በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ደግሞ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ እንደ ሀገር ገጥሞን ከነበረ ከፍተኛ ብጥብጥና ሁከት አልፎም ያለመረጋጋትና የመበተን ስጋት ሁኔታ ወጥተን ተስፋ ሰጭ የለውጥ እንቅስቃሴ መጀመራችን የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን የፈነጠቀ የለውጥ ብርሃን የተመለከቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እሰከ ምዕራብ ጫፍ የሚገኙ የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡


የክልላቸን መንግስትና ህዝብም በተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ መሪነት መምጣትና ይህንን ተከትሎም በሁሉም አገራችን አካባቢዎች ተዘዋውረው በተለይም በክልላችን በባህርዳርና በጎንደር ከተሞች ተገኝተው ህዝቡን ባወያዩበት ወቅት ባደረጉት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የይቅረታ ንግግራቸው በመላ የክልላችን ህዝቦች ዘንድ ታላቅ ድጋፍን ያተረፉና በመላ ህዝባችን ዘንድ እምነት የሚጥሉባቸው መሪ ናቸው፡፡ 
በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ “ለውጥን እንደግፍ፤ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ መሪነት በሀገራችን ለተጀመረው ለውጥ እውቅና ለመስጠትና ምስጋና ለማቅረብ በአዲስ አበባና በዙሪያው የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገራችን ህዝቦች በነቂስ ወጥተው ለመሪያችንና ለጅምር የለውጥ እንቅስቃሴያቸው ያላቸውን ድጋፍ ሰላማዊና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ በደስታ ገልጸዋል፣ መላ የክልላችን ህዝብም ልቡን አዲስ አበባ አይኑንና ጀሮውን ለመገኛኛ ብዙሃን ሰጥቶ ውሏል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም በድጋፍ ሰልፉ ተገኝተው ጥላቻና በቀልን ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን ዘረኝነትንና ሌብነትን ሳይሆን መደመርንና ሀገር ወዳድነትን፣ መተባበርንና ይቅር ባይነትን ያዘሉ መልክቶችን አስተላልፈው ለዚህም የሀገራችን ህዝቦች ከጎናቸው እንዲሰለፉ እጅ ለእጅ አስተሳስረው ቃል ያስገቡበት መድረክ እንደነበርና በአጠቃላይም የድጋፍ ሰልፉ ለላቀ የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያነሳሳ የተሰካና ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የተያበት ፕሮግራም ነበር፡፡ 
ሆኖም ዋናው መልዕከት ከተላለፈና ከተጠናቀቀ በኋላ ከሀገራችን አልፎ አለምን ያስደመመ ተስፋ የታየበትን የለውጥ እንቅሰቃሴ ለማደናቀፍ ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ ሰላም፣ አንድነትና መተባበር የሚያስከፋቸውና የማይዋጥላቸው አካላት ክፋት በወለደው የአሸባሪነት ተግባራቸው የህዝቡን ደስታ ለመንጠቅ አሲረው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ባደረሱት ጥቃትም በዜጎቻችን ላይ የሞትና ከቀላል እሰከ ከባድ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ይህንን አረመኔያዊና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በፅኑ እያወገዘ፣ በተከሰተው የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በተሰበረ ልብ እንገልፃለን፡፡ ለተጎጅ ቤተሰቦችም መፅናናትን እንመኛለን፡፡ በቀጣይም የሀገራችን መንግስት የዚህን ወንጀል ፈጻሚዎችና ከበስተጀርባው ያሉ አካላትን ለማጣራት በሚያደርገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡
በዚህ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት የሚሰናከል የለውጥ ጉዞ አልጀመርንም፡፡ የህዝባችን ደስታም እንዲህ በወረደ ኢ-ሰብዓዊ የሽብር ተግባር አይደናቀፍም፡፡ ይልቁንም የለውጥ እንቅስቃሴው በበለጠ በይቅር ባይነት፣ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በትብብር፣ ከብረት ጠንክሮ እንዲወጣ የሚያነሳሳን እንደሆነ በፅኑ እናምናለን፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግስትና ህዝቡ ከለውጡ ጎን በመቆም የበኩላችንን በፅናት እንወጣለን፡፡
በመጨረሻም ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን።
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
ሰኔ 16/2010 ዓ.ም  ባ/ዳር

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ዶክተር አብራሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *