ኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ትላንት በሶማሌ ክልል ነዳጅ ማውጣት መጀመሯን ተከትሎ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ተግባሩን እንደሚቃወመው አስታወቀ።

ነዳጅ የማውጣት ስራውን ለማስቆምም የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ የግንባሩ ቃል አቀባይ አብዱልቃድር ሃሳን አዳኒ ከቢቢሲ ሶማልኛ አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

”የሶማሌ ክልል ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት እስካላገኙ ድረስና ለረጅም ጊዜ የቆየው የሶማሌ ህዝብና የኢትዮጵያ መንግስት አለመግባባት እስካልተፈታ ድረስ፤ የነዳጅ ማውጣት ስራው የህዝቡን ሃብት ያለአግባብ እንደመጠቀም ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ አካል ስላልሆንን፤ ምንም አይነት ባህላዊ ቁርኝት የለንም፤ ስለዚህ የሶማሌ ህዝብን የተፈጥሮ ሃብትና መሬት ለሌላው ጥቅም ማዋል የማንቀበለው ነው በማለት ግንባሩ አቋሙን ገልጿል።

”መሬታችን በሃይል የተወሰደብን ሲሆን፤ እሱን ለማስመለስና የተጀመረውን ነዳጅ የማውጣት ስራ ለማስቆም የምንችለውን ነገሩ ሁሉ እናደርጋለን። ምክንያቱም በክልሉ ያለው ሃብት ለክልሉ ህዝቦች ብቻ ነው መሆን ያለበት፤ ማንም ሊጠቀመው አይችልም ሲሉ ቃል አቀባዩ ጨምረዋል።

ምንም እንኳን ግንባሩ በይፋ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባይነጋገርም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም ቡድኖች ያቀረቡትን የውይይት ሃሳብ ግን በበጎ ጎኑ እንደሚመለከተው ገልጿል።

አቶ አብዱልቀድር አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የግጭት ዋና ምንጭ የሆኑት ጉዳዮች ላይ በማተኮር አዲስ ምዕራፍ የመጀመር አጋጣሚው እንዳላቸውም ጨምረው ተናግረዋል።

ግንባሩ ኤርትራን ዋና መቀመጫው ያደረገ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት አስመራ አማጺዎችን ትደግፋለች ሲከስ ነበር፤ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርንም አሸባሪ ብሎ ፈርጆታል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ከለቀቃቸው የፖለቲካ እስረኞች መካከል የግንባሩ አመራሮች ይገኙበታል።

ከሌሎች ቡድኖች በተለየ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ከ1976 ጀምሮ የሶማሌ ራስ ገዝ አስተዳደር መኖር አለበት ብሎ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ነበር።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የቻይናው ነዳጅ አፈላላጊ ድርጅት ላይ ግንባሩ በ2001 ጥቃት ፈጽሞ 74 ኢትዮጵያውያንና ዘጠኝ ቻይናውያን መሞታቸው ይታወሳል።

በዛው ዓመት የኢትዮጵያ መንግስት ከአካባቢው የተውጣጣ ግንባሩን የሚዋጋ ልዩ የፖሊስ ቡድን አቋቁሞ ነበር። በዚህ ምክንያት ግንባሩ ከአካባቢው ለቅቆ እንዲሄድ ተገዶ የነበረ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ አባላት በአሁኑ ሰአት በውጪ ሃገራት ይገኛሉ።

BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *