አሉላ ዮሃንስ የተባለ ሰው በትግራይ ኦንላይን ላይ እውን ኢህአዴግ አለወይ በሚል አርዕስት የከተባት ነገር ሳበችኝና ተመለከትኳት።ፅሁፏ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ከሆነች ፀሃፊውን ከአንገቴ ዝቅ ብዬ አድናቆቴን እገልፃለሁ።ከተሳካ ግሩም ሙከራ ነው።ነገር ግን አቶ አሉላ በእውን ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ነበረ አሁን ግን የት ገባ ብሎ የፃፈውን የሚያምን ከሆነ ግን ትልቅ ችግር አለ። አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል ያለው አይነት መሆኑ ነው። ፅሁፉ የሚጀምረው በሚከተለው  ነው።

“እስከ ቅርብ ግዜ ኣህኣዴግ እሚታወቅ የነበረው ሲወስን በማእከላዊነትና በብዱን እንጂ ኣንድ ስው መሪም ቢሆን ከመተማመንና ይሁንታ ሳያገኝ ትንፍሽ ኣይባልም ነበር፡፡ የኣሁኑ ኣካሄድ እንድሚያሳየው ግን ኣንድ ሰው የፈለገ የሚሾምበት፣ የፈለገውን የሚሽርበት፣ ትላልቅ የሃገር ፖሊሲዎች እንዳሻው በኣንድ ሰው የሚወሰንበት ደረጃ መድረሳችን ለሃገራችን እድገትና ብልፅግና ሲሉ ሂወታቸውን ለገበሩት ማንቋሸሽ ይሆናል፡፡”

ይህን በጥሬው ካየነው የእውነቱ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው።ዶር አብይ ስለአብይ ማን ተነጋገረ ያሉትን ያስታውሷል። ጀርመንኛውን ወደ አማርኛ መልሰን ስናነበው ግን መልዕክቱ የሚከተለው ነው

“እስከ ቅርብ ግዜ ኣህኣዴግ እሚታወቅ የነበረው ሲወስን በህወሃት ፍቃድ እንጂ ኣንድ ከህወሃት ያልመጣ ሰው መሪም ቢሆን የህወሃት መተማመንና ይሁንታ ሳያገኝ ትንፍሽ ኣይባልም ነበር፡፡ የኣሁኑ ኣካሄድ እንድሚያሳየው ግን ኣንድ ህወሃት ያልሆነ ሰው የፈለገ የሚሾምበት፣ የፈለገውን የሚሽርበት፣ ትላልቅ የሃገር ፖሊሲዎች እንዳሻው ህወሃት ያልሆነው ሰው የሚወሰንበት ደረጃ መድረሳችን ለክልላችን እድገትና ብልፅግና ሲሉ ሂወታቸውን ለገበሩት ማንቋሸሽ ነውና የጦር መሪዎች ቼ ሊሉ ይገባል ፡፡”  – ትርጉም

ይሄ ትርጉም እውነት ነው።ባለፉት 27 አመታት የኢትዮጲያ ህዝብ ያየውና የሚያውቀው እውነታ ነው።እረጋ ብለን ያሰመርኩባት ‘ትንፍሽ አይባልም ነበር’ የምትለዋን ቃል ስንመለከታት በስህተት የገባች ግን አሉላ ህወሃት ምን ያህል ሌሎቹን አሯሯጭ ድርጅቶች ጠርንፋ እንደነበር የሚያውቅ መሆኑን ታሳያለች።ትንፍሽ አይባልም የሚል በዲሞክራሲያዊ አሰራር መዝገበ ቃላት ውስጥ ልትኖር አትችልም። በመቀጠል የሚከተለውን አስቀምጧል

“ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን የመጡበት ኣካሄድ መሰረታዊ ስህተትና የህግ ጥሰት እንዳለበት እየታወቀ መመረጣቸው ኣጠቃላይ የኢህኣዴግ ውድቀት የሚያሳይ ነው፡፡ እነጃዋር በግልፅ እየነገሩን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን የመጡት በኢህኣዴግ ሳይሆን በቄሮዎች ኣመፅ መሆኑን ነው በኔ እምነትም በኢህኣዴግ ሳይሆን በኣመፅና ሳቦታጅ መሆኑን ነው፡፡”

ይህኛው ለመተርጎም በጣም አስቸጋሪ ነው። ቁጭትን ወይም መሆን ነበረበት ብለው ያሰቡትንም ያዘለ ስለሆነ ትክክለኛ የአማርኛ መልዕክቱ በጣም የራቀ ነው ግን አንብቤ የተረዳሁት የሚከተለውን ነው።

“ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን የመጡበት ኣካሄድ መሰረታዊ የህወሃት ድክመት ፤የፀጥታ ሃይሉ ቄሮውንና ፋኖውን በከፍተኛ ሁኔታ በመግደል ማሰርና ማሰቃየት ፤የኦህዴድና የብአዴን አባላትን አስገድዶ ህወሃት የሚፈልገውን ጠቅላይ ሚኒስትር በማስመረጥ ህዝብን ማፈን ሲገባ ዶር አብይ መመረጣቸው ኣጠቃላይ የህወሃትን ውድቀት የሚያሳይ ነው፡፡ እነጃዋር በግልፅ እየነገሩን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን የመጡት በህወሃት ሳይሆን በቄሮዎች ኣመፅ መሆኑን ነው በኔ እምነትም  በህወሃት ሳይሆን አልታዘዝም ባለው ካሁን በኋላ ዘራፍ ባለው ኢህአዴግ ሳቦታጅ መሆኑን ነው፡” – ትርጉም

በመቀጠል የሚከተለውን ጀርመንኛም ተመልክቻለሁ።

“ከዚህም ባሻገር በሚድያዎች እየታየ ያለው ቅንነት የጎደለው ኣዘጋገብ፣ በተለይ በክልል ኣከባቢ ደግሞ እየተላለፉ ያሉ ዲስኩሮች መረን የለቀቀ ብቻ ሳይሆን በሁለት ጠላት ሃገሮች እንኳን ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ ነው፡፡ በተለይ በኣማራ ቴለቨቪዥን በየቀኑ እየተላለፉ ያሉ መርዘኛ ፕሮፖጋንዳዎች መላ ካልተበጀለት፣ መርዙን በተለይ በወጣቱ እየሰረፀና በስሜት የመነዳት ሁኔታዎች በስተመጨረሻ ወደማያባራ ኣዘቅት የሚከት ስለሆነ ቆም ተብሎ ዳግም ሊታሰብበት የሚገባ ነው እላሎህ፡፡”

ኋላ ምን ያረጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ አሉ? አቶ አሉላ የኢትዮጲያ ብሄረሰቦችን በእኩልነት የማይመለከት፤የህወሃት አካሄድ ይጠቅመኛል ወይም ተጠቃሚ ነኝ በማለት ፤ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት አማራው ህዝብ ከተለያዩ ክልላት እየታረደ፤እየተዘረፈ፤እየተቀማ እንዲወጣ ሲደረግ ከወያኔ ጎን ቆሞ በለው ሲል የነበረ ስለሆነ ይህን ጀርመንኛውን ወደ ትክክለኛ መልዕክቱ መመለስ የተገባ ነው።

“ከዚህም ባሻገር በሚድያዎች እየታየ ያለው የህወሃትን አቋም የተጋፋ ኣዘጋገብ፣ በተለይ በክልል ኣከባቢ ደግሞ እየተላለፉ ያሉ ዲስኩሮች ከህወሃት መስመር የወጣ ብቻ ሳይሆን እንደ በአዴንና ኦህዴድ ካሉ ታዛዥ ድርጅቶች ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ ነው፡፡ በተለይ በኣማራ ቴለቪዥን በየቀኑ እየተላለፉ ያሉ ፀረ ህወሃት ፕሮፖጋንዳዎች መላ ካልተበጀለት፣ መርዙን በተለይ በወጣቱ እየሰረፀና በስሜት የመነዳት  ሁኔታዎች በስተመጨረሻ ወደማያባራ የህወሃት ኣዘቅት የሚከት ስለሆነ ቆም ተብሎ ዳግም በጦር ጄኔራሎች ሊታሰብበት የሚገባ ነው እላለሁ፡፡ – ትርጉም

ይቀጥላሉ አቶ አሉላ

“ኣሁን እነዚህ ሁሉ ወንጀለኞች በተለቀቁ ማግስት፣ ለርካሽ ተወዳጅነት ኣገሪትዋ ሳትረጋጋ በኣመፅ ወደ ስልጣን መምጣት ኢላማውን ስለመታ ብቻ ኣስቸኳይ ግዜ ኣዋጁን ያለግዜው ኣንስቶ ኣመፅ ሲቀሰቀስ የቀን ጅቦች ሊበሉን ሊያባሉን እሚሉት ንግግር እንደምታው ምን ይሆን? ጅቦቹስ እነማን ይሆኑ፡፡ እንግዲህ ሁሉ ወንጀለኛን በመፍታትና የነበራቸውን ኣገር የማፈራረስ ውጥን እንዲገፉበት እውቅና እየሰጡ ኣሁን ደግሞ የቀን ጅቦች ብሎ ማለት በራሱ የሚምታታ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ኢህኣዴግ የለም እንጂ ቢኖርማ ንሮ እንዲህ ኣይነት ኣምባገነናዊና ከህገመንግስቱ በተቃራኒ ከማእከላውነት ባፈነገጠ መልኩ ውሳኔዎች እየተላለፉና እየተተገበሩ ኣናይም ነበር፡፡ እኔ ስሀገምተው የኣሁኑ ኣመራር ማማለጃ ካገኙ የኣባይ ግድብም ይቁም ብለው ከማዘዝና ከማስቆም ወደውሃላ የሚሉ ኣይመስለኝም፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው እውን ኢህኣዴግ ኣለን? ያልኩት፡፡”

አለ ነገር ነው ያለው ሰውየው? አቶ አሉላ ህዝብን  አባይ ግድብ ይቁም ሊያስብል የሚችል ሚስጥር እንዳለ የሚያውቅ ይመስላል።ማማለጃ ካገኙ? የምን ማማለጃ? ከማን? ዶር አብይን ሌባ ወይም የሃገር ጥቅም ሻጭ ለማለት ነው? የት? እንዴት? አልገባኝም? ለማንኛውም ጀርመንኛው ወደ አማርኛ ሲመለስ እኛ የምንረዳው የሚከተለውን ነው።

“ኣሁን እነዚህ ሁሉ ወንጀለኞች በተለቀቁ ማግስት፣ የኛን ጥቅም ረግጦ የአብዛኛውን ህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ኣገሪትዋ ሳትረጋጋ በኣመፅ ወደ ስልጣን መምጣት ኢላማውን ስለመታ ብቻ ኣስቸኳይ ግዜ ኣዋጁን ያለግዜው ኣንስቶ ኣመፅ ሲቀሰቀስ የቀን ጅቦች ሊበሉን ሊያባሉን እሚሉት ንግግር እንደምታው ምን ይሆን? ጅቦቹስ እነማን ይሆኑ፡፡ እንግዲህ ሁሉ ወንጀለኛን በመፍታትና የነበራቸውን ኣገር የማፈራረስ ውጥን እንዲገፉበት እውቅና እየሰጡ ኣሁን ደግሞ የቀን ጅቦች ብሎ ማለት በራሱ የሚምታታ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ዘራፍ እኔ የህወሃት እሽከር የሚል ኢህአዴግ የለም እንጂ ቢኖርማ ንሮ ወይም መለስ ቢኖር ኖሮ እንዲህ ኣይነት ዲሞክራሲያዊና ህገመንግስታዊ ከህወሃት በተቃራኒ ባፈነገጠ መልኩ ውሳኔዎች እየተላለፉና እየተገበሩ ኣናይም ነበር፡፡ እኔ ስገምተው የኣሁኑ ኣመራር ማማለጃ ካገኙ የኣባይ ግድብም ይቁም ብለው ከማዘዝና ከማስቆም ወደኋላ የሚሉ ኣይመስለኝም፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው እውን ኢህኣዴግ ኣለን? ያልኩት፡፡” – ትርጉም

የትርጉሙ ነገር በቀላሉ መታለፍ የለበትም።አቶ አሉላ ፖለቲከኛ ነው።ፖለቲካ ደግሞ መሽከርከርን ይጠይቃል። ግን ምንም ቢሆን ለሁሉ ነገር መጠን ወይም ለከት ሊኖረው ይገባል።ወደድንም ጠላንም ዶር አብይ ህዝቡን ወደ ዲሞክራሲያዊ ባቡር እያሳፈሩት ነው።በዲሞክራሲ ደግሞ የሌሎችን ሃሳብ ማክበር ግድ ነው።እናም እንደነ አቶ አሉላ ያሉ ሰዎች ሃሳባቸውን በግልፅ ቋንቋ ቢያስቀምጡ ጠቃሚ ነው።ለህወሃት የበላይነት ማክተም እየተቆጩና እየተንገበገቡ ህወሃት ሌላውን ህዝብ እየገረፈ እያሰቃየና እየዘረፈ በበላይነት ለምን አልቆየም እያሉ ድፍረቱ ኖሯቸው የህወሃት የበላይነት ብለው አይፅፉም።ኢህአዴግ አለን ? እያሉ ላሞኛችሁ አይናችሁን ጨፍኑ ይሉናል። ትርፉ ግን ትዝብት ነው።

የዚህ ፅሁፍ አላማ የአሉላን ሃሳብ ለመሞገት አይደለም።አሉላ የፃፈውን ሃሳብ ከህወሃት ወገን ያልሆነው ተበደልኩ ፤ታሰርኩ፤ተገረፍኩ ፤ተሰደድኩ፤መንግስታዊ ሽብርተኝነት ተፈፀመመብኝ እያለ ያለው ህዝብ  የሚያነበውንና የሚረዳውን እራሱ አቶ አሉላ እንዲመለከት ወይም አሉላና መሰሎቹ  ከተኙበት እንዲነቁ ለመቀስቀስ  ነው።ዶር አብይ በትክክል አስቀምጠውታል። ህወሃት የበላይ ካልሆነ እሰቀላለሁ የሚል ፓርላማው ውስጥ ቁጭ ብሎ ሃሳቡን መናገር መብቱ ነው።አሉላ ያን ሰው የመሆን መብት አለው።ግን ድብቅ መልዕክት ይዞ ብዕርን ማንሳት ትክክል አይደለም።በተለይ ፊደል የቆጠረው ሁሉንም ኢትዮጲያውያን በእኩል ማየት ይጠበቅበታል።

አንድን መጥፎ አካሄድ የምንቃወም ከሆነ ማንም ይስራው ማን ያንን አሰራር በፅኑ ማውገዝ ይኖርብናል።ለምሳሌ ህወሃት ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በተለይ አማራውን ነጥሎ ለለመምታት ጨቋኝ ብሎ በመፈረጅና በማስፈረጅ ፤የተቀናጀ የፖለቲካና የፕሮፖጋንዳ ስራ ሲሰራ ቀይቷል።እንደ አንድ የህወሃት ደጋፊ አሉላ የአማራውን ቴሌቪዥን መተቸት የሚችለው ችግሩን ከመሰረቱ ተመልክቶ ኢትዮጲያውያንን በሚያግባባ መልኩ፤ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ትክክል እንዳልሆነ የህወሃትን ፖሊሲ ጭምር በማውገዝ ነበር።ግን አላደረገውም።ለምን ህወሃት ህዝብን ከህዝብ ሲያጣላ በዛም አማራው ዛፍ ቆራጭ አየተባለ በሃገሩ ስደተኛ ሲሆን ዝም፤ህወሃትን በሚጎዳ መልኩ ያው አሰራር ሲመጣ ደግሞ ዘራፍ ማለት ትዝብት ውስጥ የሚጥል ነው።የአማራ ቴሌቪዥን አድርጎት ከሆነ።

ባጠቃላይ የዶር አብይን እርምጃዎችና በዚያም እፎይታውን እያጣጣመ  ያለው የኢትዮጲያን ህዝብ የአሉላን ፅሁፍ አንብቦ የሚረዳው አሉላ ምን ያህል ከህዝብ ጥቅም በተፃራሪ የቆመ መሆኑን ነው።አሉላ በፅሁፉ “ለውጥ ኣስፈላጊ መሆኑ ለማንም ቅን ህሊና ላለው ኣስፈላጊና ትክክለኛም ነው” በሚል የለበጣ ያስቀምጣል። የሱ ችግር ግን የህወሃትን የበላይነት ያለተቀበለ ለውጥ፤ ለውጥ አይባልም።ይቀጥልና ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የኢትዮጲያ ህዝብ የደረሰበትን መከራና ስቃይ የማናውቅ ይመስል የሚከተለውን ከትቧል።

“ኣሁን የመሰለንን እና እንደልባችን ለመናገር፣ ለመፃፍ፣ ለመደገፍ፣ ለመቃወምና ኣዲስ ሃሳብን ለማፍለቅ የቻልነው እነዚህ መስራች የህወሃት መሪዎች በኣፍላ ወጣትነታቸው፣ ለዚህ ህዝብ ከደርግ መንጋጋ ላማውጣት ሲሉ ሙሉ እድሜኣቸውን የከፈሉ በመሆናቸው ነው”

አይ አመክንዮ! ህዝብ እንደልቡ መናገር፣ መፃፍ፣ መደገፍ፣ መቃወም የቻለው በህወሃት ትግል ነው!በሰብሃት ነጋና በረከት ስምዓን መሆኑ ነው።እረ ተው እንደዚህ አይን ያወጣ ውሸት ማንንም አይጠቅምም።ህዝብ እንደልቡ መናገር፣ መፃፍ፣ መደገፍ፣ መቃወም የቻለው አሁን ነው።ለዛም የታገለው ቄሮውና ፋኖው ነው።የምን ሰብሃት የምን በረከት።አሁን ለህዝባችን የሚጠቅመው ሸፍጥ ሳይሆን ግልፅነት፤እውነት፤ሰላም፤ ፍቅርና ኢትዮጲያዊነት ብቻ ናቸው።የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል እንዲሉ በጎሳ እየተቧደኑ መሸረብ መጨረሻው ታይቷል።ለማንም አይጠቅምም።እውነት ብቻ ይፃፍ።የአቶ አሉላ ጥያቄ ህዝብ ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ነው።ኢህአዴግ አለወይ ነው።መልሱም ባጭሩ አዎን ኢህአዴግ አለ ነው። ዶር አብይ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑ ወዲህ ኢህአዴግ ከአኗኗሪነት ወደ ነዋሪነት ተሸጋግሯል።

ጥያቄው እራሱ ግን ጀርመንኛ ከሆነና የህወሃት አባል የሆነው አቶ አሉላ ዮሃንስ እራሱ ኢህአዴግ አለወይ ካለ የምንረዳው አንድም ጥያቄው በተዘዋዋሪ የቀረበው ለከፍተኛ የህወሃት መሪዎችና ጦር ውስጥ ላሉ የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ሲሆን ሁለትም መልዕክቱ አንድ ነገር አርጉና መኖራችሁን አሳዩን ነው።

አቶ አሉላ ጥሩ መልስ የሚያገኝ አይመስለኝም።የኢትዮጲያ ህዝብ አሸንፏል።

የዶር አብይ ራዕይ ለኢትዮጲያውያን ይበጀናል። መደመር መደመር መደመር ።

መላኩ ከአትላንታ – ከሳተናው የተወሰደ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *