ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም ሀገራት ትብብራቸውን እያሳዩ መሆኑንን አስታወቁ፤


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ከአገሪቷ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ውይይት ውይይት ሲያደርጉ ነው፤ ጉዳዩ በውጭ አገር ባለስልጣናትን የሃብት ክምችት ይመልከት አይመልከት በግልጽ ባይነገርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ዱባይ፣ ቻይናና ቱርክ የመሄድ መርሃ ግብር እንዳላቸው ታውቋል፤

አዲሱ መሪ ከባለሃብቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ “ከአገሪቱ ያሸሻችሁትን ብር አምጡ” በማለት ዶላሩ ቻይናና ዱባይ እንደሚገኝ ስም ጠተው ተናግረው ነበር፤ ይህንን ሲናገሩ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ ማለትቸውም አይዘነጋም፤ ከአገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ መዘረፉን የተለያዩ ጥናቶች ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፤

የመፍትሄ አፈላለግን አስመልክቶ “ችግሮቸንም ለመፍታት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ እየተጠቀመችባቸው ያሉት አሰራሮች እንደማያዋጡ እና አሰራሩ ሀገር መለወጥ የማያስችል ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፤ ይህንን ለማሻሻል የተወካዮች ምክር ቤት ከእያንዳንዱ አስፈጻሚ ጋር ኮንትራት እንደሚፈራረም አመልክተዋል።

የኮንትራት ስምምነቱ በይፋ በዌብ ሳይት ላይ እንደሚለጠፍና በንኡስ ኮሚቴ አፈጻጸሙ ሲገመገም ለሕዝብ በቀጥታ የሚተላለፍና ቀጥታ ህዝብ ጥያቄ የሚጠይቅበት እንደሚሆን ዶክተር አብይ ተናግረዋል። በዚህ መልኩ በሚሰራው ምዘና ብቁ ያለሆነና እቅዱን ተግብሮ የማይቀርብ ሃላፊ ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ አመልክተዋል።

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

በጋራም ሆነ በግል እሳቸውን ጨምሮ ማለት ነው ውጤት ላይ ማተኮር ግዴታቸው መሆኑንን ያመለከቱት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ውጤት ላይ አተኩሮ መስራት ግድ መሆኑንን ሲገልጹ ” ጊዜ የለም” በማለት ነው። 

አገሪቱ ብሁለት ጽንፍ እንደተወጠረች ያልሸሸጉት አብይ ብሄር በሄረሰብ የሚባል ነገር አያስፈልግም የሚሉና አገር የሚባል ነገር አይስፈልግም ፣ ስትፈልግ ትበጣጠስ የሚሉ ወገኖች በሚሉ ሁለት ጽንፍ መካከል ብንሆንም ተስፋ እንደሚታያቸው፣ ይህንን ተስፋ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ከሁሉም የካቢኔ አባላት የሚጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

 
 

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

ፋና እንደሚከተለው ዘግቦታል

 

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየታየ ያለውን አገራዊ መነቃቃት ለመጠቀምና ወደፊት ለማራመድ የህብረተሰቡን ጥያቄ በአዲስ አሰራር መመለስ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአገሪቷ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ወቅት ለውይይት መነሻ እንዲሆን ባቀረቡት ጽሁፍ የህዝበ አገልጋይ የሆነ አመራር ምን አይነት ሰብዕና ሊላበስ እንደሚገባ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራሩ ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አንዳለበት ነው የጠቆሙት።

አሁን ላይ በአገሪቷ ተስፋ ሰጪ የሆነ የህብረተሰብ መነቃቃት ቢኖርም በፍጥነት መልስ ሊያገኙ የሚገባቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልፀዋል። የመንግስት አመራር አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በውይይት ወቅት አንስተዋል።

ችግሮቸንም ለመፍታት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ እየተጠቀመችባቸው ያሉት አሰራሮች እንደማያዋጡ እና አሰራሩ ሀገር መለወጥ የማያስችል መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። ችግሮቹን ለመፍታት በተሻለ ዘዴና ቅልጥፍና ስራዎችን ማከናወን መፍትሄ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ስራን ከማቀድ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በምን ያህል ጊዜና ወጪ መስራት እንደሚገባ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም ሀገራት ትብብር እያደረጉ እንደሆነም ገልፀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎችም ከሚከታተሏቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የስራ ስምምነት መፈጸም እንደሚገባቸውና ስራቸውን በዚህ አግባብ ሊሰሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ሳምንታዊው የካቢኔ ስብሰባ ከአርብ ወደ ቅዳሜ የተዘዋወረ ሲሆን፥ ሚኒስትሮች አርብን በስብሰባ ማባካን እንደሌለባቸውና መደበኛ ስራቸውን መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪ በአገሪቷ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትነ ከመተግበርና ውጤታማ ከማድረግ አኳያ ችግር ያለ መሆኑን ገልፀው፤ የአሰራር ስርዓቱን ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *