May 9, 2021

ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሕግ ሚና በልማታዊ መንግሥት

በርካታ መሪዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ግል ካዝናቸው አዛውረዋል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን የፌዴራሉን ዋና ኦዲተር ሪፖርትን ብቻ እንደመለኪያ ብንወስድ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ግለሰቦች (ባለሥልጣናት) የግል ሀብትነት መግባቱን እንድናምን ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የልማታዊ መንግሥት ፈተናው እንዲህ ዓይነት የዝርፊያ አስተዳደር ሊሰፍን መቻሉ ነው፡፡

እነዚህ ውሳኔዎች በዋናነት በመንግሥት ሥር ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ድርጊት ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ለግሉ ወይም ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ መንገድ የሚጠርግ ይመስላል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በሞኖፖል የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠቱን እንደያዘ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እነዚህ ድርጅቶች ወደ ግል የማዛወሩና አክሲዮን የመሸጥ ተግባሩ ከልማታዊ መንግሥት መርሆችና ባህሪያት በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራት እንዳለበት የሥነ ሥርዓትና አካሄድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የልማታዊ መንግሥት አካሄድን ተከትለው ከነበሩ አገሮች ባህሪያት አኳያ በምን ዓይነት የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የአሠራር ማዕቀፍ ያስፈልጋል? የሚለውን ጉዳይ ማመላከት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡ አስቀድመን የልማታዊ መንግሥት ባህሪያትን በአጭሩ በመግለጽ በእንዲህ ዓይነት ሥርዓት የግሉን ዘርፍ በሚመለከት የመንግሥትን ሚና ቢያንስ አዝማሚያውን በመቀጠል እንመለከታለን፡፡  
ስለልማታዊ መንግሥት በዝርዝር መጻፍ ከዚህ ጽሑፍ ዓላማ ውጪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አገራችን የልማታዊ መንግሥት ዘይቤን ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ የልማትና የዕድገት መመርያ በማድረጓ በጥቅሉ ከሕገ መንግሥታዊ መርሆቹና ድንጋጌዎቹ ጋር አብረው መሄድ አለመሄዳቸውን እንመለከታል፡፡ ስለ ልማታዊ መንግሥት ምንነት፣ ጎላ ጎላ ያሉ ፀባያት፣ የተለያዩ አገሮች በዚህ መርሕ ሲመሩ ያጋጠማቸውን ተግዳሮትና ስኬትን በሚመለከት በርካታ መጽሐፍትና ሌሎች ጽሑፎች ከሚጋሩዋቸው ነጥቦችን ልማታዊ መንግሥት (Developmental State) ንፁህ ገበያ መር ኢኮኖሚ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚን ገበያው በነፃነት እንዲመራው አይተውም፡፡ መንግሥትም ገበያውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር አያንቧችርም፡፡ በመሆኑም ከገበያ መርም ይሁን ከዕዝ ኢኮኖሚ የተለየ ነው፡፡
መንግሥት ኢኮኖሚውን ይመራል፡፡ ችጋርን በቶሎ ለመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ማኅበራዊ ልማትን በማመጣጠን ለመጓዝ ይጥራል፤ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ዘርፎችን ይለያል፡፡ የግል ባለሀብቱ እንዲሳተፍበት ያበረታታል፡፡ ካልሆነም ራሱ ይገባና ቀስ በቀስ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዞር ያደርጋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የግል ባለሀብቱን ይንከባከባል አያገልለውም፡፡ ልማታዊ መንግሥት እንደ ርዕዮተ ዓለምም ሊታይ ይችላል፡፡ የመንግሥት ዋናው ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማምጣት፣ ልማትን በዘላቂነት በማስቀጠልና በማስፋፋት ቅቡልነትን ማግኘት ግቡ ነው፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማት ግንባር!›› መሆኑ ነው፡፡  በደንብ በማዕከላዊ መንግሥት ታቅዶ እንጂ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ወጥ የሆነ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ ያንን ዕቅድ በመላ አገሪቱ እንደየአካባቢው ሁኔታ እየተስተካከለ ከዋናው፣ ከማዕከላዊ ዕቅድ ሳያፈነግጥ ይተገበራል፡፡ ይህን ለማድረግ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል የሚሉም አሉ፡፡ ልማታዊ መንግሥት ዘለዓለማዊ ርዕዮተ ዓለም አይደለም፡፡ መሸጋገሪያ እንጂ! ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚያደርስ ፈረስ ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያ ሽግግር ለዚህ ዓብይ ማስረጃ ነው፡፡
ልማታዊ መንግሥት ከጽንሰ ሐሳቡ ተግባሩ የቀደመ ነው፡፡ የበርካታ አገሮች የልማት ተሞክሮ ተጠራቅሞ ሲቀመር የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የዕድገት ጉዞዎች ታይተው እነ ቻልመርስ ጆንሰን የቀመሩት፡፡ በተለይም የጃፓንን የዓለም አቀፍ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እስከ 1975 ዓ.ም. የተጓዘበትን ጎዳና በሰፊው ሲያጠና ነው ንድፈ ሐሳቡን የቀመረው፡፡ የእነኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ታይዋን የልማት ጉዞ ተመሳሳይ ስለነበር ልማታዊ መንግሥት ተባሉ፡፡ የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ አውጃ ግን ከተግባሩ ወጉ ነው የቀደመው፡፡ ራሳቸውን ልማታዊ መንግሥት ብለው ሰየሙ፡፡ የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮችን ከልማቱ በኋላ ሌሎች ሰየሟቸው እንጂ ራሳቸውን ቀድመው ልማታዊ መንግሥት ነን አላሉም፡፡
ልማታዊ መንግሥት አምራች የኢንቨስትመንት ዘርፍን፣ ኤክስፖርትን (የወጪ ንግድን)፣ ሰብዓዊ ዕድገትን ማዕከል ያደርጋል፡፡ አስተዳደራዊውም ይሁን ፖለቲካዊ መዋቅሩ ማጠንጠኛው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ዕውቀትና ክህሎት ላይ ተመሥርተው በነፃነት መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የግሉን ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን እንቅስቃሴም ጭምር የልማት ተሳትፎና አቅጣጫቸውን ያስቀምጣል፡፡ ይኼንን ሊመራ የሚችል ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛ ያስፈልጋል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ ከግሉም ይሁን መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ሠራተኞች በላቀ ሁኔታ ምሁራንን ሊያቅፍ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም የግሉንም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑትንም ዘርፎች ዕቅዳቸውን ስለሚተልም፡፡ በመሆኑም ሲቪል ሰርቪሱ የሚዋቀረው በዕውቀትና በክህሎት እንጂ በፖለቲካዊ ተዓማኒነት አይደለም፡፡ ስለግሉና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ከላይ ሆኖ አቅዶ ለመምራትና ለማገዝ የተሻለ መሆንን ይጠይቃል፡፡ አንዱ የልማታዊ መንግሥት ትኩረት ዕሴት የሚጨምሩ አምራች ኢንቨስትመንት ነው ብለናል፡፡ ለውጤታማነቱ ደግሞ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ሊሰማሩ የሚችሉ ባለሀብቶችን ማፍራትና መንከባከብ እንዲሁም ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆን የሰው ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ ማፍራት ነው፡፡ ለዚያም ነው በከፍተኛ ሁኔታ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተስፋፉት የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የኢንጂነሪግና ሌሎች ከኮምፒውተርና ሒሳብ ጋር የተያያዙ ትምህርቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ 70 በመቶ እንዲሸፍኑ የተደረገው፡፡ ግልጽ የሆነ የልማታዊ መንግሥት መገለጫ ነው ይኼ፡፡ ሌሎች አገሮችም ይኼንኑ አድርገዋል፡፡
እነ ጃፓንና ኮሪያ በዓለም ላይ ምርጥ የተባሉ የተፈጥሮ ሳይንስ በተለይም የኢንጂነሪንግ (የምህንድስና) ትምህርቶች በሚሰጡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን በመላክ አስተምረዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ከመፍጠር ይልቅ ኩረጃ ላይ አተኩረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ማዕረግ ለሚመረቁ ተማሪዎች ከአገር ውጭ ባሉ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዕድል ይፋ ማድረጋቸው ከልማታዊ መንግሥት ጉዞ ጋር የሚስማማ ይመስላል፡፡ይህንን ተልዕኮ በሰፊው የሚያስፈጽም ተቋም በልማታዊ አገሮች ነበሩ፡፡ የእኛም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተቋቋመው ለዚህ ሲባል እንደሆነ መገመት ከባድ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአንድ በኩል በእርስ በርስ ጦርነት በነበረባት አገር በአማፃኒት ተሠልፈው የነበሩ ወታደሮች በትምህርትም በክህሎትም ላቅ ያለመሆናቸው ጉዳይ ዓለማዊ ሀቅ ነው፡፡ እነዚህ ወታደሮች እጅግ ምርጥ የተባሉ ቴክኖሎጂዎች ሊያመነጩ፣ ሊኮርጁና ሊያላምዱ የመቻላቸው ነገር አጠያያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪም ከዚህ በተለየ ሁኔታ አልተስተዋለበትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሱ ይህ ድርጅት በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከመንግሥት ቢረከብም በወቅቱ ማጠናቀቅ የተሳነው ሆኗል፡፡ በርካታ ገንዘብም በማባከን የታወቀ ሆኗል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብልሹ ተግባራት እንዳይከሰቱ ቀድሞውንም በመገመት ለክትትልና ቁጥጥር የሚረዱ የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋት አሠራሩን ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ማድረግ ይጠበቅ ነበር፡፡
በልማታዊ መንግሥት መሪዎችም ይሁኑ ተራ ሠራተኞች የላቀ ትጋትና አገር ወዳድነትን እንዲያንፀባርቁ ግድ ይላል፡፡ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ትልቅ ቦታ ሊኖረው እንደሚችል ከላይ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ  መንግሥት ብዙውን ነገር ስለሚመራና ስለሚደግፍ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ አንዲት አገር ልማታዊ መንግሥት ከሆነችና በዚሁ አካሄድ ለውጥ አመጣለሁ ብላ ቆርጣ ከተነሳች ሥልጣን ያዥ የፖለቲካ ፓርቲ ማንም ይሁን ማን የመንግሥት ሚና ላይ ስምምነት ካልደረሰና በዚያው መልኩ ካላስቀጠለ ፖሊሲው ውጤታማ ላይሆንም ይችላል፡፡ ልማታዊ መንግሥት ለአውራ ፓርቲ መፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይህንን ፈለግ ተከትለው ከነበሩ አገሮች ልማድ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ደቡብ ኮሪያ በአንባገነኑ ፕሬዚዳንት ፓርክ ሥር ትተዳደር በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አሳይታለች፡፡ ሌሎቹ መሪዎችም ይሁኑ፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ሥልጣን የያዙት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጭምር የልማቱን ጉዞ አስቀጥለዋል፡፡ በኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥም የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር ይችላል ማለት ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ ከአርባ ዓመታት በላይ ሥልጣን ይዞ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እንደሚቻልም ታይዋን ዋቢ ናት፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ነፃነት፣ በነፃነት ሐሳብን መግለጽ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባትን ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ከሆነ ከዚህ በተቃራኒው መጓዝ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ መሆንን ያመጣል፡፡
ሌላው ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማት ግንባር›› ነው ብለናል የልማታዊ መንግሥት መፈክር፡፡ ይህንን ለማምጣት  የግድ ሁሉም ሕዝብ በዚሁ መቃኘት አለበት ማለት ነው፡፡ ሊብራላዊ አደፍራሾች እንዳይኖሩ መቆጣጠር አንዱ የልማታዊ መንግሥት ባህሪ ነው፡፡ ሁሉም ለልማት መጓዝ! መንግሥት ኅብረተሰቡ ውስጥ ሰርጎ በመግባት የማስረፅና ሁሌም ይኼንኑ መኮትኮት ለነገ ተብሎ የሚያድር ሥራው አይደለም፡፡ በመሆኑም አንድ ለአምስትና የመሳሰሉት አደረጃጀቶች ተፈጠሩ፡፡ ከማዕከል በጥቅል የሚዘጋጅን ዕቅድ እየመነዘሩ በመተግበር ስለልማት ብቻ የሚወራበትና የሚገማገሙበት አደረጃጀት፡፡ አካሄዱ ከላይ ወደታች እንጂ በተቃራኒው አይደለም፡፡ ማስረፅና ማሳመን ይበዛዋል፡፡ አሳትፎ መተግበር ነው፡፡ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በፌዴራል ተዘጋጅቶ ወደታች እየተሸነሸነ ወረደ፡፡ ያንን የማይፈጽም ገበሬን ‹‹ታካች››፣ አመራር ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹ልማታዊ››! በሌሎች ዘርፎችም ያው ነው፡፡ ሊብራሊዝምን በሰፊው የሚሰብክ ፓርቲና ሰፋ ያለ ተከታዮች የሚያፈራ ከሆነ አመራሮቹ ‹‹መላ መላ›› ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ልማታዊ መንግሥትነትን ያደፈርሳሉና! ይኼ ያው ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጥ በፊት ሲከናወን የነበረ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ ውጭ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የልማታዊ መንግሥት ባህሪያትን ከሕግ አንፃር እናያለን፡፡
መንግሥትና ፓርቲ ግንኙነት
የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ግንኙነትም ይሁን ልዩነት በግልጽ በሕግ አልተደነገገም፡፡ ባልደነገገበት ሁኔታ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ገዥነቱን ተጠቅሞ ከሥልጣኑ የዘለለ ነገር መሥራቱ የተለመደ ነው፤ በተለይ በኢትዮጵያ፡፡ ፓርቲው ንፁህ መንግሥታዊ ሥራዎችን ሲፈጥርም ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ጉዳይን መቀበል፣ በርካታ ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዛወሩ መወሰን ወዘተ. ንፁህ መንግሥታዊ ሥራዎች ናቸው፡፡ መንግሥትንና ፓርቲን መነጣጠል ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ግን በአንድ በኩል ከሕገ መንግሥቱ የማፈንገጥ ተግባር ሲሆን፣ ሁለትም አውራ ፓርቲነትን መንከባከብና መኮትኮት ነው የሚሆነው፡፡
ኢኮኖሚያዊ ብሔርተኝነትና የሕገ መንግሥቱ
የልማታዊ መንግሥት ዓበይት ትኩረት በፍጥነት ልማት ማምጣት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ልማት፡፡ የልማታዊ መንግሥትን ትልም ይከተሉ የነበሩ አገሮች ዜጎቻቸውን ከሚያስተሳስራቸውና አንድ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች ዋናው በፍጥነት ከድህነት መላቀቅ ነው፡፡ ይህንንም ኢኮኖሚያዊ ብሔርተኝነት ይሉታል፡፡ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ዋና ጠላታችን ድህነት ነው ሲል ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ በድህነት ላይ በመዝመት ኢኮኖሚያዊ ብሔርተኝነት ተፈጥሯል ማለት አይቻልም፡፡ እንደውም ከዚህ ይልቅ የዘውጌያዊ ብሔርተኝነት ስሜት ይመስላል በማደግ ላይ ያለው፡፡ ዘውጌያዊ ብሔርተኝነት በሚበረታበት ጊዜ አገራዊ ብሔርተኝነትም (ኢትዮጵያዊነትም) በትይዩ ካልተጠናከረ የጋራ ማንነት መዳከሙ አይቀርም፡፡
ሌሎች ልማታዊ መንግሥታትን የጋራ ማንነት የፈጠሩት በፍጥነት በኢኮኖሚ ማደግ በመሆኑና በዚህም ኅብረተሰባዊ ስምምነት በመኖሩ ለአገር ግንባታም ጠቅሟቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሹመታቸው በፊትም ይሁን በኋላ ትኩረት ያደረጉት አገራዊ አንድነት ላይ ነው፡፡ ለወትሮው ይነገር የነበረው የሹመኞች ብሔር አሁን ላይ መቅረቱን ልብ ይሏል፡፡ እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዘውጌያዊ ብሔርተኝነት አልፈው ከዚህ የተያያዙ ድርጊቶችን ዘረኝነት በማለት ሲጠሩ ይደመጣል፡፡ አገራዊ አንድነትና በጋራ ዕጣ ፋንታ ላይ መስማማት ለልማት መፋጠን ለልማታዊ መንግሥት ጥሩ እርካብ በመሆን ያገለግላል፡፡ ነገር ግን ዘውጌያዊ ብሔርተኝነት ከአገራዊ ብሔርተኝነት ብሎም ወደ ኢኮኖሚያዊ ብሔርተኝነት ማሸጋገር ወይም መፍጠር በራሱ ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ኢኮኖሚያዊ ብሔርተኝነት ለአገር ምርት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ የአገር ውስጥ የማምረት ተግባርን ያበረታታል፡፡ ስለኢኮኖሚው ሲባል መንግሥት ጣልቃ ይገባል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ የሚኖረው ቀረጥ ይጨምራል፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይኼንን ዓይነቱን አካሄድ ሕዝብ አምኖበት፣ ወዶት ከተቀበለውና በአወንታዊነት ከተገበረው የእርስ በርስ ማያያዣና ማስተሳሰሪያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰዷቸው ያሉት ዕርምጃዎች አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ የእስረኞች መፈታትም ይሁን በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የምሕረት አዋጅ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁንም ቢሆን ያልተፈቱ መገለሎች አሉ፡፡ የተጀመሩት ቀድመው ነው፡፡ አሁንም ግን ቀጥለዋል፡፡ ለዚህ ምሳሌዎቹ አምስቱ ክልሎች (ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረር፣ አፋር፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) ናቸው፡፡ አገራዊ አንድምታቸው ከፍተኛ የሆኑ ውሳኔዎች በፓርቲ (በኢሕአዴግ) ሲወሰኑ እነዚህ አምስት ክልሎች ግን አልተሳተፉም፡፡ ለአብነት ባሳለፍነው ሳምንት የተወሰኑት የኢትየጵያና ኤርትራ ጉዳይና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎቹን ማንሳት እንችላለን፡፡ እንዲህ ዓይነት መገለሎች ልማታዊ መንግሥት ለስኬቱ ከሚፈልገው ምቹ ሁኔታ በተቃርኖ ያሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ ማሳካት ከሚፈልጋቸው ግቦች መካከል አንዱ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ነው፡፡ በኢኮኖሚ የተሳሳረ፣ መለያየት የማይችል ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ብዙም መሻሻል ያልታየበት የዜጎች ከየክልሉ መፈናቀል ባለበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ፈተና መሆኑ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡
ዘራፊ መንግሥትና ልማታዊ መንግሥት
ልማታዊ መንግሥት መሆን ጀምረው መጨረሻው ዘራፊ መስተዳድር (ክሌፕቶክራሲ) ሆነው የቀሩ አሉ፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ ማዘዝ የሚችል ሰው ሌሎች የቁጥጥር ሥልቶች ካልተጠናከሩ ዝርፊያው እንደሚጠናከር የዛየርና የላቲን አሜሪካ አገሮች አመራር ምስክሮች ናቸው፡፡ በርካታ መሪዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ግል ካዝናቸው አዛውረዋል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን የፌዴራሉን ዋና ኦዲተር ሪፖርትን ብቻ እንደመለኪያ ብንወስድ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ግለሰቦች (ባለሥልጣናት) የግል ሀብትነት መግባቱን እንድናምን ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የልማታዊ መንግሥት ፈተናው እንዲህ ዓይነት የዝርፊያ አስተዳደር ሊሰፍን መቻሉ ነው፡፡
እስከዛሬ በነበረው ሁኔታም የሕዝብና የመንግሥትን ገንዘብ ወደ ግል ሀብትነት ያዛወሩ ሰዎች በአትራፊነታቸው የታወቁ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በተናጠልም ይሁን በከፍተኛ ገንዝብ አክሲዮን በመግዛት አዛዥ ናዛዥ መሳፍንት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለመንደርደሪያ ያህል የቀረበ ነው፡፡ በልማታዊ መንግሥት አስተዳደራዊና ቁጥጥራዊ አሠራሮችን በተለይም የኢኮኖሚውን ዘርፍ የሚመለከተውን በክፍል ሁለት እንቀጥላለን፡፡

 አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡ FacebookTwitterLinkedInShare

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በቡድን ተደራጅተው የውንብድና ወንጀል የፈጸሙት ተከሳሾች ከ18 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ፡፡
0Shares
0
Read previous post:
የገንዘብ እጥረት ቀውስ በኢኮኖሚው ላይ ሥጋት መደቀኑን መንግሥት አመነ-

- ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ዘንድሮ መሰብሰብ አልተቻለም - የ2011 ዓ.ም. በጀት 59 ቢሊዮን ብር...

Close