«ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤቴን – ቁርጥ ሆኗል መለየቴ – ነጠለኝ ክፉ ዘመን – ከምወዳት ባለቤቴ»
ይህ ከአስር ዓመታት በፊት የተዜመ ዜማ የብዙዎችን ልብ የነካ፣ በተለይ በሁለቱ አገራት መካከል በነበረው ግጭት ቤተሰባቸው ለተለያዩ ህዝቦች እንባን ያራጨ ዜማ ነበር፡፡

ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል፡፡ በሁለቱ አገራት ህዝቦችም መካከል ለሃያ ዓመታት የቆየው የመለያየት ዘመን አብቅቶ የፍቅርና የመደመር ዘመን ተተክቷል፡፡ ያለፉት የመለያየት ዘመናት የፈጠሩት መራራቅም የናፍቆት ረሃብ ሆኖ የሁለቱ አገራት ህዝቦች በአዲስ መንፈስ አዲሱን ግንኙነት በእንባ ታጅበው እንዲያጣጥሙት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡
የመለያየት ታሪክ አብቅቶ የኤርትራና ኢትዮጵያን ህዝቦች የሚያገናኘው ድልድይ በአዲስ መልኩ ተገንብቷል፡፡ እነሆ ሁለት የነበሩትን ህዝቦች አንድ ያደረጉ ግንኙነቶች በይፋ ከተመሰረቱም ሁለት ሰንበቶች አለፉ፡፡ ባለፈው ሰንበት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ የተደረገው ጉብኝትና በህዝቡም የተደረገው አቀባበል በዚህኛው ሰንበትም ቀጥሎ በድምቀት አልፏል፡፡ 
ለዓመታት በናፍቆት የተራበው የሁለቱን አገራት ህዝብ ለማገናኘት በዚህኛው ሰንበትም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተገኙበት የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ማብሰሪያ መድረክ በሚሌኒየም አዳራሽ ተከናውኗል፡፡
በዚህም መሰረት ትናንት ቦሌ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መሸከም ከምትችለው ህዝብ በላይ ሲታይባት አምሽቷል፡፡ መንገዶቹ ሁሉ የሁለቱ አገራት መሪዎችን ምስል በያዙና «የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በፍቅር መደመርን መርጠናል»፣ «የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር በፍቅር ድልድይ ፈርሷል» በሚሉ ጥቅሶች አሸብርቃለች፡፡
ታዳሚዎች የሁለቱን አገራት መሪዎች ምስል የያዘና የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ተስፋ ያዘሉ መልዕክቶች በመያዝና ቲሸርቶችን በመልበስ እና ፊታቸውንም በሁለቱ አገራት ብሄራዊ አርማዎች በማስዋብ ደምቀው አምሽተዋል። ሁሉም ወደ ስፍራው የተጓዘው ህዝብ በቦታ ጥበት ምክንያት ወደ ውስጥ መዝለቅ ባይችልም ከውጭ በመሆን መርሃ ግብሩን ግን ጆሮውን አቅንቶ ይታደማል፡፡ 
በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አንዷለም አሸብር በስፍራው ለመታደም በስፍራው ከተገኙ ታዳሚዎች አንዱ ነው፡፡ እንደወጣቱ ገለፃ የተሰማው ደስታ ቃላት አይገልፁትም፡፡ አገር መምራት ማለት ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠት ማለት ነው፡፡ ሆኖም በጥቂት አካላት አለመግባባት ምክንያት በደም የተቆራኘ ህዝብ ፈጣን ምላሽ ተነፍጎት ለዓመታት ቆይቷል፡፡ ለዚህም የረጅም ጊዜ የህዝብ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ምላሽ መሰጠቱ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ ታሪክም ጭምር ነው፡፡
እንደ ወጣት አንዷለም ገለፃ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው የእርቅ ሂደት በማህበራዊ መስክ የነበረውን ግንኙነት ያጠናክረዋል፡፡ በኢኮኖሚውም አገሪቱ የምትከተለው ሰጥቶ የመቀበል መርህ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች ልማቶቿን ለኤርትራ በማጋራት፣ በተመሳሳይ ኤርትራም ያላትን የተፈጥሮ እምቅ ሀብት ለልማት እንዲውል በማድረግ ሁለቱ አገራት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ይሰለፋሉ፡፡ በግስጋሴውም ፈጣንና ተከታታይ እድገት ለማስመዝገብ በአንድነት መሥራታቸው የሚኖራቸው ጥቅም የትየለሌ ነው፡፡ይህም ኢትዮጵያን በቀጣይ ያቀደችውን ባለሁለት አሃዝ ተከታታይ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ ያግዛታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሸጎሌ አካባቢ ነዋሪ የሆነችውና በዓሉን ለመታደም የተገኘችው ሌላኛዋ ወጣት ማህሌት አባቡ ደግሞ ዳግም የመፈጠርን ያህል ደስታ እንዳገኘች ትናግራለች፡፡ ምንም እንኳን ኤርትራ ዘመድ ባይኖራትም ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል አንድ አገር በመሆናቸው አንድ የነበሩ አገራት በመሆናቸው ዳግም አብሮነታቸው መታደሱ ለቀጣይ ለሁለቱም አገራት እድገት የተስፋ ጭላንጭልን ያሳየ ነው፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል እርቅ መፈጠሩ ከምንም በላይ ሰላም ቀዳሚ ቢሆንም ይህን ተከትሎ የሚደረገው የንግድ ልውውጥኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋዋን ገልፃለች፡፡
ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ህይወት ገብሩ እንደምትለው ግማሽ የቤተሰቧ አካል ከወዲያ ማዶ የጋረደው መጋረጃ መቀደዱ ለበርካታ ቤተሰቦች ዳግም መገናኛ ሆኗል፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት ያላየቻቸው ቤተሰቦቿም ዳግም ልታገኝ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብም ሆነ በድንበር የተከለለው ኤርትራ ህዝብ አንድ ቋንቋን ተናጋሪና ባህሉንም የሚጋራ በመሆኑ የሚደረገው እርቅ ለቀጣይ ግንኙነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ከኤርትራ አስመራም ከመጣች አምስት ዓመታትን እንዳስቆጠረች የምትናገረው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ቃሊቲ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወ/ት ሜሮን ግርማ ናት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችበት ሁኔታም እጅግ አስከፊ እንደነበር አስታውሳለች፡፡ አንድ የሆኑ ነገር ግን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የተለያዩት እነዚህ ሁለት ህዝቦች ለዓመታት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ መቅረታቸውንም ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የሰላም ሂደት ዳግም ሁለቱን ህዝቦች የሚያገናኝና ወደ እድገት ጎዳና ሽቅብ የሚያወጣ መሰላል መሆኑንም ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረው የዕርቅ ሂደት አስመልክቶ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሚሊየም አዳራሽ የተዘጋጀው ህዝባዊ አቀባበል ለኢትዮ- ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የቆዩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች እውቅ ሰዎች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች አልፏል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሰላምን አስመልክቶ ፀሎት ያደረጉ ሲሆን፤ ሰላምን የሚሰብኩ የተለያዩ ዜማዎችም ቀርበዋል፡፡ 
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመርን ጉዳይ ነው፡፡ እውነትና ፍቅር ከምንም በላይ ነው ያሉት ዶክተር አብይ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያደረግነው ግንኙነት ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም ብለዋል፡፡
ከጀብዳዊ ጭካኔ ይልቅ ሰላም፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከመከፋፈል ይልቅ መሳሳብ ስለመረጣችሁ ዝቅ ብዬ አመሰግናለሁ ሲሉም ታዳሚውን አመስግነዋል፡፡ ጤናና ሰላም በእጅ ሲሆኑ ርካሽ የሚመስሉን ስናጣቸው ግን በምንም ዋጋ የማናገኛቸው ውድ ሃብቶች በመሆናቸው ልንንከባከባቸው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ 
ሰላም የብልፅግና እናት ናት ያሉት ዶክተር አብይ ከሰላምና ነፃነት ውጪ ብልፅግና ከንቱ ነውም ብለዋል፡፡ ስለህብረ ብሄራዊ አንድነትም ሲናገሩ «ልዩነት ካወቅንበትና ከተጠቀምንበት ጠቃሚ ነው፤ ሰበቃ የሁለት ድንጋይ ፍጭት ውጤት ነው» ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ችግር ለምን ተፈጠረ ሳይሆን ችግርን የምንፈታበት መንገድ መሰረታዊ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ ከሰላም የሚገኘውን ትርፍ ለመቋደስ ግጭት እንዳይፈጠር ሳይሆን ግጭት ሲፈጠር የምንፈታበትን ጥበብ ልንላበስ ይገባልም ሲሉ አክለዋል፡፡
ይቅር ባይነት ደግሞ ከሚመጣው ኪሳራ ስለሚጠብቀን ጥላቻና ክፋትን ከውስጣችን አውጥተን ይቅር ልንባባል ግድ ይለናል ያሉት ዶክተር አብይ ሀገር እንደሰው በመሆኗ እኛ ይቅር ስንባባል ሀገርም ይቅር ትለናለች፣ ስንፋቀር አቅፋ ትይዘናለች ብለዋል፡፡
የእኛ የመደመር ስሌት የመጀመርያው ምዕራፍም የጥላቻን ግንብ ማፍረስ ነው ያሉት ዶክተር አብይ «እኔና አንተ፣ እኔና አንቺ ስንደመር እኛ እንሆናለን» ሲሉም ገልጸውታል፡፡ በእኛ የመደመር መርህም በደል፣ ቂም፣ ክፋት፣ ጥላቻ፣ ስንፍና፣ ቀማኛነት፣ አገርን አለመውደድ የሚቀነሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በመደመር ስሌት ውስጥም የሚካፈሉ ነገሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ፍቅር፣ ጥበብና ነዋይ እንዲሁም ኀዘን ናቸው ሲሉም ገልፀዋል፡፤
«እኛ ከኔ ይልቃል» ያሉት ዶክተር አብይ «ኢትዮጵያና ኤርትራ ለየብቻ ግንጥል ጌጦች ናቸው፤ ሲደመሩ ግን ለአፍሪካ ቀንድና ለመላ አፍሪካ ፈርጥ ናቸው፤ ኢትዮጵና ኤርትራን ለመለያየት የሚችል አንዳችም ኃይል የለም፤ ለውጡንም ሊያቆም የሚችል አንዳች የሞት ሃይል የለም፤» ሲሉም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ አንዴ ካመለጠን ዋጋ ያስከፍላል፣ እንዳያመልጠን ተደምረን ዘብ ልንቆም ይገባልም ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው በአማርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር ያለፈው ጥላቻና የቂም በቀል ባህላችን ተወግዶ በሁሉም መስክና ግንባራት ልማት፣ ብልፅግና እና መረዳዳት ይዘን አብረን ለመጓዝ ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል፡፡ ፍቅራችንን የሚሸረሽር እና እድገታችንን የሚፈታተን አንዳችም ኃይል አንፈልግም፤ በጋራ ጥረታችን የከሰርነውን አስመልሰን ለመጪው ጊዜ መልካም ሥራ ሠርተን እንደምናሸንፍ እርግጠኖች ነን ብለዋል፡፡

ዜና ሐተታ – ፍዮሪ ተወልደ addiszemen

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *