ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ምኞታችን እንዲሳካ ከቸልተኝነት የፀዳ ጥንቃቄ ያስፈልገናል!

‹ሌብነትን እምቢኝ አሻፈረኝ ያላችሁ ዕለት እኔን እንዳመሠገናችሁ ይቆጠራል፡፡ ይኼ ክልል የእኔ፣ ይኼ ወሰን የእኔ ነው ውጡልኝ መባባልን አቁመን፣ በፍቅር ተግተን ለአገራችን መሥራት የጀመርን ዕለት ያኔ ምሥጋናችሁ በሌላችሁበት እንደደረሰን ቁጠሩት፡፡

ልጆቻችሁን ከፊደል እኩል የአገር ፍቅር አስተምራችሁ ኢትዮጵያዊነትን ያላበሳችኋቸው ዕለት ያኔ ምሥጋናችሁ በፍሬ ይደርሰናል» ያሉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አደራ የሰጡት ቃል ሆኖ ይታወሳል፡፡
‹‹ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ›› በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ሕዝባዊ የድጋፍ ሠልፍ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹ኢትዮጵያን ሊተካ የሚችል አንዳች ነገር አልተሰጠንም፤ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምትመለስ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አይኑራችሁ፡፡
‹‹ገና ኃላፊነት ከተረከብን መንፈቅ ሳይሞላን ፊት ለፊታችን እንደ ተራራ የተቆለለውን ግርዶሽ ሳንገፍፍ ፊት ለፊታችሁ ቆመን ምሥጋና ለመቀበል የሚያስችል አቅም አላደረጀንም፡፡ ነገር ግን ጥላቻ አክስሮናል፣ አጉድሎናል፣ ፍቅር ግን ያተርፋል፤ ያሻግራል ብላችሁ በተስፋ ተሞልታችሁ በምሥጋና ጀምራችኋልና በፍቅርና በአንድነት ጀምሮ መጨረስ የተሳነው ስለሌለ ለዛሬው የፍቅርና የምሥጋና ቀን መድረስ ከሚገባን ማማ የሚያደርሰን የመጀመርያው ጡብ መቀመጡን ያሳያል›› ካሉ በኋላ ‹‹የዛሬዋን ቀን እንድናይ የዛሬዋን ቀን ያላዩ፣ እንድንኖር ሲሉ የሞቱ፣ እንድንከበር ሲሉ የተዋረዱ፣ እንድንፈታ ሲሉ የታሰሩ፣ ለሕይወታችን ሕይወታቸውን የገበሩ ሰማዕታትን በዚህ የከበረ ቦታ ቆመን ልናመሠግናቸው ይገባል፤ እነርሱ ያለ እኛ ሊኖሩ ይችሉ ነበር፡፡ እኛ ግን ያለ እነርሱ መኖር አይቻለንም›› በማለት የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ለከፈሉ ቀደምት ታጋዮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ያየም የሰማም እውነታውን የሚያረጋግጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ ንግግር እያንዳንዱ አንቀጽ በጭብ ጨባና በሆታ የታጀበ ነበር ፡፡ ‹‹አገራችንን ከወደድን የምትባክነው እያንዳንዷ ሳንቲም የኢትዮጵያ ናት ብለን እንሳሳላት፤ አገራ ችንን ከወደድን የምትጠ ፋው እያንዳንዷ የሥራ ሰዓት የኢትዮጵያ ናት ብለን እንቆርቆርላት፤ አገራችንን ከወደድን የሚበላሸው እያንዳንዱ ንብረት የእናቴ የኢትዮጵያ ንብረት ነው ብለን እንጩህላት፣ ኢትዮጵያን ሊተካ የሚችል አንዳች ነገር አልተሰጠ ንምና፡፡
‹‹ግለሰቦችን ከሕዝቦች እንለይ፤ እሾሁን ከጽጌሬ ዳው እንነጥል፤ አይጥ በበላ ዳዋ አይመታ፤ በአንድ ጠማማ ዛፍ ምክንያት ደኑ አይለቅ›› በማለት ሕዝቡ እንዲተቃቀፍ በማድረግ መዋደዱንና አንድነቱን እንዲገልጽ፤ ፍቅር ከዚያው ከሰልፉ አደበባይ እንዲጀመር ምሳሌ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ በንግግራቸው ማሳረጊያ በተለያየ አቅጣጫ ሕዝቡን እጅ ነስተው ሲያበቁ ወደመቀመጫቸው ተመለሱ ፡፡
ጥቂትም ሳይቆይ እርሳቸው ከተቀመጡበት ከመድረኩ በስተቀኝ የቦምብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ ፍንዳታው ሲከሰት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወንበራቸው በመነሳት ወደ ፍንዳታው አቅጣጫ ሲመለከቱ አጃቢዎቻቸው መጥተው በፍጥነት ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ ይህ ድርጊት በወቅቱ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከተሰራጩ ምስሎች በግልፅ ይታያል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን መሰሉን ደስታና ሀዘን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ስናስተውል፤ በዚምባቡዌ ቡላዋዮ ከተማ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ የኤመርሰን ምናንጋግዋ የድጋፍ ሠልፍ ላይ ተመሳሳይ የቦምብ አደጋ ደርሶ ነበር፡፡
በሁለቱ አገሮች የተከናወኑት ሠልፎች የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ሊደግፋቸው የወጣ ሕዝብና የተፈጸመ የቦምብ አደጋ ፡፡ 
በአዲስ አበባ የተከሰተው የቦምብ ፍንዳታ በፖሊስ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ ሲዘገብ፤ በዚምባብዌ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በፕሬዚዳንቱ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራ ነው ሲሉ የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ከመስቀል አደባባዩ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ 26 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካ ሄደባቸውም ይገኛል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣የ14 ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አምስቱ ኮማንደሮች፣ አንድ ምክትል ኮማንደር፣ አንድ ምክትል ኢንስፔክተር፣ ሁለት ሳጅኖች ሲሆኑ፣ 16ቱ ሌሎች ተጠርጣሪዎች እንደሆኑም እየተገለፀ ነው፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው በመስቀል አደባባይ የተገኘውን ሕዝብ መጠበቅ ሲገባቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ቦምብ ፈንድቶ 165 ሰዎች እንዲጎዱ አድርገዋል በሚል በመጠርጠ ራቸው ነው፡፡
የምርመራው ሒደትም የቀጠለ ሲሆን፣ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ.ቢ.አይ.) በምርመራው ዕገዛ ለማድረግ ኢትዮጵያ በመግባት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የአሜሪካው 35ኛው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ. ኬነዲ አሜሪካንን ለመምራት እ.አ.አ በ1960 ሥልጣን ሲይዙ 43 ዓመታቸው ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ጥቂት ዓመታት ለአሜሪካን ገናናነት በርካታ ተግባራት ያከናወኑት ኬነዲ እ.አ.አ. በኖቬምበር 22/1963 በዳላስ ግድያ ሲፈፀምባቸው የአገሪቱ የደህንነት ተቋም በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ ህይወታቸውን ሊታደግ ሳይችል ቀርቷል፤ ገዳያቸውም ማን እንደሆነ ሳይታወቅ ተዳፍኗል፡፡
የዛሬው የዚህ ፅሁፍ መነሻ የሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት መከሰት በርካታ ዜጎቻችንን ለጉዳት በመዳረጉ በተከሰተው የጥበቃ ክፍተት ላይ ለማተኮር ነው፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው የጥበቃ ክፍተት ሆን ተብሎ ወይስ በቸልተኝነት? ሚሊዮኖች በተሰባሰቡበት የድጋፍ ሰልፍ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበረው ፍተሻ ከዚህ በፊት ከነበሩት የላላ መሆኑ በርካቶችን አነጋግሯል፡፡
ወደ አደባባዩ ለድጋፍ ሰልፉ ከሚያመሩት ውስጥ በጥቂቶች አካባቢ ፍተሻ ሲደረግ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በቡድን እየዘፈኑ የሚመጡትን ሳይፈትሹ የማሳለፍና በአንዳንድ ቦታዎችም ፍተሻው የላላ መሆኑ ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አብረዋቸው የነበሩ ባለሥልጣኖች በነበሩበት መድረክና በሠልፉ ተሳታፊዎች መካከል የነበረው ርቀት በጣም የተቀራረበ መሆኑ የመጀመሪያው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ሲሆን፤ ጥቃቱ እንደተቃጣ ቦምቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ አብረዋቸው በነበሩ ባለሥልጣኖች ላይ ግድያ ቢያስከትል ሊደርስ የሚችለውን መጠነ ሰፊ ጥፋት እንዴት መግታት ይቻል ነበር?
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አዲስ ለውጥ የማይፈልጉና ጥቅማቸው እንደነካባቸው የማይፈልጉ ወይም የተፈጠረውን ክፍተት_ በመጠቀም ከሚከሰተው የእርስ በርስ ዕልቂት ለመጠቀም የሚሞክሩ እንዳሉ እንደምን መገንዘብ ይሳነናል? ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፉን በሚያሳይበት ወቅት ይህንን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ አካላት የሆነ ተንኮል እንደማያስቡ እንደምን ይዘነጋል? 
የሕዝቡን አንድነት በመሸርሸር ለመለያየትና የተጀመረው ለውጥ እንዳይሳካ ለማድረግ የሚታትሩ እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የጥበቃውን ክፍተት ያጤኑና የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ያለሙ አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ ቀደም ሲል የጥቂት አገራትን የግድያ፣ የጥቃትና የጥፋት ክስተት እንደተ መለከትነው በአሁኑ አይነት ቸልተኝነታችን ከቀጠልን አሳዛኝ ክስተት የማናይበት ሁኔታ የለም፡፡ 
የአሁኑን የቦምብ ጥቃት እንደ ተሞክሮ በመውሰድ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በልዩ ልዩ ሥፍራዎች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ከአደጋ የፀዱ ማድረግ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩን ማጠናከር፣ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ክፍተቶችን ማስወገድ የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ለማሳካት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአደጋዎች መጠበቅ አገሪቱን ወደ አደጋ ሊመልሱ የሚችሉ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ ነው፡፡ በርግጥ አንድ ስለ ደህንነት አጠባበቅ በቂ ሙያ የሌለው ሰው ታላቅና እስከዛሬ በርካታ አገራዊ ጥቃቶችን ሲመክትና ዜጎቹን ሲንከባከብ ለኖረ የደህንነት መዋቅር መምከር አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ለቀጣዩ ደህንነታችን ሲባል ትኩረት እንዲደረግበት ማሳሰብ የዜግነት ግዴታ ነው፡፡ 
ባለፈው ቅዳሜ በተከሰተው የቦምብ ጥቃት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕይወት ለማዳን መስዋዕት የሆኑ ወጣቶች መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን በማመን ነበር ያንን መስዋዕትነት የከፈሉት፡፡ ነገአችንን አጨልመው፣ ከለውጥ እርምጃችን ሊያደናቅፉን የሚሞክሩትንና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚጥሩትን በንቃት መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው፡፡
ከልዩነት ይበልጥ አንድነት፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ታጋሽነትን በማስቀደም አገራችንን መውደዳችንን በተግባር በማሳየት ጠቅላይ ሚኒስትራችን የጣሉብንን የአደራ ቃል ጠብቀን በተግባር የተረጋገጠ ውጤት ማስመዝገብ መቻል ይኖርብናል፡፡ ምኞታችን እንዲሳካም ከቸል ተኝነት የፀዳ ጥንቃቄ ያስፈልገናል!

አያሌው ንጉሤ   አዲስ ዘመን