“ለሃገር ግንባታ እና ዴሞክራሲ እድገት ከሚሰራ ማንኛውም ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን። ከማንኛውም ቡድን ጋር መስራታችን ይቀጥላል። አቋማችንን የሚቀይር ነገር የለም’

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከመንግሥት ጋር ድርድር መጀመሩ ከግንቦት 7 ጋር ያለውን ግኑኘነት እንደማይቀይር አስታወቀ።

ከሀገር ውጭ መታገልን እንደ አማራጭ ይዞ የቆየው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ ገልፀዋል።

ግንባሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ድርድር መጀመሩን እና በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ቅድመ ውይይት ላይ መድረሳቸውን የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ሌንጮ ባቲ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት በጠላትነት ለዘመናት ቢመለከተንም ግንባሩ ከተመሰረተ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃገር ውስጥ ገብቶ ለዴሞክራሲ እድገት መስራት ፍላጎታችን ነበር” ሲሉ አቶ ሌንጮ ይናገራሉ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ከግንቦት 7 ጋር አብሮ ለመስራት በወረሃ ነሐሴ 2008 ዓ.ም ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

ኦዴግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይት ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ ከግንቦት 7 ጋር ያላቸው ስምምነት ይቋረጥ ይሆን ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሌንጮ ሲመልሱ “ለሃገር ግንባታ እና ዴሞክራሲ እድገት ከሚሰራ ማንኛውም ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን። ከማንኛውም ቡድን ጋር መስራታችን ይቀጥላል። አቋማችንን የሚቀይር ነገር የለም” ብለዋል።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦነግ) ጨምሮ ግንቦት ሰባት፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ሌሎች ፓርቲዎች በኢፌዴሪ መንግስት አሸባሪ ተብለው መፈረጃቸው የሚታወስ ነው።

የግንባሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሌንጮ ለታ እና አንዳንድ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የአመራር አባላት የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር አባላት እንደነበሩ ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ በውይይታቸው ወቅት ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን እንዴት ማስፋት እንደሚቻል፣ ሃገራዊ አንድነት እና ሰላም እንዴት ማስፈን እንደሚቻልና ወደፊት መለወጥ አለባቸው የሚሏቸው ጉዳዮችም ላይ እንደተመካከሩ አቶ ሌንጮ ይናገራሉ።

የተደረገው ውይይት ስኬታማ መሆኑንም ተከትሎ የሚቀጥለውን ስብሰባ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ፓርቲው ልኡካን ቡድኑን ወደ አዲስ አበባ በቅርቡ እንደሚልክ አቶ ሌንጮ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ውይይታቸውንም አስመልክቶ መሰረታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን አቶ ሌንጮ ይገልፃሉ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ለመሳተፍም ጥያቄ ለመንግሥት ቢያቀርብም ሳይሳካለት ቆይቷል።

BBC Amharic
 
 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *