመለከተ አግባብነት ያለው ህግና ደንብ ሳይበጅለት፡ ሀገራዊ መግባባት ላይ ሳይደረስ፡ የወደፊት የህዝቡ ተስፋ ሳይብራራ ሾላ በድፍኑ ሆነና ምርጫው ተደረገ ተባለ፡ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ አሸናፊ ለሆነው ሙስሊም ወንድማማቾች ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ብዙኃኑ ትኩረት የተነፈገው ከመስኩ ላይ ተጣለ፡ በአብዮቱም ለተገኙ ትሩፋቶች የበይ ተመልካች በመደረጉ ላይ አኩራፊ ቡድን ሆኖ ተገኛ፡፡ ወደ ስልጣኑ ማማ በተፈናጠጡትና የሙርሲ ደጋፊና ወታደራዊው ኃይል መካከል ፍጥጫ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ቀደም ተብሎ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህዝባዊነትንና አንድነትን ከመሸርሸር ባለፈ ወታደራዊውንና ተዳክሞ ለነበረው የደህንነት ኃይል ብርታት ጥንካሬ እንዲያስገኝለት አጋዥ ኩነቶች ፈጠሩለት፡ በታጋይ ወጣቶችና ለውጥ ናፋቂዎች ደም የተገኘው ድል እንዲጨነግፍ የበኩልን ሚና ተወጣ፡፡

በዚህ መንገድ በተቃራኒ የተጓዘውና ባስደናቂ ድል የተጠናቀቀውን ሳለምና ዲሞክራሲን ላስገኘው የጎረበት ሀገር ቱኒዚያን አብዮት መልካም ተሞክሮ አለማነፃፀር ደግሞ ዳተኝነት ሊያስብል ይችላል፡፡ የቱኒዞች አብዮት ለምን በድል ተጠናቀቀ?ምላሹ አከራካሪና ምርምርን የሚጤቅ አይደለም፡ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ቱኒዞች ሞሀመድ ሙርሲና አጋሮቹ የተጓዙበትና መስመርና ስህተት አለመድገማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፡ አምባገነን የነበረው የቤን አሊ መንግስት ከስልጣን ሳይወረውሩት ቀድመው የሀገሪቱ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ሊባልለት የሚችል የመግባቢያ ቻርተር በማዘጋጀት ከስምምነት ላይ ደርሰው ስለነበረ ነው፡፡ከ2003 ጀምረው በህቡዕም ሆነ በግልጽ በሚፈቅድላቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ሲሰሩ ስለነበረ አምበሰገነኑ መንግስት ሲወድቅ አስቀድመው ሰርተው በጃቸው ላይ የነበረውን የበሰለ ሰነድ አነሱ፡፡ ከግላዊ የስልጣን መሻት በመላቀቅ ማን ስልጣን መያዝ እንዳለበት ከመነታረክና ከመገፋፋት ርቀው ወደ ዲሞክራሲ የሚወስዳቸውን መንገድ መጥረጉን አስቀድመው ተያያዙት፡፡ በዚህ ወቅት ሊዘነጋ የማይገባና ……….. ከፈረዖኖቹ ጋር የሚያመሳስለቸው ጉዳይ ቢኖር የ……. የቀድሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደፈርዖኖቹ ሁሉ የተዳከሙና እርባና ቢሶች እንደነበሩ ሊታወስ ይገባል፡፡ እንዲያው ግን ሊጠቀስ ይገባል ከተባለ ካሉቱ በጥቂቱ ኤናሂ የተባለው ሃይማኖታዊ ዘውግ ያለው ሊጠቀስ ይችል እንደሆን እንጂ ምንም አልነበረም፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ፈረዖኖቹ በቀጥታ ዘለው ወደ ምርጫ ቢገቡም ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መገመት ተላላ አያስብልም፡ መናልባትም በከፍተኛ ውጤት ታጅቦ ይሆን ነበርና፡፡ ነገር ግን እነሱ እንደነዚያኞቹ አልተቻኮሉበትም፡፡ ሌሎች የተቀሩትን ፓርቲዎችባካተተና ባሳተፈ መንገድ ሀገራዊ አንድነት ያስጠበቀ መንግስት ለመመስረት አስቻላቸው፡፡ አስቀድሞ የምርጫ ሁደትና አስፈፃሚ ተቋማት ሳይጠናከሩና ኃይልንሳይጨብጡ ከምርጫው ድጥ ለመግባት ከመጣደፍ መታቀብ ጠቃሚ መፍትሄ ስለመሆኑ ላቀረቡ ሌሎች ፓርቲዎች ሀሳብ እውቅና ተሰጠ፡፡ ሌላው በጣም አስፈላጊ ስምምነት የነበረው ኤናህ ፓርቲ ቀድሞ ሀገሪቱ ስትተዳደርበት የነበረው የሸርዓ ህግ ማስቀጠል የሚፈልግ የነበረ ቢሆንም በተደረገው ውይይት ሃይማኖታዊ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ሆኖ ነገር ግን ሀገራዊው መተዳደሪያ ህግ ሁሉን ዓቀፍ (secular) እንዲሆን ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
እዚህ ላይ ሊታወስ የሚገባ ጉዳይ አምባገነኑ የቤን አሊ መንግስት ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ስልጣኑ በወታደራዊ ኃይሉ አዛዥ ጀኔራል ራሺድ አማር እጅ ነበረች፡፡ እሱም እንደሌሎቹ ጎረቤት ሀገሮች ስልጣኑ ከእጁ እንዳይወጣ ስለመፈለጉ መጠርጠሩ አያስቸግር ይሆናል፡፡ ቁምነገሩ የለውጥ ፈላጊው ኃይል ጥምረትና ስምረት ለህዝባዊው የትግል ኃይል ብርታትና ፈር ቀዳጅ ስለነበረ ለጄኔራሉና ወታደራዊው ክንፍ የተተወ ቀዳዳ አልነበረም፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ ምንም ተቃውሞና ሽኩቻ አልነበረም ማለትም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወታደራዊውና የደህንነቱ ኃይል ውስጣዊ ሁከት በመፍጠር መልሰው ስልጣን ለመቆጣጠር መንግስት የመገልበጥ ሴራ ተደርጎ እንደነበረና በህዝባዊው ኃይል ፈጣን እርምጃ ሀሳባቸው መና እንደቀረተመዝግቧል፡፡ ጄኔራሉም የህዝቡን ተቃዉሞ በመፍረት በቀድሞ መንግስት ወቅት ጠ/ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግል ለነበረው መሀመድ ጋኖቺ አሳልፎ ለመስጠት ተገደደ፡፡ ይህም ሰው በበኩሉ የስልጣን ጥም ሳይኖረው በመቅረቱ ሳይሆን አሳልፎ ለመስጠት የበቃው የፖለቲካው ሞተር የነበሩ አክቲቪስቶች በተገኘው ድል ተፍነክንከው ሳይገቱ ባዲስና በተቀኛጀ መልኩ ዳግማዊ ተቃውሞ በማስነሳት የሽግግሩ ወቅት ሁሉን ያካተተና ያሳተፈ እንዲሆን ጥረት ማድረጉን ቀጠሉበት፡፡
በዚሁ መሰረት የሽግግር ወቅቱን የሚመራ ኮሚሽን ሀገር ከሚመራ ፓርቲ፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ፡ ከተለያዩ ማህበረሰብ አካላት የተውጣጣ ተቋም ተመሰረተ፡፡ በሀገሪቱ አቃቤ ህግ ያዳህ ቤን አኾር አመራር ስር የተመሰረተው ኮሚሽን በሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሀገሪቱን የሽግግር መራኼ መንገድ (road map) ማቅረብ ቻለ፡፡ ከቀረቡቱ ጠቃሚ ሀሳቦች መካከል ዋነኛው ሀገሪቱ በቀጥታ ወደ አስተዳደራዊ ምርጫ ከመግባቷ ቀደም ብሎ ህገ መንግስት አርቃቂ ጉባኤ (constituent assembly) እንዲቋቋም ማስቻሉ ሊጠቀስለት ከሚገባ ሥራዎቹ አንዱ ነበረ፡፡ ይህ ደግሞ ህገ መንግሰቱ ህዝባዊ ወገንተኝነት ባለው ኮሚሽን እንዲረቀቅ በመደረጉ ረቂቁ ህገ መንግሰት ሀገራዊና ሁሉን ያማከለ እንዲሆን ስላስቻለው ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያገኝ አደረገው፡፡ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ምርጫው ተመጣጣኝ የህዝብ ውክልና እንዲኖረው ወሰነ፡፡ ይህ አዲስ ስርዓት ጠንካራው ፓርቲ ድምፅ ስላገኘ ብቻ በትረ መንግሰት መጨበጥ እንዳይችል በማገድ ስልጣን ክፍፍል እንዲኖር አደረገ፡ ፓርተዎች በመስማማትና በመደጋገፍ እንዲጓዙ ያስገዳጅ መንገድ ያመቻቸ ሆነ፡፡በተነፃፃሪው ይህ አካሄድ ሊመሰረት ባለው መንግስት ውስጥ ፓርቲዎችና የማህበረሰብ አካላት ሁሉ ሀገራዊ የተሳትፎ ድርሻ እንዲያገኙ በማስቻሉ አንድነትና ህዝባዊ ኃይል ተጠናክሮ የወታደራዊው ኃይል ሂደቱን ለማደናቀፍ ሊያገኝ የነበረውን ዕድል አጠበበው፡፡ በዚህ ተራማጅና በሰከነ መንገድ የተጓዘው የቲኒዞች አብዮት ወደ ዲሞክራሲ ሲያዘግም የጎረቤት ግብፆች ግን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ለመመለስ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
እነዚህን የሁለቱሀገራት ተሞክሮን ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት ልምዳቸው ጠቃሚና የሚያስተምረው ነገር ስላላው ነው፡፡ የሀገራችን አሁን አብዮት የደረሰው 2011 እነሱ ደርሰው ከነበረው ገና በመድረሱ ነው፡፡ ከስህተተኛው የፈርዖኖቹ መንገድ በመማር የቱኒሶችን ዱካ መከተሉ ይበጃል ብዬ በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ወንድሜ ደረጀ ገረፋ አዲሱን ጠ/ሚኒስትር የአክቲቪስቶች መንቀፍም ሆነ መተቸት መንግስታቸውን በማዳከም መልሶ ወታደራዊ ኃይሉን ወደ ስልጣን በማምጣት የበላይነቱን እንዲይዝ በር ይከፍታል በማለት ስጋቱን የገለፀበት ንባቤ ፅሁፌ መነሻ እንደነበር ላስታውሳችሁ፡፡ ነገር ግን የወያኔ ጦር ስልጣን እንዲይዝ መንገድ የሚከፍተው አካሄድ በቅድሚያ ጠ/ሚኒስትሩና ግብረ አበሮቹ የሚፈጥሩት ስህተትና ቀድመውም እየፈጠሩ ያሉትም መሆኑ ነው፡፡ በመቀጠል ለውጥ ፈላጊው ኃይልና ህዝብ፡ ቄሮ፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ ሚዲያውና ምሁራን ሊፈጥሩት የሚችሉና እየተስተዋለ ያለው ስህተት ተጠቃሽ ነው፡፡ የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስተዳደር የሁለቱ ሀገራት ተሞክሮና ትኩረት አቅጣጫ ሊሆን የሚገባው፡-
1. ህዝባዊ ኃይሉን በመደገፍና በማጠናከር ያገኙትን ስልጣን ወደ ፈፃሚ ኃይል በማሸጋገር የወታደራዊ ኃይሉን ተፅዕኖና ስንዘራ በመሰባበር መራመድ መቻል አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አሁን ያገኙትን ህዝባዊ ድጋፍ ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃዎችና ወሳኔዎች መስጠት መጀመር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳትና የፖለቲካ እስረኞችን በመሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት

2. ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገውን ሽግግር እኛው እንደ ሀገራዊ ፓርቲ ብቻችን ለማምጣት እንችላለን በሚል ቀድሞ የፓርቲያቸው መሪዎች ሁሉ በግብዝነት እንዳደረጉት የሚያደርጉ ከሆነ እራሳቸውን ከማሰናከል ባሻገር የሽግግሩን ሂደት እንደሚያደናቅፉት ትውስ ሊላቸው ይገባል፡፡ የሽግግር ዑደቱን ሊያሳልጥ የሚችል ነፃና ገለልተኛ የሆነ ከራሱ ከገዢ ፓርቲ፡ ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ ከምሁራን የሲቪል ማህበራትና ከማህበረሰብና የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሽግግር ኮሚሽን አባላት ማዋቀር ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ብሄራዊ ተዋፅዖ ያለው ኮሚሽን ቀደም ሲል እንዳየነው እንደ ቱኒዞቹ የሽግግር ኮሚሽን የህግ ማዕቀፎችን ማውጣት፡ የምርጫ ሂደቶችን ማሳለጥ፡ በተለያዩ የውንብድናና ወንጀል ስራዎች ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ አካላትን ወደ ፍትህ የማቅረብ፡ ዕርቅና ሰለም በሀገር እንዲሰፍን ይሰራል፡፡ በዚህ መልክ በመጓዝ ለለውጥ የሚደረግ ማናቸውም እርምጃ የአንድ ጠ/ሚኒስትር ወይም ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ይህን ማድረግ በሌላ መልኩ የወያኔ ጦር ኃይል ለሽግግሩ ስርዓት ሊፈጥር ስለሚችለው ተግዳሮት በጋራ ለመመከት ያስችላል ማለት ነው፡፡ በየወቅቱ የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች በሀገሪቱ ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ የተቸራቸው ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በተናጥል መሞከር ግን ከህዝብና ከሌሎች ፓርቲዎች ድጋፍ ማጣት፡ መገለልና ኩርፊያን ማትረፍ፡ ለወታደራዊው ጥቃት መጋለጥና ለለውጥ እንቅፋት መሆን ይከሰታል፡፡

3. ወታደራዊው ኃይል በየጊዜው እየተመዘገበ ካለው ለውጥ ጋር መራመድ እንዲቻለው ለማድረግ ማስገደድና(fast and sequenced action) መወሰድ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ እርምጃ ከላይ ያሉትን ወታደራዊ ባለስልጣናት ማንሳት ብቻ ሳይሆን ወታደራዊውን መዋቅር መበወዝ ያካትታል፡፡ በተለይም አሁን ያለው ወታደራዊ ዕዝ (military council) መዋቅራዊ ለውጥ እንዲደረግለት ማድረግ ጊዜ ሊሠጠው የሚገባ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ እርምጃ በደህንነቱ መዋቅር ላይም ሊሰራ ይገባል፡፡

ከመንግስታዊው ተቋም ውጭ ወደላው ጎራ ደግሞ በመሸጋገር

የተደገው የለውጥ ትግል ሂደቱ እንደተጠናቀቀና ነፃነት እንደተገኘ በመቁጠር ወደ “አስረሽ ምቺው” በመዞር ጭፈራና እየየስዳዳን መታየት እሰካሁን የተከፈለውን መስዋዕት ካለማወቅ ወይም ሳይገባን እንደተቀላቀልን በመቁጠር የታጋዮችን ደም እሳት የገባች ቅቤ ከማድረግ በመታቀብ በቀጣይ ሊሰሩ ስለሚገባቸው ነገሮች ባስተውሎት መመካከርና ሂደቱን በጥንቃቄ መከታተል ብልህነት ይሆናል፡፡ ከኛ የሚጠበቀውም ይህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ተቃዎሞና እምቢተኝነቱ መልኩንና ብልሃቱን በመቀያየር ሊቀጥል ይገባል፡፡ የሽግግሩንና የለውጡን ሂደት ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ያመቻቻሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ሳይሆን ቂልነት ነው፡፡ ከህዝባዊ እምቢተኝነትና ተፅእኖ ውጭ ፍላጎት አይኖራቸውም፡ ፍላጎት ቢኖርስ እንኳ ኃይል አይኖርም፡፡ ሁሌም የለውጥ ትልቁ ኃይል ህዝብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ ይህን የለውጥ ሽግግር ኮሚሽን ማቋቋምና መደገፍ ሀገር የሚያስተዳድር ፓርቲ፡ የተፎካካሪና ሌሎች ምሁራን፡ ሲቪክና የጥበብ ባለሙያዎች የስራ ድርሻና ኃላፊነት ነው፡፡ መንግስት ይህን እንዲያደርገ ጫና መስከተል ደግሞ የለውጥ ፈላጊው ሚኛ ነው፡፡ መንግስት በፖለቲካው ድስኩሩ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እሄዳለሁ እያለበተግባሩ ደግሞ ስንዝር ታህል ፈቀቅ ሳይልና የጉዞ መንገድን አለመጥረግ ወይም ማዘግየት፡ የለውጥ ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ምልክቶች በመሆናቸው በከፍተኛ ጫና ማስገደድ ግድ የሚል ይሆናል፡፡ ተቃዋሚ ሃይሎች ደግሞ እንደ እንኳዬ ድመትቱ ተረት ዝም ብለው የገዢው ፓርቲ እርጥባን የሚናፍቁ ከሆኑ ያደረ አፋሽ ለመሆን ሳይበቁ ሊቀሩ ስለሚችሉ ትግሉን በማቀጣጠል ሚኒናቸውን ሊወጡ ይገዳቸዋል፡፡ ለምሳሌ የሽግግሩ ማሳለጫ መንገድ ሊሆን ይችላል ብለው ያመኑበትን (road map) በጋራ በማዘጋጀት ራሳቸው ተወያይተው በማፅደቅ ለሀገርና ለመንግስት ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ግዳጃቸውና ለሽግግሩ በሚያደርጉት ተሳትፎ ልክ የራሳቸው መጫወቻ ሜዳ እያዘጋጁ ስለመሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በማድረጋቸው በገዢው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ነግር ግን ይህን ማድረግ ከተሳናቸውና እንደቀድሞው ሁሉ ተበታትነውና ተራርቀው በመጠላለፍ ጊዜ የሚያባክኑ ከሆነ ራሳቸው የሽግግሩ ሂደት ዋነኛ አደናቃፊና ተጠያቂ ከመሆን የማይድኑ መሆናቸውን ሊያውቁት በተገባ ነበር፡፡

በተለመደው አጠራር “የኛ ሰው” በሚሉት ጥቂት የፓርቲ ካድሬዎች፡ ወዶገቦችና አሽርጋጆችና አክቲቪስቶች ምክንያት ወደ ስልጣን መጥተናል ወይም ተጠግተናል በሚል የተሳሳተ ስሌት በሚጓዙ ብልጣብልጦች ተደልሎ ከትግሉ ጎራ መውጣት ወይም ጥግ መያዝ ስህተትና ትልቅ ኪሳራ እንደሚያመጣ ለስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ የትግላችን ዋናው ግብ ለአጠቃላዩ ህዝባችን የሚደላ ሀገራዊ ፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ነበር እንጂ ወንድም ወይም እህታችንን ለስልጣን ማብቃት እንዳልነበር ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡ አሀን ለስልጣን ያበቃናቸው በትግላችን ገፍተን እንዳመጣናቸው ሁሉ ሀገሪቱንም ወደ ሁለንተናዊ ዲሞክራቲክና ፍተኃዊነት በማሸጋገር ዘላቂ ነፃነት ለመጎናፀፍ መተቸትና ሲያስገድደን መንቀፍ ልንከለከል ወይም ፍቃድ መጠየቅ እንዳለብን በሚመስል ማስፈራሪያ አዘል መልዕክቶች ሊነገረን ባልተገባ ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉት ጫናዎችና ግፊቶች ከማለዳው ካለተበራከቱ ባለስልጣናቱ በመዘናጋት፡ በማዝገምና በስህተቶች በመጨማለቅ የህዝብና ሀብትና ጉልበት ለኪሳራ በመዳረግ የተለመደ አሰለቺ የህይወት ዑደት ውስጥ እንድናልፍ ያስገድዱናል፡፡ ዛሬ በትናንሹ እየፈጠሩ ያሉትን ስህተቶች አጉልተን ካላሳየናቸው ነገ ሊፈጠሩ ያሉትን ስህተቶች አቀጭጮ የማየት አባዜ ሊከትል እንደሚችል ልምዱም ግምቱም ስላለን ነው፡፡ በዛሬው ስህተቶቻቸው ላይ ሳሉ ልንመልሳቸው የምንችልበት ስብዕና በጋራ ሊኖረን ይችላል፡ የነገው ግን እኛ ሳንሆን ሌላ ስለሆነ እሱን መጠበቅ ደግሞ ከፍተኛ ኪሳራ ነው፡፡

ባጠቃላይ የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲን የገጠመው ዕድል ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድን ሊገጥም ይችል ይሆን ወይ? የሚለው ጥያቄ ከባድ ፍርሃት ባይሆንም እንኳ የሽግግሩ ሂደት ለመደናቀፍ ያለው አጋጣሚ ግን የማይናቅና ሰፊ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩና አባሪዎቻቸው አሁን ባገኙት ድጋፍና ዳንኪራ ተዘናግተው ሀገሪቱን ወደ ሽግግር የሚመራውን አውራ መንገድ በፍጥነት ከወዲሁ ካልተያያዙት ለስልጣን ያበቃቸው ህዝባዊው ሃይል የፍላጎቱና ጥያቄውን ወደ ተሰጡ ምላሾች በማዘንብል መመዘንና መገመት ስለሚጀምር እየተንጠባጠበ በመሄድ እርቃናቸውን ያስቀራቸዋል፡፡ ህዝብ ገሸሽ ካለ በኋላ እርምጃ ለመውሰድ ቢጥሩ እንኳ ለለውጥ ፍላጎት በሌላቸው ኃይሎች መበለጥ ሊከሰት ይችላል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁለት ምርጫዎች ይኖራሉ፡፡ እንደ ሞሀመድ ሙርሲ በቀረቻቸው ጥቂት የተበታተነ ኃይል ለመፋለም በመጣር መሸነፍ ወይም ለወያኔ ጦርና ደህንነት እጅ በመስጠት አሻንጉሊት መሆን ናቸው፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ያሉቱ በፍጥነት ለሽግግሩ ሂደት መንገድ የመክፈት ስራ ውስጥ መግባት፡ በውጭ ያሉት ደግሞ ወደ ሂደቱ የሚደረግ ሰራ እንዲቀላጠፍ ግፍት ማድረግ፡ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ወደ ስልጣን በመጡት ዘንድ ለመወደድ ተብሎ ከበሮ መደለቅና ያንቀላፉትን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ወደጎን መተው ውሎ ሲያድር የሚያስከፍለው ዋጋ መኖሩ ስላለው እኔ በበኩሌ ወደ ስልጣን ለተሳፈሩት እሳት፡ ላንቀላፉት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ቀዝቃዛ ውኃ በመቸለስ ከንቅልፋቸው መቀስቀሱን መርጫለሁ፡ የናንትን ግን እንጃ!

( Someone translated an article I wrote last week in Afaan Oromo. Thank you Ihave not proof read the translation for accuracy so in case some points are lost in translation, you will have to firgive )

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0