1. አማራ መደራጀት ለምን አስፈለገው? ምክንያቱስ?

ላለፉት 27 ዓመታት የህወሃት “የጎሣ ፌደራሊዝም” ንድፍና ስርዐትና “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” ርዕዮት አማራውን እንደ ህዝብ “ጨቋኝና በዳይ” በማድረግ ስሎና በራሱና ከሌሎች ጎሣ አባላት በቀጠራቸውና ባሰማራቸው ምንደኞች አማካይነት አሃዙን በቁጥር ማስቀመጥ የማይቻል ዕልቂት ፈፅሟል። ለምሣሌ ህወሃት ከኦነግና ሌሎች ጋር የፀረ-አማራ ግንባር ፈጥሮ በአርባጉጉ፣ በበደኖ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በቤኒሻንገል፣ ኤሊባቡር ወ.ዘ.ተ. አማሮች ገደል እየተጨመሩ እንዲሞቱና እንዲገደሉ ተደርጓል። በኢሊባቡር፣ በጉራፈርዳና ቤኒሻንጉል ይህን የዘር ማፅዳትና ጭፍጨፋ (Ethnic Cleansing & Genocide) በአማራው ላይ ፈፅሟል። አማራውን ከኢትዮጵያዊ ጥቅሙ በመነጠል ተበድሏል። አማራው የመቋቋም እርምጃ ተደራጅቶ እንዳይወስድ ትግሬዎች በሚመሩት “ብአዴን” ጫናና እቀባ እየተደረገበት ቆይቷል።

አማራ ኢትዮጵያዊነቱን ጥሎ፤ ወይ በዘሩ አሊያም በኢትዮጵያዊነት እንዳይደራጅና መብቱን እንዳያስከብር ተገዶ በወያኔና ወያኔን ብቻ እንዲያገለግል ታስቦ በደደቢት በረሃ በተነደፈውና በጠላትነት በፈረጀው “የጎሣ ፌደራሊዝም” ስርዐት ስር በባርነት እንዲኖር ተፈርዶበትና “በእብዮታዊ ዴሞክራሲ” መፅሃፈ-ዲያቢሎስ ርዕዮት ማለትም “በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት” እንዲደራጅ ለዚህም የህወሃት ኮንዶም “ከኢህዲን” ወደ “ብአዴን” ስሙ የተቀየረው ድርጅት አማራውን በምስለኔነት እንዲያደራጅ ተወጥኖ የቆየ መሆኑን ለሁሉም ግልፅ ጉዳይ ነው። የዚህም ህወሃታዊ ሴራ ግብ ኢትዮጵያዊነትን ከአማራው ውስጥ በማውጣት የቀስ በቀስ ኢትዮጵያን የማዳከምና የማጥፋት ውጥን የያዘም ነው። አማራንና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው። ልክ ቱርኮች የአርሜንያን ዘር ለማጥፋት የወጠኑት እቅድና ቀጥለውም የተገበሩት የእልቂት ንድፍ አካል ነው። ይህ ወያኔያዊው ፅንፈኛ ዕይታ ነው።

የአማራ ትግል ከማንነት ጋር የተያያዘ በመጥፋትና ባለመጥፋት ወይም በማንነቱ ላይ የተቃጣና በመቃጣት ላይ ያለን የህልውና ጥቃት (existential threat) ለመከላከልና ለመመከት የሚደረግ የህልውና ትግል ነው። አማራነትና አማራዊ አደረጃጀት ግብ እራስን መከላከል (self-defence) እንጂ በህወሃትና ኦነግ የፈጠራ ትርክት “የበላይነቱን” ዳግም ለመጫን የታለመ አይደለም። የበላይም የበታችም አልነበረም። ጣሊያን ልክ እንደ ህወሃት “አማራንና ሃይማኖቱን ማጥፋት” ተብሎም እየተዘመተበት ነው። ልብ ማለት ያለብንም ይህን የጣሊያን “አማራነትን የማጥፋት” ዕቅድ አፄ ሚኒሊክ ያመከኑት ኢትዮጵያዊነታቸውን ኮንነውና አማራነትን ብቻ ይዘውም አልነበረም። አማራነታቸውን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጋብተው የድላቸውም ሚስጥር በአማራነትና በኢትዮጵያዊነት መሃል ያለውን መስተጋብር ያጠነከሩበት ኬሚስትሪ ነው። አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት፤ ኢትዮጵያዊነትን ከአማራ ውስጥ በቀዶ ጥገና ጥበብ ማውጣት አይቻልም። የአማራ ትግል እራስን የመከላከል ፍትሃዊና ህልውናን የማቆየት ተጋድሎ ነው። ኢትዮጵያን ለማኖር አማራ እራሱን ማትረፍ አለበት። እራሱንም ባተረፈ ቁጥር ኢትዮጵያም ትታደጋለች።

2. ምን አይነት አደረጃጀት ለአማራ?

የአማራ አደረጃጀት የሲቪክ ብሔረተኝነት የሚከተል መሆን አለበት። ከጎሣ ብሄረተኝነት የራቀ አደረጃጀት መሆኑንና ለዚህም የጠራና ግልፅ መስመር ማስመሩ እጅጉን ይበጃል። ይህ ‘የሲቪክ ብሔረተኝነት’ አደረጃጀት ልዩ ጥቅምን የምናስተውለው የሚከተለውን የካናዳዊው ፀሃፊና ፖለቲከኛ ሚካኤል ግራንት ኢግናቲፍ በሲቪክ ብሔረተኝነት (Civic Nationalism) እና በጎሣ ብሔረተኝነት የሣለውን ንፅፅር ስንቃኝም ነው።

ይህንን ሚካኤል ግራንት ኢግናቲፍ በዚህ መልኩ ያቀርበዋል “የሲቪክ ብሔረተኝነት (Civic Nationalism) ሐገርን በጋራ ዜግነት (common citizenship) ይገልፀዋል:: የሲቪክ ሐገር (Civic Nation) ማንኛውንም ጎሣ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታና ቀለም ያላቸውን ሁሉ የሚጠቀልልና በመርሆ ደረጃም እኩል የሆኑ፣ መብታቸውን ያወቁና በአርበኝነት ስሜት ፖለቲካዊ ልማድና እሴትን የሚጋራ ማህበረሰብ ነው:: የሲቪክ ሐገር ነፃነትንና የራስ አስተዳደርን ለዜጎች ስለሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ነው:: የአሜሪካንና የፈረንሣይን ሪፑብሊኮች የፈጠረውም ይኸው የሲቪክ (civic) ብሔረተኝነት ነው::
የጎሣ ብሄረተኝነት (Ethnic Nationalism) ሐገርን በጥቅሉ በጎሣ ወይም በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በልማድና ወግ ይገልፀዋል:: በጎሣ ብሔረተኞች እምነት ሐገርን የፈጠረው መንግስት ሣይሆን መንግስትን የፈጠረው ሐገር ነው (It is not the state that creates the nation but the nation that creates the state):: በተጨማሪም የጎሣ ብሄረተኞቹ “ህዝብን በአንድ ላይ አሰባስቦ የሚይዘው ህዝብ በጋራ የሚቋደሰው የፓለቲካ መብት ሳይሆን የጎሣ ባህሪያት ናቸው (The glue that holds people together is not shared political rights but pre-existing ethnic characteristics)” ይላሉ::

ሚካኤል ግራንት ኢግናቲፍ በመቀጠልም “የሲቪክ ብሔረተኝነት (Civic Nationalism)’ እንደ ‘ጎሣ ብሔረተኝነት (Ethnic Nationalism)’ ከእውነት ያልራቀና የሐገራዊ ማንነትና ምንነት መገለጫ ነው:: የጎሣ ብሄረተኝነት ወይም ማንነት በሌሎች ጎሣዎች ላይ ለመነሳት ይጥቀም እንደሁ እንጂ በራሱ በጎሣው ውስጥ ለሚነሱ ወይም ላሉ የመደብ፣ የፃታና የመዋዕለ ንዋይ ክፍፍል ችግርን ለመፍታት አይችልም:: በአንፃሩ የሲቪክ ብሄረተኝነት (Civic Nationalism) ልዩነቶችን ለመዳኘት የሚያስችል የህግ መዋቅር፣ የፖለቲካ ተሳትፎና የህግ አመንጭነት ዕድልን ያጎናፅፋል” ይለናል::

3. የአማራ አደረጃጀትና ኢትዮጵያዊነት

አማራ ያለው ብቸኛ ምርጫና መፍትሄው መጀመሪያ ጥቃትን ለመመከት በአማራነት ተደራጅቶ እራስን በማስከበር በመቀጠልም የኢትዮጵያን ትንሣኤ መታደግ ነው። አማራ የጠላቶቹን ጥቃት ከመከተ፤ ምከታው በራሱ ኢትዮጵያን ይታደጋል። አማራና ኢትዮጵያዊነት ይመጋገባሉ እንጂ አይጣረሱም። የአማራ ሲቪክ ብሔረተኝነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቹ ተበታትነው የሚኖሩባትን ‘ኢትዮጵያን አላውቅም’፤ ‘ጉዳይሽ ጉዳዬ አይደለም’ ካለ የሚክደው ኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን እራሱንና እነዚህን ወገኖቹንም ነው። ኢትዮጵያን የመካድ አባዜም ህወሃታዊ ነው። ከዚህ የጥፋት መንገደኛም ጋር የአላማ አንድነት መፍጠር ነው።

እደግመዋለሁ። አማራነት ኢትዮጵያዊነት፤ ኢትዮጵያዊነትም አማራነት ነው። ኢትዮጵያዊነትን መካድ አማራን መካድ ነው። ለኢትዮጵያዊነት ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሠከሱትንና ህይወታቸውን ገብረው በነፃነት ያኖሩንን ጀግና አብቶቻችንንና አያቶቻችንን መካድ ነው። በኢትዮጵያዊነት ተሰልፈው ነፃ ሃገር ያቆዩንን አርበኞች እጀ ሠባራ ማድረግ ነው።

የአማራ እራስን የመከላከል ጉዞ ግቡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሆነ አማራ እራሱን ያፈርሳል (self-distructive move or suicidal)። በኢትዮጵያዊ ማንነትና በአማራ ምንነት መካከል ሚዛን (delicate balance) የመጠበቅ ግዴታም የአማራው ነው። አማራው ይህንን ያውቃል። የአማራ እራስን የመከላከል አደረጃጀት አማራዊ የፓለቲካ ትርፍ እንጂ አማራዊ ፓለቲካዊ የስልጣን ግብ ሊኖረው አይገባም። የአማራ አደረጃጀት መመሥረት ያለበት በፓለቲካ ወጥነት (political uniformity) ላይ ሣይሆን በአማራዊ አንድነት (unity) ነው።

አማራን ማንነቱን ለመታደግና ጥቃቱን ለመከላከልየሚያደርገውን ፍልሚያ ወይም ወደ ፍልሚያው ያስገቡትና የመሩት “የጎሣ ብሔረተኞች” አይደሉም። በአማራ ላይ የተነጣጠረ የሚደርስበትና እየደረሰበት ያለው ግፍና በደል ነው። እስከሚገባኝ ድረስ አማራ በአማራነት ከነባሩ ሕብረ-ብሄራዊ ቀዘፋው ወርዶ እንዲደራጅ ያስገደደው ፀረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሆነው “የጎሣ ፌደራሊዝም” እና የደቀ መዝሙሮቹ ገደብ አልባ ጥቃት እንጂ “የጠባብ ብሔረተኞች” የገደል-መንገድ አለመሆኑን ማስመር ይገባል። የአማራ የመመከት ገድል ልክ አይሁዶች በነርሱ ላይ የተነጣጠረን የዘር ማፅዳትና ጭፍጨፋ ለመታደግ እንደተደራጁት ነው።

ከሁሉም በላይ አማራ ክልል ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ያላነሰ በተለያዩ ክልሎች በመኖሩ ኢትዮጵያዊነቱን ያጎላል። አማራ ከተለያዩ ነገዶችና ጎሣ አባላትና ማህበረሰብ ጋር በፍቅር፣ በሠላምና በበጎ መስተጋብር ያለ ምንም የተለየ ዘር ተኮር የመንግስት ወይም የጎሣ ጥቃት ጠባቂ ሳያስፈልገው ለዘመናት መኖር የቻለው በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ብቻ ነው። አማራ የሌለበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም። አማራ ከተለያዩ የጎሣ አባላት ጋርም በከፍተኛ ቁጥር በጋብቻ የተጠላለፈ ህዝብ ነው። ሊፈጠር የሚችለውን ህዝባዊና ማህበራዊ ቀውስ ከስሜት በፀዳ መልኩ መቃኘት አለበት።

የአማራ ብሔረተኝነት ኢትዮጵያዊነትን የሚክድ ከሆነ ያነገበው ህወሃታዊ “ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት” ይሆንና የእራሱን ቤት በእራሱ ክብሪት ሊያቃጥል ነው። “ኢትዮጵያን የሚያብጠለጥልና የሚኮንን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባኝም” የሚል “ብሔረተኝነት” አማራዊ የሲቪክ ብሄረተኝነት ሣይሆን የጠባቦች የጎሣ ብሔረተኝነት ይሆንና ውሉን ስቶ ወያኔያዊና ኦነጋዊ ይሆናል። በመላ ሃገሪቱ ተሰራጭተው ከቁጥር በላይ የሚኖሩት አማሮች ላይ እሣት መለኮስ ነው።

የአማራ ብሔረተኛነት ‘የሲቪል ብሄረተኝነት ነው። አላማውና ግቡ የአማራን መብት ማስጠበቅ፣ ጥቃትን መመከትና ለማንነቱ መቆም ነው።

ኢትዮጵያዊነትን የሚክድና የሚያስክድ በአማራ ስም የሚሣለቅ አደረጃጀት ህወሃታዊና ነው!

የአማራ ‘የሲቪክ ብሔረተኝነት’ ጊዜያዊ ግቡ አማራን አደራጅቶና የአማራን ጥቃት ታድጎ በዘለቄታው የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንደ አባቶቹ ማብሠር ነው!!!

ሐይሉ አባይ ተገኝ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *