በደቡብ ክልል ሲዳማ፣ ወላይታ እና ጉራጌ ዞኖች እና ቀቤና ወረዳ አመራሮች በየአካባቢዎቹ ሰሞኑን ለተፈጠሩት ግጭቶች ኃላፊነት ወስደው ስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ሊለቁ እንደሚገባ እና ያንንም አመራሮቹ እንደሚፈፅሙ እምነት እንዳላቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት ጀምሮ በሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ እና ወልቂጤ ከተሞች ከየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። በዛሬው እለት ከጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር በወልቂጤ ከተማ ባደረጉት ውይይት፥ ከህብረተሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በጉራጌና ቀቤና ህዝቦች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት፣ የመሰረተ ልማትና መልካም አስተዳደር፣ የጉራጌ ዞን ክልል ይሁን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ምላሽም፥ አመራሩ በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ለተፈጠሩ ግጭቶች ሃላፊነት ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በክልሉ ሲዳማ፣ ወላይታ እና ጉራጌ ዞኖች እና ቀቤና ወረዳ የሚገኙ አመራሮች በየአካባቢዎቹ ሰሞኑን ለተፈጠሩት ግጭቶች ኃላፊነት ወስደው ስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ሊለቁ እንደሚገባ ተናግረዋል። አያይዘውም አመራሮቹ ይህንን እንደሚፈፅሙ እምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።

የአካባቢው ወጣቶችም ችግሮችን ፈተው የሰላም ዘብ ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት፤ ወጣቶቹም በቀጣይ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተውላቸዋል።

የክልሉ መንግስትም ጉዳዩን በማጣራት በክልል ደረጃ መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች መፍታት እንዳለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከፍ ያሉ ጉዳዮች ደግ በፌደራል ደረጃ እንደሚፈቱም ገልጸዋል። ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች በቅርቡ በቂ ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ክልል ይሁን በሚል ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም የጉራጌ ህዝብ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ የሚሰራ ታታሪ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከክልል ጥያቄ ይልቅ አካባቢያቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ በአካባቢዎቹ ሰላም ለማምጣትና ህዝቡን ለማረጋጋት የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አውስተዋል። ችግሮች ሲፈጠሩም ስህተትን በስህተት ሳይሆን፥ በይቅርታ፣ በአብሮነትና በአንድነት መንፈስ በመስራት መፍታት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የሃይማኖት መሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ከፖለቲካዊ አስተሳሰብና ወገንተኝነት መራቅ አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህብረተሰቡም ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ኃይሎችን መታገል እንደሚገባው አስረድተዋል። መላው ህዝብም ባደገበት ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ወግና ስርዓት ጸንቶ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *