“Our true nationality is mankind.”H.G.

የአንዳርጋቸው ጽጌ አፈታት ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ያለኝን እይታ ቀይሮታል – መሳይ መኮንን

የአንዳርጋቸው ጽጌ አፈታት ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ያለኝን እይታ ቀይሮታል። በፊትም የለውጥ ሃይል ቤተመንግስት እንደገባ የሚሰማኝ ስሜት ላይ ተጨማሪ እምነት እንዳሳድር አድርጎኛል። ዶ/ር አብይ በየዕለቱ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የራሳቸው ጥቅምና ጉዳት ቢኖራቸውም በጥቅል ስንመዝናቸው ሰውዬው አንዳች ታሪክ ለመስራት ከልብ ቆርጠው መነሳታቸውን መመስከር ግድ ይላል።

በእርግጥ ለውጥ ገና ነው። ለለውጥ የቆረጠ መሪ በዙፋኑ ላይ መቀመጡን ስድስተኛው የስሜት ህዋሴ አረጋግጦልኛል። ጉዞው ረጅም ነው። የለውጡ ደሴት ሩቅ ነው። ግን ተጀምሯል። 1ሺህ ኪሎሜትር ጉዞ የሚጀመረውም በአንድ እርምጃ ነውና።

በአንድ ቀን ውስጥ የተወሰዱትን እርምጃዎች እንመልከት። የመለስ ራዕይ፡ ሌጋሲ፡ ምናምን የሚባለውን የእነሳሞራን ቅዠት እንዳይሆን ተደርጎ አከርካሪው የተሰበረበት ውሳኔ ነው ከአብይ በኩል የተሰማው። እነአለምሸት ደግፌን ተዋርደውና ማዕረጋቸው ተገፎ እንዲባረሩ ያደረገው መለስ ዜናዊ መሆኑን ላስታወሰ የእነዚህ ወታደራዊ መኮንኖች በክብር ማዕረጋቸው እንዲመለስ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነ ይገባዋል። ሳሞራ የመለስ ዜናዊ ራዕይ አስፈጻሚ ነው። ከትቢያ ተነስቶ ያለዕውቀትና ችሎታው የሀገሪቱ ጦር የበላይ አዛዥ እንዲሆን የተደረገው በአቶ መለስ ዜናዊ ፍጹም እምነት ስለተጣለበት ነው።

ሳሞራ የመለስ ራዕይ ብቻ ሳይሆን የመለስ ሴጣናዊና ጭካኔያዊ እርምጃዎች አስፈጻሚ መሆኑ እርግጥ ነው። መለስ ያለውን የሚያደርግ፡ እንደፈጣሪ ለቃሉ የሚገዛ በዚህም ባህሪው ለስልጣን እንደበቃ ሁሉም ያውቀዋል። የመለስ ራዕይ ተሸካሚ ለመሆኑ ከመለስ ሞት በኋላ ከእነስብሃት ነጋ ጋር የገባበትን ግብግብ በመጥቀስ ማሳየት ይቻላል። ሳሞራን መገላገል፡ የመለስን ራዕይ የመገላገል አንዱ እርምጃ ነው። በምን ይሁን በምን ሳሞራን ከዚያ ቦታ ማንሳት መልዕክቱ ቀላል የሚባል አይደለም። የተንከባለለ ውሳኔ ቢሆንም በዶ/ር አብይ ዘመን ወደ ተግባር መለወጡ በተጀመረው ጉዞ ላይ አንድ ግዙፍ መሰናክል እንደማስወገድ የሚቆጠር ነው።

በእርግጥ ጄነራል ሳዐረ መኮንንም ህወሀት ናቸው። እንደሚባለውም ከሳሞራ ያልተናነሰ ዘረኝነት በደማቸው የተቀበረ ሰው ናቸው። ሆኖም እንደሳሞራ የመለስ አምላኪ እንዳልሆኑ ይነገራላቸዋል። በአባታቸው የአማራ ተወላጅ መሆናቸው በእነመለስ ዘንድ ሙሉ እምነት እንዲያጡ እንዳደረጋቸው የውስጥ መረጃዎች ይፈነጥቃሉ። ለህውሀት ፍጹም ወገንተኝነት ቢኖራቸውም በመለስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የታማኝነትን መስፈርት ያላሟሉ ሆነዋል። እሳቸውን እናውቃለን የሚሉት እንደነዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሰሞኑን ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ እንደተናገሩት ጄነራል ሳዐረ መኮንን የመርህ ሰው መሆናቸውን ይመሰክራሉ። ሳሞራ ዘንድ መርህ የሚባል ቃሉም አይታወቅም። የሳሞራ አለፋና ኦሜጋው መለስ ዜናዊ ነበር። ጄነራል ሰዓረ የአቶ መለስን ቀልብ ያልገዙት አንድም በመርህ ላይ የተመሰረተው አካሄዳቸው መሆኑን የሚያውቋቸው ይናገራሉ። ሆነም ቀረም እሳቸውም የህወሀት ዘረኛ ፖሊሲ አስፈጻሚ ከሆኑት ፊት መሪ ሰዎች የሚመደቡ ናቸው።

ዶ/ር አብይ የጄነራል ሳዐረን ኤታ ማዦር ሹም ቦታ ባይፈልጉት እንኳን መስጠት እንዳለባቸው ወታደራዊ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንደኛው ምክንያታቸው የሲኒየሪቲ ጉዳይ ነው። በወታደዊ የዕዝ ሰንሰለትና አሰራር ከሆነ ቦታው የሚገባው ለጄነራል ሳዐረ መኮንን ነው። ዶ/ር አብይ ይህን ወታደራዊ አካሄድ መጣስ አይችሉም። እንደወታደራዊ ባለሙያዎች አገላለጽ ጄነራል ሳዐረ የትኛውም ዓይነት ሰው ይሁኑ መከላከያ ሰራዊቱ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ወሳኝ ነገር ነው። ዶ/ር አብይ እንደሚናገሩት በመከላከያ ውስጥ ስርነቀል የሆነ ማሻሻያ ካደረጉ ሳዐረም ተቀመጡ፡ ሳሞራም ዳግም ቢመለሱ የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም። ዶ/ር አብይ በሳሞራ ሽኝት ላይ የተናገሩት በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ያሳዩትን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው። መከላከያ ብሄር የለውም፡ ዘር የለውም የሚለው አገላለጽ ዝም ብሎ የሚጣል አይደለም። ትልቅ መልዕክት ያዘለ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ቀጣይ አቅጣጫ ያመለከተ ነው።

መከላከያውን ከዘር ጥብቆ ማላቀቅ መቻል ስር ነቀል ለውጥ ነው። የመለስ ራዕይ አንዱ መገለጫ መከላከያውን በአንድ ብሄር የበላይነት ማዋቀሩ ነው። ዶ/ር አብይ ይሄን ራዕይ ለመደርመስ ማቀዳቸውን በጎን እየነገሩን ነው። የህወሀትን ጄነራሎች ሰብስበው የተናገሩትም መከላከያው የስርዓት ለውጥ የሚሸከም ተቋም መሆን እንደሚገባው ነው። ይህ የህወሀትን አጥር የሚያፈርስ ውሳኔ ነው። በህዝብ ልብ ውስጥ ኖሮ የማያውቀው ህወሀት ዙፋኑን ጠብቆ ያቆየለትን መከላከያ ከእጁ ፈልቅቆ የሚወስድ ሃይል ከደጃፉ የቆመ ይመስላል። በቀላሉ እጅ ባይሰጥም መሆኑ የማይቀር ክስተት ነው።

በእርግጥ ለዶ/ር አብይ በመከላከያው ላይ የሚወስዱት እርምጃ በፈተናዎች የታጠረ ለመሆኑ መገመት የሚከብድ አይደለም። ህወሀት የኢኮኖሚ የበላይነቱን አስጠብቆ ለማቆየት መከላከያውን በጽኑ ይፈልገዋል። የፖለቲካውን ጉልበት እያጣ መሄዱን ተከትሎ በመከላከያው ላይ የመጣበትን አደጋ ለመመከት ምሽግ ቆፍሮ እስከመግባት ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል። የሰሞኑ የእነስዩም መስፍን እንደጀማሪ ጎሬላ ተዋጊ ቡድን ”ዘራፍ፡ እንዋደቃታለን” ዓይነት ሽለላና ቀረርቶ የሚያሳየው ህወሀቶች በመከላከያ ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ መስመር ለማደናቀፍ ምን ያህል ቆርጠው መነሳታቸውን ነው። ጄነራል ሳሞራ የኑስም ወይን ለተሰኘ መጽሄት በሰጡት ቃለመጠይቅ ”መከላከያውን መንካት በእሳት መጫወት” አድርገው አስቀምጠውታል። ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በትግራይ በተካሄደ ሚስጢራዊ ስብሰባ ላይ የተገለጸውም ህወሀት መከላከያውን ላለማስነካት እሰከየት ርቀት እንደሚጓዝ ያመላከተ ነው። አየር ሃይሉንና የመረጃ ክፍሉን ጨምሮ ዋና ዋና የመከላከያ ተቋማትን ወደ ትግራይ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን በመጥቀስ ”የመከላከያው ጉዳይ የህወሀት የህልውና ጉዳይ” ነው እንደሆነ የሚገልጹ ወገኖች አሉ።

በእርግጥ የህዝብ እምቢተኝነት ያመጣው የለውጥ አየር በየትኛውም ምድራዊ ጉልበት የሚቀለበስ አይሆንም። የህወሀቶች ቀረሮቶና ሽለላ መጨረሻው ከአጉል ውደቀት ጋር ከማላተም ውጪ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ዶ/ር አብይ በጥበብና በቆራጥ አካሄድ በጀመሩት የለውጥ ጉዞ ከመግፋት ውጪ አማራጭ የላቸውም። የደህንነት ሚኒስትሩን አሰናብተው ጄነራል አደም ኢብራሂም እንዲይዙት ማድረጋቸው ምን ያህል ይረዳቸዋል የሚለው በቅጡ መፈተሽ አለበት። የጌታቸው አሰፋ ዞር ማለት ቀላል የሚባል አይደለም። ጄነራል አደምን የሚያውቁ ሰዎች በባህሪም በወታደራዊ ብቃትም ቦታው ይበዛባቸዋል ይላሉ። ዶ/ር አብይ እኚህን ሰው ያደረጉት በዘር ኮታ የአማራ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ አይመስለኝም። ደካማ ሰው በወሳኝ ቦታ ማስቀመጥን እንደአንድ በሳል እርምጃ የሚወስዱ ወገኖች አሉ። እንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ ጠንካራ የሆነ ሰው ማስቀመጥ በራሱ የሚያመጣው መዘዝ አለ። ምናልባት ዶ/ር አብይ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ለመለወጥ የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ በተጨማሪ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ደርበው ሊመሩት አስበውም ሊሆን ይችላል። ለቤቱ እንግዳ አለመሆናቸው፡ ውስጡን በሚገባ ስለሚያውቁ ከላይ የሚያስቀምጡት ሰው ምን ዓይነት መሆኑን የሚያውቁት እሳቸው ናቸው።

በአጭሩ በመከላከያውና ደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚታየው የለውጥ አዝማሚያ ወዴት ያመራል የሚለውን አሁን ላይ በእርግጠኝነት መናገር አይቻል ይሆናል። ነገር ግን ለውጥ ለማምጣት የቆረጠ መሪ ፍላጎቱን ነግሮናል። ለዚህም አንዳንድ ምልክቶችን በማሳየት እየተጓዘ ነው። ህወሀቶች ደስተኞች እንዳልሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ የህወሀት አፍቃሪ በማህበራዊ መድረክ ያስተላለፈው መልዕክት እንዲህ ይላል ”መለስ ሆይ የገነባሃት ሀገር እንዲህ ስትፈርስ ተንስተህ ባየሃት”

ኢትዮጵያ እየፈረሰች አይደለም። ምንም እንኳን በዶ/ር አብይ የሚሾፈረው የለውጥ መኪና አቅጣጫው ወደ ምንፈልገው ደሴት የሚወስድ ለመሆኑ በእርግጠኝነት ለመግለጽ ጊዜ ገና ቢሆንም አነሳሱ ተስፋ የሚሰጥ ነው።

 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0