ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ይድረስ ለዶክተር ጥላዬ ጌቴ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር

ጉዳዩ፡- ፖለቲካ እንዳይጫንዎ ስለማሳሰብ

ክቡር ሆይ፣ በቅድሚያ እንደሀገራችን ባህል “ለጤናዎ እንደምን ሰነበቱ?” ማለት ይኖርብኛል፡፡ እርስዎ ባህልዎን እንደሚያከብሩ በሚገባ አውቃለሁና፡፡ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ጊዜ ለሀገራችን ባህል በሚሰጡት ትኩረትና በሚያደርጓቸው ቀስቃሽ ንግግሮችዎ እቀናብዎት ነበር፡፡ በቅድሚያ ይህን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አከብርዎታለሁ፤ በተማሩት ትምህርትም ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አቅም እንዳለዎት ይሰማኛል፡፡

አንዳንድ ውሳኔዎችዎም ብዙዎቻችን የማናደርጋቸው ስለሆኑ ወደዩኒቨርሲቲያችን ተሹመው ሲመጡ “ከእንግዲህስ ዩኒቨርሲቲያችን አለፈለት” እስከማለት ደርሼ ነበር፡፡ እውነትም ግንባታን በማስፋፋት ዙሪያ የሠሩት ሥራ ዘመን የማይሽረው ነው፡፡ በዋናው ግቢ፣ በቡሬ ካምፓስና በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያደረጓቸው ማስፋፊያዎች ሁልጊዜም የእርስዎን ድንቅ ውሳኔ ሲያስታውሱ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በሌላ ጎን ሳይዎ ደግሞ ፖለቲካ ያለቅጥ የተጫነዎ ይመስለኛል፡፡

ክቡር ሆይ፣ በማንኛውም የትምህርት ተቋም ፖለቲካ እንግዳ እንጂ ባለቤት እንዳይሆን መሥራት ያለብን ይመስለኛል፡፡ እርስዎን ጨምሮ አንዳንዶች ግን ባለቤቱን እንግዳ፣ እንግዳውን ባለቤት እንዲሆን ሲጥሩ ይታየኛል፡፡ በእውነቱ ይህ ደግ አይደለም፡፡ የትምህርት ዓላማ ከዳር የሚደርሰው ፖለቲካ ደጋፊ ሲሆን እንጂ መሪ ፊታውራሪ ሲሆን አይደለም፡፡ ትምህርትን መምራት ያለበት በዋናነት ባለሙያነት እንጂ የፖለቲካ ካድሬነት ሊሆን አይችልም፡፡

ክቡር ሆይ፣ እንደሚያስታውሱት በአንዳንድ የሥራ እንቅስቃሴዎ ስናመሰግንዎት በኩራት “ይህኮ የተላክሁበት ዓላማ ነው፡፡ እኔ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብቻ አይደለሁም፤ ካድሬም ነኝ፡፡ የመንግሥትን ዓላማ ነው የማስፈጽመው” ይሉን ነበር፡፡ እንዲህ ሲሉ ቃልዎ ቢጸነኝም በየዋሕነት ነበር የምቀበልዎ፡፡ በዩኒቨርሲቲያችን የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የሕዝብን ድምፅ አክብረው ፈጣን ውሳኔ አለመስጠትዎን ሳይ ግን አሁንም የተጫነዎ ፖለቲካ ችግር እየፈጠረብዎ እንደሆነ ተጠራጠርሁ፡፡

ክቡር ሆይ፣ ለመሆኑ የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚደንት “ሹመት” ጉዳይ ለምን የውኃ ሽታ ሆነ? ለምን ሰዉ ሁሉ ቡድን ለይቶ እንዲቆራቆስ መንገድ ይከፍታሉ? ከሕዝብ ድምጽ በላይስ የሚፈልጉት ማረጋገጫ ምንድን ነው? እንደሚያውቁት እርስዎ ወደፌደራል መሥሪያ ቤት ሲሄዱ “ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ” ብለው የሾሙት “የቀድሞው” ፕሬዝዳንታችን ሲለቅ የውድድር ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር፡፡ ሁኔታውን “ይበል!” ብለናል፡፡ ተወዳዳሪዎች በውጤት ተለይተው በአስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ከተደረገ ግን ይኼው ሁለት ወር ሆነው፡፡ እስከአሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ የለም፡፡ እኛም “ምነው በሰላም ነወይ?” እያልን እንጠያየቃለን፡፡

ክቡር ሆይ፣ በምርጫ ሕግ የሕዝብ ድምጽ ይከበራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመትም ይህን የብዙኀንን ድምጽ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነበር ብየ ስለማምን ፕሬዝዳንት የመሾም ሂደቱም ይህን ያክል ጊዜ ይፈጃል የሚል ሐሳብ በፍጹም አልነበረኝም፡፡ አንቱዬ፣ እንዴት ሰው ይህን ያህል ከሀገር መማር ያቅተዋል? የምር ግን ምን ነካዎት? ለምን እኛንስ ያልሆነ ሐሜት ውስጥ ያስገቡናል? ለአንዳንድ መሠሪዎችስ ለምን በር ይከፍታሉ? ፖለቲካውስ ቢሆን የእርስዎ ብቻ ነው እንዴ?

ክቡር ሆይ፣ እኛ በውጤቱ መሠረት የሹመት ደብዳቤ እየጠበቅን ባለንበት ሰዓት እርስዎና “ቦርዱ” ግን ሌላ የማጣራት ሂደት እንደጀመራችሁ ሰማን፡፡ ይገርማል! ያ ማጣራት ከተካሄደም ግን ይኼው ሁለት ሳምንት ሆነው፡፡ አሁንም መልስ የለም፡፡ ለመሆኑ ጉዳዩን ይህን ያክል ያዘገየው ያው የተጫነዎ ፖለቲካ ካልሆነ ሌላ ምን ምክንያት አለው? በእውነትስ ይህን ለመወሰን የተቸገሩበት ነገር ምንድን ነው?

ምነው፣ አንቱ? ሰዉ በሐሜት ሲጎዳ አያሳስብዎትም? ሀገራዊ ለውጥኮ በአንድ ጊዜ አይመጣም፡፡ ለውጡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤትም መጀመር አለበት፡፡ እንኳን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የቀበሌ ሊቃነ መናብርትም የሚመረጡት በዋናነት በአስተዳደር ብቃት እንጂ “በካድሬነት ብቻ” ባይሆን ደግ ነው፡፡ ሕዝብ የሚሻው ፍትሐዊ አገልግሎትን እንጂ የድርጅት ታርጋ የተለጠፈበት መሠሪ ሰብእናን አይደለምና፡፡

አንቱዬ፣ ስንት ምሁራን ያሉበትን ዩኒቨርሲቲ አሁንም በፖለቲካ ዐይን ብቻ ሊያዩት ይፈልጋሉ ማለት ነው? ከሆነ በጣም ተሳስተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብስ ምን ያክል ቢንቁት ነው እንዲህ አስቦበት፣ ግራ ቀኝ ተመልክቶ፣ አውጥቶ አውርዶ በሰጠው ድምጽ አለማመንዎ! እንዴት ቢያስቡት ነው እጁን ተጠምዝዞ እገሌን መርጦ ሳይሆን አይቀርም ብለው የተጠራጠሩ? ኧረ ደግ አይደለም፤ ያለንበትን ደረጃ ያስቡት እንጂ፡፡ ምርቅና ፍትፍት የምንለይ መሆናችንን እንዴት ይረሳሉ?

ክቡር ሆይ፣ አሁንም አደራ እልዎታለሁ፡፡ የሕዝብን ድምፅ አክብረው ለዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዝዳንት በፍጥነት ይሰይሙልን፡፡ በአካል ተገኝተው ወይም ስልክ ደውለው ክፉ ከሚነግሩዎ መሠሪዎች ይልቅ፣ የሕዝብን ድምፅ ያክብሩ፡፡ አሁንም እልዎታለሁ፤ የበለጠ ሊሰማዎትና ሊያደምጡት የሚገባው በምርጫ ወቅት የተሰጠው የሕዝብ ድምፅ እንጂ የፖለቲካ ካድሬነትንና “በሬ ወለደ” ዓይነት ወሬን መሆን እንደሌለበት ይሰማኛል፡፡ ካድሬነትምኮ የተለዩ አካላት ተመርጠው የተቀቡት አይደለም፡፡ በፖለቲካም ቢሆን ካድሬነት አገልግሎት ነው፤ ኃላፊነት ነው፡፡ ቦታውን ይወቅ አልሁ እንጂ ካድሬነት አያስፈልግም የሚል ጭፍን ሐሳብ የለኝም፡፡ ካድሬነት ከታመነበት ብዙ የሀገር ሥራ የሚሠራበት እንጂ ደካሞች ጥግ የሚያደርጉት መደበቂያ ሊሆን አይችልም፡፡ በፍጹም እንዲያ አይደለም፤ ይህ የእውነተኛ ካድሬዎችን ስም የሚያጎድፍ ወራዳ ሥራ ነው፡፡

ክቡር ሆይ፣ ይህን ሁሉ የምልዎት አሁንም ውሳኔዎን ፖለቲካ እንዳይጫነው ለማሳሰብ ነው፡፡ እንዲያውቁልኝ የምፈልገው ነገር ማንም ቢሾም ግድ የለኝም፡፡ የሕዝብ ድምጽ የሚከበርበት አሠራር እንዲዘረጋ ግን ጽኑ ፍላጎቴ ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ምሳሌያዊ አሠራር ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ በላይ ሊኖር አይችልም፡፡ እስኪ ያስቡት! በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የመራጮች ድምጽ ካልተከበረ በቀበሌ ደረጃ እንዲከበር እንዴት እንጠብቃለን? እባክዎ አሁንም ደጋግመው ያስቡበት! እንግዲህ ሐሳቤን ሁሉ ከቅንነት አይተው በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ አምናለሁ፡፡ “እንዴት እንዲህ ይደፍራል?” ብለው ፖለቲካዊ ትርጉም ከሰጡት ግን እንደጲላጦስ መስፍን “የጻፍሑትን ጽፌያለሁ” መልሴ ነው፡፡ ሰላም ይሁኑ!

ምንዋጋው ተመስገን
(ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ)
ሚያዚያ 25/2010 ዓ.ም

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0
Read previous post:
የህወሓት ዕቅድ፥ የእስር ማዘዣው እና የብአዴን ጆከር!

በእርግጥ ፖለቲካ ማለት ልክ “Bicycle” ነው፡፡ ሁልግዜም በማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል መሽከርከር አለበት፡፡ ለውጥና መሻሻል ከቆመ...

Close