በዘረኝነት አረንቋ ተዘፍቀን አንዱ በይ ሌላው ተመልካች ሆነን ለዓመታት ባጅተናል፡፡ በዘረኝነት ልክፍት ታውረን የኛ አይደለም ያልነውን ጎሣ ዕቅድና ስትራቴጂ ነድፈን፣ በፖለቲካ ፕሮግራማችንም ሣይቀር በግልጽ አስፍረን በገሃድም በድብቅም ስናጠፋው ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህች ቅጽበት የዶ/ር በያን አሶባን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግምባር (ODF) መልእክተኞች ወደ ሀገር ቤት የመላክ ጉዳይ በተመለከተ እየተናገሩት ያለውን በ’OMN’ የቴሌቪዥን ጣቢያ እየተከታተልኩ ነው፡፡ ንግግራቸውን በየዋህነት ለሚከታተል ሰው በደስታ መንፈስ ሰውነቱ ፈካ ሊል ይችላል፡፡ እንደኔ ዓይነቱ በአዲስ አበባ በወያኔ አፍንጫ ሥር ለሚኖርና ወያኔን ከሥር መሠረቱ ጠንቅቆ ለሚያውቅ ግን የሰውዬውን ከእውነታዎች ዐውድ መውጣት በመታዘብ በዶክተሩ አነጋገር ሊያዝንም ሆነ ሊተክዝ ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ የአንዳንድ ተረቶችን ቅርጽና የዘት መቀያየር ከወቅታዊነት አኳያ ተገቢ ነው፡፡ እናም “ወያኔን ማመን ቀብሮ ነው” ወይም “ወያኔን ያመነ ጉም የዘገነ” ብንል ትክክል ነን፡፡ እውነት ነው! በርግጥም ወያኔን ማመን ቀብሮ ነው – ለዚህ ዋቢ መጥቀስ ቢያስፈልግ ደግሞ ከኦነግ የሚቀድም የለም – ያኔ በ83 አካባቢ ወያኔን አምኖ ከ20 ሺህ በላይ የሠራዊቱን አባላት ለሕወሓት ጎረኖ አስክቧል፡፡ ከዚህ የማይሞት የማይደበዝዝ ሀገራዊ እውነታ አንጻር የወያኔን ባሕርይ እስካሁን ድረስ ማወቅ ያልቻለ ሰው ለዚያውም በዶክትሬት ደረጃ የተማረና ብዙ የሕይወት ገጠመኝ ያሣለፈ ምሁር ዜጋ ሲያጋጥም በርሱ ሣይሆን በወያኔዎች በራሳቸው አንደርባዊ ትብታብና ሰይጣናዊ የዋሃንን ወደራሳቸው አዙሪት ጎትቶ የማስመጥ “ድግምት” መገረማችን አይቀርም፡፡ ዶክተር በያንና ቡድናቸው ወደ ሀገር የመግባት ናፍቆት ናላቸውን አናፍሏቸው ሊሆን ይችላል፤ የመግባትም ሆነ ያለመግባት መብትም አላቸው፡፡ የማይችሉትና መሆንም እንደሚከብዳቸው የምገምተው ግን ወያኔን መሆን ነው – ያንንም ቢሆን ይችላሉ – ግን ቆምንለት ከሚሉት ዓላማና ግብ ይቃረኑና እነሱን አንጋጦ በተስፋ ከሚጠባበቃቸው ሕዝብ ጋር ይቆራረጣሉ፡፡ ኦዲግንም ይሁን ሌላ ቡድን በአሁኑ የተዘበራረቀና ምኑም ያልለዬ ወቅት ያን ያህል አውርዶ የወያኔ ፕሮፓጋንዲስት እስከመሆን ሊያደርስ የሚችል አመርቂ ሀገራዊ ለውጥ እንደሌለ እኛ በሚገባ እናውቃለን፡፡ ተቆጥረው የማይዘለቁ ነዳፊ ምላሶቹን በኦህዲድና በብአዴን የቤተ ሙከራ ሥሪቶቹ ውስጥ እንዲመሽጉ አድርጎ ወደወጥመዱ የሚገባለትን ቀድሞ ለመንደፍና አፓርታዳዊ ሥርዓቱን አድሶ ለመቀጠል ያቆበቆበውን ሕወሓትን በተቻለና ባለ አቅም ሁሉ ተረባርቦ ከውድቀት ለመታደግ ካልታሰበ በስተቀር በአሁኑ ሰዓት “ኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልና ነፍጣችሁን አስቀምጣችሁ ግቡ፤ በሕዝባችሁ ውስጥ ሆናችሁም በሰላማዊ መንገድ ታገሉ” ብሎ ጥሪ ማቅረብ የተስፋ መቁረጥ ካልሆነ የጤንነት አይመስለኝም፡፡ ዶክተር በያን እንደሚናገሩት እውት ቢሆን ደስታውን አልችለውም፤ ስለቴንም ለማስገባት የሚቀድመኝ ባልኖረ፤ ግን ውሸት ነው፡፡ አንዳንድ ጥቃቅንና አነስተኛ ለውጦች መታየታቸው የማይካድ ሆኖ ተፎካካሪም እንበላቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ወያኔ በደስታ ጮቤ እየረገጠች የመንግሥቱ ኃ/ማርያምን ዘፈን ደግማ ታቀነቅናለች – “ለእራት ሲያስቡን ለምሣ አደረግናቸው”ን፡፡ ምን ማለታቸው ነው ግን ዶክተር በያን አሶባ? ገና ለገና ከኦህዲድ አንድ ብላቴና ለጠ/ሚኒስትርነት ተመረጠ ተባለና ሁሉም ነገር በወያኔ ቁጥጥር ሥር ባለበትና ወንድም ከወንድሙ ጋር ይቅርና ስለፖለቲካ ስለጋራ ቤተሰባቸው እንኳን ፈታ ብሎ መናገር በማይችልበት የአፈና ቆፈን ውስጥ እንደዚያ መስበካቸው ምን ቢነካቸው ይሆን? ለምሣሌ በስልክ የምናወራው ሁሉ ስለሚጠለፍ ስናወራ እየተሳቀቅን ነው፡፡ አጠገባችን ወያኔ-ትግሬ ካለ ለምናደርገው ብቻም አይደለም ለምንናረው ምን ይይዝብን ይን በሚል እየተሸማቀቅን ነው፡፡ ይሄ ነው ዴሞክራሲ? ይሄ ነው የምህዳር መስፋት? መቀለድ ተፈልጎም ከሆነ ለምን በአግባቡ አይቀለድም?

እንደሚታወቀው በተለይ ያለፉት 27 የወያኔ አገዛዝ ዓመታት የብዙዎቻችንን ባሕርይ ለዋውጦታል፡፡ እኔን ጨምሮ ብዙዎች ተጠራጣሪና በሥርዓቱ ተስፋቢስ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ የምንሰማው፣ የምናየው፣ የሚደርስብን፣ የሚወራው… እንደኢትዮጵያዊነት ይቅርና እንደሰውም ለመኖር በእጅጉ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነብን እንደምንቸገር ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ከየትኛውም የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ወይም የዘር ሐረግ ጎራ የሚመደቡ ዜጎች ቢያንስ በሥጋዊ ኑሯቸው ደልቷቸውና ተንቀባርረው የሚኖሩ ይመስላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የነፍስያቸውና የኅሊናቸው ነገር ወደ ጎን ተቀምጦ በሀብት ላይ ሀብት በሥልጣን ላይ ሥልጣን እየደራረቡ ላይ ላዩን ደህና መስለው ሲኖሩ መታየታቸው ግልጽ ነው፤ የውስጣቸውን ግን እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

በዚህች ሀገራችን ልዩነቶች ገዝፈው እንደሚታዩ ይታወቃል፡፡ ልዩነቶቻችን በፈጠሩት ክፍተት ምክንያት አንዱ አሣሪ ሌላው ታሣሪ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ሟች፣ አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ፣ አንዱ ጥጋበኛ ሌላው ርሀብተኛ…. እየሆን ልዩነታችን የሰማይንና የምድርን ያህል ገንኖ የአንዲት ሀገር እኩል ዜጎች መሆናችን ተረስቷል፡፡ በአንዲት ሀገር ዜጎች መካከል የሚታየው የሕይወት ውጣ ውረድና የድሎት ልዩነት ከቃላት የመግለጽ አቅም በላይ ነው፡፡  ከዚህም የተነሣ ይህችን ሀገር ሊወር የሚመጣ አንድ የውጭ ኃይል ቢኖር እንደጥንት እንደጧቱ ማን ሆ! ብሎ ተነስቶ በመዝመት የተረፈችውንም ድንበር ቢሆን እንደሚከላከል አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡

በዘረኝነት አረንቋ ተዘፍቀን አንዱ በይ ሌላው ተመልካች ሆነን ለዓመታት ባጅተናል፡፡ በዘረኝነት ልክፍት ታውረን የኛ አይደለም ያልነውን ጎሣ ዕቅድና ስትራቴጂ ነድፈን፣ በፖለቲካ ፕሮግራማችንም ሣይቀር በግልጽ አስፍረን  በገሃድም በድብቅም ስናጠፋው ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በጎሠኝነት ረግረግ ተዘፍቀን ከራሳችን ጎሣ ውጭ በተለይ የመንግሥትን ኃላፊነትና የጥቅም ቦታዎች ለምንጠላቸው ወገኖች ስንነፍግና ከዚያም በባሰ በእሽክርናና በተላላኪነት ስንጠቀምባቸው ብዙ ባጅተናል፡፡ በዘረኝነት ተዘፍቀን መላውን የመከላከያና የደኅንነት እንዲሁም የፖሊስና የፀጥታ ተቋማት በአንድ ነገድ ቁጥጥር ሥር አውለን ሌሎችን ስንሸነቁጥባቸው፣ ስንገድልባቸው፣ ስና(ሳ)ስርባቸው፣ ስንከስባቸው፣ ስናስፈርድባቸው፣ ስናስገርፍባቸው፣ ሊነገር የሚሰቀጥጥ ግፍና በደል በህግ ስም በታሠሩ ዜጎች ላይ ስንፈጽምባቸውና በቀላጤና በስልክ ቀጭን ትዕዛዝ  ስናስፈጽምባቸው ባጅተናል – በዚህም ፀያፍ ተግባራችን ስንኮራበትና ስንኮፈስበት እንጂ ስናፍርበትና ስንጸጸትበት አልተስተዋልንም – ይህም አንዱና ዋናው የማይምነታችንና ደመነፍሳዊ የእንስሳነት ባሕርያችን መገለጫ ነው፡፡ በዘረኝነት በሽታ ተለክፈን እኛው በሠራናቸው ክልሎች አንዱን ወደታች ሌላውን ወደላይ፣ አንዱን ማክበር ሌላውን ማደኽየት፣ አንዱን ማስማር ሌላውን ማደንቆር፣ አንዱን ማበልጸግ ሌላውን ማራቆት …. ዋና ዓላማችን አድርገን ብዙ ስንለፋ ቆይተናል፡፡ በማይምነት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተዘፍቀን ከሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል በቀጥታ ጄኔራልና ፕሮፌሰር እየሆንን የብርሃንን ዓለም ጭላንጭል እንኳን ሳናይ በሌለን ትምህርትና ዕውቀት የአንዲት ታላቅ ሀገር ዕጣ ፋንታ ላይ ስንፈርድ፣ አንድን ታላቅ ታሪካዊ ሕዝብ በዓለም ታሪክ ስናዋርድና በቁሙ መቀመቅ ስንከት ለዓመታት ባጅተናል፡፡ በዚህም ሳቢያ ምትክ የሌላቸው የመጪዎቹ በርካታ ትውልዶች ሣይቀር መድኅን ሊሆኑ የሚችሉ ብርቅዬ ዜጎችን በአካልም በመንፈስም በሥነ ልቦናም ገድለናል፤ ለሀገር ልማት ቢውል በአሁኑ ሰዓት ከሲንጋፖርና ከማሌዥያ አጠገብ ሊያስቀምጠን የሚችል በበርካታ ቢሊዮኖች የሚገመት ብር እንዲሁም የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብትና ንብረትም አውድመናል፡፡ ይህን ስናስብ ድንቁርናችንና ያንንም ተከትሎ የገባንበት የጥላቻና የመበቃቀል አዙሪት ምን ያህል እንደጎዳንና የኋሊት እንደጎተተን እንረዳለን፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ “በርግጥም እንረዳለን ወይ?” የሚለው ነው፡፡ ለምን ቢባል ብዙዎቻችን ይህን እውነት ብንረዳ ኖሮ ቆም ብለን በማሰብ ከእንስሳዊ የመናከስ ባሕርይ በመውጣት በምክክርና በመግባባት ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ እንሸጋገር ነበር፡፡ …. ይህን ሁሉ ጠ/ሚንስትራችን ያውቃሉ ብቻ ሣይሆን በእጅጉ እንደሚቆጩበትም አውቃለሁ፡፡ እርሳቸውም ከዚህ ዝግንትል ታሪካችን የወጡ ናቸውና ለርሳቸው የሚነገር አዲስ ነገር የለም፡፡

ኑዛዜም በሉት ንስሐ ይሄውላችሁ …. በወያኔ ዘመን የኔ የምለው አንድም ባለሥልጣን ኖሮኝ አያውቅም – እርግጥ ነው “ኣ! መለስ አእምሮውን ለአወንታዊ ነገር ቢጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን ምንኛ በተጠቀመች!” ብዬ ቅዠታዊ ምኞት የተመኘሁበት ወቅት ነበር፡፡ አፈጣጠሩ ከታችኛው ጽልመታዊ ዓለም (Netherworld) ሆነና ራሱንም እኛንም ሀገራችንንም አበለሻሸና እስከወዲያኛው ዐረፈው፡፡ ለማንኛውም መለስም የራሱ ድውይ ዓላማ ጠ/ሚኒስትር እንጂ የኔ ወይም የሀገሬ ጠ/ሚ አልነበረምና እንደባዕድ … እንደዐረመኔ የባዕድ ባለሥልጣን እንደቆጠርኩትና ስሙ በተጠራ ቁጥር በንዴት ፀጉሬ እንደቆመ እርሱም ከኔ እኔም ከርሱ ተገላገልን፡፡ የኃ/ማርያምን ተውት፡፡ ለቤት ጥበቃም የማይበቃ ደምበኛ አሻጉሊት ነበር – ሕይወት እንጂ ነፍስ ያልነበረው አሻንጉሊት – በቅርጽ እንጂ በይዘት ሰውን የማይመስልና የማይወክል ዞምቤ ሆኖ በተላከበት ቦታ ሁሉ እንደጅብራ ተገትሮ ሲጃጃልና ሲያስቀንም ሲያሳቅቀንም ከረመ፡፡ ይህ ወጣት ሣተና ግን የኔ የሆነ ያህል ውስጤ ይነግረኝ ጀምሯል፡፡ ስለዚህም “ጠ/ሚኒስትራን” ስል ከአንጀቴና በፍቅርም ነው – እንዲህ ብሎ መጥራት በሕይወቴ ብርቄ ስለሆነ፡፡ ለዚህ በመብቃቴም ፈጣሪን አመሰግናለሁ፡፡ የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመረዳት አቅም እንደማያንሰኝ ግን በተጓዳኝ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ “Rome wasn’t built in a day.” … ደግሞም ቀድሞ ማመስገን ኋላ ለማማት ወይም ለመውቀስ አስቸጋሪ ሁኔታን እንደሚፈጥር አልዘነጋሁም፡፡ ቢሆንም ለአሁኑ እኚህን ወጣት ጠ/ሚ በይሁንታ ተቀብዬ ወፌ ቆመችን ብዘምር ለኔ ነውር አይሆንብኝም፡፡ ሃሳብን አለመቀየርም ዶግማ አይደለም፡፡ ሲያስፈልግ አስተካክላለሁ፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚኒስትራችን!

ከፍ ሲል ስለሀገሬ ግልጽና የዘመናት ቁልል ችግሮች በአጭሩ የገለጽሁት ለመግቢያ ያህል ነው፡፡ እርስዎ በአንደበትዎ እንደተናገሩት በያካባቢው የሚሰሙት የሀገራችን ሕዝብ ችግር ወደ ሥልጣን መሄድን ሳይሆን ከሥልጣን መሸሽን እንደሚያበረታታ እኔም አውቃለሁ፡፡ እኔ ብሆን እንኳንስ ኢትዮጵያን የመሰለ ለ3 ሺህ ዓመታት የተጠራቀመ ውስብስብ ችግር ያለባትን ሀገር መምራት ቀርቶ 100 አባዎራዎች የሚኖሩበትን አንድ ቀበሌ መምራት በራሱ ከባድ ነው – እኔ በተፈጥሮ ችግርም ይሁን በዲኤንኤ የጥንካሬ ጉድለት የቀበሌ አመራርም መሆን እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ አንድ የግል አባባል አለኝ ደግሞ – “አሥር ኢትዮጵያውያንን ከማስተዳደር 1000 ፍየል መጠበቅ(ማገድ) ይቀላል፡፡” በውነቱ ኢትዮጵያውያን ለአስተዳደር የምንመች አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቻችን ባሕርያችን ክርት ነው፤ ሲመቸንም ሆነ ሲደላን በሁለቱም ወገን እንጎረብጣለን፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም መሪዎቻችን በአብዛኛው ጨካኝ የሚሆኑብን ወይም ዐረመኔያዊውን የአገዛዝ መንገድ የሚመርጡ(ልን)፡፡ እስኪ ለሁለታችንም ልብ ይስጠንና ይህን “ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ” ዓይነት መጥፎ ጠባያችንን ለማረም ያብቃን፡፡ ይሄ ስደትና ሞት ቀዳሚው ምርጫችን የሆነ ያህል ዓለም እስኪታዘበን ድረስ በገዛ መሪዎቻችን እንዲህ እየተሰቃየን መላውን ዓለም በስደት የምናጥለቀልቅበት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ደግሞ በአፋጣኝ መቀልበስ አለበት፡፡

… ወደርስዎ ልመለስ — እንደታዘብኩዎ እርስዎ ብርቱ ስብዕና መላበስዎ ያስታውቃልና ሀገር መምራት ይችላሉ –  ግን ቢስ አይይብን፡፡ በመጀመሪያ ስገምት ፈጣሪ ይህችን ሀገር ሊታረቃት ያሰበ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ ወደ መንበሩ ከመጡ ወዲህ ቢያንስ ወጀቡ ቀንሷል፡፡ 40 ዓመት የታወረ ሰው “ነገ ትድናለህ” ቢሉት “ዛሬን እንዴት አድሬ?” እንዳለው ካልሆነብን በስተቀር አንዳንድ አበረታች ለውጦችም እየታዩ ነው፡፡ ፈጣሪ ከእርስዎ ጎን ከሆነ በተለይ ገና ብዙና ብዙ ለውጦችን ማየት እንችል ይሆናል፡፡ የእርስዎ ወደ ሥልጣን መምጣት ይበልጥ የሚጠቅመው ደግሞ ሕወሓትን ነው – የውስጥ ዐይናቸውን ገለጥ አድርገው የፈጠጠውን እውነት ከተመለከቱ፡፡ ለነሱ ሲል እግዚአብሔር እርስዎን አመጣ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሣሌ እኔ ሁለት ወር እንኳን ባልሞላው የሥልጣን ጊዜዎ ኢትዮጵያን ካለርስዎ ማሰብ እየከበደኝ ነው – ከምን ጊዜው አይሉኝም? በውነቱ ይህ ፀጋ ነው፡፡ ይህ መታደል ነው፡፡ ዜጎች በመንፈስ እየቀኑ የርስዎን ፈለግ እንዲከተሉ ሁላችን ጠንክረን እንጸልይ፡፡

የለውጥ መምጫ መንገዶች ብዙ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በግድ በዱላና በመትረየስ ሊሆን አይጠበቅም፡፡ ሙሤ ከፈርዖን ዕቅፍ ወጥቶ ነው እስራኤላውያንን ከግፍ አገዛዝ ነፃ ያወጣው፡፡ ነፃ አውጭ ከጨረቃ ወይም ከህዋ አይመጣም፡፡ እግዚአብሔር ወደፊት የሚመጣውን የደም መፋስስ አይቶ በአቋራጭ በርስዎ በኩል ሀገራችን ወደምንፈልገው የነፃነት አምባ እንድትወጣ ሊያደርግ የሚችል ኃይልና ሥልጣን አለው፡፡ (የሚገርመኝ ነገር ሙሤ ኮልታፋ ነበር አሉ፡፡ እርስዎም ለሁሉም ሰው ግልጽ የምትሆን የማትመስለኝ ትንሽዬ ኮልታፋነት ያለችብዎ መሆንዎን ስረዳ የሁለታችሁ መመሳሰል ጉልኅ ሆኖ ይታየኛል፡፡) ጀግናን መግደል እንጂ ማፍራት እምብዝም የማያውቀው ማኅበረሰባችን ውስጥ ስለርስዎ መልካም ነገር ስናገር በነገር የሚሸነቁጠኝ እንደማይጠፋ እገምታለሁ – እነኝህ ቅናትና ምቀኝነት የሚሏቸው ጉድፎች ፍቱን ጠበል አጣንላቸውና በነሱ ቆስቋስነት የአንዱ ስኬት ለሌላው ምርኩዝና አርአያ መሆኑ ተዘነጋና እንደ ሥጋት ምንጭ እየተቆጠረ ሲያበላላን ይኖራል፤ መጥፎ ባህል! ሰውን ከቀብር መልስ እንጂ በቁሙ ማመስገን ዕርም በሆነበት ሀገራዊ ድባብ ስለሰው ደግ መናገር አደገኛና በወያኔ ቋንቋ በጥቅመኝነት የሚያሰፈርጅ መሆኑን ብገነዘብም እኔ የሚሰማኝን እናገራለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሙሽራዋ እሚዜ ጫንቃ ላይ ሳትወጣ በአቋራጭ ጥሩ ጋብቻ ልትመሠርት የምትችልበት አጋጣሚ ካለ እሰዬው ነው፡፡ ታንክ መጠመድ፣ መድፍ መደርደር፣ ክላሽን መታደል፤ ራሽን መከፋፈል፣ የጦርነት ዐውድማ  መለቅለቅና ሠራዊት መሠለፍ  ሳያስፈልግ በጊዜ ሂደት ብቻ በጥበብና በዕውቀት ነፃነታችን ሊገኝ ከቻለ ይህም አማራጭ ተፈልጎ  የማይገኝ ነውና እልል በቅምጤ ነው – ለሀገራችንም አዲስ ግኝት ነው፡፡ ውጤቱ ደግሞ ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፡፡ የመሣሪያ ጦርነት ግን አንድን ወገን ብቻ ነው አሸናፊ የሚያደርገው፡፡ ነገር ግን በተለይ ሥልጣን ፈላጊዎችና ከሀገርና ሕዝብ ይልቅ ለራሳቸው ዝናና ክብር ቅድሚያ የሚሰጡ የወደፊት ተስፈኞች – የሰይጣን ፈረሶች ቢባልም ያስኬዳል – ሀገር ሳትተረማመስና በደም አላባ ሳትነከር ነፃነት የሚገኝ ላይመስላቸው ይችላል – እነሱ የሚመኙልን ነፃነት ደግሞ ሌላና ከአሁኑም ሊከፋ የሚችል ባርነት ነው፡፡ ስለሆነም ከነዚህ ዓይነት የዓዞ ዕንባ አንቢዎች ሁላችንም መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ በሞቀ ቦታ ላይ ተቀምጦ ድሆችን ማራኮት ቀላል ነው፡፡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቁጭ ብሎ በውስኪና በጮማ ግፊት የጦፈ ጦርነት መምራትም እንደዚሁ ከባድ አይደለም፡፡ ለጭቁኖች እናስብ፡፡ ለሀገር እንጨነቅ፡፡ ከራስ ወዳድነት ወጥመድ በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ ለዘመናት ለተጨቆነው ሕዝባችን እናስብ፡፡

ውድ ጠ/ሚንስትር!

የተቀመጡበት ወንበር እሳት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ግን የተላኩበትና የፈጣሪ ረድኤት የታከለበት መሆኑን ስለማምን በድል ይወጡታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ስለርስዎ የአመራር ጥበብና ለዜጎች የመጨነቅ ስስ ባሕርይዎ በግል የሰማኋቸው አሉ፡፡ አሁን መናገር አልፈልግም፡፡ ከአንድዬ የተላኩ ስለመሆንዎ በሙሉ እምነት ለመናገር ጥቂት ጊዜ ቢቀረኝም እንደ አሁኑ ግን ትልቅ የሀገራችን ተስፋ መሆንዎን በደስታ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ሀገርዎ የእርስዎን የልጅ ዐዋቂነት አጥብቃ ትሻለችና በጀመሩት መንገድ ሳይሰለቹ እንዲቀጥሉ በዜግነቴ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡ ዳገት ቁልቁለቱ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እርስዎ ከጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ውጪ ያለን አማራጭ በጣም ደም አፈሳሽና አውዳሚ በመሆኑ ያለ መታከት በጸሎትም በጥበብም ተግተው ይሥሩ፡፡ ሕዝብና እግዚአብሔር ከርስዎ ጋር መሆናቸውን ቅንጣት አይጠራጠሩ፡፡ በብዙ ቦታዎች እገባለሁ/እወጣለሁ፤ ስለርስዎ የምሰማው ጥሩ ነው፡፡ ግን የሕዝብ ተስፋ እንዳይሟጠጥ ከጊዜ ጋር አብረው ይሩጡ፡፡ ሕዝብ ተስፋ ከቆረጠ ወደማንመለስበት አዘቅት እንወርዳለን፡፡ ጊዜ የወጥን ጥፍጥና ከማሳመር ጀምሮ ለብዙ ነገሮች የመጀመሪያው አቢይ ግብኣት ነው፡፡ የተራበ ሆድ በሰዓቱ ምግብ ካላገኘ የመመገብ ፍላጎት ይዘጋና ምግብ ቢገኝ እንኳን አይበላም፡፡

ሀገርንና ሕዝብን ከዕልቂትና ከችጋር ለማዳን በሚያደርጉት ሩጫ የኢትዮጵያን ጠላቶች ደንቃራነት በመረዳት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግዎን ለአፍታም እንዳይዘነጉ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ቀድመው ይጠብቋቸው፡፡

“በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንደሚባለው የእርስዎን አመራር ለማጠልሸትና እርስዎ ላይ አደጋ ለመጣል ቀን ከሌት የሚደክም ኃይል መኖሩን አይርሱ፡፡ ለአብነት ሰው ሠራሽ የዕቃና የምግብ ሸቀጦች አቅርቦት ችግርና የዋጋ ንረት በመፍጠር በዜጎች መካከል እሮሮና ዋይታ ተባብሶ እንዲቀጥል በውጤቱም የእርስዎን አመራር ሕዝቡ እንዲያማርር ለማድረግ አንዳንድ መሠሪዎች እየሞከሩ መሆናቸውን እንረዳለን፤ የሀገር ካዝናና የጓዳ ምሥጢርን ጨምሮ ገንዘቡም ሆነ እያንዳንዱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁልፍ በነሱው እጅ በመሆኑ እግዜር ይብቀን እንጂ እነዚህ ሰዎች መጉዳት የሚፈልጉትን ለመጉዳት ኃይላቸው ገና አልተነካም፡፡ ለነገሩ ያ እርስዎን የሚጻረር ኃይልም ቢሆን በርስዎ መኖር እንጂ አለመኖር በፍጹም ሊጠቀም እንደማይችል አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የታወቀ ነው፡፡ ሕወሓት እርስዎን በማግኘቱ ታላቁ የዓለም ሎተሪ ወጥቶለታል ማለት ይቻላል፡፡ በፈረንጆቹ ፈሊጣዊ አነጋገር a blessing in disguise የሚሉት ዓይነት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ እንጂ አንድ ሁከት ተፈጥሮ ሁሉም በየጓዳው የሚስለውን ጩቤ በተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ በማሣረፍ በግርግሩ ሀገሪቱን እንደሦርያና ኢራቅ ለማድረግ የሚፈልግ ኃይል በየሥርቻው አድፍጦ እንደሚጠባበቅ መገመት አያስቸግርም፤ ነገር ግን እንኳንስ ከፎከረ ከወረወረ የሚያድነው አምላክ እርስዎን ተመስሎ ለዚህች ሀገር መፍትሔ የላከ ይመስላልና ታሪክ ለመሥራትና ልጆቼና ልጆችዎ አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚኖሩባትን የጋራ ሀገር ለመፍጠር በጀመሩት መንገድ የድርሻዎን ይወጡ – እግዚአብሔርም ከርስዎ ጋር ይሁን፡፡ ለማንኛውም አቢይን ማጥፋት በጣም ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ጦሱን ለማጥፋት ግን የሚቻል አይሆንም፡፡ የሩዋንዳ መሪ በአየር ላይ ተቀልበው በሚሣይል በተገደሉ ማግሥት ምን እንደተፈጸመ ታዝበናል – እናም “የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት ሊጫወት” አይገባውም፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ አሟረትህ አትበሉኝ እንጂ አቢይን የሚያጠፋ ኃይል ቢቆይ ሦስት ቀናትን ነው – እንደግምታዊ የማይም ትንቢት ቃል፡፡ የተላከው ከላይ ነውና ግን ምንም እንደማይነካው በአንድ አምላክ ያለኝን እምነትና ተስፋ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ወያኔዎች በተለይ አቢይን ጠብቁት! ከእርሱ ሌላ ያላችሁ መውጫ ቀዳዳ በጣም ጨለማና ከመርፌ ዐይንም የጠበበ ነውና፡፡

ውድ ጠ/ሚኒስትር ሆይ!

የሕዝብን ይሁንታና ፍቅር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማግኘት የሚከተሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ቢሰጡ ደግሞ በግሌ ደስ ይለኛል፡፡ የነፃነት ርሀብና የግፍ ደለል በተጫነበት ሕዝብ ዘንድ አንድ ሰዓት አንድ ዓመት ነው፡፡ ስለሆነም የሕዝብን የልብ ትርታ ከማዳመጥ አይቦዝኑ፡፡ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ መሆኑ አሉታዊ ጫና እየፈጠረብን እንጂ – እርግጥ ነው – ያሉብዎትን ተግዳሮቶች ብዙዎቻችን በደምብ እናውቃለን፡፡ ቢሆንም ….

  1. በፖለቲካና በዘር ጥላቻ ምክንያት የታሠሩ ዜጎች ሁሉ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ያድርጉ – ለምሣሌ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በግሉ ወደ ወህኒ የሚያስወርደው አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ እርሱን ለእሥር የዳረገው ብቸኛ ምክንያት እርስዎም የሚጮሁለት የኢትዮጵያ ነፃነትና የሕዝብ ብሶት ነው፡፡ እርሱ የሚሰቃየው ለርስዎም ለኔም ለርሱም ልጆች የወደፊት ሕይወት መሻሻል ነው፡፡ እርሱ የስደትም ቢሆን የሞቀ ትዳርና ኑሮ ነበረው – ያን ትቶ ነው ለሀገር መንገላታትን የመረጠው፡፡ ስለዚህ አማራጮች ሁሉ ተዘግተውበትና ጠበውበት በምንም ዓይነት መንገድ ቢታገል የመጨረሻ ዓላማና ግቡ የሕዝብና የሀገር ነፃነት እስከሆነ ድረስ እርሱን ከባዕድ ሀገር በገንዘብ ኃይል ጠልፎ ማሠሩ የአጋንንት ተግባር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከእሥር የመልቀቁ ጉዳይ ግን በፍጹም የሚያጠያይቅ ሊሆን አይገባም፡፡ አሣሪዎቹም ተፈጥሯዊ ያስመሰሉት ድንቁርናቸው ዐይናቸውን ጋርዶባቸው እንጂ የአንዳርጋቸው የትግል ፍሬ ለነሱም በጠቀመ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዘረኝነትም ይባል በሀብትና በሥልጣን ሱስ ተጠምደው ሰውን እያሰቃዩ በሚገኝ ደስታ እየተዝናኑ ለዘላለም መኖር የማይቻል ከመሆኑም ባሻገር በስቃይ መደሰት የጤና ስላልሆነ ትግሉ ከዚህ መሰሉ ኅሊናን ከሚያሳድፍ ደዌ ይፈውሳቸው ነበርና፡፡ የነፃነት ጥቅም ለባርያም ለጌታም ነው፡፡ ገራፊና ተገራፊ እኩል እንደሚሰቃዩ አንዳንድ የሥነ ልቦና ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
  2. ኢንተርኔት በሀገራችን ዝግ ነው፡፡ የውጭ ሚዲያዎች በአብዛኛው ይታፈናሉ፡፡ ሰዎችን ከመረጃና ከዜና በማራቅ ሀገር አትገነባም፡፡ ይህን የሚያደርጉ አምባገኖች ብቻ ናቸው፡፡ ሕዝብ ሲታፈን አማራጭ መፈለጉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እርስዎ ይህን የተዘጋጋ የመረጃ ምንጭ ሁሉ እንዲከፈት ያድርጉ፡፡ ዛሬ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፡፡ ከዚህ የዓለም ማዕድ የለየን ወያኔ ነው፡፡ እርስዎ በጀመሩት መንገድ ይግፉበትና ይህን አጥር ያፍርሱልን፡፡ በተጨማሪም ማንም ዜጋ በደኅንነት የክትትል (surveillance) ማዕቀፍ ውስጥ መግባት ያለበት ለሀገር ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ ወይም መግባቱ ሲጠረጠር እንጂ በጎሣውና በነገዱ ምክንያት ወይም ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠየቁ ሳቢያ ሊሆን አይገባምና የደኅንነቱን መሥሪያ ቤት በጤናማ ዜጎች እጅ ያስገቡ፡፡ አሁን ያለው በዕብድ ወያኔዎች እጅ በመሆኑ በጥላቻና በበቀል የሰከሩ ወያኔ-ትግሬዎች ሕዝብን እያሰቃዩበት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የስልክን መጠለፍ፣ የግል መብትን (privacy) መደፈር፣ ወዘተ. በሚመድቧቸው ሰዎች በማጥናት አስፈላጊውን እርምጃ ይውሰዱ፡፡ ተሳቅቆ መኖር በኛ ይብቃ!!
  3. ከአሁን በኋላ በፖለቲካ ምክንያት ማንም ዜጋ የማይታሠርበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ያድርጉ፡፡ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ የሚያሳስር፣ ደብዛ የሚያስጠፋ፣ ከሥራና ከመኖሪያ ቤት የሚያፈናቅል፣ ከቀየ የሚነቅል፣ የሚያደኸይ… እንዳይሆን ያድርጉ፡፡ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ሀገርን ያሳድጋል፡፡ በሃሳብ መፋጨት ያፋፋል እንጂ አያጫጫም፡፡ መናገር ሰውኛ ነው፤ አለመናገር እንስሳዊ ነው፡፡
  4. የሥራና ሠራተኛ ግንኙነት በጎሣዊ ማንነት ላይ ሣይሆን በችሎታና በብቃት፣ በትምህርትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያድርጉ፡፡ ይሄ በአንዳንድ የማስመሰያ አጋጣሚዎች ብቻ የሚተገበር የብሔር/ ብሔረሰብ ኮታ ወይም ተዋፅዖ ቀርቶ በችሎታ ይሁን፡፡ ለምሣሌ 11 የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሲመለመሉ አሥራ አንዱም ጉራጌ ወይም ሽናሻ ሊሆኑ ይችላሉ፤ የመፈተኛው ሜዳ የእግር ኳስ ሜዳ እንጂ በወረቀት ላይ የሠፈረው ጎሣዊ ማንነት ሊሆን አይገባም፡፡ እንደዚያ ከተደረገ ሽንፈትን መጋበዝ ይሆናል – በብዙ ሀገራዊ ክስተቶች እየሆነ ያለው ይሄው ስለሆነ ነው እንዲህ የምለው፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድ ሰው ባህር ውስጥ እየሰመጠ ነው እንበል፡፡ ያን ሰው ለማውጣት ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ እንበል፡፡ በኮታ ከወሰድን ከኮንሶና ዳዋሮ በኮታ ብቻ የመጡና ዋና የማይችሉ ሁለቱ ሰዎች ሲንደፋደፉ ያ ሰው ሰምጦ ይሞታል፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር ሊወገድ ይገባል፡፡ በበኩሌ በኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ትግሬዎች መብዛታቸው ለኔ እንደችግር የምቆጥረው አይደለም፤ ችግሩ ከፍ ሲል ለመግለጽ ከሞከርኩት በዘር ከመጠቃቀም፣ ያለትምህርትና ችሎታ ማይማን ሥራን እንዲያበላሹ ከመመደብ፣ ኢ-ፍትሃዊነትንና አድልዖን ከማስፋፋት፣ የሌሎች ብቁ ዜጎችን በሀገራቸው ሠርተው የመጠቀም ዕድል ከመንፈግ፣ ወዘተ፣ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ የሀፍረት-የለሽ ደናቁርት አሠራር መሆኑ ነው፡፡ ከመነሻው የዜጎች ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጂ ጎሣዊ ማንነት በመታወቂያቸው ላይ ሊሰፍርም ለሥራ መያዝና አለመያዝ ጥቅም ላይ ሊውልም አይገባም፡፡ እንደሰው ማሰብ መጀመር አለበት፡፡ ሥራ ለማግኘት ሰውነትና ዜግነት መሟላት ከሚገባቸው ሌላ ሌላ የሙያና የዕድሜ መሥፈርት ጋር ከበቂ በላይ ናቸው፡፡
  5. በመጣንበት የተሳሳተ መንገድ አላግባብ የበለፀጉ ወገኖች ትምህርትና ዕውቀት ተሰጥቷቸው እንደሰው እንዲያስቡና እንደሰው እንዲኖሩ የሚደረግበት ሁኔታ ይመቻች፡፡ ዋናው ችግራችን የድንቁርና መስፋፋት ነው፤ የሆዳምነት መስፋፋት ነው፤ ያለመተሳሰብ መስፋፋት ነው፡፡ ብሔራዊ የአንድ ሀገር ዜግነት ስሜት መጥፋት ነው፤ ይህም ሁሉ የወያኔ አገዛዝ ውጤት ነው፡፡….
  6. በየእሥር ቤቱ ሰዎችን የሚገርፉና የሚያሰቃዩ ዕኩያን ዜጎች ጡረታ እንዲወጡ ያድርጉ፡፡ በዘር ጥላቻ የተለከፉ ድውያን ዜጎች በየማረሚያ ቤት ተብዬው የወያኔ ወህኒ ቤቶች ሞልተዋልና ነገ ዛሬ ሳይሉ ማሰብ በሚችሉ ከጥላቻም በፀዱ የተማሩ ዜጎች ይተኳቸው፤ በበቀልና በጥላቻ የተሞላ መርማሪ በማንኛውም ዓይነት መለኪያ መርማሪ ሊሆን አይችልም፤ አይገባምም፡፡ የወንጀል ምርመራ ሣይንስ እንጂ ዱላና ስድብ አይደለም፤ አፀያፊ የዘረኝነት ዘለፋና ዛቻም አይደለም፡፡ ደግሞም በዜጎች መሀል ምርትና አመሳሶ እየፈጠሩ አንዱን አሣሪና ገራፊ ሌላውን ታሣሪና ተገራፊ ማድረግ ዛሬውኑ መቆም አለበት፡፡ ታሣሪዎች ዜጎች ናቸው፡፡ ወንጀል ሠርተው ቢታሠሩ እንኳን መብታቸው ሊጓደል አይገባም፡፡ ለምሣሌ “ሰው ደብድበሃል” ተብሎ የታሠረን ዜጋ በድብደባ እንዲያምን ማድረግ ሌላ ወንጀል በህግ ስም መፈጸም ማለት ነው – ከዚህ የከፋ ድንቁርናና ሕግ ወጥነት ደግሞ የለም፡፡ የጠ/ሚኒስትር አቢይ መንግሥት አሁን ባለው የሕግ አፈጻጸም ጉድለት ቢጓዝ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ ቀን የሚሠሩትን ማታ ሲያፈርሱብዎ ያድራሉና እነዚህን ዓይነት አስነዋሪ ዜጎች ከእርስዎና ከሕግ አፈጻጸም ተግባራት ያርቁ፡፡ አላግባብ ዜጎችን ያሰቃዩና አካል ያጎደሉ እንዲሁም ከኢትዮጵያዊ የጨዋነት ባህል በእጅጉ ባፈነገጠ ብዙ በደሎችን የፈጸሙ የየእስር ቤቶቹ ኃላፊዎችና መርማሪዎች ለሕዝብ ተጋልጠው በጥፋታቸው መጠን በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ይደረግ፡፡ ሕዝብ በርስዎ ሊተማመንና “ከእንግዲህ ሃሳቤን ብገለጽ የሚያሰቃየኝ የመንግሥት አካል የለም” ብሎ የሚረጋጋው እንዲህ ሲያደርጉ ነው፡፡ አለበለዚያ እንደተፈራራንና እንደተማማን ለውጡንም እንደተጠራጠርን እንቀጥላለን፡፡ እኔም በብዕር ስም እንደጫርኩ ወደማትቀርልኝ ጉድጓድ እነጉዳለሁ፡፡ እናም ለኔም ቶሎ ይድረሱልኝ እባክዎን፡፡
  7. የኑሮ ውድነቱ እንደሮኬት በየደቂቃው ሽቅብ እየተሽቀነጠረ በተለይ ድሃው በደመወዙ መኖር አልቻለም፡፡ በእውነተኛ ገቢ መኖር በፍጹም የማይቻልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም ምክንያት ሙስናና ስርቆት፣ ማጭበርበርና ማታለል፣ …. እንደባህል ተቆጥረዋል፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ሲባል ዜጎች ከህጋዊው መንገድ ይልቅ ጠማማውን የንቅዘት መንገድ ይመርጣሉ፡፡ ሕጋዊ አሠራር ጠፍቶ በሁሉም ሥፍራ በከፍተኛ ፍጥነት እንደወረርሽኝ እየተዛመተ የሚገኘው ህገወጥ አሠራር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሀገርን ዕድገትና ግንባታ ክፉኛ ያደናቅፋል፤ ወደ ኋላም የሚያስኬድ ክፉ ማኅበራዊ ነቀርሣ ነው፡፡ ጥራት የሚባል ነገር እጅግ አጠያያቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ እንደነገሩ ብዙ ንዋይ ፈጅቶ የተገነባ ነገር ከመመረቁና ምናልባትም ሳይመረቅ ሊፈርስ ይችላል – ለአብነት መንገድ ወይም ህንጻ፡፡ ጨረታ አሰጣጡ በሙስናና በዘር ነው፤ ዕቃ ግዢው በሙስናና በዘር ነው፤ የሰው ኃይል ቅጥር በሙስናና በዘር ነው፤ ምን አለፋን – ሁሉም እንቅስቃሴ በሙስናና በጎሠኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ነገር እያለ እርስዎ ጠ/ሚኒስትር መሆን ይከብደዎታልና ያስቡበት፡፡ መሞሰን ከነውርም ከኃጢኣትም ከወንጀልም የማይቆጠሩ የጽድቅ መንገድ ሆነዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የርስዎና መሰል ጓደኞችዎ ልፋት ከንቱ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ አፋጣኝ የድርጊት መርሐ ግብር ነድፈው ይንቀሳቀሱ፡፡ የፈለገውን ያህል ኃይለኛ መዓዛ ቢኖራትም እንኳን በትልቅ ሽንት ቤት ውስጥ የምትረጭ አንዲት ብልቃጥ ሽቶ ምንም የጠረን ለውጥ እንደማታመጣ ይረዱ፡፡ ሙስና ካለ ሥራዎ አይቃናም፡፡ ሙስና ትልቅ የእግር ብረት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ካለሙስና የሚንቀሳቀስ መሥሪያ ቤት አይገኝምና በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
  8. ዘረኝነትና ጎሠኝነት የሀገራችን ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከንግግሮችዎ ውስጤን የነካኝ ባለፈው በሕዝብ ፊት የሰው ልጆች መመሳሰል 99 ከመቶ መሆኑን ሲናገሩና ሰዎች ለአንዲት መቶኛ ልዩነት ሲባል ይህን ያህል መራኮት እንደሌለባቸው ያሳሰቡት የጥበብ ንግግር ብዙ ነገር አስተምሮኛል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በሰውነትና ዝቅ ሲልም በአንዲት ሀገር ልጅነት መሳሳብና መተባበር ሲገባቸው ይሄ እርጋጭ እርጋጭ የሚል አማራና ኦሮሞ ትግሬና ሶማሌ የሚባለው ከእንስሳነትም በታች የሚያወርድ ሕወሓት ዘራሽ መጥፎ ባህል እንዲወገድ ጥረት ያድርጉ፡፡ ከኦሮሞ በፊት ሰው ነበረ፤ ከአማራ በፊት ሰው ነበረ፤ ከትግሬ በፊት ሰው ነበረ፡፡ ትግሬነትና ጠምባሮነት፣ ብሌንነትና ሳሆነት ከሰው ልጅ መፈጠር በኋላ በሰው ልጅ በራሱ ለልዩነቱ የተሰጡ ፍረጃዎች ናቸው – የፈጣሪ አይደሉም፡፡ ልዩነት ሁሉ ደግሞ ማጣላትና ማገዳደል የለበትም፡፡ አስፈላጊ ልዩነትም አለና!

በዙ ነገር መናገር በተቻለ – (አንድ ያንዠት ጓደኛየ “ስትጽፍ አትምበዛበዝ ወደ ገደለው ግባ” የሚለኝ አሁን ትዝ አለኝ – ዘፋኙ “ወድጄ እኮ አይደለም” ብሏልና አሁንም ለብዙኛ ጊዜ ይቅርታ ወዳጄ፡፡) የሆኖ ሆኖ ምንም ያህል የተናገርኩ ባይመስለኝም ለአሁኑ በዚህ ይብቃኝ –  አስለፍላፊ ሀገር! በዋናነት ግን – ውድ ጠ/ሚኒስትር -በዙሪያዎ የተኮለኮሉ የሥርዓቱ አዋላጆችና የግፈኛው ዘረኛ መንግሥት አስቀጣዮች በአብርሃም ማስሎው የሰው ልጅ ዕድገት ትንታኔ ገና በመጀመሪያው እርከን ላይ ተዘፍቀው የሚርመጠመጡ በመሆናቸው ሥራዎን እንዳያበላሹብዎ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ በመብላትና በመጠጣት የሆድ አምላኪነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው ከሆዱ ሌላ ሃይማኖት የለውም፡፡ ለሆዱ ሲል ሀገሩን አይደለም ቤተሰቡንና “ከነፍሴም በላይ እወዳቸዋለሁ” የሚላቸውን ልጆቹን ሳይቀር ይሸጣል፡፡ ስንቶች ሀብታሞች የቅርብ ዘመዶቻቸውን ለሰይጣን ጭዳነት እየገበሩ ሰማይ ጠቀስ ፎቅና ታላላቅ የንግድ ማዕከላትን እንደሚገነቡ ይነገራል፡፡ የአንጎል አለማደግ የሰው ልጅ አደገኛ ጠላት ነው፡፡ ሆድ ደግሞ መጥፎ ጠላት ነው፡፡ … እነዚህ በሕወሓት ውስጥ የመሸጉ የሦስተኛና አራተኛ ክፍሎች ምሩቃን “ጄኔራሎች”፣ “ዶክተሮች”ና “ፕሮፌሰሮች” ያላቸው የአፍራሽነት ተፅዕኖ ቀላል አይደለምና ጠንቀቅ ማለቱ ይበጃል፡፡ ….

netsanetz28@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *