ግንቦት 30/2010 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ማምሻውን ከወደ ታችኛው ቤተ-መንግሥት የተሰማው ዜና የኢትዮጵያዊያንና የዓለምአቀፉን ሚዲያ ትኩረት የሳበ ነበር።

 ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ (መከላከያ በአዲሱ አወቃቀር በኮሚቴ (ወታደራዊ ካዉንስል) ሊመራ ነው) በሚል ርዕስ ከሦስት ሳምንት በፊት መከላከያ ሠራዊት እንደተቋም በአመራሩ ላይ ብወዛ ሊያደርግ መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ወደአንባቢያን አድርሶ ነበር። በወቅቱ ወደ አንባቢያን ባደረስነው መረጃ ላይ፡-

  • መከላከያ ሠራዊት ሪፎርም ሊያደርግ እንደሆነ፣
  • በአገሪቱ “ሕገ-መንግሥት” ላይ የሌለ ቢሆንም ሦስት ምክትል ኤታማዦሮች መሾማቸውን፣
  • የ“ኤታማዦር ኮሚቴ” በሚል የቡድን አመራር መከላከያ ሠራዊት ሊመራ እንደሆነ፣
  • የመከላከያ ሠራዊት “ወታደራዊ ካውንስል” እንደ አዲስ ሊደራጅ እንደሆነ፣
  • ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቅ/መነሳት በኋላ ባሉ ጥቂት ቀናት ውስጥ ሳሞራ የኑስ በይፋ እንደሚሰናበት፣
  • የኤታማዦር ቦታው ለህወሓት ቃል የተገባለት በመሆኑ፤ የሳሞራን መነሳት ተከትሎ ጄኔራል ሳዕረ መኮንን እንደሚተካው፣…

ወዘተ የመሳሰሉ አንኳር መረጃዎችን ያካተተ ጽሁፍ አስነብበን ነበር።

በዚህ ባወጣነው መረጃ መሠረት መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የአመራር ብወዛው ለሕዝብ ይፋ ሆኗል።ከነዚህ መረጃዎች ጎን ለጎን ለብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከታታዮች ያልተጠበቀ ዜናም ተሰምቷል።ከ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል ጋር ተያይዞ በሻለቃ ጸሐየ የተገደለውን ክንፈ ገ/መድህንን የተካው ጌታቸው አሰፋ እንደመንፈስ ራሱን ጋርዶ ለአስራ ስምንት ዓመታት ሲዘውረው ከነበረው የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተነስቶ በኢህዴን/ብአዴኑ ጀኔራል አደም መሐመድ ተተክቷል። በተጨማሪም ድህረ-ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ በተለያየ ጊዜ “የመከላከያ ሪፎርም አደናቃፊ” በሚል ማዕረጋቸው ተገፎ ከሠራዊቱ የተሰናበቱ ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ እና ሜ/ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ማዕረጋቸው ተመልሶ በክብር በጡረታ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።

የጎልጉል የአዲስ አበባ መዋቅራዊ የመረጃ ምንጮች እነዚህንና ሌሎች ዜናዎችን ተንተርሰው ከህወሓት ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና ጋር አያይዘው የላኩልንን መረጃ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡-

የሳሞራ ስንብት

ወታደራዊ ልብሱም ሆነ በውድ ዋጋ የሚገዛው የሱፍ ልብሱ እያደር የሚሰፋው ሳሞራ የኑስ ለአስራ ስምንት ዓመታት ከቆየበት የመከላከያ ሠራዊት ኤታማዦርነቱ መነሳቱ ተጠባቂ ሲሆን ሰውየው በስኳር በሽታ የሚሰቃይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቢሮ ውስጥ ረዥም ሠዓት መቀመጥ ይቸግረው ነበር። አብዛኛውን ወታደራዊ ውሳኔዎች የሚሰጠው በመኖሪያ ቤቱ እና አዘውትሮ በሚገኝበት “መኮንኖች ክበብ” ውስጥ እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይመሰክራሉ። የሟቹ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ታማኝ ወታደር የነበረው ሳሞራ፣ ከሰውየው ህልፈት በኋላ መከላከያ ውስጥ በነበረው መተጋገል ውስጥ ከጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ከሌ/ጀኔራል አበባው ታደሠ እና ከሌ/ጀኔራል ዮሓንስ ወልደጊዮርጊስ ጋር መቃቃር ውስጥ ገብቶ ነበር።

ከመለስ ህልፈት በኋላም ለጊዜውም ቢሆን አሸናፊ ሆኖ የወጣው ሳሞራ፣ ባላንጣዎቹን ጄኔራል ሳዕረ መኮንን ከሰሜን ዕዝ አንስቶ በቅርበት ለመቆጣጠር እንዲያመቸው ወደ መከላከያ የሥልጠና መምሪያ ኃላፊነት፣ በአፍሪቃ ብቸኛው ወጣት ጄኔራል ይባል የነበረውን የኢህዴን/ብአዴኑን ሌ/ጀኔራል አበባው ታደሠ ከማዕከላዊ ዕዝ ኃላፊነት በማንሳት በጡረታ ሲሸኝ፣ ሌ/ጀኔራል ዮሓንስ ወልደጊዮርጊስን ደግሞ ከምዕራብ ዕዝ ኃላፊነት በማንሳት ወደ መከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን በማዘዋወር ተጽኖ ፈጣሪነቱን አጉልቶ ቆይቷል።

ድህረ-መለስ ህወሓት ውስጥ መተካካቱ ወደመገፋፋት መቀየሩን ተከትሎ አዜብ መስፍን ከፖሊት ቢሮ አባልነት ስተነሳ ወትሮውንም ቢሆን “የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን አመራሮች አጠገባችኋቸው፤ ቀና ብለው ሊያዩን የማይጋባቸው ፈሪዎች እኛን እስከማንጓጠጥ ደረሱ፣…” እያለ ሲዘልፋቸው የነበሩት የህወሓት አመራሮች በሰውየው እብሪት ደስተኞች አልነበሩም። በህወሓት በኩል ከ2008ዓ.ም ህዳር ወር ላይ ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በተፈራረቀ መንገድ የቀጠለውን ህዝባዊ አመጽ ለመግታት በአፈጻጸሙ ላይ ሰፊ ልዩነት ነበረባቸው።

የህወሓት የፖለቲካ ክንፍ ምዕራባዊያን ጌቶቹን እያሰበ በደህንነት መስሪያ ቤቱ አማራጭ መፍትሄ እየተመራ ህዝባዊ ተቃውሞውን የአመጹ መሪና ቀንደኛ ተሳታፊዎች የሚላቸውን በማፈን ለማስቆም ጥረት ሲያደርግ፣ በሳሞራ በኩል “የምዕራብ አገራት ተጽዕኖ ሊበግረን አይገባም” በሚል፣ ህዝባዊ ተቃውሞውን በወታደራዊ ኃይል ካልፈታን የሚል አቋም ነበረው። በተለየ መልኩ ኦሮሚያና አማራ ክልል ላይ በነበረው መንግስታዊ ፍጅት ላይ የሳሞራ ውሳኔዎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። “የቀበርነውን የአማራ ትምክህት ከመለስ ሞት በኋላ ኮትኩታችሁ አሳደጋችሁት፤ ኦነግ በኦህዴድ በኩል መልኩን ቀይሮ ሊበላን ያሰፈሰፈው በህወሓት የፖለቲካ አመራር በኩል የትግል ዓላማ ጽናት ቀጣይነት በማጣቱ ነው” እያለ የሚሳደበው ሳሞራ የኑስ እብሪታዊ ባህሪው ከህወሓት አመራሮች ጋር ልዮነቱን እንያሰፋበት በመሄዱ የፖለቲካ አመራሩ ፊቱን ወደ ጀኔራል ሳዕረ መኮንን ማዞር ጀመረ።

ሳሞራ አጋሬ ይሆናል በሚል ከደቡብ ምስራቅ ዕዝ አመራርነት አንስቶ ወደዘመቻ መምሪያ ኃላፊነት ያመጣው ሌ/ጀኔራል አብርሃ ወ/ማርያም (ኳርተር) እንኳ በሳሞራ ወታደራዊ ውሳኔዎችና የህወሓት የፖለቲካ አመራሮች ጋር የገባው እሰጣ አገባ እንዳላስደሰተው በመግለጽ ውሎውንና አመሻሹን ከእነ ሳዕረ መኮንን ጋር በማድረጉ ሳሞራ ማዕከላዊ ኃይሉ እየተመናመነ ሊሄድ ችሏል። ኃይል አልባው ኃይለማርያም ደሳለኝ በስንብቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ ለበርካታ ወታደራዊ አመራሮች ሹመት እንዲሰጣቸው ሲያደረግ በወቅቱ አራት የሙሉ ጀኔራልነት ማዕረግ ካገኙት መኮንኖች ውስጥ ሁለቱ ሳዕረ መኮንን እና አብርሃ ወ/ማርያም የህወሓት ነባር ታጋዮች ናቸው።

በአገሪቱ ወታደራዊ አደረጃጀት ባልተለመደ መልኩ ሦስት ምክትል ኤታማዦሮች (ሳዕረ መኮንን፣ ብርሐኑ ጁላ፣ አደም መሐመድ) መሾማቸው፣ በግልፍተኛ ባህሪው አስቸጋሪ የሆነውን ሳሞራ የኑስ በ“ቡድን አመራር” ለመግራት ታስቦ ነበር። አሁን ልዩነቱ በመስፋቱና የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለስር-ነቀልተኝነት የቀረበ ሪፎርም በማየሉ የኤታማዦር ቦታው እንደማይነካበት ቃል የተገባለት ህወሓት ሳሞራን ሸኝቶ ቀድሞውንም ቢሆን ለቦታው ተጠባባቂ ሆኖ የተመቻቸውን ሳዕረ መኮንን እንዲተካበት አድርጓል።

ሳሞራ ከአብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ አመራሮች ጋር እንደተቃቃረ እና “ክልስ” እያለ በሚያንጓጥጠው ሰው ተተክቶ መሰናበቱ ሽንፈቱን አክፍቶበታል የሚሉን የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፤ በቀጣይ ጊዜ መኮንኖች ክበብ ውስጥ የጎልፍ ኳሱን እያንከባለለ እንደሚውል ይገመታል። ከወራት በፊት ከሚሚ ስብሓቱ ባለቤት ዘሪሁን ተሾመ ጋር የተገናኘው ሳሞራ የኑስ፣ ዘሪሁን የተሻለ የሥነ-ጽሁፍ ችሎታ ያለው በመሆኑ የህይወት ታሪኩን በመጽሐፍ መልክ እንዲጽፍለት አስፈላጊ መረጃዎችን አቅርቦለታል። ሳሞራ በቀጣይ በሚጻፍለት የህይወት ታሪኩ ውስጥ ምን ያህል ነፍስ እንዳጠፋ፣ ስንት ገንዘብ እንደዘረፈ፣ ዘማዊ ባህሪውንና ፀረ-ኢትዮጵያ መሆኑን እንዲነግረን ባንጠብቅም አዳፋ ማንነቱን የሚተርክበትን መጽሐፍ በትዝብት ለማንበብ ግን ዝግጁ ነን ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ለጎልጉል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከራሱ ኢህአዴግ ሕገመንግሥት ጋር በመጻረር ሳሞራ የመከላከያ አመራር ሆኖ ሳለ ለፓርቲ ያለውን ወገናዊነት የህወሓትን ቆብ በማድረግ ብቻ ሳይሆን በፓርቲው ስብሰባ ላይ በድፍረት ሲገኝ እንደነበር ጎልጉል የዘገበውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

የሳዕረ መኮንን መንገሥ

ከአማራ ወሎየው አባቱ መኮንን ይመር እና ከትግራይ እንደርታዋ እናቱ የተወለደው ሳዕረ መኮንን ነባር የህወሓት ታጋይ ነው። በዕድሜም ሆነ በትግል ተሞክሮው ከሳሞራ የሚበልጥ እንጅ የሚያንስ አይደለም። በባህሪው ተግባቢ መሆኑ ቢነገርለትም ለአብዛኛዎቹ የህወሓት አመራሮች በተፈጥሮ የተጫነባቸው የሚመስለው ስሜታዊነት እና የዝሙት ባህሪ ሰውየውን በእጅጉ ያጠቃው መሆኑን የጎልጉል ወታደራዊ የመረጃ ምንጮቻችን ይጠቁማሉ። ከመለስ ዜናዊ ጋር ብዙም ፍቅር ያልነበረው ሳዕረ መኮንን የትግራይ አክራሪ ብሔርተኝነት ባህሪው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

የአባቱን ቤተሰቦች በጨቋኝነት በይኖ የተነሳው ሳዕረ መኮንን ከሳሞራ የኑስ ጋር የጎሪጥ ሲተያይ የኖረ ቢሆንም የማታ ማታ ዕድል ከርሱ ጋር ሆና የኤታማዦር ሹምነቱን ቦታ ከምንግዜም ባላንጣው ሳሞራ የኑስ ሊረከብ ችሏል። የሳዕረ ወደ ኤታማዦርነት መምጣት በብዙዎቹ የትግራይ አክራሪ ብሔርተኞች የተወደደ እንጅ የተጠላ አካሄድ እንዳልሆ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ይጠቁማሉ።

በሳዕረ መሾም ከህወሓት እስከ አረና፣ ከኣጋዚያን እስከ ትህዴን ድረስ ያሉ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነት ያላቸው አይመስልም። በትግራይ ወጣቶችም ሆነ በባለሃብቶች በኩል ተቀባይነት ያለው ጀኔራል ሳዕረ መኮንን መከላከያ ሠራዊቱን የትግራይ ርስትና ጉልት አድርጎ እንዲያስቀጥልላቸው ፍላጎት አላቸው። ከባድመ ጦርነት እሰከ 2005ዓ.ም ድረስ ረዘም ላለ ጊዜ የሰሜን ዕዝ ኃላፊ ሆኖ የሰራው ሳዕረ መኮንን የወታደራዊ ሳይንስ እውቀት ባይኖረውም ሳሞራ የመራውን ተቋም መምራት አያቅተውም የሚለው አስተያየት የጎላ ቢሆንም ሰውየው ህወሓት ውጥረት ውስጥ በገባበትና መከላከያ ሰራዊቱ ሪፎርም ላይ በሆነበት ጊዜ ወደከፍተኛው ወታደራዊ ሥልጣን መምጣቱ የተጠበቀዉን ያህል ህወሓትንም ሆነ ትግራዋያንን ሊከላከል የሚችል አይመሰልም የሚሉ አስተያየት ሰጭዎችም አልጠፉም።

የብሔር ተዋፅዖን ለማመጣጠን በሚል የብርጋዴል ጄነራልነት ማዕርግ ከታዳጊ ክልሎች ለተገኙ የሠራዊቱ አባላት እስከ መስከረም ወር 2011ዓ.ም ድረስ ባሉ ጊዜያት ውስጥ ሹመት ሊሰጥ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቀደም ሲል የጠቀስነው የምክትል ኤታማዦር ቦታዎች ላይ ምን አይነት መተካካት እንደሚኖር ውሳኔ ያልተሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም ጄኔራል ሳዕረ ዋና ኤታማዦር መሆኑ፣ ጄኔራል አደም መሐመድ የሲቭል መረጃና ደህንነት ኃላፊ መሆኑ፣ በብቸኝነት ምክትል ኤታማዦር ሆኖ ያለው ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ ነው። አሁን ባለው የማዕረግ ደረጃ ለቦታው የሚመጥነው ተጨማሪ ሰው ሙሉ ጀኔራል ማዕረግ ያለው አብርሃ ወ/ማርያም በመሆኑ ህወሓት በዋና ኤታማዦርነቱም ሆነ በምክትልነቱ ፍላጎቱን ለማስጠበቅ መተጋገሉ አይቀሬ ነው። በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት “ወታደራዊ ካውንስል” እንደ አዲስ በሚደራጅበት ሁኔታ ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ይገመታል። በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተጀመሩ ሪፎርሞች ቀጣይነታቸው የሚታየው በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብርቱ ክትትል ቢሆንም ጀኔራል ሳዕረ መኮንን ስውር የማፍረስና የማደናቀፍ ወይም “ሳቦታዥ” መፈጸም ከጀመረ አገሪቱ ወደትርምስ ማምራቷ አይቀሬ መሆኑን የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ።

(በቀጣይ ዕትም የጌታቸው አሰፋን ሌጋሲን እና በምትኩ ስለተሾመው አደም መሐመድ ዘገባ እናቀርባለን) 

goolgule.com
 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *