ለአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አመራር እና መላው አባላት በዛሬው እለት ምስረታችሁን እውን በማድረጋችሁ ደስታችንን እየገለጽን መጭው የትግል ዘመናችሁ የተሳካ እንዲሆን እንመኛለን። እኛም የአንድ አማራ ንቅናቄ አባላትና ደጋፊዎች በምታደርጉት የትግል ጉዞ ሁሉ እንደ አንድ አማራ አብረናችሁ የምንቆም መሆኑን ስናበስር በታላቅ አማራዊ ጨዋነት ነው።

የአማራ ሕዝብ የተደቀነበትን ሁለንተናዊ የህልውና አደጋ ለመታደግ በተደራጀ መልኩ ትግል ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረድና አስቸጋሪ ሁኔታ አልፋችሁ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ለምስረታ መብቃቱ ትግሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው:: ንቅናቄያችን አንድ አማራ ከመነሻው በሃገር ውስጥ ሕዝባችንን የሚወክል ተቋም እንዲመሰረት ድምጻችንን ከፍ አድርገን ስንጮህለት የነበረ አላማ ጅማሮውን ለማየት በመቻላችን ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቶናል:: ጥያቄችንም መልስ አግኝቷል አስብሎናል:: ስለዚህም ድርጅታዊ አቅማችሁ እንዲጎለብት የተነሳችሁለት ታላቅ አላማም ከግቡ እንዲደርስ በምታደርጉት ትግል ከጎናችሁ እንቆማለን::

የአማራው ሕዝባችን ከተደቀነበት ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማሕበራዊና ፓለቲካዊ ችግሮች በላይ ሕልውናው ላይ የወደቀው አደጋ በተደራጀ ሁኔታ ለመመከት በማንነቱ መደራጀት ከነበረበት ወቅት እጅግ የዘገየም ቢሆንም ያለበትን ተቋማዊ ክፍተት ለመሙላት መደራጀታችሁ ለአማራው ሕዝባችን ታላቅ ተስፉን የሚፈነጥቅ ነው::

የአንድ አማራ ንቅናቄ ሲመሰረት ትግላችን የአማራዉን የመኖር ህልዉና ማስከበር በመሆኑ “አንድ አማራ ለሁሉም፥ ሁሉም ለአንድ አማራ ” በሚል መርሆ ትግል መጀመራችን ይታወቃል። እናንተም ይህንኑ በመረዳት አንድ አማራ ለሁሉም ሁሉም ለአንድ አማራ ማለታችሁ ያለንን መናበብ የሚያሳይ ነው:: መደራጀታችሁ የአማራዉ የግፍ ዘመን የሚያከትምበትና ታሪኩ የሚታደስበት የመጨረሻው መጀመሪያ ቀን መቅረቡን የሚገልጥ ነው።

ይህ አዲስ የተቋቋመ የአማራ ድርጅት ከ40ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብን ሊወክል የሚችል ከብዙ ግዜ እርቀትና መከራ በሗላ የተገኘ በመሆኑ ተቋሙን ውድና ብርቅ ሊያደርገው ይችላል የሚል እምነት አለን:: ገና በዋዜማውም የታየው የሕዝብ ምላሽ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው:: ስለሆነም ይህ ተስፋ የተጣለበት ድርጅት ካለፈው እና አሁንም ካለው የፖለቲካ ባህል ተገቢውን ግምገማ በማድረግ ጠላቱን ከመታገል ባሻገር የወየበውን የትግል ባህል እንዲስተካከል የማድረግ ሃላፊነት ይኖርበታል የሚል እምነት አለን:: እነደሚታወቀዉ አማራዉ በታሪኩ ተሸንፎ የማያዉቅ ብርቱ ማህበረሰብ ነዉ። የዚህ ዘመን የአማራ ትዉልድ ጠላቱ ከብቸኛዉ ህወሃት ባሻገር ከባህልና ወግ ያፈነገጠ የስድብና ተራ አሉባልታ ፤ በጎጥ የመቧደን ሁኔታ ፤ መርህ አልባ የድጋፍና ተቃውሞ ፤ የመንጋ ፖለቲካ ፥ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነና ጠላትን አለመቀነስ ለአማራ ህዝብ ትግል ሳንካ እና መከራን የሚያራዝሙ አካሄዶች መሆናቸዉን ከትግል ተሞክሮ ለመረዳት ችለናል። ስለሆነም እነኝህን ጎጂና ሗላቀር የፖለቲካ ልማዶች በማሶገድ ይዛችሁ የተነሳችሁትን ትግል የጋራ አላማችን ይሆን ዘንድ ከታላቅ አክብሮት ጋር ለመጠቆም እንወዳለን።

በመሆኑም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ያለፋት የትግላችን አረሞች አቆጥቁጠው ሕዝባዊ አቅጣጫውን እንዳይበርዙት ከፍ ያለ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ንቅናቄያችን አንድ አማራ አጥብቆ አደራ ይላል:: የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የአማራው ሕዝባችን አባቶቹ መስፈሪይ የሌለው መስዋዕትነት ከፍለው ባቆዪት ኢትዮጵያ በነጻነትና በእኩልነት እንዲኖር ትግሉን በጥበብና በማስተዋል በመምራት ለድል እንዲበቃ የትውልድ ታሪኩን ያድሳል ብለን በጽኑ እናምናለን::

የአማራ ሕዝብ ተጠሪና የሁሉም የአማራ ድርጅቶች የትብብር መዐከል ሆናችሁ የሕዝባችንን የነጻነት ቀን እንዲቃረብ በሃሳብ ጥራትና ዘመኑ በሚጠይቀው የአመራር ክህሎት ተጋግዛችሁ ትግሉን በሚፈለገው ደረጃ እንደምትመሩት እምነታችን የጸና ነው:: በመጨረሻም አንድ አማራ ንቅናቄ በምታደርጉት እንቅስቃሴ በደጋፊነት አብረናችሁ ልንሰለፍ ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን::

እውነተኛ አማራ አይደለም ተነጋግሮ ተያይቶ መግባባትኣለበት!!
አማራው አያቶቹ በገነቧት ሃገሩ ኢትዮጵያ ላይ በክብር ይኖራል!!

የአንድ አማራ ንቅናቄ !!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *