ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በጠላትነት የምትተያየው ኢራን ግን አልጋወራሹ በቤተመንግሥት አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ቆስለዋል ወይም ሞተዋል በማለት በርግጠኝነት ትናገራለች።

በሙስና ወንጀል በሚል በርካታ የሳዑዲ ባለሃብቶችን ዘብጥያ የጣሉት የዙፋን ተስፈኛው የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን በሳዑዲ ሚዲያ ከታዩ አንድ ወር አልፏቸዋል። በአንዳንዶች ግምት በቤተመንግሥት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገድለዋል ይባላል። አልጋወራሹ በህይወት ከሌሉ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ አህመድ አላሙዲንን “አስፈትተው” የመጡት ማንን አነጋግረው ነው የሚል ጥያቄ ተነስቷል። የሳዑዲ መንግሥት አልጋወራሹ በሥራቸው ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።

የሳዑዲ የዙፋን ተስፈኛ አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን 11 ልዑላንን እና 38 የመንግሥት ባለሥልጣናትን (የቀድሞውን ጨምሮ) እንዲሁም የንግድ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን፤ ደላላ (ተጠሪ ወይም front man) ባለሃብት እንደሆነ የሚነገርለት በግማሽ ኢትዮጵያዊ የሆነው ሞሐመድ አላሙዲ (አል-አሙዲ) በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል መሆኑን በኅዳር ወር ጎልጉል አረጋግጦ መዘገቡ ይታወሳል።

ይህ “በሳዑዲ አረቢያ ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅም” ተብሎ የሚነገርለትን የጸረ ሙስና ዘመቻ የሚያካሂደው ኮሚቴ “ማንኛውንም የማሰር፣ የመያዝ፣ ወዘተ ሥልጣን” እንደተሰጠውና ይህንንም በኃላፊነት የሚመሩት አልጋወራሹ መሆናቸውን አስመልክተው ንጉሥ ሳልማን በሳዑዲ ቲቪ ላይ እንደተናገሩት፤ “የሕዝብን ገንዘብ በነካ፣ በመዘበረ፣ ወይም እንዳይሰረቅ ባልተከላከለ ወይም ሥልጣኑን ተጠቅሞ (ይህንን ዓይነት ተግባር በፈጸመ) በማንኛውም ግለሰብ ላይ ሕጉ በጽናት ተግባራዊ ይደረጋል። ይህ የሚፈጸመው በትልልቆቹም ሆነ በትንንሾቹም ላይ ይሆናል፤ ማንንም አንፈራም” ማታቸውን የጎልጉል ዘገባ በወቅቱ ትንታኔ የሰጠበት ነበር

በዚህ ዓይነት ከፍተኛ ሥልጣንና ተስፋ የፊት መሪ የተደረጉት አልጋወራሽ ሳልማን ከኤፕሪል 21 ወዲህ በሳዑዲ ሚዲያ ፈጽሞ ያልታዩ መሆናቸውን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የሚዲያ ዘገባዎች ሰሞኑን ጠቅሰዋል። ይህንንም ተከትሎ የምዕራቡ የዜና ዘገባዎች ሁልጊዜ የሚዲያውን ትኩረት የሚሹት አልጋወራሹ ለሕዝብ ሳይታዩ የመቆየታቸውን ሁኔታ በማንሳት ሲዘግቡ ሰንብተዋል።

ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በጠላትነት የምትተያየው ኢራን ግን አልጋወራሹ በቤተመንግሥት አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ቆስለዋል ወይም ሞተዋል በማለት በርግጠኝነት ትናገራለች። የጸረ ሙስናውን ዘመቻ እና የአገሪቱን ሥልጣን ለብቻቸው ጠቅልለው በመያዛቸው በሳዑድ ቤተሰብ በተከፈተው ጠላትነትና የሥልጣን ሽኩቻ ኤፕሪል 21 ቀን ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ እንደነበር የኢራን ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል።

ካይሃን የተባለው የኢራን ጋዜጣ የስለላና የመረጃ ምንጮች ዘገባ ጠቅሶ እንደሚለው ከሆነ በተኩስ ልውውጡ ወቅት አልጋወራሹ “ቢያንስ በሁለት ጥይት ተመትተዋል፤ በዚህም ሳቢያ ሞተዋል” ይላል። በመቀጠልም አልጋወራሹ በህይወት ካሉ ለምን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በሳዑዲ ጉብኝት ሲያደርጉ ከአልጋወራሹ ጋር የተነሱት ፎቶ ይፋ አልተደረገም በማለት ይጠይቃል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ግን ይህንን አቋም በግልጽ ይቃወማል። አልጋወራሹ በህይወት እንዳሉና መንግሥታዊ ሥራቸውንም በሥርኣት እያከናወኑ መሆናቸውን ይናገራል። ለዚህም የተለያዩ ፎቶዎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በዋቢነት ያቀርባል። ሆኖም የትኞቹም ምስሎች ቀን የሌላቸው ከመሆናቸው በላይ በየትኛውም ምንጭ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ሲኤንኤን ዘግቧል

በኤፕሪል 21 የተካሄደውን የተኩስ ልውውጥ በተመለከተ የሳዑዲ መንግሥት ተኩስ አልተሰማም በማለት አይክድም። ሁኔታው የተከሰተው ለመዝናኛ የሚውል ሰው አልባ በራሪ (ድሮን) ሳይፈቀድለት በቤተመንግሥቱ ሰማይ ሲበር በመታየቱ ያንን ለማክሸፍ የተወሰደ እርምጃ ነው በማለት ያስተባብላል።

የምዕራብ ዜና ወኪሎች በተለይም ሲኤንኤን የአልጋወራሹን በህይወት አለመኖር አጽንዖት ሰጥቶ ከዘገበ የተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የሳዑዲ መንግሥት መቼ እንደተከሰተ የማይታወቅ አልጋወራሹ የንግድ ልማት ስብሰባ ሲመሩ የሚያሳይ ቪዲዮለቋል። የሳዑዲ መንግሥት ስብሰባው ከሁለት ቀን በፊት የተካሄደ ነው ቢልም ሲኤንኤን ግን ስብሰባው በቅርቡ ወይም ከኤፕሪል 21 በኋላ ለመቀረጹ ማረጋግጥ አልቻልኩም ብሏል።  ከዚህ በተጨማሪም የሳዑዲ መንግሥት አልጋወራሹ  የየመኑን ፕሬዚዳንት ሲቀበሉ የሚያሳይ ተጨማሪ ቪዲዮ ለቋል። በሌላ በኩል አልጋወራሹ የፊፋውን ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ባለፈው አርብ አነጋግረዋል በማለት አረብ ኒውስ ቢዘግብም የተጠቀመው ፎቶ ግን ከፋይል ክምችቱ እንደሆነ አልካደም።

አልጋወራሹ በህይወት አሉ፤ ይህ የሳዑዲና የምዕራቡ ዓለም ጠላት የሆነችው ኢራን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ነው የሚሉ የአሜሪካና የአውሮፓ የፖለቲካ ተንታኞች ልዑሉ ከጸረ ሙስናው ዘመቻ ጋር በተያያዘ ምናልባት በብዛት በሚዲያ ሲታዩ ስለነበሩ አሁን ለመቀነስ የወሰዱት እርምጃ ነው ይላሉ። ይህንንም እንደሽፋን አድርጋ ኢራን በሳዑዲ አለመረጋጋት መኖሩን በመጠቆም የራሷን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት እየተጠቀመችበት ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

ከጸረሙስናው ጋር በተያያዘ አላሙዲንን ለውርደትና በሌብነት ክስ ለእስራት የዳረጉት አልጋወራሽ በህይወት ከሌሉ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ አህመድ ባለፈው ወደ ሳዑዲ በሄዱ ጊዜ በርግጥ አልጋወራሹን አግኝተዋቸዋል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። በኢትዮጵያ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚቆጣጠራቸው የሚዲያ ውጤቶች ጠ/ሚ/ሩ በአልጋወራሹ ጋር መገናኘታቸውን በስፋት ቢዘግቡም ያሳዩት ቪዲዮም ሆነ ፎቶ አልነበረም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠ/ሚ/ሩ ከሳዑዲ እንደተመለሱ በፍጥነት በሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘት በሌብነትና ዝርፊያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለውን አላሙዲንን ለማስፈታት ስምምነት ላይ መደረሱን ለተሰብሳቢው ይፋ አደረጉ። ከመስመርም አለፍ ብለው አላሙዲንን በተዋቡ ቃላት አሞካሹት፣ አወደሱት፣ አመሰገኑት። ምንም እንኳን በወቅቱ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ በአገራችን ሕግ በተገቢው አላሙዲንን እንጠይቃለን ቢሉም ትርፍ የሄዱበት መንገድ ሳዑዲ ሄደው ያከናወኗቸው ሌሎች ተግባራት የበለጠ ሚዛን በመድፋታቸው እንጂ ስለ አላሙዲን የተናገሩት ኢትዮጵውያን አሳዝኗል፤ አስቆጥቷል።

ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንደሚሉት በርግጥ አልጋወራሹ በህይወት ከሌሉ የአላሙዲን “ተፈትተዋል” መባል፤ “ከተፈቱም ወደ አገር ሳይመጡ መቅረታቸው” ከዚህ ውስብስብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ለበርካታ ዓመታት ግብር ባለመክፈል፣ እጅግ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን (በተለይ ከኦሮሚያ)  አጥሮ ያለ ሥራ በማስቀመጥ፣ እስካሁን ያልተከፈለ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በመውሰድ፣ ወዘተ በርካታ ጥያቄዎች የሚቀርብበት አላሙዲ ወደ አገር እንዲመጣ የተፈለገው ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ከእነዚህ ያልተወራዱ ሒሳቦች በተጨማሪ የአላሙዲ ሚድሮክ በስሙ የያዛቸውና ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ዋስትና የገባችባቸው፣ ያልተጠናቀቁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። የእነዚህንም ሒሳብ ማወራረድ የፌዴራሉ ብቻ ሳይሆን የኦሮሚያም ከፍተኛ ፍላጎት ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች

ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በቶሎ ወደፍጻሜ አለማድረስ በሚድሮክ ሥር የሚገኙት ሃምሳ ሺህ ሠራተኞች ኅልውና አደጋ ላይ በመጣል ያልተፈለገ ችግር ውስጥ ላለመግባትና በሕጋዊ መልኩ እስከመውረስ ለመሄድ እንዲቻል በሚል ነው ጠ/ሚ/ሩ አላሙዲንን ለማስፈታተ የፈለጉት የሚለው አስተያየት በርካታዎችን የሚያሳምን ነው።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ የአልጋወራሹ በህይወት መኖርም ሆነ አለመኖር በተጨባጭ አልተረጋገጠም።

goolgule online

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *