“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለቅሶ ቤት ስንተዛዘብ

ገና ትኬት ያልቆረጡ፤ የመሞትን ሳይንሳዊ መስፈርቶች ያላሟሉና እድርም አድባርም በመዋቲነት ያልተቀበሏቸው ነፍሳት አጠገባችን ያጣጥራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነፍስ የከዳቻቸው፣ ልባቸው ‹‹እሩጫዬን ጨርሻለሁ›› ብላ ጫማ የሰቀለችባቸው ገላዎች በየማይክሮ ሴኮንዶች ከአጠገባችን ይነጠቃሉ፡፡

አጠገባችን እንደ አውድማ የተከበበችው ለምለም ሳር የመቃብር ስፍራ የሙታን የተፈጥሮ መኝታ ቤትም አቀባበል ለማድረግ እጇን ዘርግታ ትጠብቃለች፡፡ እኔና መሰሎቼ ደግሞ ለሞተው ከንፈር መምጠጥ ለታመመው ኪስ መቧጠጥ ተግባራችን ይሆንና ኑሯችን ይቀጥላል፡፡ 
ጉዞአችንን እንቀጥል ወቅቱ የክረምት መቀበያ ሃምሳ ሜትር ጸሐይ አምስት መቶ ሜትር ደግሞ ዝናብ እየተፈራረቁ ይሸኙናል፡፡ ችምችም ካለው የለቅሶ መንደር ወሬዎች ተከተሉኝ! 
ብዙ ሞት የሚያይ ሰው አለና በሞት መቀለድም ሞትን ያፋጥናልና ሞትን ትቼ ዘለፋዬን በለቀስተኛውና ለቅሶ ላይ ከሚያጋጥሙ ድርጊቶች ላይ ላሳርፍ፡፡ አብዛኛው ሰው ለቅሶ የሚሄደው ሲሞት ቀባሪ ላለማጣት እንጂ በመሄዱ ደስተኛ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሞትን የመርሳት ፍላጎት አለው፡፡ እንግዲህ የሚሄደው ቅር እያለው በመሆኑ ሁሉንም ነገር በትኩረት ይከታተላል፡፡ አስከሬን በሌለበት አስከሬን የሚጠበቅ ከሆነ ብለን እናስብና አንድ ቀልድ አለ፦ አስከሬኑ እየተጠበቀ በጣም ከመቆየቱ የተነሳ ሀሜት ተስፋፋ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ይሄ እኮ በቁሙም ቀርፋፋ ነበር›› እያሉ ከሞተ በኋላም ሲያሙት ድንገት አስክሬኑ ሲመጣ አንደኛው ነገሩን ቀበል አድርጎ ‹‹ስሙን ስናነሳው መጣ፤ እድሜው እረጅም ነው፡፡›› በማለት ተሳለቀ፡፡ ሀሜት ለቅሶ ቤት ያለ ትልቁ ባህሪ ነው፡፡ እንደውም ለቅሶና ቡና መጠራራት ሰው ለሀሜቱ ምላሱን እንዲያሾል የሚያደርግ ልዩ መድረክ ነው ባይ ነኝ፡፡ 
ነጠላቸውን አዘቅዝቀው ‹‹ወንድሜን … ወንድሜን፣ አልሰማሁም…. አልሰማሁም›› በሚል ድምጽ የቤቱን ጣራ ይዞት ሊበር እስኪደርስ እንደምስጥ ክምር ጩኸት ከአፋቸው እየዘለለ በዙሪያችን ኡኡ የሚሉና ፤ የአንድ ሰው ጩኸት አስራ አንድ ሰው ከሚያደርገው በላይ የለቅሶውን የድግስ አዳማቂ፣ የአለቃቀስ አቃቂር አውጭ፤ ድንኳን ሲያዩ ለመልስ የተጣለ ዳስ የሚመስላቸው፣ (መቼም በእኛ አገር በውልደት ገንፎ በሞት ንፍሮ አይጠፋምና) የውሸት እንባ የሚያነቡ … ወዘተ… ሰዎችን ሳይ አንድም ያዝናኑኛል አንድም ያሳዝኑኛል፡፡ 
እንደተቀጣጠለው ቢሾፍቱ አውቶቡስ ተደራርበው፣ ጫማ ለጫማ እየተሳሳሙ ከለቅሶ ቤት የሚደርሱ ዘመንኛ ለቀስተኞችን አይታችሁልኛል? የማልቀስም ሆነ የማስለቀስ ልምድ ስለሌላቸው ለታይታ ብቻ ጥቁር ልብሳቸውን ከላይ እስከ ታች ገጭ አድርገው ፊታቸውን በቀለማት በማስዋብ ከእድርተኛው ራቅ ብለው ይቀመጣሉ፡፡ አይነኬ አይጠጌ ናቸው፡፡ ከተቀመጡ ደቂቃዎችን ሳይቆዩ የለቅሶ ቤቱን ድባብ ወደ ልደት ይቀይሩታል፡፡ ያዘነን ማጽናናት ባልከፋ ነግር ግን መረን ያለፈ ሳቅና ጨዋታ ሟቹንስ ደስ ይለዋል? (መንፈሱ ለቅሶ ቤት ይኖራልና) ከሁሉም በላይ ደግሞ የእነዚህ ሰዎች ችግር ምን እየተባለ ማፅናናት እንደሚቻል አለማወቅ ነው፡፡ በተለይ አስተዛዝነው ሲወጡ፤ ህመምተኛ እንደጠየቀ ሰው ‹‹ቀላሉን ያርግላችሁ›› የሚልም አይጠፋም፡፡ ምን አለፋችሁ እኔን ባያጋጥመኝም ዓመት ዓመት ያድርስልን የሚልም አይጠፋ ይሆናል፡፡ እንዲህ ብሎ ለሚያጽናና ሰው ብድር መላሽ ያድርገኝ ብሎ መመለስም ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የግድ ሆኖባቸው እንጂ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ምናቸውም አይደለም፡፡ 
ሞትን ማገልገል እንጀራው ያደረገ ሰው መቼም እድሜው ይረዝማል ቢባል፣ ምችን ምች መች ይመታዋል ነገር ነውና ሁሌም ሰው ሲሞት ተግባራቸው ቀይ ምስርና አልጫ ክክ በጥድፊያ የሚያዘጋጁ የእድር ‹‹ፋኦ››ዎችንም አልዘነጋ ሁም፡፡ እነዚህ ሰዎች የወጥና የእንጀራ ጣእሙን በማሰብ ይመስለኛል ሁል ጊዜ በምግብ ነክ ስራዎች ላይ የሚሰማሩት፡፡ 
እንግዳ የሆኑ ነገሮችን ለቅሶ ቤት ውስጥ ማየታችን ትልቅ ቅኔ ነው፡፡ በተለይ ኮሜዲያን የሆኑ ሰዎችን መመልከት፡፡ ማለቴ ሰው መጀመሪያ ያው ሰው ነው፡፡ ቀጥሎ ስራ ይኖራዋል፡፡ እንግዲህ ስራው ማንነት ይሆንና ያርፋል፡፡ ከዚያ ከሰውነት ተራ ያባርራል፡፡ እናም ኮሜዲያን ሰው ቢሆኑም ስራቸው ከሰውነት ተራ አውጥቷቸዋል፡፡ ኮሜዲያን ተብለዋል፡፡ በጥንት ዘመን ቧልተኛ ነበር የሚባሉት፡፡ እንግዲህ ሲያዝኑም እየቀለዱ ይመስልባቸዋል ማለት ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ያሳዝኑኛል፡፡
አንዱ ኮሜዲያን እንዲህ ብሎ ተርኮ ነበር፤ ‹‹ማግባት እንደማልፈልግ ብነግረውም ጭቅጭቁን ያልቻልኩት አንድ ሽማግሌ ጎረቤቴ የሆነ ሰርግ ላይ ተጠርተን ‹‹ቀጣዩ ሙሽራ አንተ ነህ›› ብሎ አናደደኝ፡፡ በሌላ ጊዜ ሰው ሞቶ ለቅሶ ላይ አገኘሁትና ‹‹ቀጣዩ ሰው አንተ ነህ›› አልኩት ብሎ ሲያወጋ አስታውሳለሁ፡፡
ቤት ውስጥ ሳይሆን በለቅሶ ቦታዎች ቀብር ላይ የሚገኙ ዝነኞችን በተመለከተ በተለይም ኮሜዲያን እንደማንኛውም ሰው መሆናቸው የሚረሳበት ሁኔታ ሲፈጠር ሳቅ ይፈጠራል፡፡ እንባና ሳቅ ይቀላቀላል፡፡ ከማፅናናት አንፃር ፍቱን ቢሆንም ቂም ያስይዛል፡፡ ስለዚህ ኮሜዲያን ለቅሶ ቤት ሲከሰት ጥርሱን የሚገልጥለት አለ፡፡ ጥርሱን ሊነክሰው የሚሻም አለ፡፡ በጥርሱ ሊዘለዝለው የሚቃጣውም አይጠፋም፡፡ ኮሜዲው ሌላውን ቢያስቅም እርሱ ግን ያሳዝናል፡፡ 
ቀብር ላይ ብዙ ሰው ፎቶ ተሸክሞ የሚያለቅ ሰው ለምንድነው? ፎቶ አይናገር አይጋገር፡፡ እንዲያው አትታዘቡኝና ፎቶ አስቂኝ የሚሆንበት ሁኔታ ጎልቶ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም ለቅሶ ላይ ስለሟች የሚነበበው የህይወት ታሪክ ለአብዛኛው ሰው ውሸት ከመሆኑ አንፃር ከሚፈጠረው መተዛዘብ ስለሚመነጭ ይመስለኛል ፎቶ ተሸክመው ወደ መቃብር ስፍራ የሚመጡት፡፡ 
የነገሬ መቋጫ ገናዥና ለከፋን የተመለከተ ይሆናል፡፡የሟችን አስክሬን ሊገነዝ የተዘጋጀ ሰው ገላ ላይ ያልበቃት ነፍስ አልወጣሁም ስትለው ለበርካታ ጊዜ ሲደመጥ የቆየ ገጠመኝ ነው፡፡ ታዲያ መታገሉ አድክሞት ወደ ቤቱ ማምራቱ ባይቀርም ክፍያ እንዳይጠይቅም እፍረት ይይዘዋል፡፡ ገንዞ ቢሆን ያለ ቫት ደረሰኝ የሚቀበለው ገንዘብ የእለት ጉርሱን ታሟላለት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያልበቃትን ነፍስ ለማራዘም ብሎ ዋጋ ባለማውጣቱ የልፋቱን ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ይህ ነገር ለቀጣይ ሟቾች ማሳሰቢያ ይሁንልኝ፡፡ የመነጠቅ እንቅልፋችሁ ሳይመጣ ባታጣጥሩ ይመከራል፡፡ ካልሆነ ግን እንዲህ አይነቱ ክስተት ሲፈጠር እድር ካልሆነም ቤተሰብ ገናዥ የሰራበትን ሊያስብለት ይገባል፡፡
ወደ ለከፋው ልመለስ፤ ልክ እንደ ሰርግ ቤት ሁሉ ለቅሶ ላይም ጠበሳ አይጠፋም፡፡ ይህንን በተመለከተ በቅርቡ የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፦ አንዲት ሴትዮ ባሏ በሞተ በዘጠኝ ወሯ ወለደች፡፡ የወለደችው ግን ከሟች አልነበረም፡፡ የባሏን ሞት በማፅናናት ሂሳብ ሌላ ወዳጅ አቅርባ ስለነበር ነው፡፡ እናም ማፅናናት አዋጭ ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ባሏ የሞተባት ሌላኛው ሴት በነጠላዋ ተከናንባ ስታነባ (የውሸት ይሁን የእውነት አይታወቅባትም) አንዱ ጠጋ ብሎ ‹‹ አይዞሽ እርሱ ቢሞት እኔ አለሁ አገባሻለሁ›› ሲላት በሲቃ ውስጥ ሆና ‹‹አዝናለሁ ወንድሜ ተቀድመሃል ትናንትና ሳጥን ይዞ የመጣ ሰው ቃል ገብቶልኛል›› አለችው፡፡ 
ሞት ከተበየነባቸው ሰዎች ይልቅ ለሟቹ ሽኝት በማድረግ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ድርጊት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተራው ደርሶ ወደዚያኛው ዓለም እስክንሄድ ያለነውና በሰልፍ ላይ ያለነው በተለይ በለቅሶ ቤት ቆይታችን ብዙ ሊያስተዛዝቡን የሚችሉ ድርጊቶችን ስናከናውን ታይተናል፡፡ አሁንም ሟች እስካልጠፋ ድረስ እርስ በእርስ የምንተዛዘብባቸው የለቅሶ አውዶች ይቀጥላሉ፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን

0Shares
0