“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለጠ/ሚኒስትር አቢይ የተላከ ጠቃሚ ደብዳቤ! – የማይታመን እውነት!

የትናንትናዋ ዕለት እጅግ ታሪካዊት ናት፡፡ ይህችን የመሰለች ታሪካዊት ቀን ትመጣለች ብሎ የጠበቀ ወይ ያሰበ ካለ በርግጥም ነቢይ መሆን አለበት፡፡ ቀኒቱ ለዘላለም ልትዘከር ይገባታል፡፡

በአንድ በኩል የወያኔን አገዛዝ የሚነቅፍ በሌላ በኩል አንዳርጋቸው ጽጌን በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት የሚፈራም ሆነ የሚጠላ ግንቦት 21/2010 ዓ.ምን ቢያስባት በኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል ላይ ጭላንጭል ብርሃን መፈንጠቁንና በእግረ መንገድም ፍትህ-ወዳድ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ “ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ” ማለት አይገባም፡፡ የአንዳርጋቸው መለቀቅ ካላንዳች ቅድመ ሁኔታ ሁላችንንም ሊያስደስት የሚገባ ያልተጠበቀ ክስተት ነው፡፡

እኔ በበኩሌ የወያኔን ሰይጣናዊ ተፈጥሮ አሳምሬ ስለማውቅ የገዛ ልጇን ለማስያዝ ከራሷ ካዝና የዘረፉት የሀገር ሀብት ቢሆንም ስንትና ስንት ሚሊዮን ዶላር ከስክሰው፣ ስንትና ስንት ዲፕሎማሲያዊ መስዋዕትነትን ከፍለው፣ ስንትና ስንት የአይበገሬነታቸውንና የከሃሌ-ኩሉነታቸውን ጉራ ለዓለም ማኅበረሰብ አሳውቀው(Understandably, they did all those maneuvers in Yemen to show off their omniscience, omnipotence, and omnipresence whereas, on the contrary, they are ignorant full of brimless arrogance.))፣ ስንትና ስንት ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ህግጋትን ጥሰው፣… ስንትና ስንት መከራና ስቃይ ያሳዩትን አንዳርጋቸው ጽጌን በዚህ መልክ ይለቁታል ብዬ በውኔ ቀርቶ በልሜም አላሰብኩትም፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ አሁን ይህን ካሳየን ከዚህ ዕጥፍ ድርብ የሚበልጠውንና ዋናውን የሀገራችንን ነፃነት ደግሞ በቅርብ እንደሚያሳየን አልጠራጠርም፡፡ ይህ ክስተት በራሱ ቀላል እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ የአንበሣን መንጋጋ ፈልቅቆ ሊውጠው ሊሰለቅጠው የደቀነውን ሙዳ ሥጋ እንደማውጣት ያህል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ትልቁን ሚና በመጫወቱ ሊመሰገንና ለቀጣይ ድሎችም ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

ኢሳትን የመሰሉ የሕዝብ ዐይንና ጆሮዎችም ይህን ጉብል በተቻላቸው መጠን ሊያግዙት እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ የኢሳትን አንዳንድ ፕሮግራሞች ስከታተል – ለምሣሌ የትንናት ምሽቱን የሁለት ወጣት ዶክተሮች ትንተና ዓይነት – በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ለመርካት የመጓጓት ስሜትን አንብቤያለሁ – በመሠረቱ ጉጉት ጥሩ ነው፡፡ ፍላጎታቸውን የመግለጽ መብታቸውን የማከብር ሆኜ ሳለ ከሀገራችን ክምርና ድድር ችግሮች አንጻር ግን አሁን የምናየው መልካም ነገር ራሱ ከሚጠበቀው በላይ ነውና ተገቢው ከብርና ድጋፍ እንደሚያስፈልገው መረዳት ተገቢ ነው – እዬዬም እኮ ሲደላ ነው፡፡ ብዙ መጠበቁ እንዳለ ሆኖ ያለውንም ማወደሱና በፀጋ መቀበሉ መጥፎ አይመስለኝም፡፡ ሰውን ተስፋ ማስቆረጥም አግባብ አይደለም፡፡ ከጅብ ጎሬ ሆኖ ይህን ያህል ሥራ መሥራት ቀላል አይደለም፡፡ በተከፈቱ የርሀብተኛ ጅቦች አፍ ሥር ተቀምጦ አሁን አንዳርጋቸውንና ቀደም ሲል ደግሞ እነእስክንድርን ማስፈታት መቻል በራሱ ለትልቅ ሜዳሊያ የሚያበቃ የጀብድ ሥራ ነው፤ ቀላል ይመስላል እንጂ የትልቅ ጦር ሜዳ ውሎ ተግባር ነው፡፡ ለተጨማሪ ድሎቹ ደግሞ የመፍትሔ ሃሳቦችን መሰንዘር፣ መንዶገችን መጠቆም፣ በሃሳብና በሞራል መደገፍ፣ ግርዶሽን እየከሉ በስልክም፣ በኢሜልም፣ በደብዳቤም ከጎኑ መቆም… ይገባል፡፡ አታሞ በሰው እጅ እንደምታምር ሲይዟት ግን እንደምታደናግር መረዳት አለብን – መናገር ቀላል ነው፤ መተቸትም ቀላል ነው – በተማርነውና ባነበብነው መሠረት ትንተና መስጠት ከባድ አይደለም፤ ወደ ተጨባጩ የሀገራችን ሁኔታ ስንገባ ግን ከሶማሊያና ከሦርያም የተለዬ ጣጠኛ በመሆኑ ባማረ ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሚነጋገሩበትን ያህል ቀላል አይደለም፡፡ (በልጅነቴ አንድ የቤተሰብ ታሪክ አስታውሳለሁ – አንድ ያጎቴ ልጅ ትልቅ ሆኖ ሲገረዝ እናቱ “አይዞህ! ቻል አድርገው!” ትለዋለች፡፡ እሱም መልሶ “አይ እማዬ! አንቺ ምን አለብሽ!” አላት፡፡ በዚህ ንግግሩ ቅኔው የገባቸው ሣቁ፤ እኔ ግን ልጅ ነበርኩና ስላልገባኝ ያኔ አልሣቅሁም)፡፡ አንድ ነገር በሩቅ ሆኖ ሲያዩትና ተጠግተው ሲያዩት ወላፈኑም ሆነ ሙቀቱ ይለያያልና የፖለቲካ ተንታኞቻችንና ተቺዎች እየተጠነቀቁ ቢናገሩና ቢተቹ ተጨማሪ ድሎችን ከማጣት እንድናለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ “ለቦና ጥጃ ‹ውስ!› ምን አነሰው?” የሚለውን የአለቃ ገ/ሃናን ታሪክ እናስታውስ፡፡ በዚህን አጭር ጊዜ ውስጥ ይህ ሁሉ እስረኛ መፈታቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ፍላጎትን በጨዋና ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ መግለጽንም እንልመድ፡፡ የሚሰማኝን ነው የምናገረው፡፡

ለማንኛውም በድጋሚ እንኳን ደስ ያለን!

የነፃነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ጽጌ በርግጥም ተፈትቷል፡፡ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህን ስኬት በኔ እምነት ሰው አላመጣውም፡፡ ሰውን ምክንያት አድርጎ የኢትዮጵያ አምላክ መገፋታችንን አይቶ ያመጣው በብዙ ዘመናት አንዴ ሊከሰት የሚችል ታላቅ ድል ነው፡፡ ከነተረቱ “ደስታ ቀላል ነው!” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ይህ ድል በራሱና ብቻውን ብዙ የሚያስፈነጥዝ ነው፡፡ አንድ ሽህ ኪሎ ሜትር በአንድ እርምጃ እንደሚጀመር ይህ ክስተት ለታላቁ ነጻነታችን ትንሣኤ ትልቅ ጅማሮ ነው፡፡ እርግጥ ነው –  መታሰር የሌለበት ሰው ታስሮ አለወጉም “ይቅርታና ምሕረት ተደረገለት!” ተብሎ መለቀቁ ከመነሻው ስህተት ነው፡፡ ሀገርና መንግሥት ቢኖረን ኖሮ በስህተት የታሰረ ሰው ሲፈታ “መንግሥት በስህተት ያሰረውን ዜጋ ይቅርታ ጠይቆትና ለታሰረበት የሞራል ካሣ እንደዚሁም በእስራቱ ሳቢያ በሥራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱ ያጣውን ጥቅማ-ጥቅምና ደመወዝ በመክፈልና የሀገራችንን መላ ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ በዛሬው ዕለት ከእስር ቤት አሰናበቶታል” መባል ነበረበት፡፡ በካፈርኩ አይመልሰኝ የቆረቡት እነዚህ ሰይጣኖች ግን በድንቁርናቸው የፀኑ ዋልጌዎች በመሆናቸው ይህን ማድረጋቸውም የሚያኮራቸው የማይም ግብዞች ናቸው፤ ስህተታቸውን እንዲያምኑ ደግሞ ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ እኛም የምንገዛው ከሲዖል ባመለጡ ወምበዴዎች እንደመሆናችን የጽድቁ ቀርቶብን የኩነኔውም እየናፈቀን እንገኛለንና በየትኛውም ሁኔታና መንገድ ውዶቻችን ቢፈቱልን የለማኝ ተጓዳጅ ልንሆን አይገባንም – ደጅ ጠኚ የሰጡትን ይቀበላል እንጂ ሰጪን የመውቀስ መብት የለውም – እንኳንስ ወያኔን የመሰለ ጭራቅ፡፡ ጀግንነቱ ካለን እንደነሱ በረሃ ወርደን ሥልጣኑን በኃይል መቀማት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ራሷ ሄዳ ጣፊያም የተከለከለች ድመት ትሁን ውሻ “ምላስ ሰምበር ላኩልኝ አለች” እንደተባለው መሆን ነው፡፡  ስለዚህ “ይህንንስ ማን አይቶበት?” በሚለው ባህላዊ መጽናኛችን እየተጽናናን ለኛ ሲሉ የተገፉና የተበደሉ ልጆቻችንን በደስታ መቀበል ነው ያለብን፡፡ ስንቀበላቸው ግን ስለጉድለታችን እንደተሰቃዩ ጉድለታቸውን ልናሟላላቸው ይገባናል፡፡ ለምሣሌ ለአንድ ቀን ምሽት የምናጠፋውን ገንዘብ ለነሱ ብናውል ቢያንስ በቁሣዊ ሕይወታቸው ልንክሳቸው እንችላለን፡፡ የሥነ ልቦና ጉዳታቸውን ደግሞ ፈጣሪ በጊዜ ሂደት ይጠግነዋል ብለን እናምናለን፡፡

ለዶ/ር አቢይ አጭር መልእክት አለኝ፤

ብዙዎች ዜጎች እንወድሃለን፤ እናከብርሃለንም፡፡ ያላየነውን ዓለም ማየት የጀመርነው ባንተ ነው፡፡ ጀግናን መውለድ እንጂ ማሳደግ የሚያቅታት ሀገራችን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ባከናወንካቸው ድንቅ ተግባራት ተገቢውን ፍቅርና ክብካቤ ልትሰጥህ ቢያዳግታትም አንተ ግን ተስፋ ሳተቆርጥ ሥራህን ቀጥል፡፡ የምትሠራው ደግሞ ለስምና ለታይታ ወይም ሰዎችን ለማስደሰትና ለማስከፋት ሳይሆን ለማተብህ መሆኑን እርግጠኛ ሁን፡፡ ዜጎችን ሁሉ በአንዴና በእኩል ደረጃ ማስደሰት ባትችልም ሁሉንም በጥሞና አዳምጥ – ነፍስና ሥጋ ያለውን የእግዚአብሔርን ፍጡር ብቻም ሳይሆን ተፈጥሮንም አዳምጥ – ሜዳ ሸንተረሩ፣ ሣርና ቅጠሉ… ብዙ የሚነግርህ ምሥጢር አለው –  ጠቢብ ከሆንክ፡፡ በዜጎች መሀል ግርድና አመሳሶ የለውም፡፡ ሁሉም እኩል ነው፡፡ ዕብድም ጤናማም፣ አጭርም ረጂምም፤ ቆንጆም ፉንጋም፣ የተማረም ያልተማረም፣… ሁሉም የአንዲት ሀገር ዜጎች ከነእንስሶቻቸውም ጭምር እኩልና አንዱ ከሌላው ሊዳላላቸው የማይችሉ የማይገባም ናቸውና በጀመርከው ዜጎችህን የማክበር ድንቅ ጅምርህ ቀጥል፡፡ በሁሉም ቦታ ተገኝ፡፡ በአሜሪካን ሀገር በሚካሄደው የዲያስፖራው የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት የጠየቅኸው ጥያቄም ግሩም ነው – አርቆ አሳቢነትህን ያሳያል – አየህ፣ የአንድ እጅ ጣቶች ሁሉም ሚና ስላላቸው አንዱ ቢጎድል – ለምሣሌ እንደቀላል የምትታየው ትንሽዋ ጣት ብትቆረጥ –  በሥራቸው ላይ ጉድለት እንደሚታይ ገብቶሃል ማለት ነው፤ ሀገራዊ ምሉዕነት የሚኖረን ሁሉም ልጆቿ ተቀራርበውና ተሳስበው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ስትፈጠር፣ አንዱ በላተኛ ሌላው ተመልካች፣ አንዱ ስደተኛ ሌላው አሳዳጅ… ሳይሆን የሁሉም የምትሆን ሀገር ስናገኝ መሆኑን ተረድተሃል ማለት ነው – ከዚህ ዘመን መሪዎች የማንጠብቀው አዲስና ማራኪ የአስተዳደር ዘይቤ ነው –  ግፋበት፡፡ ጥያቄህ የቀረበላቸው የኮሚቴ አመራሮችም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈቅዱ ይገባል – ለበጎ ነውና ህገ ደምባቸውንም ቢሆን በአስቸኳይ ስብሰባ አሻሽለው፡፡ ሁለታችሁም የማታገኙት ዕድል ነው፡፡ አንተም- የስፖርቱ ኮሚቴም፡፡ ይህ ነገር ለአቢይ ወይ ለኮሚቴው ሲባል የሚደረግ ወይ የማይደረግ አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ሲባል ነው፡፡ የምንገኝበት ዘመን የሥነ ልቦናም በሉት የሞራል የበላይነት ወይ የበታችነት የማግኘት ወይ ያለማግኘትና የመበላለጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደሕዝብና እንደሀገር የመኖር ያለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናልና ከዚህ ዓይነቱ አጉል ፉክክርና የተለመደ ፉክቻ በአፋጣኝ ልንወጣ ይገባል፡፡ ለጉራና ትዕቢት ጊዜ የለንም፡፡ ስለዚህ በሎጂክና በዶግማ የታጠረ አጉል ክርክር ውስጥ ገብተን በከንቱ የምናጠፋው ጊዜም ሆነ ወርቃማ ዕድል ሊኖር አይገባም፡፡

ውድ ወገኖቼ!

የምሥራች! እባቡ አንገቱን ተይዟል! መርዙን ግን አልተፋውም፡፡ ትልቁ ሀገራዊ ጥረት መሆን ያለበት አናኮንዳው እባብ መርዙን እንዲተፋ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ በከንቱ ስንጯጯህ አንገቱን የተያዘው እባብ ካመለጠና  እንደበፊቱ በሙሉ ኃይሉ መንቀሳቀስ ከቀጠለ ማናችንንም እንደለመደው ከመንደፍ አይመለስም፤ እባብ በተፈጥሮው ርህራሄም ሆነ ይሉኝታ የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ንድፊያ ደግሞ በመርዛማነቱና በኃይለኝነቱ ከእስካሁኑ የሚብስ ይሆናል፡፡ ይህ እባብ በእግዚአብሔር ዕርዳታና በጥቂት የበቁ ሰዎች ልባዊ ጸሎት እንደዚሁም ከኅሊናቸው ጋር በታረቁ ውሱን ፖለቲከኞች ጥረት በአሁኑ ወቅት ማንጅሩን ተይዞ ጭራውን እየቆላ በመንከላወስ ላይ ይገኛል፤ ዕድል ካገኘ ግን አፈር ልሶና አጋጣሚ ጠብቆ ወደቀደመው ኃያልነቱና አስፈሪነቱ አይመለስም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህን የሰሞኑን ጥቃቅን ለውጦች ማየት የቻልነው እንግዲህ በዚህን እባቡ በሞትና በሕይወት መካከል ባለበት አጋጣሚ ነው፡፡ የእባብ ታሪክ ብዙ ነው፡፡ ዱሮ በእናታችን ገብቶ ከገነት አወጣን፡፡ ከዘመናት በኋላ ደግሞ አሁንና በዚህ ዘመን በወንድሞቻችን ገብቶ ከሀገራችን ከኢትዮጵያ አውጥቶ በመላው ዓለም ለስደትና ለግዞት በተነን፡፡ ይህ እባብ ፈለገ ግዮንን እንዳሳደደ ይኖራል፡፡ አሁን ግን የመጨረሻው ዘመን ደርሷልና መሳደድ ለእርሱ ይሆናል፡፡ ግዮንም ነፃ ትወጣለች፡፡

ውድ ጠ/ሚኒስትር!፣

ወጣት ነህ፡፡ ብዙ አንባቢ መሆንህ ያስታውቃል፡፡ ሀገርህን መውደድህም እንደዚሁ፡፡ አንባቢ ሰው፣ ሰው ሰው ይሸታል፡፡ የሚያነብ ሰው ሕይወትን ከመጻሕፍትም ስለሚያገኛት የትም ሳይሄድ ባለበት ብዙ ይማራል፡፡ በዚያውም የራሱን አካሄድ ይቃኛል፡፡ ለሰው አዛኝና ሩህሩህም ይሆናል፡፡ የማያነብ ደግሞ በተቃራኒው ልቡ ድንጋይ ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን ይቅርና ለራሱም ፍቅርና ክብር የለውም – ለቤተሰቡም ጭምር፡፡ ለዚህ ዓይነቱ “ሰው” ልክ እንደብዙዎቹ ሌሎች እንስሳት ሁሉ ዋና ዘመዱ ሆዱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንተ ታድለሃልና ፈጣሪህን ልታመሰግን ይገባሃል፡፡ እኛም አንተን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን፡፡

ይህችን ጦማር እንደምታነብልኝ ቆጥሬ አንዲት የክት ነጥብ ላካፍልህ – ከሰው የሰማኋት ናት፡፡ ትግሬዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ 1. “አየ(ጆ)ሁም ናይና” 2. “ኩልኹም ናይና” ይባላሉ፡፡ ቀደም ያለ ታሪክ ነው፡፡ በጊዜ ሂደት “ኩልኹም ናይና”ዎች በ“አየሁም ናይና”ዎች ተሸነፉና ሀገር ጉድ ሆነች፡፡ “አየ(ጆ)ሁም ናይና” ማለት “የኞች አይዟችሁ” ማለት ሲሆን “ኩልኹም ናይና” ማለት ደግሞ “ሁላችሁም የኛ” ማለት ነው – አንደኛቸው ሽል መንጣሪ ከፋፋይ ጎሠኞች ሲሆኑ ሌላኛቸው አካታቾችና ሀገራዊ ስሜት የነበራቸው ለዘብተኞች ነበሩ፡፡ በምናባችን ለአፍታ ወደ ሩዋንዳ ብንሄድ “extremeist”እና “liberal” ሁቱዎችን አስታውሰን መመለስ እንችላለን፡፡ በዚያ በሩዋንዳ የሆነውም እንደዚሁ ነው፡፡ አክራሪዎቹ የገጀራውን እጀታ ለሦስት ወራት ያህል የመጨበጥ ዕድል አገኙ፤ ሕጻን ሽማግሌ ሳይሉ ያገኙትን ቱትሲ ሁሉ ፈጁ፡፡ “አየሁም ናይና”ዎችም በሀገራችን የመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ቁልፍ ከሊቀ ሣጥናኤል ከጓድ ሊ/መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅ በጠራራ ፀሐይ ተረከቡ፤ ላለፉት 27 ዓመታት በግላጭ ኢትዮጵያውያንን በሚሊዮኖች ጨፈጨፉ – በተለይ የፈረደበትን አማራ፡፡ በዚህ የጭፍጨፋ ሂደት “ኩልኹም ናይና”ዎችም አልተረፉም፡፡ እነሱም ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተሰደዋልም፡፡ ዱሮ በትግሉ ወቅት በባዶ ስድስትና ኋላም በመንግሥትነት የወያኔ ዘመን በግልጽ በሚታወቁ እስር ቤቶች እነዚህ ገርና የዋህ ኢትዮጵያዊ ትግሬዎች ተንገላትተዋል፤ ደብዛቸውም ጠፍቷል፤ ዘራቸው እየተፈለገ እንዲጠፉ ተደርጓል፡፡ ይህን እውነት ከተረዳን ዘንድ የ“ኩልኹም ናይና” ብሩካን ተጋሩን አቅፈንና የነሱን የትግል ሱታፌ አስተባብረን ኢትዮጵያን ከነሕዝቧ የበታተኑትን  የእፉኝት ልጆች ወደማይቀርላቸው የመጨረሻ ፍርድ ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ይህን ስናደርግም እንደነሱ መጨከን፣ እንደነሱ በዕብሪት መወጠር፣ እንደነሱ መታበይ፣ እንደነሱ በጥላቻና በበቀል ስሜት መታወር… በሰማይም በምድርም ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከነሱ ትምህርት ወስደን ጤናማ የትግል እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ “የዘሩትን ማጨድ አይቀርም” የምንለው የዘወትር ብሂል ተረት ሳይሆን እውነት ነው፡፡

በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ አብዛኞቹ የእባቡ መርዞች የሚከተሉት ናቸው፡-  

 1. መከላከያ
 2. ደኅንነት
 3. ፖሊስ
 4. የሀገሪቱ ካዝና
 5. የ1968ቱ የእባቡ ሕወሓት ማኒፌስቶ (በተለይ አማራንና ኦርቶዶክስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቃል ኪዳን የገባባቸው አንቀጾች)
 6. መላውን የሀገሪቱን ሥልጣንና የገንዘብ ዝውውር የተቆጣጠሩት የእባቡ የዘር ግንድ አባላትና የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት የጥቅም ተጋሪዎቻቸው (ቻይና፣ ህንድ፣ ቱርክ፣….)
 7. የግንዛቤና የዕውቀት ዕጥረት
 8. ፍርሀት (የሚታወቅንም የማይታወቅንም ነገር መፍራት)
 9. አለመተማመን
 10. ጎሠኝነትና ጎጠኝነት
 11. በተፎካካሪዎች መሀል ያለ መጠላለፍ
 12. ሥልጣንና ራስ ወዳድነት
 13. ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት መደብዘዝ ወይም ጨርሶውን መጥፋት
 14. አፍቅሮተ ንዋይ
 15. ሙስና
 16. ማይምነት
 17. ጨለምተኝነት ወይም ተስፋ መቁረጥ
 18. ጭራቃዊ ህጎችና ዐዋጆች(የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ የፀረ-ሽብር ዐዋጅ፣ የነፃ ፕረስ አፋኝ ዐዋጅ…)
 19. የሲቪክ ማኅበራት መፈራረስ
 20. የሃይማኖት አባቶቸና የምሁራን አድርባይነትና እበላ ባይነት እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገራት መፍለስና መሰደድ

እነዚህንና መሰል የእባቡ መርዞችን በሥልት መዋጋት ይገባል፤ በነዚህ ላይ ጦርነት ማወጅ ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም፡፡ በተለይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 5 የተጠቀሱት የእባቡ መርዞች በዘዴ ከመንታ ምላሱ ካልተወገዱ አደጋው ትልቅ ነው፡፡ እነዚህ ደነዝ ወያኔዎች ገና ለገና ትንሽ ለውጥ መጥቶ ዜጎች መተንፈስ በመጀመራቸው “‹ጠባብና ትምክህተኛ› ብለን እንኳን መሳደብ እንደነውር የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ ከ27 ዓመት በፊት የነበረው አስተሳሰብ እያንሰራራ ነው…” የሚል አስቂኝ ነጠላ ዜማ ማቀንቀን ጀምረዋል፡፡ የድንቁርናቸው በዛት እስከዚህ ነው – በነማን እንገዛ እንደነበር እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ “የመሳደብ መብቴ ተገደበ፤ እንደልብ የመግደል መብቴን ተነፈግሁ…” የሚል ክስና ወቀሳ ሲቀርብ ተመልከቱ፡፡ አዎ፣ “የማይቀጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” እንደሚባለው እንዳሻቸው ሲገድሉና ሲዘርፉ፣ እንደልባቸው ሲሳደቡና ሰውን በዘሩ ሲያንቋሽሹ … 27 ዓመታትን የዘለቁ ሰዎች የሌሎች ዜጎች መብት መከበር ሲጀምር ቢጨንቃቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ለማንኛውም ጠ/ሚኒስትር አቢይ ይህን ሁሉ ጉድ በጥሞና ተከታተል፤ ችግሮቹን ተረዳና ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ከሁነኛ ሰዎችህ ጋር ሆነህ ምከር – ዝከር፡፡ ከጎሠኝነት የገማ ጭቃ ውስጥ ሊያነካካህ የሚፈልግ የግል ስሜትም ይሁን የቅርብ ጓደኛ ቢኖርህ በቶሎ ራቀው – መቼም ወደማትወጣው አዘቅት ይጨምርሃልና – አንተን ብቻም ሳይሆን አንተን ያመነውን ሁሉ ይዞ ነው ወደ እንጦርጦስ የሚወርድ፡፡ ለአንተው ደኅንነትም ጠንቀቅ በል – አንተ ደኅና ስትሆን ነውና ዓላማህ ግቡን የሚመታው፡፡ እባቡ ቀን አይቶና ጊዜ ጠብቆ አዘንግቶ እንዳይነድፍህ ለራስህም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ አለማየሁ አቶምሳን ያዬ በታሸገ ውኃ አይቀልድም ወንድማለም፡፡

በመጨረሻም፤

ውድ ጠ/ሚኒስትር አቢይ –  የእስር ቤቶችን ኃላፊዎች አሁኑኑ በጤናማ ዜጎች ለውጥ፡፡ እስካሁን የነበሩት በጥላቻ የደነዘዙ የእባቡ ልጆች ነበሩ፡፡ እነዚህ መርዘኛ እባቦች ሕዝቡን ነድፈው ፈጁት፡፡ የታሰረ ሰው አንድም ሳይቀራቸው በመርዛቸው እየነደፉ ከሰውነት ተራ አስወጡት- እነብርቱካን ሚዴቅሳን፣ አልማዝ ሠይፉን፣ ደበበ እሸቱን፣…. አስታውስ፡፡ ስለዚህ መታሰርና መመርመር ያለ ሆኖ የህግ ሠራተኞች ግን በሙያው የሠለጠኑና ዘመናዊ የታራሚ አያያዝ ዕውቀትና ትምህርት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሰዎች ወንጀል ሠሩም አልሠሩም አንዴ ማረፊያ ቤት ከገቡ በኋላ በጥላቻና በቂም በቀል እንዲሁም በዘረኝነት በሽታ በተለከፉ ዕብድ ሰዎች ሊሰቃዩ አይገባም፡፡ መቼም እዚሁ ቁጭ ብለህ ይሄን ሁሉ የወያኔ ጉድ ሳትሰማ አትቀርም፡፡ አንተ በሆነ አጋጣሚ ምናልባትም ወደህ ባልተወለድህበት የቤተሰብህ ዘር ምክንያት አንዱ የሚጠላህ አሳሪህ በጨለማ ክፍል ዘግቶብህ የእጅህን ጣቶች አሥሮቹንም ጥፍሮች በጉጠት ቢያወልቅ ምን ይሰማሃል? በአንድ ወንድምህ የወንድነት መለያህ ላይ ሁለት ሊትር ፈሳሽ የያዘ ኮዳ ቢያንጠለጥሉበትና በስቃዩ ቢደሰቱ ምን ትላለህ? ከዚህም ባለፈ እዚህ ላይ ልገልጸው የሚያሣፍረኝና ሰይጣን ራሱ እንኳን ተጠይፎ የማያደርገው ድርጊት በአንዱ ወዳጅህ ላይ ቢፈጽሙበት፣ በርሀብ ቢቀጡት፣ ለወራትና ዓመታት በጠባብ ጨለማ ክፍል ውስጥ ከብዙዎች እስረኞች ጋር ቢዘጉበት፣… ምን ይሰማሃል? የምልህ ሁሉ በዕብዶቹ እባቦች በዚህች ደቂቃ ሳይቀር በንጹሕ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለ ነገር እንጂ ልብ-ወለድ አይደለምው፡፡ ባንተ አስተዳደር ይህ አጸያፊ ተግባር በፍጥነት ተወግዶ ድርጊቱን ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ወንጀል ሠርቶ መታሰር፣ በፍርድ ቤት ትዛዝም መገደል እኮ ያለና የነበረም ነው፡፡ በሀገራችን የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሳይቀር በትግራይ ውስጥ የሚሰቃዩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በቅጡ ቢገደሉ እኮ ለነሱ ለሟቾቹም ሆነ ለኛ ለቆምነው እንደውለታ የሚቆጠር ነው፡፡ ይህን ርህራሄ የተሞላበትን በአግባቡ የመሞትን ዕድል እንኳን ወያኔዎች ሊሰጡን ፈቃደኛ አይደሉም – ማሰቃየትን እንደትልቅ የማሸነፊያ ስትራቴጂና የሥነ ልቦና እርካታ ምንጭ ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ እነዚህን እባቦች ከየማረሚያ ቤቶች ባፋጣኝ ካላወጣህ ጅምርህ ሁሉ የእምቧይ ካብ ይሆንና ደክመህ እንዳልደከምህ ትሆናለህ፡፡ የአንጀት ምክሬ ነውና ችላ እንዳትለው አደራህን፡፡ መታሰራቸውን ሰው ያወቀላቸው ተፈቱ፤ ያልታወቀላቸው በሽዎች የሚቆጠሩ አሉና ለነሱ በቶሎ ድረስላቸው፡፡ በመርዘኛ እባብ መነደፍ በዚህ ትውልድ ይብቃ፡፡

በሌላም በኩል በየትግሬዎች ቤት ሳይቀር የታሰሩ ዜጎችንና በትግራይ ዋሻዎችና ልዩ ልዩ ግልጽና ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ ታጉረው የሚሰቃዩ በተለይ የአማራው ብሔር ተወላጆችን አሁኑ አስለቅቅ፡፡ ይህ ካልሆነ በነዚህ እባቦች ላይ አማራው ጊዜ ጠብቆ ለሚወስደው እርምጃ ኃላፊነቱን የሚወስድ አይኖርም፡፡ ታሪክና ፈጣሪ አንተን በዚህ የጭንቅ ቀን ወደ መድረክ ካመጡህ ዘንዳ የነዚህን እባቦች ዕኩይ ዓላማና ሤራ ጊዜ ሳትሰጥ አንድ ባንድ ግን በጥንቃቄ አክሽፈው፡፡ ይሄ የእባቡ ትክል ፌዴራሊዝም የሚባለው ጨዋታም አያሞኝህ፡፡ የውሸት መሆኑን አንተም ታውቃለህ፡፡ ለምሣሌ እነዚህን “የፌዴራል መንግሥታችን”ን ክልላዊ መንግሥታት አስታውስልኝ –  “የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት”፤ “የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት”፤ “የአፋር ክልላዊ መንግሥት”፤ “የአማራ ክልላዊ መንግሥት”፣… ሣቅህ አልመጣብህም? እኔ ስቄ ስለጨረስኩ አሁን ይህን ዐረፍተ ነገር ስጽፍ ራሱ በንዴት እየተንጨረጨርኩ ነው፡፡ ፈረንጆቹም እንደመዝናኛ ወስደውት ሊስቁብን ፈልገው እንጂ ይህን በታማኝ ግሩም አገላለጽ የፌዝ-ራሊዝም የዕቃ ዕቃ ጨዋታ እንኳንስ አንተና እኔን የመሰልን ፊደል የቆጠርን ሰዎች ይቅርና የልጄን ልጅ አቡቹን ሣይቀር በሣቅ ጦሽ የሚያደርግ ቧልት ነው፡፡ የቤንሻንጉልን የፖሊስ ኮሚሽነር ሚስት ታውቃታለህ? ባሏን ከነፕሬዝደንታቸው የምታሽከረክር ትግሬ ናት፡፡ ትንንሾቹንና ወያኔ ግልጽ ትያትር እየተወነ የሚጫወትባቸውን ጋምቤላንና ቤንሻንጉልን የመሳሰሉትን “መንግሥታት” ተዋቸው – ወዝ ላለው ቀልድም አይበቁም፡፡ አማራን የመሰለ ትልቅ ክልል በረከት ስምዖንንና ኅላዌ የሱፍን የመሰሉ አማርኛ ተናጋሪ ትግሬዎች በወሳኝ የሥልጣንና ኃላፊነት ቦታዎች ላይ አስቀምጦ ላለፉት 27 ዓመታት እንዴት እንደተጫወተበት ታውቅ የለም? በሌሎች ክልሎች ውስጥ እንደማንኛውም ወገኑ ለፍቶ የሚያድረውን አማራ በደቦ እንደዐይጥ ከማስጨፍጨፋቸው በተጓዳኝ የራሱ ክልል ውስጥ አንድም የልማት አውታር እንዳይኝገና ልጆቹም ትምህርት ሳይማሩ ወይም በበቂ ሁኔታ ትምህርታቸውን ሳይከታተሉ ደንቁረው እንዲቀሩ የተደረገውን ወያኔዊ ሸርና ተንኮል ሁሉም ያውቃል – አንተም ጭምር፡፡ የዚህን ሁሉ ውዝፍ ሂሳብ ማን ይከፍል ይሆን? ዐዋቂ ወጌሻ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ በሰው ስቃይ ማላገጥ፣ ለባለጊዜ ማሽቃበጥና አንደኛው በሌላኛው ላይ መሣቅ መገልፈጥ ቀላል ነው፡፡ ግን ታሪክ ደብተራ ነው- ደጋሚ! ታሪክ ሲደግም ደግሞ በዕጥፍ-ድርቡ ነው፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚ አቢይ ብዙ ሥራ አለብህ፤ ከነካካሃው አይቀር አትፍራው – ተረቱም – ‹አማራ› ደግሞ ለተረት – ተረቱም “ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽ ባላፈርሽ” ነውና ለውጥ ለማምጣት ከተነሣህ አይቀር በእናንተው አገላለጽ መሬት የረገጠ ለውጥ አምጣ፡፡ በሁሉም ሂድበትና ያበጠው ይፈንዳ፡፡ የጋምቤላውን ዳግማዊት ወልቃይትም መርምር (አንዲት ታሪክ ትዝ አለችኝ – አንድ የሒሣብ መምህር ጥቁር ሠሌዳ ላይ አንዲት ጦጣ ይስልና “የዚችን ጦጣ ጅራት ርዝመት የሚነግረኝ!” ብሎ ተማሪዎችን ይጠይቃል፡፡ ተማሪዎቹ እጅ እያወጡ አንደኛው አንድ ሜትር ሌላኛው ግማሽ ሜትር…. እያሉ መመለሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በመጨረሻ የመለሰው ልጅ “ጋሼ! አምስት ሣንቲ ሜትር ይሆናል” ይለዋል፡፡ ያኔ መምህሩ “አይይ! ብላችሁ ብላቸሁ ይቺን ጦጣ ካለ ጅራት ልታስቀሯት መሰለኝ!” አላቸው አሉ፡፡) ወያኔ ኢትዮጵያን ከያቅጣጫው እየሸራረፈ ባወጣች ሲሸጥና ሲለውጥ፣ ወደራሱ የህልም ሪፓብሊክም ሲጨምር ከናካቴው ባዶዋን ሊያስቀራት ደረሰ፡፡ ይሁን፡፡ ለማንኛውም ዕንቅልፍ የለህም ውድ ጠ/ሚኒስትር፡፡

የዲፕሎማሲውን መንደር በአፋጣኝ አስተካክል፡፡ እባቡ የሾማቸው የዲፕሎማቲክ ሠራተኞች በአብዛኛው ትግሬ መሆናቸው በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ ብዙዎቹ ማይማን መሆናቸው ነው፡፡ እንኳንስ ለዲፕሎማትነት ለተራ የቢሮ ተላላኪነት ሥራም የሚያበቃ የትምህርት ደረጃና ዕውቀት የሌላቸው መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ የሚላኩት ሌላ እንዳይጠቀምና ለሥርዓቱ ይበልጥ ታማኝ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ ዋና ሥራቸውም “እከሌ ምን አለ?” በሚል ወሬ ለመለቃቀምና ዜጎች በስደት እየኖሩም ሰላም እንዳይሰማቸው በስለላ መረብ አጥምዶ የአእምሮ ዕረፍት ማሳጣት ነው፡፡ ከዚያ በተረፈም በኮንትሮባንድ ንግድ እንዲከብሩና በየኤምባሲው ባላቸው ሥልጣን በሙስና ተነክረው የዕድሜ ልክ መጦሪያቸውን እንዲያካብቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ነገር በቶሎ ማስተካከልና የኢትዮጵያን ምሰል በትክክል ሊያሳውቁ የሚችሉ የተማሩና የበቁ ዜጎችን ከትግሬም ጭምር መመደብ አለብህ፡፡

አየር መንገድን ከ90 በመቶ በላይ፣ መከላከያን ከ80 በመቶ በላይ፣ ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከ80 እና 90 በመቶ በላይ በተለይ በኃላፊነት ቦታ ላይ የተመደቡት በተገቢው ያልተማሩ ትግሬዎች መሆናቸው ዘወትር ይነገራል፡፡ ይህንም ሁኔታ ማስተካከል ይገባል፡፡ የሀገራችን ቢሮክራሲ የውስጥ አፍንጫችን ከሚቋቋመው በላይ ተግማምቷልና በአፋጣኝ መጽዳት አለበት፡፡ አለበለዚያ ሽንት ቤት ውስጥ ተቀምጦ ፈስ ገማኝ ማለት ስለማይቻል አንድ ነገር ከመታጠቡ እየቆሸሸ ባሉበት መንከባለል ባህላችን እንደሆነ እንኖራለን፡፡ ስንነጋገር በግልጽ መሆን ስላለበት ነው በቃላት አጠቃቀሜም ሳልሸማቀቅ እንዲህ  እንደልቤ የማወራው፡፡ በስንቱ ልሸማቀቅ!

ዜጎች በነፃነት ይኖሩ ዘንድ የደኅንነቱን መሥሪያ ቤት በአፋጣኝ ከእባቦቹ እጅ አውጣ፡፡ ስልክንና ኢሜይልን መጥለፍ፤ ኢንተርኔትን መዝጋት፣ አንድ ሰው ሃሳቡን በነፃነት በመግለጹ ምክንያት የክትትል ራዳር ውስጥ ማስገባት፣ በቋንቋውና በዘውጉ ምክንያት በገዛ ሀገሩ ቀን ከሌት በደኅንነት የስለላ ቀለበት ውስጥ መግባት፣…  ጊዜ ሳይሰጠው መቋረጥ ይኖርበታል፡፡ ከየት እንደተላኩብን የማይታወቁት መፃጉዓኑ ወያኔዎች ሕዝቡን እንደባዕድ ስለሚቆጥሩት እንጂ የአንድ ሀገር ሕዝብ በገዛ ሀገሩ መንግሥት የስለላ ክትትል ውስጥ አይገባም፤ ነውርም ወንጀልም ነው፡፡ እነሱ ግን ጥላቸውንም ስለማያምኑ ኢ-ትግሬን በተለይ ዘወትር እንደተከታተሉና እንዳሳቀቁ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የሚሠሩትን ሁሉ ሰዎች የሚያውቁባቸው እየመሰላቸው የገዛ ተንኮላቸው ዕረፍት ስለሚያሳጣቸው ነው፡፡ ሰውን በተለዬ የግፍና መከራ ዓይነት የሚያሰቃዩትም ለዚህ ነው፡፡

የመንግሥት ሚዲያ ቲቪና ጋዜጣው የተለመደ ውሸቱን ከመንዛት መቆጠብ አለበት፡፡ “ከአሁን በኋላ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ክልክል ነው፤ የለውጡን ሂደት ስለሚያጠይም የውሸት ዜናና ሀተታ ከአሁን በኋላ ታግዷል” የሚል  መመርያ ለኢዜአና ለፋና ብሮድካስቲንግ ይተላለፍላቸው፡፡ ውሸትን ከተው እስተንፋሳቸው ሊዘጋ ቢችልም ይህ ግን መደረግ አለበት፡፡

በተጨማሪ ውድ ጠ/ሚኒስትሬ ሆይ – አንዳንዴ ስትናገር ከስሜት ወጣ እያልክ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ስሜታዊነት የአመክንዮታዊነትን ኃይልና ሚዛን ሊያዛባ ይችላልና ጥንቃቄ አድርግ፡፡ በተጨማሪም በሚዲያ የሚነገርና የማይነገር ነገር አለ –  ያንንም መለየት ጥሩ ነው፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነው – አይመለስም፡፡ ለብዙ የሰላ ትችትም ይዳርጋል፡፡ የምንናገረው ጣፈጠም አልጣፈጠም በመጀመሪያ እኛው ውስጥ እያለ “ኤዲት” እናድርገው – እናቀው(‹ር› ትጥበቅ!) – እንኳንስ ለአቃቂር በር የሚከፍት ነገርና አፍ የሚያስከፍት ጣፋጭ ታሪክም ከጓደኛሞች ተራ ጨዋታ ባለፈ ለሚዲያ ፍጆታ የማይሆን ብዙ የግል ነገር አለ፡፡ ከገዛ እንትኑ ጋር ከመጣላት ወደኋላ የማይለው አብዛኛው የዘመኑ ሰው ደግሞ ከቁንጫ መላላጫ የሚያወጣ ሆኗል፡፡ ለኔ ደስ የሚለኝ ንግግርህ ለሌላው የአቃቂር ምንጩ ነው፡፡ ስለዚህ ጠንቀቅ! በምሣሌ ላስደግፍልህ፡- ባለፈው ሰሞን በቤተ መንግሥት ተጋሩን ስታጽናና – ማነው – ስታነጋግር- “እኔ እያለሁ … አትታሰሩም፡፡….” ያልከውን ደግመህ እየው፡፡ አንተ አንድ ሰው ነህ፡፡ በዚህች ሀገር ውስብስብና ትልቅ ታሪክ ውስጥ ድንገት ዱብ ያልክና በኔ እምነት በፈጣሪ የተፈቀደልህን አወንታዊ አስተዋፅዖ ለማድረግ ቀና ደፋ የምትል ከመቶ ሚሊዮኑ መንጋ መሀል አንዱ ዜጋ ነህ፡፡ ይህን ካለመረዳት በሚመነጭ ስህተት ውስጥ ከገባህ የማትወጣው አረንቋ ውስጥ ልትዘፈቅ ትችላለህ፡፡ አንተ የዕቅዶችህ መሣሪያ እንጂ የወንጀለኞች ጋሻ አይደለህም – እንድትሆንም አይጠበቅም፡፡ አንተ ፍርድ ውስጥ ለመግባት አትሞክር፡፡ “በኔ ይሁንባችሁ አትታሰሩም!” ማለት በቀጥታ የፍርድ ቤትን ሥራ መቀማት ማለት ነው –  እነሱ ምን ሠርተው ይብሉ? እንዲህ ከሆነ ደግሞ “ዋጮን ቢገለብጡት ያው ዋጮ ነው” እንደሚባለው ሊሆን ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ውድ ልጃችን፡፡ ስለምወድህ ነው በግልጽ የምመክርህ፡፡ የሠራኻውንና የምትሠራውን በዜሮ እንዳታበዛው በአባትነቴ አስታውስሃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ትዕቢትን አይወድም፤ የኢትዮጵያ መሬት ትኅትናን እንጂ ዕብሪትንና ትምክህትን አይወድም፡፡ ታሪክን እናጥና – የታበየና በጉልበቱ ወይ በሀብትና ሥልጣኑ የተመካ የትም ሲደርስ አላየንም፡፡ ቀ.ኃ.ሥ፣ መንጌ፣ መሌ… ከዚያ በኋላ መሪ ስላልነበረ አልዋሽም፡፡ በነገራችን ላይ “ከዚህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በኋላ ‹የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር› ለመባል…” ብሎ በሣቅ የገደለኝ “የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር”  በሀገራችን የከፍተኛ ሥልጣን ባለቤቶች ስም ዝርዝር ውስጥ እንዳይገባ ከሚታገሉ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡

ስለዚህ አቢይዬ – አደራህን – የፍርድን ነገር ለባለሙያዎቹ – ከንቅዘትና ከሙስና ነፃ ሆነው ለሚበይኑ የሙያው ባለቤቶች ስጣቸው፡፡ አንተ ሁሉንም መሆን አትችልምና ሰው መድብ፡፡ ታማኝ ሰዎችን በኩራዝና በፋኖስ እየፈለግህ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ላይ አስቀምጥ፡፡ ያኔ አንተም ዘና ትላለህ፡፡ የእባቡ መርዝ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እርግጠኛ ስሆን እኔም ካለ ደመወዝም ቢሆን ሙያዬ የሚፈቅድልኝን አንዲት ትንሽዬ ቦታ በመያዝ የምትለፋላትን ሀገራችንን ለማገልገል ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ ሀገራችን “የሰው ያለህ!” የምትልበት ቀን መምጣቱን አልጠራጠርምና በዚህች በመጨረሻዋ ቃሌ ምክንያት  “ማን ሊስምሽ ታሞጠሙጭ” እያልሽ አዳሜ ብትቀልጂብኝ በልጅ ልጆቼ አነጋገር ‹አልሰማሽም›፡፡ የምለምነው ይልቁንስ ዕድሜና ጤና ብቻ ነው፡፡ አበቃሁ፡፡

(ብሥራት ደረሰ – ከአዲስ አበባ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው
0Shares
0