ጀርመኖች የዌመር ሪፐብሊክ የውድቀት ታሪክ ምን እንደነበረ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከዚያ ውድቀት ወዲህ፤ ‹‹ሰርድሪኽ›› የጎተተባቸውን መከራ ፍፁም አልዘነጉትም፡፡ ሐገራቸው ለሁለት መከፈሏ ቢቆጫቸውም ከዚያ መዐት ተርፈው፤ ምዕራብ ጀርመኖቹ ‹‹ዜሮ ሰዓት›› ብለው ከሚጠሩት ከ1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ፤ ጉዟቸውን እንደ አዲስ ቀጠሉ፡፡ የዌመር ሪፐብሊክ የፈፀማቸውን ስህተቶች ላለመድገም በብርቱ እየተጠነቀቁ አዲስ ሐገር እና ህብረተሰብ ለመፍጠር ጉዞ ጀመሩ፡፡

ይህን ስሜት እና አመለካከታቸውን ያጤኑ ጎረቤቶቻቸው እና ሌሎች ወገኖች፤ በአስደናቂ ቸርነት ተቀብለው በኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ትብብሮች እንዲሳተፉ ስላደረጓቸው፤ ጀርመኖች በአስቸጋሪው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን፤ የምዕራቡ ዓለም ሰላምና ብልጽግና ተጠብቆ እንዲዘልቅ ለማድረግ ያገዘ አስተዋጽዖ ለማበርከት ቻሉ፡፡ ምዕራብ ጀርመኖች በዚህ መልካም አቀባበልና ‹‹ማርሻል ፕላን›› ተብሎ በሚጠራው ዕርዳታ ተጠቅመው፤ ሁለት አስርት እንኳን ባልሞላ ጊዜ፤  በአውሮፓ ምድር ግንባር ቀደም  የሚባል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቻሉ፡፡

በሶሻሊስት መርሆች የሚመራው የጀርመን ክፍል (ምስራቅ ጀርመን) መሪዎች በበኩላቸው፤ በምዕራብ ጀርመን በተፈጠረው የኢኮኖሚ ተዓምር እየማለለ ድንበር ተሻግሮ የሚነጉደውን ህዝባቸውን ከስደት ለመግታት፤ በ1961 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ሁለቱን ሐገሮች የሚለያይ ግንብ ለመገንባት ተገደዱ፡፡ ሆኖም ይህ ግንብ ከሃያ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ ፈረሰ፡፡ ግንቡ ሲፈርስ፤ የምስራቅ ጀርመን ህዝብ በገፍ ተሰደደ፡፡ ሆኖም የምዕራብ ጀርመን ህዝብ ለስደተኛው ህዝብ የሚበቃ ዕድል ይዞ አስተናገደው፡፡

ጀርመኖች፤ ከዚህ የአጭር ጊዜ ታሪካቸው አንድ ነገር ተገንዝበዋል፡፡ በረጅሙ የሐገሪቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማ ጀርመናዊ ትውልድ የተፈጠረው  ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት መሆኑን ተረድተዋል፡፡ ጀርመኖች፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለዓለም ሰላም መከበር ያላቸውን ትልቅ ግምት አሳዩ፡፡ ከኋላ ታሪካቸው ጋር ለመታረቅ ሞከሩ፡፡ እብሪት ከተላበሰ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መራቃቸውን የሚመሰክር ጥረት አደረጉ፡፡  

ከሃያ 27 ዓመታት በፊት፤ የበርሊን ግንብ በፖለቲካ ማዕበል ተንጦ በወደቀ በሁለተኛው ዓመት፤ ከአዲስ አበባው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ጽ/ቤት ከዋናው በር ዝቅ ብሎ፤ ከቡልቡላ ወንዝ ደግሞ ከፍ ብሎ ቆሞ የነበረው ቭላድሚር ኤሊች የሌሊን ሐውልት፤ ከአውሮፓ ምድር በተነሳው የፖለቲካ ወጀብ ተገንብሮ ወደቀ፡፡ ታዲያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተገነባውና ሁለቱን ጀርመኖች የከፈለው ግንብ ከነበረበት ሥፍራ ጥቂት ራቅ ብሎ አንድ ዝነኛ ቡና ቤት ነበር፡፡ ታዲያ በዚያ ቡና ቤት የቀዝቃዛው ጦርነት እንደ ቀጠለ ነበር፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከፍ ሲል ከተጠቀሰው የጀርመኖች ታሪክ ልንማረው የምንችለው ጉዳይ አለ፡፡ ቀደም ሲል የአፍሪካ ቀንድ መለያ ባህርይ የሆነውን፤ መጥፎ የጥርጣሬ እና የመዘራጠጥ ባህል በማስወገድ ለልማት ምቹ የሆነ ክፍለ አህጉራዊ ቀጣና ለመፍጠር መስራት እንችላለን፡፡ አንዱ የአንደኛውን ቤት በእሣት ለመለኮስ የማድፈጥ ሥር የሰደደ የፖለቲካ ባህልን በመቀየር፤ ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር አርአያ የሚሆን እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ክፍለ አህጉራዊ ትስስር፤ በክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ብዛት ሳይሆን በኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚፈጠር መሆኑን ተገንዝበን አዲስ ታሪክ ለመስራት መጣጣር ይኖርብናል፡፡ ይህ ኃላፊነት በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ የወደቀ ሸክም ነው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ሐገራት መካከል፤ እውነተኛ እና ጠንካራ ሐገራዊ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው፤ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር መሆኑን ተገንዝበን፡፡ የአንደኛው ሐገር የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት፤ በሌላኛው ቤት በሚኖር ሰላም መሆኑን የሚያስቡ መሪዎች ያስፈልጉናል፡፡ ይህ አመለካከት መሬት ወርዶ በእውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ትስስር ሲገለጥ ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ግንኙነት ይመሰረታል፡፡ በፖለቲካ መሪዎች (ፓርቲዎች) መለዋወጥ የማይናዋወጽ ዘላቂነት ያለው የሐገራት ግንኙነት ይፈጠራል፡፡

ይህ ትውልድ፤ በዙሪያው በሚነሳ ጊዜያዊ ጫጫታ በቀላሉ ከግቡ ሳይናጠብ፤ እንደ ህዳሴው ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ፤ ኢኮኖሚያችን ሊያድግ በሚችለው የተፈጥሮ ገደብ ልክ እንዲያድግ በመጣጣር፤ እንደ ጀርመኖች ባለ ከፍ ያለ የአርበኝነት ስሜት በመንቀሳቀስ፤ ያለውን ውሱን ሐብት ሳያባክን በመጠቀምና ቁጠባን በማጠናከር፤ በእሣት ማጥፋት ግርግር ኃይሉን ሳናባክን እንደ ጀርመኖች ተጠንቅቆ በመጓዝ ተአምር መስራት ይችላል፡፡

ይህ ትውልድ፤ ቀበቶውን አጥብቆ ከሠራ፤ በድንገተኛ ግለት ቱግ ብሎ የማይከስም የመንፈስ ኃይል ይዞ፤ በሰከነ እና ሩቅ አላሚ በሆነ አስተዋይነት እየተመራ፤ ዘመኑ በሚጠይቀው መንገድ መጓዝ ከቻለ፤ ለመጭዎቹ ተከታታይ ትውልዶች የመንፈስ ኩራት ሆኖ፤ ሐገሪቱን ለታላቅ ደረጃ ሊያበቃት ይችላል፡፡ ይህ የቤት ሥራ ከአሁኑ ትውልድ ፊት ተቀምጧል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን የሥራ መንፈስ፣ የትጋት፣ የጽናት፣ የሥራ ፈጣሪነት እና የሩቅ አሳቢነት መንፈስ የሚመለከት ሰው፤ ይህ የመንፈስ ኃይል እንኳን ኢትዮጵያን መላ አፍሪካን ሊቀይር ይችላል ብሎ ተስፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡

እያንዳንዱ ትውልድ የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነትን ይሸከማል፡፡ አባቶቻችን ከኢምፔሪያሊዝምና ከፋሺዝም ኃይል ጋር የመጋፈጥና ነጻነትን የማስከበር ታላቅ ኃላፊነት ተሸክመው ነበር፡፡ ይህን ኃላፊነትም በታላቅ ፅናት አልፈው ሐገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ አብዛኛው ዓለም፤ በፈተናው እየወደቀ ለቅኝ ተገዢነትና ለባርነት ሲዳረግ፤ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ትውልድ ተሻጋሪና ቅስም ሰባሪ የግፍ ፅዋ ለመጨለጥ ሲገደዱ፤ አባቶቻችን በፅኑ ተጋድሎ ከዚያ መከራ ጠብቀው፤ ሰብአዊ ክብርን ያህል ትልቅ ሐብትን ሰጥተውን አልፈዋል፡፡ ይህን ድህነት ያልሰበረውን የሰብአዊ ክብር ስሜት አውርሰውናል፡፡ ይህ የመንፈስ ልዕልና፤ ድህነትን የሚጠየፍ እና ተረጅነትን በሚጠላ ተደማሪ የመንፈስ እሴት ሊጎለብት እና ሊፋፋ ይችላል፡፡

ሀኖም ለዚህ ጥረት መሰናክል ሀኖ የሚታየኝ አንድ ችግር አለ፡፡ ይህም የሳይበሩ ምህዳር ነው፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገጸች የሚታየው ሁኔታ ነው፡፡ የበርሊን ግንብ ፈርሶ በምሥራቅ እና በምዕራብ ተከፋፍለው የነበሩት ጀርመኖች ሲቀላቀሉ የአመለካከት ድንበሩ እንዳልፈረሰ የሚገልጽ አንድ የ‹‹ታይም›› መፅሔት ዘጋቢ፤ ‹‹የበርሊን ግንብ በነበረበት ሥፍራ የምትገኝ አንድ ቡና ቤት ነበረች፡፡ በዚህች ቡና ቤት ዛሬም የቀዝቃዛው ጦርነት እንደ ቀጠለ ነው›› ይላል፡፡ ‹‹ይህች ቡና ቤት ‹VEB-Ost Zone› ትባላለች፡፡ የስሟም ትርጉም ‹‹ያፈጀ የሰዎች ተከር›› (Now-defunct Peoples Enterprises) የሚል ነው›› ሲል ጽፏል፡፡

ይህች ‹‹ቡና ቤት›› የራሽያ ቮድካ የሚጠጣበት፣ ወደ 400 ገደማ የሚሆኑ ቋሚ ደንበኞች ያሏት፣ በየምሽቱ ታዳሚዎቿ ቮድካ ወይም ድሮ በምሥራቅ ጀርመን ይመረት የነበረውን ‹‹ሮትካፕችን›› (Rotkappchen) የተባለ ‹‹መናኛ›› ሻፓኝ የሚቀዳበት፤ በሲጋራ ጭስ የምትታፈን፤ ወልገድጋዳ ወንበሮች የሞሉባት፤ ከፈረሰ ብዙ ዓመት የሆነው አንድ የጀርመን የሮክ ስልትን የሚያቀነቅን የሙዚቃ ባንድ አልበም የሚከፈትባት፤ ጠጭው ጩኸቱ ጋር እየተፎካከረ ወሬ የሚሰልቅባት ቡና ቤት ናት፡፡ ታዲያ ብዙዎቹ ወደዚህች ቡና ቤት የሚመጡት ትዝታን እና ቁጭትን ለማስተናገድ መሆኑን የታይም ዘጋቢ ጠቅሷል፡፡

አሁን የምንገኘው በአዲስ ዘመን ምዕራፍ ቢሆንም፤ ከተጠቀሰችው ቡና ቤት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ነገር የተጠመዱ ሰዎች እያየን ነው፡፡ በትናንት ናፍቆት የሚቆዝሙ፤ በሳይበር የሚሸፍቱት እና የሐሜት ቮድካ የሚጨለጡ ሰዎች አሉ፡፡

የቀዝቃዛው ጦርነት ሲያከትም፤ ዓለም በአንድ ርዕዮተ ዓለማዊ ስርዓት ውስጥ ገባች፡፡ የዚህ ስርዓት ፖለቲካ- ኢኮኖሚ፤ ሊበራሊዝም በሚል የሚጠቀስና በነፃ ገበያ፣ በብዙሃን ፓርቲ ምርጫ ፖለቲካ መርሆዎች የሚመራ ስርዓት ነው፡፡ በዚሁ ማዕቀፍ ሥር ሆኖ ቀኝ ዘመም፣ ግራ ዘመም፣ ‹‹መሀለኛ››፣ ወግ አጥባቂ፣ ለዘብተኛ ወዘተ በሚል የሚጠቀሱ የተለያዩ ቡድኖች ይፋለሙበታል፡፡ የጦፈ ግብግብ ይካሄድበታል፡፡ ሆኖም ሁሉም ለዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መርሆች ታዛዥና ተገዢ ቡድኖች መሆናቸው አንድ ያደርጋቸዋል፡፡

በዚህ ስርዓት እንደ ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› ዘመን አጥፊና ጠፊ አድርጎ የሚያሰልፍ፤ በማይታረቅ ታሪካዊ ቅራኔ የሚያገዳድር ልዩነት የለም፡፡ የሰላ ፉክክር የሚያደርጉት፤ በአቋምና በአመለካከት ልዩነት ባላንጣ ሆነው የሚወዳደሩትና በምርጫ ሂደት ገብተው በህዝብ የተሰጠውን ዳኝነት አክብረው በ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ተጨባብጠው ፉክክራቸውን ይደመድማሉ፡፡ እኛ ዲሞክራሲያዊ፣ ፌደራላዊ፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓት ይዘን በብዙሃን ፓርቲ ስርዓትና በምርጫ ፖለቲካ ውስጥ የምንገኝ ቢሆንም፤ ነገራችን ሁሉ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘይቤ የያዘ ሆኖ ነበር፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ገና የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አላከተመም፡፡ የበርሊን ግንብ አልፈረሰም›› ያሰኝ ነበር፡፡

በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ መሆናችንን ከሚያስረዱኝ ነገሮች አንዱ በሳይበሩ ምህዳር የሚታየው ነገር ነው፡፡ ዜማው፣ ቅኝቱ፣ ይዘቱ፣ ትኩረቱ ሁሉ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የነበረውን ፖለቲካ የሚያስታውስ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ሀገራዊና ዓለማዊ ሥርዓት የደም ያይደለ የሀሳብ፣ የጠብመንጃ ያይደለ የቃል፤ የአይዲዮሎጂ ያይደለ የፖሊሲ፣ የባላንጣዎች ያይደለ የተፎካካሪዎች ትግል የሚካሄድበት ነው፡፡ የአንዱ ድል በሌላው መቃብር ላይ የማይፈፀምበት የትግል መድረክ ነው፡፡ የፖለቲካ ዘይቤው የስፖርታዊ ውድድር ባህርይ ያለው ቢሆንም፤ በእኛ ዘንድ ያለው የጦርነት ጠባይ ያለው ሽኩቻ ሆኖ ስለሚታየኝ ‹‹የቀዝቃዛው ጦርነት››አልቆመም ያሰኛል፡፡ ይህን ችግር በፍጥነት ማረም አለብን፡፡

ሰዒድ ከሊፋ  walta information

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *