ወይ ግዜ እንዴት ይሮጣል! ፕሮፌሰር ከሞቱ 19 አመት ሆናቸዉ፣ አረጀሁእንዴ? ብየ ራሴን ጠየኩኝ፣፣ የቀብራቸዉ ሂዴት ለኔ ትናንት እነደተፈፀመ ድርጊት ሁኖ ነበር የሚሰማኝ፣ ጊዜዉ ግንቦት 18 ቀን 1991 ዓ. ም. ነዉ፣፣ በዚያን ወቅት እኔ አዲስ አበባ በሚገኜዉ የቱሪዝም ማሰልኛ ተቋም ዉስጥ ተማሪ ነበርኩ፣ ከዚህ ቀን አንድ ቀን በፊት ፕሮፌሰር ሬሳቸዉ ከአሜሪካን አገር እንደመጣና የቀብር ስነስርአቱም የሚፈፀመዉ በስላሴ ካቴድራል እነደሆነ በኢትዮጵያ ቴሌቪዢንና ራዲዎ ተነገረ፣

በእለቱ ከተማዋ በወታደርና በፖሊስ ተወጥራለች፣፣ የፕሮፌሰር የመኖሪያ ቤት ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኜዉ ቡናና ሻይ ህንፃ ፊት ለፊት ካለ ትልቅ ቪላ ግቢ ዉስጥ ነበር፣፣ የእኔም ትምህርት ቤት ከእሳቸዉ ቤት ፊትለፊት ነዉ፣፣ ለክፍሉ ተማሪዎችም ቀብር እንሂድ ብየ አሳብ አቀረብኩላቸዉ፣፣ አድርባይ መምህራንና የትምህርት ቤቱ ስራስኪያጅ ስማቸዉን ካልተሳሳትኩ አቶ ዘርአይ ማንም ተማሪ ንቅንቅ እንዳይል ትእዛዝ አስተላልፈዋል፣፣ ሁሉም ተማሪ ፈራ፣፣ አንድ ስሜነህ የሚባል እና ሃሰን ሁሴን የሚባል የቦረና ሳይንት ልጅ ግን በድፍረት ተከትለዉኝ ወጥተን ወደ መኖሪያ ቤታቸዉ ግቢ ገባን፣፣    በግቢዉ ዉስጥ ብዙም ሰዉ የለም፣፣ ሬሳዉን ተሸክመን ከቤት አዉጥተን መኪና ላይ ጫነዉ፣፣ ቀስ እያልንም አጅበን ወደ ቸርቸር ጎዳና አቀናን ልክ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እንዳለፍን ከባድ ዝናብ ደበደበን በዚያን ወቅት የትምህርት ቤት መታወቂያየ ሁሉ ነበር ኪሴ ዉስጥ እንዳለ የበሰበሰዉ፣፣ ቸርቸር ጎዳና ወደሚገኜዉ  መ.አ.ህ.ድ. ፅ/ ቤት ገባን፣፣

መ.አ.ህ.ድ.የኪነት ቡድንም የተለያዩ መዝሙሮችን እያሰሙ አጀቡን፣ አዝማሪዎች በማሲንቆ ዜማዉን ያወርዱታል፣ መለከት እምቢልታዉ ተደበላለቀ፣፣ ከማስታዉሰዉ የአዝማሪዎች ግጥም

የታገተ ጥጃ የማያስመልስ ሰዉ፣

ደኅና ጀግና ሲሞት ይስቃል ሞኝ ሰዉ፣፣

አትቅበሩኝ አለ ካንገቱ በላይ ፣

ሲወጡ ሲገቡ አገሩን እንዳይ፣፣

እኛም አትነሳም ወይ ይኸ ባንዲራ ያንተ አይደለም ወይ፣ አስራት አልሞተም፣ እኛ ወጣቶች የአስራትን አላማ እናሳካለን ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉ መፈክሮችን እያሰማን ሽቅብ ወደ ፒያሳ እንተማለን፣፣ ሙሀሙድ አህመድ ሙዚቃ ቤት ስንደርስ በጣም ብዙ ሽህ ህዝብ ጠብቆን ስለነበርን ከታች የመጣነዉ ሰዎች ተዋጥን፣፣ ከዚያም በራስ መኮነን ድልድይ አልፈን ወደ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት አድርገን ወደ ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ልንገባ ስንል ወታደሮች ከለከሉን፣፣ በታች በኩል ነዉ መግባት የምትችሉት አሉን፣፣ በታች በኩል ስንገባ የቀብር ቦታዉ በሬዲዮና በቴሌቪዢን እነደተነገረዉ ስላሴ ሳይሆን ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ተነገረን፣፣ ብዙ ሰዉ ተበሳጨ፣፣ እንዴት አስራትን አይነት አርበኛ ስላሴ አይቀበርም?  አስራት አባታቸዉ በፋሽስት ጣሊያን በግፍ ከተገደሉት 30 ሽህ ኢትዮጵያዉያን አንዱ ነበሩ፣፣ ስላሴ ያርበኞች መቀበሪያ ነዉ ግን ላስራት በወቅቱ ተከለከሉ፣፣ መቸም አገሩ የጉድ አገር ነዉ የዛሬ አመት በሞቱ በ18 አመታቸዉ እንደገና ስላሴ ቀበሯቸዉ ሲሉኝ በጣም ነዉ የገረመኝ፣፣

የቀብሩ ሁኔታ፣ ካየኋቸዉ የቀብር ስነ ስርአቶች ሁሉ የሚበልጥ ህዝብ ነበር የተገኜዉ፣፣ በፍትሀቱ ወቅት አቡነ ጳዉሎስ ተገኝተዉ የሬሳዉን ሳጥን ባርከዉ ሲጨርሱ ጎንበስ ብለዉ ሳሙት፣ ታዋቂዉ የታሪክ ተመራማሪ አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ የህይወት ታሪካቸዉን አነበቡ፣ ከአማራጭ ሀይሎች አቶ አቶ ክፍሌ ጥግነህ ፣ቀኛዝማች ነቃ ጥበብ የፓርቲዉ ምክትል ሊቀ መንበር፣ እንዲሁም ሌሎችም ንግግር አደረጉ፣፣ ከአቶ ክፍሌ ንግግር ዉስጥ   አሰራት አጥብቀዉ የጎሳ ፖለቲካን እንደሚጠሉ ነገር ግን አሁን አማራዉን ነጥሎ ለማትፋት በተከፈተዉ ዘመቻ ምክንያት መአህድን እንዳቋቋሙ፣ መአህድ የሌሎች የአንድነት ፓርቲወች የመሰረቱት ፓርቲ ዉስጥ በመስራች አባልነት እንደተመዘገበ የመሳሰሉትን ተናገሩ፣፣

እኛ ግን ጭፈራችንን ቀጥለናል፣፣ በቤተክርስቲያኑ አጥር ላይ እጅግ አስፈሪ የበርሀ ወታደሮች ፊታቸዉን በሽርጥ ሸፍነዉ፣ ረጃጅም አንቴና ያለዉ የመገናኛ ሬዲዮ ይዘዉ ልክ እንደ ቀትር እባብ አይናቸዉ ቁልቁል ወደምንጨፍረዉ ልጆች ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣል፣፣  ከቤታቸዉ ጀምረን ስንመጣ ሰልፉን የሚያስተባብሩ ከነበሩት ሰዎች ዉስጥ አንዱ እድሜዉ በወቅቱ 55 እስከ 60  የሚሆን የሰሜን ሰዉ የሚመስል ሰዉ ያለ መታከት ጨፍሩ እያለ ያበረታታናል፣፣ ግን እዉነት ለመናገር ሰዉየዉ  በጣም ቀፎኝ ነበር፣፣ በመካከል ግን በዚያ ሁሉ ግርግር ዉስጥ ሰዉ ገለጥ ብሎ ሲሸሽ መሬት ላይ ስመለከት አንድ ወጣት ልክ እንደታረደ ዶሮ ወሬት ላይ ወድቆ ይንፈራፈራል፣፣ ጥቁር  ደምም እንደ ጅረት ከአንገቱ ስር ይምቦለቦላል፣፣ ያ ሽማግሌ አሁንም ጨፍሩ ይላል፣፣ በዚህ መሀል ነበር ሁሉ ቲያትር ግልጽ ኁኖ እንዲገባኝ ያደረገ ሁለተኛ ክስተት በአይኔ ያየሁት፣፣ ለካ በመካከላችን አብረዉን ያሉ ሽጉጥ የታጠቁ ሰዎች እንዳሉ የተረዳሁት፣፣ ቀጠን ረዘም ያለ ፊቱን በሽርጥ የሸፈነ ሰዉ ተንደርድሮ ወደ አንድ ወጣት ደረት በመጠጋት አፈሙዙን አስጠግቶ ምላጩን ሲስብ የሽጉጡ ድምፅ ሳይሰማ ልጁ ግን ተዝለፍልፎ ሲወድቅ አየሁ፣፣ እንግዲህ ይህንን በፊልም ሳይለንሰር የተገጠመለት ሽጉጥ ብለን የምናዉቀዉ መሆኑ ነዉ፣፣ በሚቀጥለዉ ቀን በግል ጋዜጦች 5 ወጣቶች እንደሞቱ በሰፊዉ ተዘገበ፣፣

በወቅቱ የነበሩ ወሬዎች፣ ይህንን የምፅፈዉ አንባቢ ወቅቱን እና የነበረዉን አስተሳሰብ እንዲረዳ ነዉ፣፣ ብዙዉን ነገር አሁን ሳስበዉ ያመኛል፣፣ በፕሮፌሰር ላይ የመሰከሩት ሰዎች አብዛሃኛዎች ኤርትራዉያን እንደነበሩና በኋላ ባድሜ ጦርነት ሲመጣ እነሱም እንደተባረሩ፣ የፕሮፌሰር ባለቤት ኤርትራዊ ናት የሷ ዘመዶች ናቸዉ ሰልለዉ ያስያዟቸዉ ይባል እንደነበር፣ ብዙ ምሁራንና አብዛሃኛዉ ፖለቲካ አዉቃለሁ የሚል  ፕሮፌሰርን ልክ እንደ ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ እንደሆኑ አድርጎ ያዩዋቸዉ ነበር፣ አንዳንዱ ደግሞ እሳቸዉ ህክምና እንጅ ፖለቲካን የት ያዉቁታል የሚልም ነበር፣ የሞቱት እስር ቤት ዉስጥ የሰዉነት ክፍልን የሚጎዳ እጅግ መርዛማ ንጥረ ነገር ከምግብ ጋር በትንሽ በትንሹ እየተሰጣቸዉ ስለነበር ነዉ ይባልም ነበር፣ አብረዋቸዉ የነበሩት የትግል አጋሮቻቸዉ ከድተዉ መረጃ አዉጥተዉ ነዉ ለእስር የተዳረጉት የሚልም ነበር፣ ፕሮፌሰር  ፀረ እስልምና ናቸዉ ወዘተረፈ የሚሉ ዉዢምብሮች ነበሩ፣፣

መአህድ በተቋቋመበት ወቅቱ በሀገሪቱ ብሎም በአማራዉ ምን ይፈጸም ነበር፣  

በወቅቱ ምድር አልበቃቸዉ ያለች የጎሳ ፖለቲከኞች መጠነ ሰፊ የጋራ ጥቃት በአማራዉ ላይ የከፈቱበት ወቅት ነበር፣፣ እነ ታምራት ላይኔ በሀረር፣ እነ ዳዊት ዩሀንስ በጂማ ከአማራ ክልል ዉጭ ያለ አማራ ወራሪ ነዉ ብለዉ የተናገሩበት ወቅት ሲሆን በኦጋዴን ጎዴ ደርግ አስፍሮት የነበረ ሰፋሪ  በአስር ሽዎች የሚቆጠር የወሎ ሙስሊም አማራ ዉጣ ተብሎ እናቶች ልጆቻቸዉን  በየበርሀዉ እየቀበሩ ግማሹ ወደ ወሎ፣ ግማሹ ወደ አዲስ ሰፈራ ቦታ ወደ መተማ ጎንደር፣ ሌላዉ እግሩ እንደመራዉ የሚንከራተትበት ወቅት ነበር፣ ከአሰብ እና ከኤርትራ በመቶ ሽዎች የሚቆጥር ህዝብ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በናዝሬት፣ በአዲስ አበባ በየ ድንኳኑ ተጠልሎ የነበረበት፣ ከአማራ ክልል ዉጭ ያለ አማራ የመንግስት ሰራተኛ ወደ አማራ ክልል ይመጣል ተብሎ በአማራ ክልል በየስብሰባዉ የሚነገርበት፣ እና ተፈራ ዋልዋ እና ገነት ዘዉዴ ከሀገሪቱ የተማረ ሀይል ዉስጥ 53 በመቶ አማራ ስለሆነ ሌላዉ እስከሚማር አማራ ቁሞ መጠበቅ አለበት እያሉ በይፋ የሚናገሩበት ወቅትም ነበር፣፣ በሌሎች ክልሎች የዩንቨርሲቲ መግቢያ እስከ 2.0 ዝቅ እንዲል ተደርጎ በአማራ ክልል ግን 3.0 እንዲሆን የተደረገበት፣በበደኖ፣ በአርባጉጉ እና በመሳሰሉት ቦታዎች እጂግ ዘግናኝ እልቂት በአማራዉ ላይ የተከፈተበት እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዢንም እጂግ ዘግናኝ ፎቶዎችንና ፊልሞችን የሚያሳይበት፣ በመላዉ አገሪቱ በአማራ ክልል  ጨምሮ ትግራይን ሳይጨምር በየቀኑ ቤተ ክርስቲያን የሚቃጠልበት፣ የሚዘረፍበት ወቅት ነበር፣፣ እዚህ ላይ አንድ ትዝ እሚለኝ አንድ ፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ጓደኛየ የእነሱን መፅሄት ስሙን ካልረሳሁት ማራናታ የሚል  በምእራብ ወለጋ ህዝቡ ታቦታችሁን ዉሰዱልን ብሎ ጠይቋል የሚል ዜና አስነበበኝ፣፣ ከላይ በአማራ ክልል ጨምሮ ያልኩት በአሁኑ ከሚሴ ዞን በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለዉ፣ ትናንሽ ከተሞች እንደ እርቄ አይነቶቹ ነዋሪዎቹ ተሳደዉ ከተሞቹ ባዶ የነበሩበት ወቅት እንደነበረ ስለማቅ ነዉ፣፣

መቼም ሁሉንም የማዉቀዉን ብዘረዝረዉ ደስ ባለኝ ነበር  ነገርግን አንባቢን እንዳያሰለች እዚህ ላይ ላቁመዉና  እኔ እንደምረዳዉ ፕሮፌሰር አስራት በዚያ የመከራና የዉጥንቅጥ አመት ወቅት የወለዳቸዉ ጀግና ነበሩ፣፣ ባንድ በኩል እጅግ የመረረ ጥላቻ ያነገቡ ቡድኖች በሌላ በኩል ሰማይ ምድር የተደፋበት ከርታታ ህዝብ፣ በሌላዉ አንግል ፍፁም የጎሳ ፖለቲካን የሚጠሉ ቡድኖች በተቃራኒዉ በጎሳ ልክፍት የሰከሩ ሰዉ በላዎች ጊዜ ሰጥቶአቸዉ ጉልበት አግኝተዉ በመጡበት ወቅት በዚህ መሀል የቆሙ አንፀባራቂ ኮኮብ ነበሩ፣፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የምእራቡ አለም በታቸርና በሬገን ፊት አዉራሪነት ምስራቁን አለም ከሰባ አመት ትግል በኋላ ድል ያደረገበት ታላቋ አገር ዩጎዝላቪያ የፈረሰችበት ቦስኒያኖችና ክሮአቶች ከአሸናፊዉ ሀይል ጋር ሁነዉ ሰርቦችን ለገፀ በረከትነት እንዳቀረቡት፣ በኛም አማራዉ ለምእራባዉያን የበቀል ዱላ ወንድሞቻችን አሳልፈዉ የሰጡብን ወቅት ላይ አስራት እምቢ ብሎ የተነሳ ጀግና ነገር ግን ሁላችንም ቁመን ያስበላነዉ ጀግና ነዉ፣፣

ይቆየን የፕሮፌሰርን ነብስ ይማር!

በዳዊት ሳሙኤል

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Email: dawisam74@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *