“Our true nationality is mankind.”H.G.

በደቡብ ክልል በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ 1 ሺህ 130 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው

በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ 1 ሺህ 130 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነሩ አቶ ፍሰሃ ጋረደው፥ ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ የትኛውም ግለሰብ፣ የመንግስትና የፀጥታ አካላት ጉዳዩ ተጣርቶ ሲያበቃ ለህግ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

በግጭቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በክልሉ የ27 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልፀዋል።

በሃዋሳ ከተማ በነበረው ግጭት የ15 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እና በ253 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት አጋጥሟል።

ከዚህ ባለፈ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ሲቃጠሉ 170 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች የተዘረፉ ሲሆን፥ 19 ተሽከርካዎች እና ሞተር ሳይክሎች መቃጠላቸውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በአሁን ሰዓት ከ9 ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል። 

በሌላ በኩል በጉራጌ ዞን በነበረው ግጭት በሶስት ሰዎች የሞት፣ በሰባት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እና በሶስት ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። በዞኑ 60 መኖሪያ ቤቶች፣ አንድ የመንግስት ተቋም እና ስድስት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።

በወላይታ ዞን በሶዶ ከተማ ደግሞ የሶስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ የተገለፀ ሲሆን፥ በወቅቱም አራት ከባድ እና ስምንት ቀላል የአካል ጉዳት እንዳጋጠመ ታውቋል።

በዚሁ ዞን በነበረው ግጭት 59 ሞተር ሳይክሎች እና 14 ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን፥ 28 የግል ድርጅቶች እና ስድስት የመንግስት ተቋማት ዝርፊያ እንደተፈፀመባቸው ተነግሯል። በተመሳሳይ በሲደማ ዞን ሻመና አካባቢ ስድስት የሞት፣ 24 ከባድ እና 33  ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፓሊስ አስታውቋል።

በሻመና አካባቢ በተከሰተው ግጭት በ34 መኖሪያ ቤቶች የቃጠሎ ጉዳት እና ዝርፊያ ተፈፅሞባቸዋል። እንዲሁም በዞኑ ለኩ ከተማ 471 ቤቶች እንደተቃጠሉ እና 245 ድርጅቶች ደግሞ እንደተዘረፉና እንደተቃጠሉ ተገልጿል።

በይርጋለም ከተማ ደግሞ በ59 የመኖሪያና ንግድ ቤቶች ላይ ዝርፊያ እና በወንዶገነት በ11 ቤቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተነግሯል። ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ በምዕራብ ጉጂ ዞን ይኖሩ የነበሩ ከ600 ሺህ በላይ የጌዲኦ ተፈናቃዮች በጌዲኦ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።

በክልሉ የነበረው ሰላም እየተመለሰ በመሆኑ ህዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ እና በዘረፋ የተሳተፉ አካላትን አጋልጦ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

በብርሃኑ በጋሻው fana

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››
0Shares
0