ያስቃል። ያዝናናል። ከሃያ ሰባት ዓመት በሁዋላ ኦህዴድ ለመሪነት ቢበቃ ” ገብጋባ ” ተባለ። ለልጣን የቋመጠ ሆነና ተፈረጀ። እናም ኦህዴድ ሲመራ አገር እንደምትበተን ይነገር ጀመር። ሃያ ሰባት ዓመት በጠቅላይ ጨዋታ ስልጣን ላይ ጉብ ያሉ ” ገብጋባ፣ ስግብግብ” እያሉ ኦህዴድን ሲፈርጁት መስማት የዘመኑ ድንቅ ድርሰት ሆነ። ከፈራጆቹ በስተቀር!! ፈረንጆቹ ማለቴ አይደለም። ሃያ ሰባት ዓመት አይበቃም ማለት ወይስ … ማን ነው ገብጋባ፣ ሥስታም? ሆዳም? ከርሳም? የስልጣን ሱሰኛ….

መዝሙሩ ተቀይሯል። ሽርደዳ ቢመስልም እውነት ነው ” ጌታዬ ሆይ ህይወቴን እንደ ኢቲቪ ቀይርልኝ” የሚል ምልጃ እየተሰማ ነው። ኢቲቪ ራሱ የጥንቱ መሆኑንን እስክንጠራጠር ድረስ አስገራሚ ሆኗል። በሌላ በኩል የገገሙ አሉ። እንደ ጎበጡ የቀሩ ሲያቅራሩ ይሰማል። አሁን ሁሉም ዓይነት ድምጾች ይወረወራሉ። ቦንብም የሚያስወረወሩ፣ ገጀራ የሚያስሉ፣ ለማጫረስ በጀት የሚመድቡ፣ በለውጥ ስካር ውስጥም የሚዋኙ ……. ሁሉንም የተሸከመችው ኢትዮጵያ አዳኞቿንና ቀባሪዎቿን ተሸክማ እያቃሰተች ነው። ደስተኛ አይደለችም። ያኮረፉትን ፈርታለች … ለጊዜው!!

ሰላም በያላችችሁበት። ከእስር ተፈታቹህ ታሪካችሁን እስኪሰቀጥጠን የምትናዘዙ እንኳን ለዚህ አበቃችሁ። ኢቲቪ ህይወቱ ተቀይሮ ለማየት የበቃቹህ፣ ኢትዮጵያ ዳግም ስትሰበክ ለመስማትና ለማየት ላደረሳቹህ፣ ልሳናቹህ ለተከፈተ፣ ይህ ሁሉ ላስኮረፋቹህ፣ ይህ ለውጥ ላሰከራቹህ፣ ለውጡ ለቆጠቆጣቹህ … ለሁላችሁም ወገኖች ሰላም ሻሎም … ያበደው ነኝ።

ቦሰና የድንግልን ስም እየጠራች ታነባለች። ለወትሮው የጠላችው ኢቲቪን የሚዘጋባት ጠላቷ ሆኗል። አዲሡን መሪ ትባርካለች። ” አምላክ ይጠብቅህ” ትለዋለች። ውሻዋ ደጎል የባህር ዳር ሰልፍ ይደገመ እያለ ይጠይቃል። የ”ውሾች” ሰልፍ እንዲደረግ አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ግን አይፈልግም።

Related stories   GERD second filling ends Egypt’s monopoly of Nile

የሰሞኑ ጨዋታ ሁለት ነው። የዓለም ዋንጫና የኢትዮጵያ ፖለቲካ። አንዳንድ ተንታኞች በብዙ ሊከፍሉት ይችላሉ። በነገራችን ላይ ተንታኝ ሲባል ግን ምን ማለት ነው? እንደ እኔ ግራ የገባችሁ ካላችሁ ተወያዩበት። አጓጉል ትንተና፣ አጓጉል ማብራሪያ፣ ያልበቁ ሰዎች መቀባጠር … ከስህተታቸው በላይ ድፍረታቸው … ሌሎቹ ደግሞ ሲሳደቡ ያስቃሉ። ራሳቸውን ማየት መቼ እንደሚጀመሩ ማሰብ በራሱ ያደክማል። ተስፋም ያስቆርጣል። ኢትዮጵያ ከራሳቸው ጋር የሚታረቁ ወገኖች ረሃብ ላይ ነች።

ያበደው ይበርደዋል። ጭልጥ ባለው በጋ ውስጥ ሆኖ ቆፈን ቆፈን ይለዋል። ” እኛ ካልመራን” የሚሉት ወገኖች አዲሱ ለውጥ ለምን እንዳስፈራቸው ሊገባው አልቻለም። የጎሳ ፖለቲካ ደራሲና አቀንቃኝ ሆነው በማሳነስ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመት መሩ። መሩ። ሁሉንም ካፍ እስከ ገደፉ ተቆጣጠረው ጨፈሩ። አይበቃም?

ያበደው ምራቁን ጢቅ አደረገ። ሌሎች ሲመሩ ምን አሉ? ጠየቀ። ፌደራሊዝም ማለትስ ምን ማለት ነው? አብላጫ ህዝብ፣ አብላጫ ድምጽ፣ አብላጫ መቀመጫ፣ የስልጣንና የውክልና ማመጣጠን ምን ማለት ነው? ደግሞም ምርጫው በገሃድ የተከናወነ ነው። ሰፊ ህዝብና ሰፊ ቆዳ የያዙ ፖለቲከኞች በሚወክሉት ህዝብ ብዛት መሰረት መሪ ለመሆን ቢያድሙ ምን ችግር አለው? ሽግሽግ ቢያደርጉና ቅስቀሳ አካሂደው መሪ ቢሆኑ ምን ነውር አለው? ያበደው አናቱ ጋለ። ሃያ ሰባት ዓመት እኮ …. ያበደው ዞረበት!!

የደህንነት ተቋማችንን አየነው። እድሜ ለአማራ ክልል ቲቪ ፕሮግራም። እድሜ ለኢቲቪ ቃኘነው። በድብቅ የምንሰማውን አየነው። ጥፍር የሚነቅል፣ ቁስል በጉጠት የሚቦጭቅ፣ የሚያኮላሽ፣ በኤሌትሪክ የሚጠብስ፣ በክቡር የሰው ልጆች ዘርና ገላ የሚሳለቅ፣ ሃፍረትን እርቃን እያወጣ የሚገርፍ፣ ደም እያፈሰሰ ይሚያጠጣ፣ በመቀመጫ እንጨት የሚከት…. ይህንን ሁሉ ታሪክ የሰማ አያዝንም? አያለቅስም? አያመውም? በራሴ ላይ ቢደርስ አይልም? …. ሁሉም ይቅር ይህንን ነብሰ በላ ድርጅት ሲመሩ የነበሩ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከመጠየቅ ይልቅ ” ለምን ከስልጣን ተነሱ” ብለው የሚያኮርፉትን እንዴት እንደግፍ? ያበደው ህዝብን ሆኖ ጠየቀ።

Related stories   Ethiopia leading East Africa in FDI: Ambassador Hirut

እየተወራጨ እንዲህ አለ። እናንተ ወላዶች፣ እናንተ አባቶች፣ አናንተ ወገኖች አድምጡ። ረጋ በሉና አስቡ። ለአፍታ ሰው ሁኑ። የዚህን ሁሉ ግፍ ክምር አስቡ። በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በማዕከላዊ፣ በማይታወቁ ዝግ ቤቶች የተፈጸመው ግፍ መኖርን አይፈታተንም? በራስ ዜጋና ህዝብ ላይ ይህ እንዴት ይፈጸማል ብላችሁ እንዴት አትጠይቁም። እንዴት አታዝኑም። እንዲህ ያለውን ክፉ ድርጊት  ለማውገዝ ሰው መሆን አይበቃም? ያበደው ጮኸ!! ደግሞ ጠየቀ በዚህ ሁሉ ክፉና ዘግናኝ ድርጊት ለመደሰት መሞከርና ይህንኑ ደስታ ለማስቀጠል የሚደረገውን ሩጫ ረገመ።

ጎሳና ዘር ሲቀድም ክፉ ነው። ጎሰኛነት ከሰውነት ተራ ያወጣል የሚባለው ለዚህ ነው። በሰዎች ስቃይ እየተደሰቱ እድሜ ልክ ለመኖር ፈቃድ መጠየቅና ፈቃዱ አይታደስም ሲባል ማልቀስና ክፋት መሸረብ አያዋጣም። ህዝብን እዩ። ” ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች” እያሉ መዛበት አብቅቷል። ጥቂት … ወደ ብዙዎች ተቀይሯል። አሁን ጸቡ ከመሪዎች ጋር አይደለም። ከህዝብ ጋር ነው። ከህዝብ ጋር የሚደረግ  ጦርነት አያዋጣም። ሕዝብን ያሸነፈ የለም። እናም …. ቦሰና እንደምትለው ” ተመለሱ” ደጎል በውሽኛ ይጮሃል። እናም እናንተ ልበ ድድሮች ስሙ። ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ።

እናንተ በለውጡ የሰከራቹህ ” የመደመር” ፖለቲካ ያልገባችሁ ከእልህና ቂም ተለዩ። ፍቅር ያሸንፋል ሲባል ለውጡ ለሁሉም እንደሆነ ማሰብን ያካትታል። ፍቅር የሚያሻቸው ፍቅር የማያውቁ ናቸው። ፍቅር የማያውቁትን ማፍቀርና ማስተማር ለውጡን ይበልጥ ቋሚ ያደርገዋል። ያፈጥነዋል። እንከኑንን ይቀንሰዋል።  ቦሰና በመሃይም አንደበቷ ትማጸናለች። እባክችሁን ከስካር ያልወጣችሁ ተው!! ተረጋጉ!!

Related stories   Egypt considers alternatives as Renaissance Dam second filling looms

የመለስ ሌጋሲ ይውደም። መለስ ቢወድምም ሌጋሲው አሁንም ደም ለመጠጣት አስፍስፏል። ለዚሁ ክፋት አትተባበሩ። ይህ ክፉ መንፈስ ጥዩፍ ነው። ተጠየፉት። ኢትዮጵያችንን ያወድማታል። የዛኔ አማራ ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ወላሞ፣ ትግሬ… ብሎ ነገር የለም። ኢትዮጵያ ዝላላች። ጊዜው በማስተዋል መራመደን ይጠይቃል። ሁሉም ለአገሩ ዘብ መቆም አለበት። ዘብ ቁሙ!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖር ዘንድ መፈክር አይጠቅምም። መደመር አጥፊውንም እንደሚያካትት መረዳት ግድ ነው።

ማንም ሆነ ማን ጅብነት አያዋጣም። ያለ ሰዓቱ ከጎሬው የወጣ ጅብ ወደ ጎሬው ለመመለስ የተፈጥሮን ህግ እስካልታሰ አይሳነውም። ባለፈበት ባገደመበት የድንጋይ ናዳ ይገጥመዋል። እናም ደንብሮ በሮጠበት አንዱ ስርቻ ውስጥ በድንጋጤና በእሩምታ አብዶ ይቀረቀርና ያርፋል። ይሞታል። ብዙም ከሆኑ ይሞታሉ። አንዳንዴም ጅቦቹ ራሳቸው ይበላላሉ። ግን ጣጣቸው ለሌሎች ይደርሳል። ከዚህ ይሰውረን ሲል ያበደው ጸለየ!!

አሁን ደጎል ንፋስ ይፈልጋል። ስንመለስ ኢቲቪ ላይ እንጣዳለን!! ያልሰማችሁ ስሙ። ኢቲቪ ተመልሶ እንዳይታመም እንጸልይ!! እንትጋ!! እንተባበር!! የአገር መከላከያ ከምሽግ ህይወት ልትገለገል ነው። ከደፈጣ ህይወት ልትላቀቅ ነው። ኢትዮጵያም በጀቷን ከሚያነክተው ትርጉም አልባ ጦርነት ልትላቀቅ ነው። አብይ አህመድ ካቢኔዎትን ፈትሹ!! ሰላም እንሰንብት!! ኦህዴድ ገብጋባ  አይደለህምና ከቀድሞው ስህተት ተምረህ ሁሉንም እያሳተፍክ ለታላቁ ህዝባዊ ምርጫ ንዳን። የለውጥ ሃይሎች በሙሉ ተባበሩ። የከፋችሁም ልቦናችሁን አድምጡና ለውጡን ተቀላቀሉ። እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንም እንዳን!! ነጻ እንውጣ!! ቻው!!

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *