“Our true nationality is mankind.”H.G.

የታሪክ ፈተናችን እና ያሬዳዊ ትዝታ፤ ከክላሽ እስከ ብዕር! – ሙሉዓለም ገ/መድህን

የለውጥ ውርጃ፣ የዘመናዊነት መጨናገፍ፣ የህዝባዊ ኃይል (ድምጽ) ተጽኖ ፈጣሪነት መኮላሸት፣…ድግግሞሻዊ የታሪክ አዙሪት አምሳያ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በተከታታይ ትውልዶች የደም ጎርፍ እየተንሳፈፈች እዚህ ደርሳለች።

የአገር ግንባታ ሲሚንቶ ውሉ አልይዝ ብሎ ንቃቃት በዝቶበት የታሪክ ፈተናዋን መሻገር የተሳናት ኢትዮጵያ፤ በውስጣዊ ቅራኔ እንደተናጠች፣ ቅራኔዎቹ በተከታታይ ትውልዶች የደም ጎርፍ ከቶም እየተባባሱ  የማህበራዊ ትስስሮሽ ነባር ህሊናዎች እየተናጉ፣ ዘውጋዊ መስመሮች በስታሊናዊ “ዕይታ” የልዩነት መስመሮች እየጎሉ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች እየሻከሩ፣ ደም መቃባቱ እየበዛ በመሄዱ አገሪቱ ወደመፍረስ ጠርዝ በመገፋት ሂደት ላይ ትገኛለች። ከየትኛውም ጊዜ በከፋ መልኩ የርስ በርስ መጠራጠርና አለመተማመን ከፖለቲካ አደባባዩ ተሻግሮ በየግለሰቡ ጓዳ ገብቷል። በደብተራ ፖለቲካ ስትታመስ የኖረች አገር በ“ስብከተ-ተሐድሶ ፖለቲካ” ላዩን ያሳመረች ቢመስልም የታሪክ እባጮች እያመረቀዙ ውስጧ ተቦርቡሯል፤ መቅኗም ፈሷል። ከመጋረጃው ጀርባ ዛሬም በዞረ ድምር ፖለቲካ መታመሳችን  እንደቀጠለ ነው። “ፖለቲካ ሲያረጅ ታሪክ ይሆናል” የሚለው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ትንተና እውነትነት ቢኖረውም፣ ታሪክ የፖለቲካችን አንኳር ጉዳይ ከመሆን አላመለጠም። ፖለቲካችን በአዙሪት ለመታጀቡ አንዱና ዋናው ምክንያት የታሪክ ፈተናችንን ካለማለፋችን ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ያለው ይመስለኛል።

የግማሽ ክፍለ-ዘመን ዋይታዎቻችን የታሪክን ሟችነት ሳይሆን አሁናዊነትን (ዛሬነትን) የሚያስረግጡ ናቸው። የቅርብ ዓመታቱን ግጭቶችና ግዙፍ መፈናቀሎችን ጨምሮ የዘመናት ውስጣዊ ግጭቶቻችን ማጠንጠኛዎች ታሪክን የተንተራሱ ቅራኔዎች መሆናቸውን ስናስተውል ዛሬም የታሪክ ፈተና ላይ እንደተቀረቀርን ለመቅረታችን ህያው ማሳያ ነው።

ስለ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮትና የአብዮቱ መሪ ተዋናይ ስለነበረው ያ-ትውልድ በየፈርጁና የኃይል አሰላለፉ ብዙ ብዙ ተብሏል። ለአብዮቱ መፈጠርና ስለትውልዱ ሥር-ነቀልተኝነት ባህሪያትም እንደፀሐፍቱ የፖለቲካ ዝንባሌና የጀርባ መደብ የዕይታ ልዮነቶች ቢኖሩም፤ስለጉዳዮ ትንታኔዎች ከየአቅጣጫዎች ተሰጥተዋል። ለኢትዮጵያ አብዮት መፈንዳትና ለትውልዱ ሥር-ነቀልተኝነት ባህሪያት ይህን ተከትሎ አገሪቱ ለገባችበት የአዙሪት ፖለቲካ የቅድመ-አብዮት ታሪካችን ጉልህ ድርሻ አለው። በዚህ አግባብ፣ ጠቅለል ባለመልኩ ኢትዮጵያን የታሪክ ፈተና ላይ የጣሏትን ሂደቶች በሁለት መነሻ ምክንያቶች ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል።

አንደኛ፡- የግዛት አንድነት ምስረታውና የአገር ግንባታ ሂደቱ ያስከተላቸው ለውጦችና ቅራኔዎች በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ሳይታረቁና ሂደቶቹ በሚፈለገዉ ፍጥነት ቀጣይነት አለማሳየታቸው፤ በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ የአገሪቱ ሁነኛ መሐንዲስ የሆነው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከነበሳል አመራሩ የአንድ ትውልድ (ሃያ አመት) ቆይታ አለማሳየቱ፣ የምኒልክን የአልጋ ቁራኛ መሆን ተከትሎ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አገሪቱ በሦስት ማዕዘን ፖለቲካ መታመሷ (ንግሥት ጣይቱ Vs ራስ ሚካኤል Vs ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በየራሳቸው ቡድን ፍትጊያ ውስጥ መግባታቸውን ያስታውሷል) ይሄው ትርምስ የአገር ግንባታና ማዘመን ሂደቱ ላይ ቀጣይ ተጽዕኖ ማሳደሩ፤ ይህን ተከትሎ የልጅ እያሱ ዘመነ-መንግሥት፣ በእንቆቅልሽ የተሞላ መሆኑ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለኝታን ለማጠናከር የሞከረበት አካሄድ፣ በተለይም የኢትዮጵያን የዳር አካባቢዎች በማህበራዊ ግንኙነት ወደመሀል አገር ለመቀላቀል የተጓዘበት መንገድ በውስጠ ተቃርኖ ቀጣይነት ማጣቱ፤

ቀጥሎም ዘውዲቱን ንግሥተ ነገሥት፣ ተፈሪን አልጋ ወራሽ ያደረገው የፖለቲካ ለውጥ ትኩረቱ የግዛት አንድነት ምስረታውና የአገር ግንባታ ሂደቱ ያስከተላቸውን ለውጦችና ቅራኔዎች በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች የሚያስታርቅ ሳይሆን የተፈሪን ፍጹማዊ የሥልጣን ጎዳና የሚጠርግ ሆኖ መገኘቱ ከአርባ ዓመት በኃላ ለመጣው ያ-ትውልድ ታሪክን እያጣቀሰ፣ የማህበረ-ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መሪ አጀንዳው አድርጎ ዘውዳዊ ሥርዓቱን እንዲንጠው ገፊ ምክንያት ሆኖታል።

ሁለተኛ፡- ከአገር ግንባታ ሂደቶች ጋር ተጣምሮ አትዮጵያን የማዘመኑ ሂደት በተለይም በትምህርቱ መስክ ነባሩን በማበስበስ እንጅ አዲሱን ከነባሩ (አገር በቀሉ) ጋር በማስማማት ማለምለም አለመቻሉ፤ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር መታረቅ የማይችል ሥር-ነቀልተኛ (ያ) ትውልድ እንዲፈጠር በር ከፍቷል። በዚህ ረገድ በተለየ መልኩ በድህረ-ጣሊያን ወረራ በስፋት ወደአገር ውስጥ ያስገባነው የባህር ማዶ ሥርዕተ-ትምህርት (Imported Curriculum) ትውልዳዊ ግጭቱን አስከፊ አድርጎታል። በርስ በርስ ጦርነትና የውስጥ ሽኩቻ የታሪክ ፈተናዋን መሻገር አቅቷት ያልተሟላችው (ተሰርታ ያላለቀች) አገር፤ በትምህርት ሥም ዘመናዊነትን ከነአሰስ ገሰሱ መቀበል ስትጀምር፣ የባህል መነጠሉና ከነባራዊው አውድ የማፈንገጡ ነገር እየበዛ፣ ከአዳሽ ምሁርነት ይልቅ ለሥር-ነቀልተኝነት አንገቱን የሚሰጥ ትውልድ ወደፊት መስመር ወጣ።

የሥር-ነቀልተኝነት ንቅናቄው ባለቤትና ተዋናይ መሠረቱ በጣም የጠበበ ቢሆንም የአገሪቱን ተሰርታ አለማለቅና የቅራኔዎችን አለመለዘብ ተከትሎ ንቃቃቱ በማየሉ መሠረተ ጠባቡ የትውልዱ ተዋናይ ራሱን ለእንግዳ ብሔራዊ ግብ እንዲያጭ የልብ ልብ ተሰማው። “መሬት ላራሹ”፣ “የኃይማኖት ነፃነት”፣ “የቋንቋና የባህል እኩልነት”፣ … ወዘተ ህዝባዊ ጥያቄዎች አገሪቱንም ሆነ ያን ዘመን የሚመጥኑ አጀንዳዎች ነበሩ። ችግሩ የነበረው፣ በደፋር እርግጠኝነት የሚታበየው ያ-ትውልድ ቆዳውን ዘልቆ ባልገባው በጥራዝ ነጠቅ ማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም  እየተመራ፣ ያለበትን ህብረተሰብ ከምዕራቡ ጋር እያነፃፀረ መብከንከኑና በችኩል ግንፍልተኝነት ባህሪው ያልተሟላ ቢሆንም መጠገን ይችል የነበረውን የአገሪቱን የተዋረሰ ማህበራዊ ህሊና ማናጋቱና ቅጥ ያጣ ሥር-ነቀላዊነቱ ላይ ነው። ማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮት የአስተሳሰብ ዘይቤ መሆኑ ቀርቶ የእምነት ያህል የአስተሳሰብ ልዕልና በያዘበት በዚያ ዘመን፣ መፈክር የንድፈ ሐሳብ ቦታን ከመያዙም ባለፈ የትውልዱ ፉክክር ከግራም በላይ የበለጠ ግራ ለመሆን እንደነበር የትውልዱ የታሪክ ድርሳናት ህያው ማስረጃዎች ናቸው። ዛሬም ድረስ ያለንበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ ቅርጽ የሰጠውና በተቃርኖ የተሞላውን አብዮት ያዋለደው ያ-ትውልድ የታሪክ ፈተናችን ውጤት አልነበረም ማለት ይቻል ይሆን?!

የታሪክ ፈተናችን ውጤት የሆነው አብዮት ከሰጠን ነገር በላይ ያጎደለብን ነገር በዛ ለማለት ባልደፍርም የድህረ-አብዮት ፖለቲካዊ ተላምዷችን ግን በደም ግብር የታጀበ እንዲሆን አድርጎታል። የነገሥታቱ “መለኮታዊ” ሥልጣን ያበቃበት፣ ዘመናዊና ምድራዊ ፖለቲካ የተጀመረበት አግባብ መጠፋፋትን መታያው በማድረጉ ዛሬም ድረስ የፖለቲካ ትርጉሙ “ለሥልጣን ደም መፋሰስ” በሚል የትርጉም ማዕቀፍ እንዲጠቃለለል ግድ ያለው ይመስላል።

ከዚህ በላይ በወፍ በረር ቅኝት ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው ነጥቦች በቀጣይ ለምዳስሰው መጽሐፍ ሁነኛ መንደርደሪያ ይሆናል በሚል እምነት ነው። መጠፋፋትን ባህሉ ካደረገው ያ-ትውልድ የተገኘው (ጋሽ) ያሬድ ጥበቡ (ጀቤሳ) “ወጥቼ አልወጣሁም” የሚል ርዕስ በሰጠው መጽሐፍ፤ እነሆ “የሩብ ክፍለ ዘመን ዋይታዎች” ቢለንም፤ ለእኔ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከክላሽ እስከ ብዕር ድረስ ያሳለፈውን፣ የሆነውንና የኖረውን ሙሉ ትዝታውን የሳለልን ሥራው በመሆኑ ለመጽሐፍ ዳሰሳየ “ያሬዳዊ ትዝታ፤ ከክላሽ እስከ ብዕር” የሚል ርዕስ ሰጥቼዋለሁ። ያሬድም ሆነ (ያ) ትውልዱ የታሪካችን ፈተና ውጤት ናቸው። በተጓዙበት የትግል መስመር ሁሉ ሥር-ነቀላዊ ረብሸኝነት ባህሪ-ድርጊት ከመፍጠራቸው ውጭ የአገሪቱ የታሪክ አቅጣጫ በዚህ መልክ እንዲሆን የመጀመሪያ መዛነፍ (ከአገር ግንባታው ጋር በተያያዘ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አስታራቂ ፖሊሲዎች በሚፈለገው መልኩ ገቢር አለመሆን) ታይቶበታልና ክስተቱ ከሰብዓዊ ፍቃድና አድራጎት ብቻ ሳይሆን በከፊል መዋቅራዊ ጉዳይም አለበት ባይ ነኝ እያልኩ ወደ ያሬዳዊ ትዝታ ልሻገር።

የመጽሐፉ ይዘትና አቀራረብ

መጽሐፉ፣ በይዘት ደረጃ ጸሐፊው ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ  የነበረውን የትግል ተሳትፎና የድህረ-ደርግ ፖለቲካዊ ለውጦችንና እንቅስቃሴዎችን መነሻ ባደረጉ ጉዳዩች ላይ በተለያየ አቀራረብ ትንታኔዎችንና የግል ምልከታዎቹን በመጽሐፍ ደረጃ አሰናስሎ ያቀረበበት ሥራ ነው። በሦስት ክፍልና በሦስት አባሪ ጽሑፎች የተቀነበበው ይሄው መጽሃፍ፤ በክፍል አንድ፣ አስራ ሁለት ፖለቲካዊ መጣጥፎች ደርዝ ባለው ትንታኔዊ አቀራረብ ተሰንደዋል። የፖለቲካዊ መጣጥፎች አሰዳደር (አቀማመጥ) የድህረ-ደርግን ፖለቲካዊ ለውጦችና እንቅስቃሴዎች ተከትሎ ጽሁፎቹ እንደተፃፉበት የጊዜ ቅደም ተከተል እንዲቀመጡ ተደርጓል። ጸሐፊው በግሩም ትንታኔ ከታጀበው “ከደደቢት በረሃ እስከ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት” የሚል ርዕስ ከሰጠው ቀዳሚው የፖለቲካ መጣጥፍ እስከ “ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት፤ በአይኔ ካየሁትና ከታዘብኩት” እስከሚለው ፖለቲካዊ መጣጥፍ ድረስ ባካተታቸው ጽሁፎች፣ በምልሰት ወደተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ወደትግራይ አሲምባ፣ ወደጎንደር ወልቃይት ጠገዴ፣ ከዚያም መልሶ ወደቆላ ተምቤን ተክራርዋ፣ ኤርትራ፣ መልሶ መላልሶ ስለመሐል አገር ፖለቲካ፣ አሻግሮ ሱዳንና ግብጽ እንዲሁም የሰሜን አሜሪካ የፈላሻ (ዲያስፖራ) ፖለቲካን እንደየዘመኑ ትኩሳትን ፖለቲካዊ አውድ ከክላሽ እስከ ብዕር ድረስ ያለፈበትን ያሬዳዊ ትዝታውን አጋርቶናል።

ክፍል ሁለት ላይ ጸሐፊው ባሳለፍነው ሩብ ክፍል ዘመን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከነፃው ፕሬስ ውጤቶች ጋር ያደረጋቸውን ቃለ-ምልልሶች፣ ከክፍል አንድ ፖለቲካዊ መጣጥፎች ጋር እንዲመጋገቡ በሚያስችል አቀራረብ የተመረጡ ቃለ-ምልልሶች ተካተውበታል። እዚህኛው ክፍል ላይ፣ በጋዜጠኞች የጥያቄ ፍላጎትና የቃለ-መጠይቅ ቦታ (space) የተቀነበቡ ምላሾች የመጽሐፉ አካል መሆናቸው የ“እንዴትነት” ጥያቄ ቢያስነሳም ቅሉ፣ የጸሐፊውን የአርባ ዓመት የፖለቲካ ተሳትፎ (ከክላሽ እስከ ብዕር) በያሬዳዊ ትዝታ አንባቢ የሚረዳበትን ዕድል አቀራረቡ ፈጥሯል። በተለይም ኢህዴን/ብአዴን ከምስረታው ጀምሮ ከህወሓት ጋር የነበረውን የድርጅታዊ ነፃነት መተጋገልና እጦት፣ ስለጸሐፊው የበረሃ የኢህዴን ጓዶች (ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሠ ጥንቅሹ፣…) ተለዋዋጭ የፖለቲካ ስብዕና “ከፈረሱ አፍ” ለመረዳት ጠቃሚ መረጃዎች ተካተውበታል።

በሦስተኛው የመጽሐፉ ክፍል፤ በታሪክ፣ በታሪካዊ ልቦለድና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ አምስት መጽሐፍት ላይ ጸሐፊው በተለያየ ጊዜ ያደረጋቸውን የመጽሐፍት ዳሰሳዎች አካቷቸዋል። ጸሐፊው በተለያዩ ጊዜያት የሰራቸውን የመጽሐፍት ዳሰሳዎች በመጽሐፉ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረጉ “በጉዳዮቹ ላይ ያለውን ግንዛቤና ዕይታዎቹን ለአንባቢያን አጋራ” ካልተባለ በስተቀር የ“ተገቢነት” ጥያቄ ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ ያለ ይመስላል። እዚህ ላይ ጉዳዩን በሁለት አንጓ መመልከት ይቻል ይሆናል።

በአንድ በኩል፣ በኢትዮጵያ የህትመት ልማድ የመጽሐፍ ዳሰሳዎች፣ የመጽሐፍ አካል የመሆናቸው ተሞክሮ እምብዛም ከመሆኑ አኳያ የ‹ተገቢነት› ጥያቄው መነሳቱ ተገቢ ነው ሊባል ይችላል። በሌላኛው ጫፍ ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉት የመጽሐፍ ዳሰሳ የተሰራባቸው መጽሐፍት፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልልቅ የታሪክ ምዕራፍን ያካለሉ ናቸው (የመኢሶኑን አንዳርጋቸው አሰግድ “በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ”፣ የበለሳውን ንቅናቄ ተከትሎ ከኢህአፓ ያፈነገጠውን የኢህዴን/ብአዴኑን በረከት ስምዖን “የሁለት ምርጫዎች ወግ”፣የኢህአፓዋን ቆንጅት ብርሃንን ታሪካዊ የልቦለድ ስራ “ምርኮኛ”፣ የህይወት ተፈራን “ማማ በሰማይ”፣ የክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታን “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” ላይ የመጽሐፍት ዳሰሳው ያተኩራል) አንባቢ ከመጽሐፍት ዳሰሳዎቹ ተነስቶ (መጽሐፍቱን ማንበብ እንደተጠበቀ ሆኖ) የታሪክ አቅጣጫችንን ከአሁናዊ የፖለቲካ ትኩሳታችን ጋር በትይዮ እንዲፈትሽ ወትዋች የሆነ አቀራረብ መኖሩ ዳሰሳዎቹ ‹እንኳንም ተካተቱ› ሳያስብል አይቀርም።

ያሬድ፤ ከኢህአፓ እስከ ኢህዴን

በመጽሐፉ ውስጥ ከኢህአፓ እስከ ኢህዴን ድረስ ያሬድን ፍለጋ በትዝታው ስንሳፈፍ በስፋት ለዛ ባላቸው ቃለ-መጠይቆቹና ከታሪክ ለመማር ከሚያነቃቁ የመጽሐፍ ዳሰሳዎቹ ውስጥ እንጅ በፖለቲካዊ መጣጥፎቹ ከመጠነኛ ምልሰተ ኢህአፓ እና ኢህዴናዊ የትግል ተሳትፎዎቹን ከመጠቃቀስ በመለስ በአመዛኙ በድህረ-ደርግ የለውጥ ሂደቶች የታዩ አገራዊ የፖለቲካ ችግሮችን፣ ያመለጡንን ዕድሎች፣ ቀጣይ የፖለቲካችንን ተግዳሮቶች (ተጠባቂ ክስተቶች) ቅጥ ካጣውና አይን ካወጣው የህወሓት የዘረኝነት ልክፍት ጋር እያጣቀሰ ፖለቲካዊ ትንታኔዎቹን አቅርቦልናል።

የያሬድ “ጣፋጭ የትግል ምዕራፍ” የሚጀምረው በቀዳሚነት በ“ጥናት ክበብ” (“አብዮት” በተሰኘ ፀረ-ዘውድ ህቡዕ ቡድን) ለጥቆ በኢህአፓ የከተማ ትግል ላይ ሲሆን፤ ሰፋ ያለውና የአስር ዓመት የገጠር የትግል ታሪኩ ግን የትውልድ ከተማውን ሸገር ለቆ ከወጣ ከጥር 1969 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ከታሪክ እንደምንረዳው ይህ ወቅት የቀለም ሽብር በግራ ቀኝ ኃይሉ የተፋፋመበት ዘመን ነበር። ያሬድ አዲስ አበባን ለቆ በወጣበት ዘመን መጨረሻ ወራት ደግሞ መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር በመበላት የታሪክ ምዕራፍ ወደመዘጋቱ ተሻግሯል።አገሪቱ በመጠፋፋት ፖለቲካ ትርምስ ላይ ነበረች። በኢህአፓ በኩል በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የፓርቲውን መስመር የሚቃወሙ “አንጀኞች” ቀደም ብለው እንደተነሱ የሚታወስ ነው። ዋነኛ መከራከሪያቸውም “የከተማ የትጥቅ ትግል ማድረግ የለብንም፤ ሁሉንም ኃይላችን ወደገጠር ማዞር አለብን” የሚል ነበር። ይህ በ1969ዓ.ም መግቢያ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የተነሳው ልዩነት በመጠኑም ቢሆን ወደአባላት መስፋፋት ጀምሮ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ፓርቲውም ይህን ልዩነት ያነሱ አባላቱን እያደነ የመፍጀት ውሳኔ ውስጥ ሲገባ የኢህአፓ የመስመር ስህተት በቀጣዩ ጊዜያት ከፖለቲካ ኃይሉ አልፎ ወደ አህአሠ ሊዛመት ችሏል። ወደኢህአሠ የተዛመተው ችግር ከፓርቲው ታክቲክና ስትራቴጅ መዛባት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ያሬድ አሲምባ ከደረሰ ሁለት ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ በሠራዊቱ ውስጥ የእርማት እንቅስቃሴ እንደተጀመረና የሂደቱም ግንባር ቀደም ታሳተፊ እንደነበር ከመጽሐፉ እንረዳለን።

በአመራሩ ክፍፍልና በደርጉ መንግሥታዊ ፍጅት የተነሳ የከተማ የፖለቲካ ሥራውንና ድርጅታዊ ጥንካሬውን እያጣ የሄደው ኢህአፓ፣ የእርማት ንቅናቄው መደምደሚያዎቹን ባማሩ ቃላት ቢጽፋቸውም ወደመሬት ማውረድ ግን ተሳነው።የከተማ-ገጠር ትስስሩና መረጃ ልውውጡ የላላ ሆነ፤ ሠራዊቱንም በቅጡ የሚገነባው አመራር ጠፋ። ይሄኔ ነበር ያሬድ “ታጋዩ በደርግ ጥይት በመውደቅ ከሚያገኘው ድል ይልቅ የትግል ድርጅቱን ለማረቅ የሚከፍለው መስዋዕትነት የበለጠ ክቡር መሆኑን” ለጓዶቹ መቀስቀስ የጀመረው። የያሬድ ተጋፋጭነት ባህሪ በ“ጥናት ክበብ” ጊዜ አዲስ አበባ ላይ “ቀባች” (የቀይ ባንዲራ ቡድን) ያስባለውን ያህል፣ ጎንደር-ጠለምት ላይ “ዳግማይ አንጀኛ” በሚል ያስወጋኛል ሳይል አመራሩን ተጋፈጠው። የድርጅቱ አለመታረም በቀጣይ ጊዜያት “የበለሳውን ንቅናቄ” እንዲቀላቀል ገፊ-ምክንያት የሆነው ይመስላል። ያሬድ “አናርኪስት” ብለው አስፓልት ላይ ሊዘርሩት ከሚሹ “አብዮት ጠባቂዎች” አምልጦ በሚያምነው ግን “ታርመህ አታግለኝ” ባለው ኢህአፓ እጅ ላይ እንዳይወድቅ የቅርብ ጓዶቹ “ሳያጠፉህ ጥፋ” ቢሉትም የያኔው ኮሚሳር መሪ በእጄ አላለም ነበር። የያሬድ ተጋፋጭ ባህሪ ባህር ማዶ ተሻግሮም የለቀቀው አይመስልም። “የቦይ ኮት” ፖለቲካ ቁም ስቅል በሚያሳይበት አገረ-አሜሪካ እየኖረ፣ ኢህአፓን ግልብጥ ሰቅሎ በሂስ ለመግረፍ ፍርሃት የለበትም። በመጽሐፉ ውስጥ “የአመጽን አዙሪት ለመስበር” (79-99) የሚለውን ፖለቲካዊ መጣጥፍ ሳነብ የገባኝ ነገር፣ ያሬድ ‹ለፈላሻ ፖለቲካ ልክ ልኩን ንገረው› ባይ እንደሆነ ነው። ሰሚ ቢገኝ “ስሜታችን ሳይሆን ህሊናችን የገፋንን ማድረግ ተገቢ ነው” ሲል ምክረ-ሃሳቡን ያካፍለናል። በትላንቱና በዛሬው ያሬድ መካከል ያለው ልዩነት የክላሽና የብዕር መሆኑ ነው እንጅ ምክንያታዊነት የሚጎድለው ሆኖ አላገኘሁትም። ኃላፊነት በጎደለው ወሼቤነት ይላጉ የነበሩት የኢህአፓ አመራሮች ዛሬ እንኳ የመቃብራቸው አፋፍ ላይ ሆነው ይህን መሰል ያሬዳዊ አስተያየቶች ለመቀበል በራቸው ዝግ ነው። ንዴትና ቀቢጸ ተስፋ የተቀላቀለበት ጩኸት ሳይሆን ሁሉም የየራሱን ልክፍትና ህመም እንዲሁም የትግል ልምድ ተሞክሮውን ከአሁናዊው ፖለቲካ ጋር አሰናስሎ እንዲህ እንደያሬድ ትዝታውን ለትውልድ ቢያጋራ፤ አንድም የትውልዱ ታሪክ ይደልባል ሌላም ጥፋቱ እንዳይደገም መማሪያ ይሆናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከታሪክ ፈተናችን ለማለፍ ብሎም ከታሪካችን ጋር ለመታረቅ ዕድል ይሰጠናል።

የሆነው ሆኖ አስር ዓመት የዘለቀው የያሬድ የገጠር ላይ የሽምቅ ውጊያ ተሳትፎና የአመራር ሚና፤ በቀዳሚነት በኢህአፓ አባልነት በትግራይ-አሲምባ፣ በጎንደር-ጠለምት፣ ዋልድባ፣ ቆላ ወገራና ወልቃይት ውስጥ ከፖለቲካ ኮሚሳርነት እስከ ህዝብ አደራጅነት ድረስ ባሉ ቦታዎች ሰርቷል። ‹ኢህአፓ/ሠ ከፋሽስቶች ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጡ የሚነሱ ጠላቶችንም እየታገለ ጥራቱን ይጠብቃል› የተባለለት ድርጅት ጊዜው በገፋ ቁጥር ለድርጅታዊ ህመሙ ማስታገሻ መድሃኒት በመጥፋቱ በተለያየ ጊዜ የሰራዊቱ ሴሚናሮች ቢካሄዱም ውይይቶች ሁሉ ፍሬ አልባ ሆነው ቀሩ። ኢህአፓ ከዋና ቤዙ አሲምባ በህወሓት ተገፍቶ ከፊሉ ወደ ኤርትራ፣ ቀሪው ወደጎንደር ክፍለ ሃገር ካፈገፈገ በኋላ በሁለት ዓመት ውስጥ በድርጅቱ ውስጥ ‹ከፍተኛ አለመረጋጋትና የክህደት ሁኔታ› እየበዛ መጣ።በዚህ ጊዜ (1972 ዓ.ም) የጠለምት ሪጅን ሰራዊት ውስጥ ለኢህአፓ አመራር የተቃውሞ ድምጽ በማሰማት ግንባር ቀደም ሚና የነበረው (203) ያሬድ፣ በየሪጅኖች ጊዜያዊ አመራር ለማስመረጥ በተዘጋጀው የልዑክ ቡድን ውስጥ በመካተቱ ከበለሳው ንቅናቄ መሪዎች ከእነ ዳውድ (ጋሻው ከበደ) ጋር ተገናኝቶ ሊወያይ እንደቻለ ይነግረናል። የበለሳው ንቅናቄ መነሻ ልዮነት ‹የኢህአፓ አመራር በፓርቲ አደረጃጀት፣ በሠራዊት ግንባታና በኀብረት ግንባር ምሥረታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ስህተት ፈጽሟል› በሚል ከኢህአፓ ለማፈንገጥ ያኮበኮበ ቡድን ነበር። የበለሳው ንቅናቄ ውርጃ ቢበዛበትም ለኢህዴን መፈጠር የጽንስ ያህል ያገለገለ ቡድን መሆኑ ይታወቃል።

የበለሳው ንቅናቄ አባላት ጠቅልለው ወደትግራይ ሲገቡ ያሬድ በግሉ ከጠለምት ወደትግራይ ተሻግሮ ንቅናቄውን ተቀላቀለ (183፣325) ከዚህ ጊዜ በኋላ ለያሬድ እናት ደርጅቱ ኢህአፓ ትዝታ ሲሆን፤ ኢህዴን ደግሞ ከጓዶቹ ጋር በመሆን ለወራት አምጦ የወለደው ድርጅቱ ሆነ። ከአንድ መቶ አስራ ሁለቱ ታጋዮች በሂደት ሰላሳ ሰባት ብቻ የቀሩት የኢህዴን መስራቾች፤ ለምስረታው ሂደት ቢያንስ ለ10 ሠዓት  በየቀኑ ውይይት እየተካሄደ አምስት ወራትን ፈጅቷል (233) ይህም ሆኖ በአንዳንድ አባላቱ (በከፍተኛ አመራሩ) ላይ ጓዳዊ መተማመን ሊደረስ አልቻለም። ታምራት ላይኔና ታደሠ ካሣ ከመለስ ዜናዊ ጋር በድብቅ የሚገናኙበት የሬዲዮ ኮድ እንደነበራቸው (256) ከዓመታት በኋላ እንደደረሰበት ስናነብ ከዛም አልፎ በህወሓት የግዛት ተስፋፊነት አጀንዳ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት የኢህዴን አመራሮች ወጥ አቋም አለመያዛቸው ድርጅቱን በፖለቲካ ክንፉ በኩል ቁርጠኝነት ይጎድለው ነበር ለማለት ድፈረት ይሰጠናል። የኢህዴን የታጠቀ ሠራዊት ክንፉ አልሞ ተኳሽ እንደነበር የኢህዴን ማህበራዊ መሰረት የነበሩት የጎንደር-አርማጭሆና የአገው ምድር መሬት ህያው ምስክሮች ናቸው። እነአስማረ ኮበሌው፣ አስጨናቂ፣ ኢዮብ፣ ክበበው፣ ኦስማን አሽኔ፣ አስራደ፣ ዘርጋው፣…የእነ ኃየሎምን፣ ቀለበት ታየና አግኣዚን ያህል ስማቸው ስላልተሸጠ እንጅ በፀረ-ደርግ ትግሉ ዋጋ ያለው አበርክቶ የነበራቸው ወታደራዊ መሪዎች ነበሩ። መስዋዕትነታቸውም በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም። ስለእነዚህ የኢህዴን የሠራዊት ክንፍ መሪዎችና ስላልተዘመረላቸው ሌሎች የሠራዊቱ አባለት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ፣ በአንድም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ያሬድ፣ ትዝታውን ሰፋ አድርጎ አጋርቶን ቢሆን መልካም ነበር። ፋይዳው ጀብደኝነት የብቻ መገለጫቸው እንደሆነ አድርገው ለሚያስቡት የህወሓት ሰዎች የመልስ ምት ከመሆኑም ባሻገር ጓዳዊ አደራን ከመወጣት ጋርም የተሳሰረ ነው።

በበዛ ውጣ ውረድ የታጀበው የያሬድ የውስጠ ድርጅታዊ መተጋገል የሰውየውን የማስታወስ ችሎታ ለማድነቅ ግድ በሚል ሁኔታ የጀማሪ ድርጅቱን የፈተና አይነቶችና ወቅቶችን እንዲሁም ወደስደት የተገፋባቸውን ምክንያቶች በትዝብት ያስቃኘናል። “የብአዴን መሪዎች ከህዝብ ጎን ይቆማሉ ማለት ማዘናጋት ነው” በሚል ርዕስ ከአንድ የኢህዴን ነባር ታጋይ ተጽፎ የመጽሐፉ አባሪ የሆነው ጽሁፍ (323) ጨምሮ፣ “የጌታቸው (ያሬድ) ልዩነት” በሚል የተጠቀሱት የልዩነት ነጥቦች (በብሔር ጥያቄ፣ በሶሻል ኢምፔሪያሊዝም ጥያቄዎችና የድርጅቶችን መመዘኛ) በተመለከተ ከህወሓትና ከራሱ ጓዶች የነበረው ልዩነት(208)፣ የኢህዴን ቀጣይ ድርጅታዊ ሚናን በተመለከተ (210)፣ በያሬድና በታምራት ላይኔ መካከል በነበረው የፖለቲካ አቋም ልዮነት በተለይም ታምራት ከድርጅታዊ መርህ ይልቅ የመለስ አድናቂና ተከታይ መሆን (221)፣ በኤርትራ ላይ ያለ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ሳይሆን የማጠቃለል/ማዋሃድ (annexation) መሆኑን የሚገልጽ አቋም በያሬድ በኩል መንጸባረቁ (224)፤ ህወሓት ኢህዴንን ከመደገፍ ይልቅ የመረጃ እገታ በመፈጸም ቁጥጥር ላይ በማዘንበሉ የድርጅታዊ ነፃነት ጥያቄን በማንሳት ለስደት የተዳረገው ያሬድ፤ የአድዋው ጊንጥ መለስ ዜናዊን የፖለቲካ ቁማር መመከቻ ብልሃት አልነበረውም (256)። ያሬድ ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ዓላማ፣ መስዋዕትነት፣ ጓዳዊ ቅንነት፣… ሲል መለስና ጓዶቹ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ወይም “የህወሓት የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ” በሚሉ መንታ የፖለቲካ ፕሮግራሞች እየተመሩ፤ ያሬድ ከገዛ ጓዶቹ ጋር የነበረውን የሃሳብ ልዩነት በሴራ ፖለቲካ ተቃርኖውን በማጦዝ “የከበርቴ መንገደኛ” በሚል ፍረጃ ክላሹን አስጥለው ብዕር አስታጠቁት።

ያሬድ ጥበቡ በአፍላነት ዕድሜው ማርክሳዊ ጥናት ባደረገባቸው የጥናት ህዋሶች ከነበረው ነፃነትና ክርክር አንዲሁም ከተጋፋጭ ባህሪው የተነሳ ችግሮችን አይቶ የማለፍ ባህሪ እንደሌለው በዚህ መጽሐፍ መቅድም ጀምሮ በመስመር መሃል ተረድቻለሁ። ይሄ ተሞክሮ ግን “እኛ ብቻ” ባዩን የትግራይ ጠባብ ብሄርተኝነትን በሚያራምዱት በእነመለስ ዜናዊ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። “ራስን ለዘረኛ ጥሪ ተገዥ ማድረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” የሚለው ያሬድ፣ ከኢህአፓ እስከ ኢህዴን ድረስ የተጓዘበትን አስር ዓመት የገጠር ትግል ከግራ ቀኝ ርዕዮታዊ የንባብ ተሞክሮ ጋር እያዋዛ አቅርቦልናል። የደጃች ውቤ ሰፈሩ ጆሊ፣ ራሱን ወደ አብዮታዊ ታጋይነት ቀይሮ አስር ዓመት ሙሉ ለኢትዮጵያ አብዮት ጥያቄዎች  ምላሽ ከአራት ኃይሎች ጋር ታግሏል። አንደኛ፣ በገሃድ ከምናውቅ ደርግ ጋር ያደረገው ፍልሚያ፤ሁለተኛ ከኢህአፓ አመራሮች ጋር በድርጅቱ ታክቲክና ስትራቴጅያዊ የትግል ስልቶች ዙሪያ ያደረገው የሃሳብ ትግል (ከኢህአፓ ጋር ያደረገው የሃሳብ ትግል በድህረ-ደርግ ጊዜያትም ፓሪስ ላይ ሆነው የጦርነት ነጋሪት ይመቱ የነበሩት እነ እያሱ ዓለማየሁና መርሻ ዮሴፍ ዳግም የትጥቅ ትግል ከማወጃቸው ጋር በተያያዘ የሃሳብ ትግሉ  እንዳልቆመ ልብ ይሏል)፤ በሦስተኛ ደረጃ ከህወሓት ጋር በሁለት ሰይፍ ያደረገው ትግል (ህወሓት ወልቃይትን ሲወር በክላሽ፣ ቀጥሎ ደግሞ ህወሓት የበላይነቱን በኢህዴንና በሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ ለመጫን ሲነሳ በብዕር እንደታገለውና እየታገለው እንዳለ ይሄ መጽሐፍ አስረጅ ምሳሌ ነው)፤ አራተኛው የያሬድ ትግል ከቀድሞ የኢህዴን ጓዶቹ ጋር ከበረሃ እስከ ባህር ማዶ ድረስ የዘለቀ የነቃፊ-ደጋፊ አሰላለፍ ያለው የሃሳብ ትግል ነው።

ሃሳቡን ወደ ኋላ ጥሎ ሳይሆን እንደተሸከመ አትላንቲክን የተሻገረው ያሬድ በሩብ ክፍለ ዘመን ዋይታዎቹ “ወጥቼ አልወጣሁም” ይለናል። “ኢህዴንን የለቀቅኩበት ምክንያት ይህ ነው ብሎ መናገር ያስቸግረኛል። መልቀቄን አላውቅም። ድላቸው ይናፍቀኛል። ነፃነትታቸው ይርበኛል”(234) የሚለን ያሬድ፣ ጓዶቹን  የናፈቃቸውን ያህል እነርሱ መናፈቃቸው ቀርቶ ከትዝታ ማህደራቸው ለመኖሩ ያጠራጥራል። እምነት ማጉደል ይሏል ይህ ነው። በድህረ-ደርግ ጊዜያት ራሳቸውን ወደገዥ መደብነት ለመቀየር ያልተቸገሩት የኢህዴን ሰዎች የያሬድን ናፍቆቱንም ሆነ ትዝታውን ሊመልሱለት ፍቃደኛ አይመስሉም። በግንቦት ወር 1979 ዓ.ም ካርቱም ላይ በያሬድ አገላላጽ “በጣም ከሚያምናቸው” ጓዶቹ ከአዲሱ ለገሰና ከበረከት ስምዖን ጋር ሲለያይ፤ እሱ ስደተኛ እነሱ ባለሥልጣን ሆነው ተለያይተው ለመቅረት ሳይሆን “የወያኔን ጠባብ ብሔርተኝነት ለመዋጋት ቃል ኪዳን ተገባብተን፣ የምስጢር መገናኛ የሬድዮ ኮድ ተለዋውጥን ነበር። በአዲሱ የእጅ ጽሁፍ የተለዋወጥነው የሬድዮ መልዕክት መፍቻ ኮድ ዛሬም ከእኔ ጋር አለ” (143) የሚለን ያሬድ፣ ዛሬ ላይ አዲሱም ሆነ በረከት የሬድዮ መልዕክት መፍቻ ኮዱን ወደ ደለበ የስዊስ ባንክ አካውንት አሳድገውታል። ከአሁናዊ ተግባራቸው አኳያ ካርቱም ላይ የተገባቡትን ቃል ኪዳንም ቢሆን ‹አብዮት እንኳን ቃል-ኪዳንን ልጇንም ትበላለች› ብለው የሚተርቡት ይመስላል። ያሬድ ጋር ያለው የሬድዮ መልዕክት መፍቻ ኮድ የያሬዳዊ ትዝታ አካል ነውና ለብዕር ትግሉ ይሄው በዚህ መጽሐፍ በኩል ጥቅም ላይ ውሏል። ያሬድ በጓዶቹ ላይ ለመጨከን ልቡ አልቆርጥ ብሎ ትዝታው ቢያሸንፈውም ተከታዮ ትውልድ እነርሱ ላይ ሰይፉን ከመምዘዝ ግን የሚያቆመው ኃይል አይኖርም። በመጽሐፉ ውስጥ በየገጹ  የሚታየው የያሬድ ተማጽኖም ይሄ እንዳይመጣ “ወደቀልባችሁ ተመለሱ” የሚል ቢሆንም ሰሚ አላገኘም።

ህወሓት እና መለስ በያሬድ ብዕር!

የኢህአዴግን ነገረ-ፖለቲካ በቅርበት የሚያጠኑ ምሁራን/ፖለቲከኞች ስለድርጅቱ ለመፃፍ በሚያደርጉት ጥረት የድርጅቱ አስኳል ከሆነው ህወሓት ፖለቲካዊ ቁመና ጋር አስተሳስረው ይጀምራሉ። በተመሳሳይ መልኩ በየፈርጁ የቀረቡት የያሬድ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በአመዛኙ ህወሓት ላይ ማተኮራቸው በግል ፍላጎቱ የመነጩ ሳይሆን ከኢህአዴግ ተፈጥሯዊ ባህሪ የመነጨ ሆኖ አናገኘዋለን። ያሬድ ህወሓትንም ሆነ መለስን የተመለከቱ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን ሲሰጥ/ሲጽፍ ለማንበብ የምንገደደው ብርቱ አንባቢ፣ ጥልቅ አሰላሳይና ድንቅ የሥነ-ጽሁፍ ችሎታ ስላለው ብቻ አይደለም። እንደአንጋፋ ፖለቲከኛነቱ ህወሓትንም ሆነ መለስን ከበረሃ ጀምሮ በቅርበት ስለሚያውቃቸው ጭምር ነው። በተግባር የተፈተነ ግንዛቤ ያለው ያሬድ፣ ፖለቲካዊ ትንታኔዎቹ ምልሰት ያላቸው በመሆኑ የፖለቲካውን የከፋ ተለዋዋጭነትና የአመራሮቹን መሰሪ ባህሪ በጊዜ ንጽጽር ለማየት ያስችላል። ትንታኔዎቹ ቅድመና ድህረ-ደርግ የማጣቀሻ (ምልሰት) አቀራረብ ያላቸው በመሆኑ የህወሓትንም ሆነ የመለስን ፖለቲካዊ ስብዕና አበጥሮ ለማስጣት ችሏል። የያሬድ ብዕር የህወሓትን የዘመናት እኩይ ድርጊቶቹን በተመለከተ፤ በተለይም የብሄርተኝነት ቁስል የመንቆር አባዜቸውን (44)፣ ብሄራዊ ቅራኔዎችን በማጎን ለጠባብ ብሄርተኝነቱ መገንቢያ መጠቀማቸውን (45፣55)፣ ቅራኔውን የበየኑበት እምነትና ዴሞክራሲያዊ እኩልነትን ተቀብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ አብሮ መኖር ይቻላል በሚሉበት እምነት መካከል ያልረጋ መንፈስ ይፈታተናቸው (62) እንደነበር፣ ኢህአዴግ የትግራይ ብሔርተኝነት ጥቅምና ፍርሃቶች ማስታገሻ የጎማ ማህተም መሆኑን (73)፣ ከብዙሃኑ ነጥቆ የትግራይ ጥቅም አስጠባቂነቱን (109)፣ ‹የትግራይ ዘመን ዘንድሮ ነው› በሚል ተአብዮ፣ ዛሬ የምናየው የትግራይ ልኂቃን እብለላ-ጥጋብ (255) ምንጩ ከወዴት እንደሆነ፣ትግሬ የሰፈረበት መሬት ሁሉ የትግራይ ነው የሚለው የግዛት ተስፋፊነት ባህሪያቸውን (48፣150፣257) ከአብይ ማሳያዎች ጋር በያሬድ ብዕር ተፍታተው ቀርበዋል።

በተለየ መልኩ ከዛሬ ባለፈ ለመጭው ትውልዶች ተሸጋጋሪ ዕዳ ሆኖ ቀርቦ ያለው የህወሓት የግዛት መስፋፋትና የኢኮኖሚ ነጠቃ ተግባሩ ነው። ይሄ የገደል ላይ ሰርዶ ፍለጋ ሩጫ ህወሓትንም ሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ወዴት እንደሚወስደው ጊዜና ትውልድ መልስ ያላቸው ቢሆንም፣ የያሬድ ብዕር “የለቅሶ አዙሪት ውስጥ ራሳችን እንከታለን። ልናስብበት ይገባል” ይላል። ሰሚ ካለ። ያሬድ ህወሓት ላይ ያቀረባቸው ትንታኔዎች ታሪካዊ ዋጋ ያላቸው ከመሆኑም ባለፈ የድርጅቱን ርዕዮተ ዓለማዊ ልሽቀትና ፖለቲካዊ መበስበስ (110-141) የተነተነበት አቀራረብ ህወሓትንም ሆነ መለስን ድጋሚ እንድናጠናቸው የሚጋብዝ ሆኖ አግንቼዋለሁ። በዚህ ረግድ መጽሐፉ የሚያቀብለን መረጃ መለስ ምን አይነት ፖለቲከኛ እንደነበር በተለየ አረዳድ ለመቃኘት ይጠቅማል። ስለመለስ ዜናዊ የትንኮሳ ባህሪ (73)፣ ፍጹም ብልግና ስለተሞላባቸው ንግግሮቹ (137) እና አጠቃላይ ስለአዕምሮ ሁኔታው አልተረዳነውም እንጅ ሰውየው የ“Obsessive Compulsive Disorder (OCD)” በሽታ እንደነበረበትና በርካታ ምልክቶች እንደታዩበት (138) መጽሃፉ ያብራራል። ያሬድ የበሽታውን መጠሪያ ስም “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሚል ወደ አማርኛ ተርጉሞታል። መጥፎ አስተሳሰብና የብልግና (አስቀያሚ) አነጋገርን ማዘውተር የበሽታው ምልክቶች ናቸው። ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት ያህል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ባለጌና አስቀያሚ ንግግሮች በየመድረኩ መናገር፣ ዘውግን መሰረት ያደረጉና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የሚያዋርዱና ቅስም የሚሰብሩ ስድቦችን ማዘውተር፣ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን በኢ-ሰብዓዊ መንገድ የማስቀጣት ሁኔታ፣ የመለስ ዜናዊ የባህሪ “ትሩፋቶች” ከነበሩት ውስጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ የባህሪ መገለጫዎች በቀጥታ ከ“Obsessive Compulsive Disorder (OCD)” ወይም “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶች ጋር ይገናኛሉ። አንባቢ ለግንዛቤም ሆነ ለትዝብት እንዲረዳው ከላይ የተጠቀሰውን የበሽታ አይነትና ምልክቶቹን በተመለከተ ኢንተርኔት ላይ ቢዳብስ በርካታ መረጃዎችን በብላሽ ያገኛል። መረጃዎቹን ይዞ የመለስን የፓርላማና የጋዜጣዊ መግለጫ ንግግሮቹን በምልሰት ቢቃኝ ሰውየው የበሽታው ተጠቂ እንደነበር ለማመን ይገደዳል። አሟሟቱስ ከጭንቅላት ህመም ጋር በተያያዘ አይደል!?

ያሬድ ይሄኛውን ፖለቲካዊ መጣጥፍ ሲያወዘጋጅ ጊዜው ሐምሌ 1993ዓ.ም ነበር። ያኔም ሆነ እሰከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መለስ ከአንደበቱ ብቻ ሳይሆን ከብዕር ጠብታውም ጋር ስድብ የተዋሀደው ፖለቲከኛ ነበር። የአንጃው አባል የነበሩትን የህወሓት አመራሮችን “በክት”፣ ካድሬዎችን “ዝንብ”፣ ፖሊሶችን “ውሾች” የመንግስት ጋዜጠኞችን “አዝማሪዎች”፣ የግሉን ፕሬስ ጋዜጠኞች “የቁራ ጩኸት የሚጮኹ” ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን “የጠነባ ኋላ ቀር አመለካከት ያላቸው” ኢህአዴግን “ከእንጥሉ የገማ”፣… እያለ ሲሳደብ ኑሯል። እነዚህ የስድብ ቃላት “የቦናፓርቲዝም አደጋ” በሚል በ1993 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ካወጣው 129 ገጾች ካሉት ጽሁፉ ጀምሮ ግብዓተ መሬቱ እስከ ተከወነበት ዓመት ድረስ በፓርቲው ልሳኖች ባወጣቸው ጽሁፎቹ፣ በፓርላማ ንግግሮቹ፣ በጋዜጣዊ መግለጫዎቹ የተናገራቸውና በብዕሩ ጠብታ ከተፃፉት ውስጥ እጅግ ጥቂቶቹን ለማሳያ ያህል የተጠቀሱ ናቸው።

እዚህ ላይ በቅድመ-1993ዓ.ም ከተናገራቸው እነ “ባንዴራ ጨርቅ ነው” ዲያስፖራውን “አልጋ አንጣፊ” ወዘተ የሚሉ ተንኳሽ ንግግሮቹን ሳንጨምር መሆኑ ነው።

መለስ ዜናዊ ላይ “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶችን በማየቱ ስጋት የገባው ያሬድ ሰውየው ባደረበት የአዕምሮ ቀውስ የተነሳ ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳል የሚል ስጋት አለኝ (139) ብሎ ነበር። ያሬድ ይሄን ሲል መለስ ወደ ማይቀርበት ዓለም ለመሄድ  አስራ አንድ ዓመታት ቀርተውት ነበር (ወይ የቁጥር መመሳሰል i) ያሬድ ይሄን ነገር ቀድሞ ከተነበየ በኋላ በዋናነት በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ሰጭነት ድህረ-ምርጫ ዘጠና ሰባት አዲስ አበባ ላይ የነበረውን መንግስታዊ ፍጅት ጨምሮ፤ በጋምቤላ-አኝዋኮች፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ-ኦጋዴን ላይ የደረሰው ዘግናኝ ጨፍጨፋ ሰውየውን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተጠያቂ ሊያደርገው በተገባ ነበር። ምዕራባዊያኑ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚያገኙት ጥቅም ያለ ይመስል “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ተጠቂውን መለስ ዜናዊን ጭፍጨፋ “ጉዳዩ ያሳስበናል” በሚል ተልካሻ የዲፕሎማሲ ቃላት ደጋግመው አለፉት። ሰውየው ከሞት ባያመልጥ እንኳ ከፍትህ አመለጠ።

በጊዜ ሂደት ሁኔታዎች ቢቀያየሩም ህወሓት ከጫካ አስተሳሰቡ እና ከገንጣይ አስገንጣይ ፖለቲካዊ መሻቱ አልወጣም። በመሆኑም ድርጅቱን ደግሞ ደጋግሞ በማጥናት ከአገር በታኝ አውዳሚ ተግባሩ ለማስቆም ርዕዮታዊ ትጥቅ ማሟላት ያስፈልጋል። ስለ ሟቹ መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ስብዕና ድጋሚ ማጥናት አስፈላጊ የሚሆነው ደግሞ ቢጤዎቹ በድርጅቱ የአመራር ቦታ ላይ የተኮለኮሉ በመሆናቸው እና “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶችን ስለሚያሳዮ የበሽታቸው ሁኔታ ወደ መለስ ዜናዊ የበሽታ ደረጃ አድጎ አገሪቱን ከእርሱ በከፋ መልኩ ማጥ ውስጥ እንዳይከቷት ለመመከት እንዲያስችል ስለሚረዳን ነው። ተስፋ መቁረጥ በራሱ የበሽታውን ደረጃ ላለማሳደጉ መረጃው የለንምና ዛሬ ላይ የነጋበት ጅብ ባህሪ እያሳየ ያለውን ህወሓት በጥንቃቄ ማጥናት ያስፈልጋል።

መደምደሚያ

የህወሓትንም ሆነ የኢህዴን/ብአዴንን የትግል ታሪኮች በድርጅት እና በአባላት ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የተፃፉ መጽሐፍትን አንብበናል። በሁለቱም አካላት የተፃፉት መጽሐፍት ከአቅጣጫ በስተቀር በይዘት ደረጃ መመሳሰል ይበዛባቸዋል። የድርጅቶቹን “ከምንም መነሳት”፣ “ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር መከተል”፣ “ጥቂቶች ቆራጦች” ስለመሆናቸው፣ “በሕዝብ ድጋፍ”፣… ድል እንደተቀናጁ በግነታዊ ቃላት ይተርካሉ። ከበረሃ ጀምሮ በድርጅቶቹ ውስጥ በየጊዜው ያጋጠሙ ችግሮችና የተፈቱበት መንገድ በግልጽነት ለመቅረቡ አጠራጣሪ ነው። በስማዊው “የግንባር ቀደም ኃይሎች” ስብስብ “መንግሥት” ከሆኑ በኃላ በሚጽፏቸው ድርሳናትም ቢሆን አምባገነንነታቸውን በውስን ልማት ለመሸፈን እና ችግሮቻቸውን ውጫዊ ለማድረግ ሲፍጨረጨሩ የታዘብንበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ሁለቱን ድርጅቶች አብሮ በመስራት የሚያውቃቸው ያሬድ፣ ከክላሽ እስከ ብዕር ድረስ የተጓዘበትን ያሬዳዊ ትዝታውን ሲያካፍለን፤ በታገለበትና በደረሰበት መጠን ሁለቱም ድርጅቶች በረሃ ላይ ሊቀብሯቸው የሞከሯቸውን እውነቶች ፈልፍሎ አውጥቶ ‹እነሆ› ብሎናል። በግሩም የፖለቲካ ሥነ-ጽሑፍ ችሎታው ተንትኖ ያቀረበልን ፖለቲካዊ መጣጥፎቹ፣ ቃለ-ምልልሶቹና የመጽሐፍት ዳሰሳዎቹ የእርሱን ዘመን ትውልድ ለመረዳትና በሰከነ አዕምሮ ለመገምገም ዕድል ይሰጣሉ። ቅንነቱ ካለ እንዲህ ያሉ ዕድሎች በበረከቱ ቁጥር ከታሪክ ፈተናችን ለማለፍ የሚያስችል ፖለቲካዊ መግባባት መፍጠር ይቻለናል። የያሬድ ጥበቡ መጽሐፍ የፖለቲካ ስሜት ከፍታና ዝቅታ ቢኖረውም፤ ከራስ ታሪክ ጋር ለመታረቅ ያለመ ሆኖ አግንቼዋለሁ። ከራሱ ጋር የታረቀ ከሌላው ጋር ለመታረቅ አይቸግረውም። በዚህ መንገድ ይመስለኛል አገር መገንባት የሚቻለው። “ያራዳ ልጅ ብሔር የለውም” የሚለውን ተወዳጅ አባባሉን የትኛው የመታወቂያ ደብተሩ ላይ አንደሚያሰፍረው ባላውቅም፣ ያሬድ ጥበቡን የሚያህል አንጋፋ ፖለቲከኛ ወደአገሩ ተመልሶ የለውጥ ውርጃ ላስቸገራት አገር ምጧን የሚያቀልላት የፖለቲካ ተንታኝ የሚሆንበትን ጊዜ እየተመኘሁ ላብቃ!!

(ይህ ጽሁፍ በተለይ ለጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ እንደመሆኑ ሲያሰራጩ ይህንን ማስፈንጠሪያ መጠቀም አግባብ ነው)

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0