“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢሕአዴግ መንግሥታዊ ቅርጽና ኢኮኖሚ

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በሁለተኛው ዓመት ባወጣው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማዎችና ቀጣይ ተግባራት የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዞውን አመላከተ፡፡ በኢኮኖሚ አመራሩ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ናቸው ያላቸውንም ለየ፡፡

በድርጅቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ዓላማዎች ተጠቃሚ የሚሆኑና የማይሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እነማ እንደሆኑ በመለየት በፖለቲካው ጭቁን ሕዝብና ጭቁን ያልሆነ ሕዝብ በማለት ሲከፋፍል በኢኮኖሚው መንገድም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ኀይሎች እና ጥገኛ ካፒታሊስቶች ብሎ ከፋፈላቸው፡፡

የግል ንብረት ባልነበረበት የደርግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዳተር ማግስት በጣት ይቆጠሩ የነበሩት የደርግ የፓርቲና የመንግሥት ሹማምንት እስር ቤት ከገቡ እና የጦር ኀይሉ ሙሉ በሙሉ ከተበተነ በኋላ፣ የተቀረውን ሕዝብ ጭቁንና ጭቁን ያልሆነ ብሎ በፖለቲካው ለመከፋፈልም ሆነ በኢኮኖሚው ጥገኛ ካፒታሊስት ተብሎ ሊጠራ የሚችል ማን እንደሆነ ለኢሕአዴግ ካልሆነ በቀር ለማንም ግልጽ አልነበረም፡፡ የመንግሥትነት ሥልጣን ከመጨበጤ በፊት በትግል ሜዳ ላይ ከጠላት የማረኳቸው የኢንዶውመንት ንብረቶቼ ናቸው ያላቸውን በበጎ አድራጎት ድርጅት ስም ተመዝግበው፣ ሕጋዊ አድርጎ ካቋቋመ በኋላ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኀይሎች አድርጎ በጋራና በተናጠል የግዙፍ መዋዕለንዋይ ባለቤት ድርጅቶች ሆነው ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩ አደረገ፡፡
የዴሞክራሲ ኀይሎች ከተባሉት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ፓርቲው ያቋቋማቸው ከሕወሓት “ኤፈርት”፣ ከብአዴን “ጥረት”፣ ከኦሕዴድ “ዲንሾ” እና ከደኢሕዴን “ወንዶ” ሲሆኑ፣ በውስጣቸው በርካታ ማምረቻና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ይገኙባቸዋል፡፡ በምርትና በአገልግሎት አሰጣጥ ንግድ ሥራ የመንግሥት ድርጅቶችንም ሆነ የግል ባለሀብቱን ድርሻ በልጠውና ተክተው ከሚሠሩ ከእነዚህ የፓርቲ ድርጅቶች ውስጥም ልቆ የሚገኘው የሕወሓቱ ኤፈርት ሲሆን ካሉት ወደ ዘጠና የሚጠጉ ድርጅቶች ካፒታል የዐሥራ አንዱ ብቻ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ምን ያህል እንዳደገ ከአንድ የታተመ ጽሑፍ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሰባት መቶ ዘጠና ስምንት ሚልዮን ወደ ሐምሳ ሰባት ቢልዮን ብር አድጓል፡፡ ‹ኤፈርት› ለራሱ አድጎ በአገሪቱ ቁጥር አንድ ግዙፍ ድርጅት ከመሆኑም ባሻገር በመንገድና በሕንጻ ተቋራጭነት ከባዶ አንስቶ የሰቀላቸው ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅቶችም በምርት በግንባታና በንግድ አገሪቱን ተቆጣጥረዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የእነኚህን ድርጅቶች አነሳስ ስለሚያውቅ ሆድ ሆዱን እየበላው ይኖራል፡፡ ከብአዴንና ከሃያ አምስት መሥራች አባላት በተገኘ ሃያ ስድስት ሚልዮን ብር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1987 የተመሠረተው “ጥረት” ዳሸን ቢራን ጨምሮ ዐሥራ ስምንት ኩባንያዎች እንዳሉት የሚታወቅ ሲሆን ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት ሰዓት የባሕር ዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅን ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች በሰባት መቶ ስልሳ አምስት ሚልዮን ብር ለመግዛት በዝግጅት ላይ ነበር፡፡

ከ1983 እስከ 1990ዎቹ መጨረሻዎች ድረስ ኢሕአዴግ አርሶ አደሩን እንደ ጭቁን በመቁጠር የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ አጋር መደቡ አድርጎ ነበር በአንጻሩ የከተማው ሕዝብና የኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች ወዝአደሮች ጭቁን ያልሆኑ ተብለውና እንደ ጥገኛ ተቆጥረው ትኩረት አልተሰጣቸውም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ከኒዮ-ሊብራል ምዕራባውያን መንግሥታት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ዓለም በሙሉ በግል ገበያ ኢኮኖሚ እንዲመራና በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና እንዲቀንስ የዋሽንግተን መግባቢያ ስምምነትን ተፈራርመው በሁሉም አገሮች ለማስረጽ ሲንቀሳቀሱ ወደ ኢትዮጵያም ጎራ ብለው ነበር፡፡ ይህም ለኢሕአዴግ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት የሆኑትን ድርጅቶች ለወዳጅ ዘመድ ከበርቴዎች ለማከፋፈል የሚያመቸው ንፋስ ያመጣው ዕድልና በረከት ነበር፡፡ በመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ስም በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1980 እና 90ዎቹ ዓመታት ብዙ ሰው ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች አፈናቅለዋል፣ የመንግሥት ድርጅቶች ለግል እንዲሸጡ አድርገዋል፡፡ በሮቿን ለውጭ ሸቀጥ ክፍት እንድታደርግ መክረው በከፊል ተሳክቶላቸዋልም፡፡

የጋራ ንብረቱን ወደ ግል በማዞር እርምጃቸው በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተካበቱ የአገሪቱ ሀብቶችን ደርግ የሕዝብ አድርጓቸው ከዚያም በኋላ በዐሥራ ሰባት ዓመት የደርግ ዘመን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላብ የፈሰሰበትን አንጀታቸውን አስረው የቆጠቡትንና የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው ያሏቸውን ማምረቻና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ባንኮችና ኢንሹራንስ የመሳሰሉትን የገንዘብ ተቋማት ያለካሳ መንግስት ራሱ፣ ጥቂት ግለሰቦችና የታጋዮች ኢንዶውሜንት ናቸው የተባሉ ድርጅቶች ተቀራመቷቸው፡፡ በዚህ መልክ ነው እንግዲህ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ የላቡ ዋጋ የሆነውን ንብረቱን በመንግሥት ባለሥልጣናት ለግል ወይም ለፓርቲ ድርጅቶችና ለግለሰቦች የሕዝብ ንብረት ከነበረው ንግድ ባንክ በተወሰደ የማይከፈል ብድር ራሳቸው ገዢ ራሳቸው ሻጭ ሆነው የተነጠቀው፡፡ ይህ የምዝበራው ቁጥር አንድና ጅማሮ ነው፡፡ ከዚህም ተነስተው ነው በሁለተኛው የምዝበራ መንገድ በዋጋ ንረትና በሦስተኛው የምዝበራ መንገድ ድሃው ጥሬ ገንዘብ ቆጥቦ በኪሳራ ወለድ ለንግድ ባንኮች በማበደር ሕዝቡን እያቀጨጩ እነርሱ የደለቡት፡፡ ይህን መነሻ ሀብት ተጠቅመው ነው ከበርቴዎች ሕንጻ እንዲገነቡ በማድረግ በሃያ ስድስት ዓመት ምዝበራ በድሃ አገር ውስጥ የቢልየነርነት የሀብት ጉዟቸውን የጀመሩት፣ ቢጠሯቸው የማይሰሙ ቱጃሮች የሆኑት፡፡

ከሦስቱ የብዝበዛ መንገዶች አንደኛው የሕዝብ የነበረውን ሀብት ሻጭም ገዢም ሆነው መውረሳቸው ብዙ ሙያዊ ትንታኔ የሚሻ ጉዳይ ባይሆንም በሶሻሊስት ማኅበረሰብ የሕዝብ የነበረው ሀብት ሕዝባዊ የአክስዮን ኩባንያዎችን በማቋቋም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለራሱ ለሕዝብ ሊከፋፈል ይችል የነበረን የሕዝብ ሀብት ጥቂት ከበረሃ የመጡና እዚህ የቆዩ ዘመዶቻቸው ተቀራመቱት፡፡ የጋራ የነበረው በኢፍትሐዊ መንገድ ተከፋፍሎ በተከታይም በተወሰዱት በሁለተኛው በዋጋ ንረትና በሶስተኛው በቁጠባ አማካኝነት የአገርና የሕዝብ የጋራ የነበረው ሀብት ከድሃው ወደ ሀብታሙ ከገጠሩ ወደ ከተማው እንዴት እንደተሸጋገረ በክፍል አምስት ከምዕራፍ ስምንት እስከ ዐሥራ ሦስት የተግባር ሃተታዎች በጥልቀት እናያለን፡፡

ከ1990ዎቹ መጨረሻ በኋላ ባሉት ዓመታት ግብርናው ካፒታል ሊያፈራና ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ ምርት ሊያመርት ይቅርና ለምግብ ፍጆታ እንኳ ስለአልበቃው የግብርና መር ኢኮኖሚ ፖሊሲው ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ታወቀ፡፡ በ1997ቱ ምርጫ የከተማው ሕዝብ በኢሕአዴግ ፖሊሲ አለመደሰቱ ሁከት በመቀስቀስ በመገለጡ ገጠርን ማዕከል ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደማያዋጣ አምኖ ፊቱን ወደ ከተሜው መለሰ፡፡ ከተማውና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት ተሰጣቸው፡፡

የከተማውን ኗሪ ወጣቶችና ሴቶች በድርጅት አባልነት እየተመለመሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አደራጀ፣ የውጭ ባለሀብቶች በማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሳተፉ የሚስቡ የኢነቨስትመንት ማበረታቻ ሕጎችን ደነገገ፣ በምህንድስና ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የከፍተኛ ትምህርትና የሙያና ቴክኒክ ተቋማት ተስፋፉ፣ ለኢንዱስትሪዎች በብዛት የሰው ኀይል ለማፍራት ሥልጠና በስፋት መሰጠትም ተጀመረ፡፡ መንግሥት ራሱም በመሠረተልማት ግንባታና ለገበያ በሚቀርቡ ሸቀጦች በአምራችነት ተሳታፊ ሆነ፡፡ የግል አምራቾችን ልማታዊ ካፒታሊስትና ጥገኛ ካፒታሊስት ብሎ ከፋፈላቸው፡፡

የኢኮኖሚ አስተዳደሩን ወደ ልማታዊ ኢኮኖሚ ካዞረ በኋላ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት አፈጻጸም ቢታይም ልማታዊ ኢኮኖሚ አገራዊ ብሔርተኝነትን ስለሚጠይቅ በቋንቋ ላይ በተመሠረተ የጎሳ ፌዴራሊዝም ፖለቲካዊ አስተዳደር ምክንያት ሕዝቡን ስላሳተፈ ስትራቴጂዎቹን ለማስፈጸም አልቻለም፡፡ ልማታዊ ኢኮኖሚ ማሟላት ያለበትን የሲቪል ማኀበረሰቦችን፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ፣ በአጠቃላይም ኅብረተሰቡንና የኅብረተሰብ ተወካዮችን አጋር የማድረግን ጥበብ አልተካነም፡፡ በሌላ በኩልም በልማታዊ ኢኮኖሚ መርህ ልማት መተዳደር ያለበት በችሎታቸው በላቁ ሰዎች ቢሮክራሲ መሆን ሲኖርበት፣ በኢትዮጵያ ግን የፌዴራል መንግሥት ቢሮክራሲን ለማዋቀር ዋናው መስፈርቱ የብሔር ተዋጽኦ እንጂ ችሎታና ብቃት አለመሆኑ ልማቱ ስኬታማ እንዳይሆን አደረገው፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት አገር የማስተዳደር ሕጋዊነት አንድነትን በሚሹም፣ የክልል መንግሥታትን ነጻነት በሚሹም ገና ያልፀደቀና ያልተፈታ ጥያቄ በመሆኑ እነዚህን አካላት የልማት አጋሮች ማድረግ አልቻለም፡፡ አንድነትን የሚሹት ክልሎች አካባቢያችን ለክልላችን ሰው ብቻ ነው በማለታቸው ማዕከላዊ አመራሩ ተዳክሟል ሲሉ በብሔረሰብ ደረጃ መጥበብን የሚሹት ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መጠን ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር በቂ ሥልጣን አልተሰጣቸውም ይላሉ፡፡

ከአንዳንድ መሠረተልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ከማቅረብ በቀር መንግሥት በአገር አስተዳደር ሚናው በታሪካዊ ጸጥታ ማስጠበቅና ሕግ ማስከበር ሥራዎች ተወስኖ ገበያውን በፖሊሲ ቢመራውና ገበያው ኢኮኖሚውን ቢያስተዳድረው ኖሮ ገበያው ለዚህ ክልል ሰው ለዚያ ክልል ሰው ብሎ አያደላም ነበር፡፡ መንግሥት ገበያውን ተክቶ ኢኮኖሚውን ሲያስተዳድረው ግን ወደ ክልሎች ወደ ታች በወረደው መንግሥታዊ ፌዴራላዊ መዋቅር ተጠሪነቴና ኀላፊነቴ ለክልሌ ሕዝብ ነው የክልሌን ሀብትም በፍትሐዊነት የማከፋፍለው ለክልሌ ሕዝብ ብቻ ነው ተባለ፡፡ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ያስገባናል የተባለው አገራዊ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አስታዋሽ አጥቶ ብሔራዊ አጀንዳ በክልላዊ አጀንዳ ተተክቷል፡፡ ክልሎችም የማዕከላዊው መንግሥት የዘመቻ ኢኮኖሚ አስተዳደር ተጋብቶባቸው የዘመቻ ኢኮኖሚ አብዮቶች ነድፈዋል፡፡

መጋቢት 13 ቀን 2009፣ በሪፖርተር ጋዜጣ አንድ ምሁር ስለ ኢሕአዴግና የዘመቻ ሕይወቱ፣ “ተደምሮ–ዜሮ አገርን በዘመቻ የመምራት ጥበብና ውጤቱ፤” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ጽሑፍ አስፍረው ነበር፡፡ “አገራችን ጦቢያ ለዘመቻ አዲስ ባትሆንም በእኛ ዕድሜ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ብቻ እንኳ ስንት ዘመቻዎች መጥተው ስንት ዘመቻዎች ተፈራረቁ የውሃ ማቆር ዘመቻ፣ የጤና ልማት ሠራዊት ግንባታ ዘመቻ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ዘመቻ፣ የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ዘመቻ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዘመቻ፣ የመልካም አስተዳደር ማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነት ማክሰም ዘመቻ፣ የሲቪል ሰርቪስ አሠራር ማሻሻያ ዘመቻ፣ የፀረ ሙስና ዘመቻ፣ የጥልቅ ተሐድሶ ዘመቻ፣ … ዘመቻ … ዘመቻ“

የኢሕአዴግ መንግሥት በገበያ ኢኮኖሚ መርሁም ሆነ በልማታዊ ኢኮኖሚ አስተዳደሩ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስቱ የመንግሥት ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በክፍለ ኢኮኖሚ የሀብት ድልድል፣ በለሰዎች የሀብትና የገቢ ፍትሐዊ ክፍፍልና የብሔራዊ ኢኮኖሚ መረጋጋት የትኛውንም በትክክል አልተወጣም፡፡ መንግሥት በሚሠራቸው ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ሁሉ የሕዝቡን ፈቃድና ድጋፍ አላገኘም፡፡ ያለ ሕዝብና ግብር ከፋዩ ፈቃድ ዐሥር አክሳሪ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ሲነድፍ አንድ መቶ ሃያ ቢልዮን ብር የፈጀ የባቡር ትራንስፖርት ወጪ አውጥቶ አገርን ሲያከስር ማን እንደፈቀደለትም መናገር አይችልም፡፡

ከእነኚህ በተጨማሪ መንግሥት ማምረቻና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን አቋቁሞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችንም እንዲያመርት ማን ፈቀደለት፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ማምረት የመንግሥት ሥራ አይደለም ቢልስ እንዴት ሊከለክለው ይችላል፡፡ ማን ይጠይቃል ማንስ ይመልሳል?

መንግሥት ከድሃው ሕዝብ በሚሰበስበው ግብር ለውጭ ኢንቬስተሮች የፋብሪካ ተከላ ቤት መገንባትና ጓዳቸው ድረስ መሠረተልማት ማንጠፍ ሕዝቡና ግብር ከፋዩ መክሮበት የተሰራ ሥራ ስላልሆነ ውጤት አልባ ከሆነ በኀላፊነት የሚያስጠይቀው ማንን ነው፡፡ ድሃውን አስገብሮ ለሀብታሙ ደጁ ድረስ ድንጋይ ማንጠፍስ ከሰዎች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ኢኮኖሚያዊ ግብ አንጻር እንዴት ይታያል? ብዙ ያልተመለሱና በኢሕአዴግ ዘመን የማይመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከኢሕአዴግ ሥልጣን የሚረከብ መንግሥት ይህንን በኢሕአዴግ ዘመን ተቆልሎ ሰማይ ሊነካ የተቃረበ ፍርደ ገምድልነት እንዴት ይሸከመው ይሆን?

The Black Lion

ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?
0Shares
0