ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በቃኝ የሚሉ አመራሮች እየበዙ ነው። ይህንኑ ተከትሎ ደግሞ ጉዳዩ የሰላም ይሁን የተንኮል ግራ መጋባትም እያስነሳ ነው። ሊቀመንበሩ አቶ ሽፈራው በቃኝ ማለታቸው በተሰማ ማግስት ምክትላቸው አቶ ሲራጅ ፍርጌሳም በበቃኝ ተቀላቅለዋቸዋል። 

ቀደም ሲል በወላይታ ዞን የተጀመረው ራስን ከሃላፊነት የማግለል ጉዳይ በአብዛኞች እንደሚታሰበውና በሌሎች አገሮች እንደተለመደው ከቀናነትና ስህተትን ከማመን በመነጨ ከሆነ አርአያነቱ አርጅተው ለሚንገዛገዙ ፖለቲከኞች ታላቅ ትምህርት እንደሚሆን አስተያየት የሚሰጡ አሉ።

በሃዋሳ በቅርቡ የተካሄደውን አሰቃቂ ወንጀል ተከትሎ በተደረጉ ውይይቶች ሕዝብ በግልጽ አቶ ሽፈራውን እንደማይፈልግ አመልክቷል። ቀደም ሲል ጀምሮ በሕዝብ የማይደገፉት አቶ ሽፈራው ከሙስና ወንጀልና ከብሄረሰቦች ግጭትና መፈናቀል ጋር በተያያዘ ክስ ሲቅርብባቸው የኖሩ ባለስልጣን ነበሩ።4

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቅ ብለው እሳቸው እንዳሉት ” የህዝብ ጥያቄ ስለሆነና የመፍትሄው አካል ለመሆን ስል ለቅቄያለሁ” ያሉት አቶ ሽፈራው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጭተው የህወሃትን ሙሉ ድጋፍ ያገኙና በዶክተር አብይ የተሸነፉ መሆናቸው የወቅቱ አስገራሚ ዜና ነበር። 

በተመሳሳይ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት፣ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ድርግታቸው ይፋ አድርጓል። አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን በማቅረብ ሃላፊነታቸውን ለቀዋል።

በየካቲት ወር የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሲራጅ መልቀቂያቸውን እንዳቀረቡ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ ተክተዋቸዋል። አቶ ማትያስ የደኢህዴን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል። አቶ ሲራጅ ያቀረቡት ምክንያት ባይገለጽም ቀደም ሲልም ጀመሮ በስፋት ተቃውሞ የሚቀርብባቸው ሰው ነበሩ።

ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አቶ ሽፈራውን ተክተው የደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ድርጅቱ በትናትናው እለት ይፋ አድርጓል። በየተራ ሁለቱም ክፉኛ ተገምገመው ራሳቸውን ከሃላፊነት ለማራቅ መወሰናቸው ታውቋል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *