የክፋት ሃይሎች በጠነሰሱት የክፋት ሴራ የተነሳ በዛሬው እለት በመስቀል አደባባይ በደረሰው ፍንዳታ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 9 የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ታወቀ።
የመንግስት ኦፊሳል ድረ ገጾች እንዳስታወቁት በተጠቀሱት አካላት ላይ ምርመራ የሚደረገው ከተፈጸመው “የሽብር ጥቃት “ጋር በተያያዘ ባሳዩት ክፍተት ነው። ድረ ገጾቹ የታሰሩትን ስም ዝርዝር አልጠቀሱም።
ዶክተር አብይ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ራስዋን የሳተች የአእምሮ በሽተኛ የሚመስሉ ሁለት ሴቶች፣ አንድ መታወቂያው የቤተ ክህነት ሰራተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጎልማሳን ጨምሮ በጥቅሉ አምስት ሰዎች መያዛቸው ታውቋል። አንድ በቅርብ እርቀት ሆኖ አንዷን ሴት ሲከታተል የነበረ ለመንግስት ቴሌቪዥን እንዳለው ሴትየዋ ዳግም ለማፈዳት በዝግጅት ላይ ነበረች፣ በያዘችው ከረጢት ውስጥም ተጨማሪ በስም ያልጠቀሰው መሳሪያና ተቀጣጣይ ፈንጂ ተይዞባታል።
ከአስከፊው አደጋ በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድርጊቱ የተጠናና ሆን ተብሎ በባለሙያዎች የተቀነባበረ ሲሉ ነው ድርጊቱን የገለጹት። አያይዘውም ምርመራ ሲልያልቅ ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን አመላክተዋል።
ዛሬ የተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ሲያሰራጩት የነበረው የህዝብ ማዕበል፣ የቀድሞ አስተሳሰብና አካሄድ ላይመለስ ማክተሙን የሚያረጋግጥ እንደሆነ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች በመንግስት ሚዲያ ሲናገሩ ተሰምቷል።
ድርጊቱን የተለያዩ አገራት፣ ክልሎችና አስተዳደሮች ኮንነውታል። ኤርትራ አጥብቃ እንደምታወግዝ ይፋ አድርጋለች። አሜሪካም ድርጊቱን በማውገዝ አገሪቱ በተሳካ የለውጥ ጉዞ ውስጥ እያለች ይህ መሆኑ ተቃውማለች።