“Our true nationality is mankind.”H.G.

"ሙዝዬም?" በእርግጥ ማዕከላዊ ተዘግቷል ወይስ ተዘዋዉሯል?

አቶ ኩመራ በወንጀል ተጠርጥሮ ከታሰረበት ጊንጪ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መጋቢት 09/2010 ዓ.ም በኃይል ታፍኖ ወደ ሦስተኛ ተወሰደ። ከዚያ በኋላ ለስድስት ቀናት ያለ መኝታ ልብስ በቀዝቃዛው የጭለማ ክፍል ወለል ላይ እንዲተኛ ተደረገ። ethiothinkthank

ከወራት በፊት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዲዘጋና ሙዝዬም እንደሚሆን መገለፁ ይታወሳል። ከየካቲት 29/2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 39 ቀናት በማዕከላዊ ታስሬ እንደነበር ይታወሳል። በእርግጥ በማዕከላዊ የታሰርኩት ለአንድ ወር ያህል ነው። የተቀሩትን ዘጠኝ ቀናት የታሰርኩት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “ሦስተኛ” በሚባለው እስር ቤት ነው። ወደ ሦስተኛ የተዘዋወርነው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ ሲሆን ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ደግሞ “ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘጋ” ተብሎ በተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወሳል። በእርግጥ ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘግቷል ወይስ ተዘዋዉሯል? በማዕከላዊ እና ሦስተኛ እስር ቤቶች በነበረኝ ቆይታ የታዘብኩትን እውነታ መሰረት በማድረግ ይህን ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ እሞክራለሁ።

በመጀመሪያ ደረጃ “ማዕከላዊ ተዘጋ” የሚለው ዜና ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም የተዘጋው “ማዕከላዊ” ሳይሆን በማዕከላዊ የሚገኘው የተጠርጣሪ እስረኞች ማቆያ ክፍል ነው። እንደሚታወቀው በማዕከላዊ፤ ጣውላ ቤት፥ ሸራተን (09) እና ሳይቤሪያ የሚባሉ የእስረኛ ማቆያ ክፍሎች አሉ። ጣውላ ቤት እና ሸራተን በማንኛውም መልኩ በሰው አካላዊ አቅም እንዳይፈርሱ ተደርገው በጠንካራ መሰረትና በድንጋይ የተገነቡ ናቸው። ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው “ሳይቤሪያ” የሚባለው እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ሲሆን ወደ ክፍሎቹ የፀኃይ ብርሃን እንዳይገባ ታስቦ የተሰራ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስር በሚገኘው “ሦስተኛ” እስር ቤት “ጭለማ ክፍል” የሚባል የተጠርጣሪ እስረኞች ማቆያ አለ። ጭለማ ክፍል በእንግሊዘኛ “Solitary confinement” የሚባሉ 18 ክፍሎች አሉት። በቆይታዬ ለመታዘብ እንደቻልኩት ተጠርጣሪ እስረኞች ጥፋተኝነታቸውን እስኪያምኑ ድረስ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋሉ። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የታሰሩ እስረኞች ከቤተሰብ፥ ጠበቃ ወይም የሃይማኖት አባት፥… በአጠቃላይ ከማንኛውም ሰው ጋር መገናኘት አይችሉም። በመጀመሪያ ወደ ሦስተኛ ስገባ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ አራት ተጠርጣሪ እስረኞች ነበሩ። ከእስር ከመለቀቄ አንድ ቀን በፊት ደግሞ 8 እስረኞች በጭለማ ክፍል እንደነበሩ ተመልክቼያለሁ።

በሦስተኛ በሚገኘው ጭለማ ክፍል በማዕከላዊ ሲፈፀም የነበረው የስቃይ ምርመራ፤ ጥፍር መንቀል፥ አሰቃቂ ድብደባ፥ ውሃ የተሞላ ላስቲክ በብልት ላይ ማንጠልጠል እና የመሳሰሉት አሰቃቂ ተግባራት እንደሚፈፀሙ ለማረጋገጥ ችያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ የጭለማ ክፍሎች ልክ በማዕከላዊ እንደሚገኘው “ሳይቤሪያ” እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ናቸው። ይህም በሰው ልጅ አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን በተግባር ታዝቤያለሁ። በዚህ ረገድ በአቶ ኩመራ ደፋ ላይ የተፈፀመው ግፍ መጥቀስ ይቻላል።

አቶ ኩመራ በወንጀል ተጠርጥሮ ከታሰረበት ጊንጪ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መጋቢት 09/2010 ዓ.ም በኃይል ታፍኖ ወደ ሦስተኛ ተወሰደ። ከዚያ በኋላ ለስድስት ቀናት ያለ መኝታ ልብስ በቀዝቃዛው የጭለማ ክፍል ወለል ላይ እንዲተኛ ተደረገ። በዚህ ምክንያት በጤናው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በጳውሎስ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገለት ቢሆንም አሁንም ድረስ ሽንቱን መቆጣጠር አይችልም። ወደ ሆስፒታል በመመላለስ የሕክምና ክትትል እያደረገ ቢሆንም ለዚሁ ተግባር የሚያስፈልገውን ወጪ በራሱ እንዲሸፍን ተገድዷል። ሌላው ቀርቶ እስር ቤቱ የራሱ አምቡላንስ እያለው ለአቶ ኩመራ የትራንስፖርት አገልግሎት አያገኝም። በመሆኑም ወደ ሆስፒታል የሚመላለሰው በኮንትራት ታክሲ ነው። በዚህ ምክንያት ከጤናው በተጨማሪ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን አጫውቶኛል። በአጠቃላይ፣

  1. የተዘጋው ማዕከላዊ ሳይሆን በማዕከላዊ የሚገኘው የእስረኛ ማቆያ ነው።
  2. በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደ ማዕከላዊ በእስረኞች ላይ የስቃይ ምርመራ እና ግፍ ይፈፀማል፣
  3. በሶስተኛ ያለው የእስረኞች ማቆያ ከማዕከላዊ በባሰ ሁኔታ ለስቃይ ምርመራ እንዲያመች ተደርጎ የተገነባ ነው (ከጭለማ ክፍሎች በተጨማሪ በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ “ድምፅ እንዳያሰማ” (Sound proof) ተደርጎ የተገነባ የእስረኞች ማሰቃያ ቦታ አለ)። ስለዚህ “ማዕከላዊ ተዘግቷል ወይስ ተዘዋዉሯል?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ተዘዋውሯል” ነው።
    – Image – Aerial view of “Maekelawi” compound, the main federal police investigation center, in Central Addis Ababa, on February 18, 2013.

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣
0Shares
0