ቅዳሜ፣ ሰኔ ፪ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት

በፖለቲካ ዓለም፤ አዲስ ነገር ሲከሰት፤ በጥርጣሬ ዓይን መመልከቱ የተለመደ ነው። በተለይም የራሳቸው ድርጅት ያላቸው ግለሰቦች፤ ክስተቱን ከግለሰብ ማንነታቸው በተጨማሪ፤ በድርጅታቸው መነፀር ስለሚመለከቱት፤ የመጀመሪያ ግንዛቤያቸው፤ ይህ ክስተት፤ ለኔ እናም ለድርጅቴ፤ ይጠቅመናል? ወይንስ ይጎዳናል? ለዚህስ መልሳችን ምንድን ነው? ከሚል ስለሚነሱ፤ በጎ ፈቃደኝነታቸው ልጓም አለው።

ይህ አመለካከት ደግሞ፤ ሁሉን ነገር ያሸወርረዋል። እውነትና ሐሰት፣ እኛና እነሱ፣ ወዳጅና ጠላት፣ የመሳሰሉ ፅንሰ ሃሳቦችን አዝሎ፤ ጎራ መለያየትን ያስከትላል። ስለዚህ፤ ወደፊት ለመሄድ አስቸጋሪ ጋሬጣ ይሆናል። በኛ ሀገር፤ ባለፉት ስድሳ ዓመታት የተከሰተው፤ ይሄን አባዜ ከማጦዙ በላይ፤ ማዕከል ሆኖ ሁሉን እያሽከረከረ ነው። ምናልባት የፖለቲካ መድረኩ አለመኖሩና ልምዱም ስላልዳበረ፤ በስድሳዎቹ የነበርነው ተማሪዎች ያካሄድናቸው እንቅስቃሴዎች፤ መሠረታቸው ሀገራችን እና የሀገራችንን ታሪክ መነሻ እንዳናደርግ፤ በተወሰን ደረጃም ቢሆን አግዶን ነበር። ያ ደግሞ በተራው፤ ሁሉም እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ የሚል አስከትሏል። ሆነም ቀረም፤ አሁን ያለንበትን ሀቅ ተመርኩዤ፤ አዲስ የተመሠረተውን የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሚመለከት ያለኝ ግንዛቤ የሚከተለው ነው።

የዐማራው መደራጀት ጉዳይ፤ የትናንት ጥያቄ ስለሆነ፤ ከጉንጭ አልፋ ንትርክ ያለፈ፤ ፋይዳ የለውም። ግዴታ ሆኖ ተተግብሯል። በዚህ ላይ መወያየት፤ ለትናንት ዝናብ ዛሬ ቤት መሥራት ነው። እናም አልፈዋለሁ። ይህ፤ ለምን? እንዴት? የት? እና የመሳሰሉትን ሁሉ ይመልሳል።

በባህር ዳር ተሰባስበው የመሠረቱት የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ የዐማራው የፖለቲካ ድርጅት ነው። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ላንሳ። የመጀመሪያው፤ ይህ ድርጅት ፍጹም ነው ወይ? የሚለው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ እያንዳንዱ ዐማራ ይሄን የኔ ብሎ የግድ መውሰድ አለበት ወይ? የሚለው ነው።

ይህ ድርጅት ፍጹም አይደለም። ፍጹም ሆኖ የሚወጣ ድርጅት የለም። ፍጹም የሆነ ድርጅት ሊኖር የሚችለው፤ በአእምሯችን ውስጥ ብቻ ነው። ይህን ድርጅት ያቋቋሙት፤ የዐማራው ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ፣ በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ምሕዳር ሀቅ፣ እና የዐማራው የወደፊት ሕልውና ያንገበገባቸው፤ የተገኘውን ቀዳዳ በመጠቀም፣ የሚችሉትን ሁሉ በማሰባሰብ፤ አለኝታ ለመሆን ርብርባ ያደረጉ ዐማራዎች ናቸው። እናም በከፍተኛ ደረጃ ሊደገፉ ይገባቸዋል። ከዳር ሆኖ፤ እነማን ናቸው? ምን አስበው ነው? ይሄን ማድረግ አለባቸው! ያን ካላደረጉ፤ እንዲያ ናቸው! እና የመሳሰሉት፤ በመግቢያዬ ላይ ስጀምር የዘረዘርኩት አባዜ ነው።

ድርጅቱን ላብጠልጥል ብለው ለተነሱ፤ ድርጅቱ በጎና በጎ ያልሆኑ ጎኖች አሉት። ግለሰቦች ያንን ትንታኔ ሲያደርጉ ግን፤ መገንዘብ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። አማራጩ ምንድን ነው? ያንን ስያቀርቡ፤ እሱ ወይንም እሷ፤ ምን ኃላፊነት ወስደው ነው? የጉዳዩ ባለቤት ሆነው ነው? ወይንስ ተቆርቋሪ ሆነው? ወይንስ ሚናቸው ምንድን ነው? ይሄ ወሳኝ ነው። “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ!” ይባል የለ። እንዲያው “አልኩ!” ለማለት ወይንም “የሚሰማኝን ልዘላብድ!” ከሆነ፤ ያስተዛዝባል። ይህ፤ ብዙ ሕይወት እየጠፋበት ያለ፤ የዛሬ የፖለቲካ ሀቅ ነው። ብዙ ዐማራዎች በመላው ኢትዮጵያ ተገድለዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፣ ታስረዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ተፈናቅለው የትም ተበትነዋል። ይህ የዐማራውን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እውነታ ነው። ይህ የጉንጭ አልፋ ንትርክ ማድረጊያ ጉዳይ አይደለም። ወቅቱ መረባረቢያና የምንችለውን ማድረጊያ ነው።

ይህን ድርጅት የበለጠ ለማስተካከል፤ አብሮ የልፋቱና የሂደቱ አካል መሆንን ይጠይቃል።

ሁለተኛው፤ እያንዳንዳችን ዐማራዎች፤ ይሄን ድርጅት የኔ ነው ብለን የግድ መውሰድ አለብን ወይ? የሚለው ነው። መልሱ አይደለም ነው። እያንዳንዳችን ዐማራዎች፤ እኩል በዐማራነታችን አምነን፣ ዐማራው አሁን እየተፈጸመበት ያለውን በደል ተረድተን፣ ይሄን ጉዳይ የኔ ነው ብለን፣ ለዚህ የሚያስፈልገውን ላድርግ! ብሎለን አልተነሳንም። በግል ብልፅግናችን ያተኮርን አለን። ከዐማራው ጠላትም አብረው የተሰለፉ አሉ። የለም ዐማራው ለብቻ መደራጀት የለበትም! ያሉም አሉ። ዐማራው ጥሩ እየኖረ ነው! ብለው የተደሰቱም አሉ። እኒህ ሁሉ አዲሱን የዐማራ ድርጅት፤ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄን፤ የኔ ብለው ይቀበሉ! የሚል ብዥታ የለኝም።

ነገር ግን፤ ዐማራ ነን። አሁን ዐማራው እየደረሰበት ያለው በደል ተገቢ አይደለም። ዐማራው አደጋ ላይ ነው። እኛ የዐማራነት ኃላፊነት አለብን! ያልንና እስካሁንም ለዚህ ስንታገል የነበርን ሁሉ፤ ይህን ድርጅት የኔ ብለን መውሰድ አለብን። ይህ፤ ያላግባብ በዐማራው ሕልውና ላይ ለመጣ የፖለቲካ ሂደት የተሠጠ መልስ ስለሆነ፤ ያላማራጭ የሁላችን መሆን አለበት። ይህ የርዕዩተ ዓለም ስብስብ አይደለም። ከስሙ እንደምንረዳው፤ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። ለዐማራው፤ በዐማራነቱ ለሚደርስበት በደል፤ ጠበቃ ለመሆን የተመሠረተ ነው። እናም የማንኛችንም ዐማራዎች፤ አሁን ሀገራችን ባለችበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ዐማራውን ተሳትፎ እንዲያደርግ የቀረበልን አንዱ ብቸኛ ድርጅት ነው። እናም ይህ ማለት፤ ዐማራ የሆን ሁሉ፤ የኔ ልንለው የሚገባና አስፈላጊውን እርዳታ ልናደርግለት የሚጠበቅብን ነው።

በአንጻሩ ካሁን በኋላ፤ በኔ እምነት፤ በሀገር ቤትም ሆነ በውጪ ሀገር፤ ሌላ የዐማራ የፖለቲካ ድርጅት ሊኖር አይገባም። ሁለትና ሶስት ወይንም ከዚያ በላይ፤ በፖለቲካ ድርጅትነትም ሆነ በሲቪክ ድርጅትነት፤ ከዚህ ድርጅት አንጻራዊ ሆኖ መቆም፤ አፍራሽ ነው። አዎ! ከጎኑ የሚቆሙ የተለያዩ ማህበራት ሊኖሩ ይገባቸዋል። አማራጭ ግን አይሆኑም። ሊጎድለው ይችላል የምንል ካለን፤ ይህን ድርጅት መቀላቀልና ማስተካከል ግዴታችን ነው። ከውጪ ሆነን ግን፤ ይሄን ያድርግ ወይናም ያንን አያድርግ ልንል የሞራል ብቃቱ የለንም። በተለይም አመራር የተቀመጡትን ይሄ ከኔ ጎጥ ነው፣ ወይንም ይሄ ያንን ዓይነት አመለካከት አለው፣ ወይንም ይሄ ታሪኩ እንዲህ ነው፣ ወይንም ሌላ የመተናኮያ ምክንያት መደርደሩ፤ የዐማራው ትግል ወደፊት እንዳይሄድ መሰናክል መሆን ነው።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *