“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጠ/ሚ አብይ በውጭ ምንዛሬ ክምችትና በጸጥታ ጉዳይ ጥብቅ መመሪያ አስተላለፉ፤ መከላከያ ሰራዊት ታዘዘ

” አልተነገረንም እንዳትሉ ነው” ሲሉ ነው ክፍተኛ የገንዘብና የውጭ ምንዛሬ ክምችት ያላቸውን ያሳሰቡትና የመከሩት። እጅግ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ከፊት ለፊት መኖሩን በመጠቆም፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ምንዛሬ ወደ አገር እንደሚገባ በማመላከት በግል ዶላር ያከማቹ ወደ ባንኮች በመሄድ ራሳቸውን ከኪሳራ እንዲጠብቁ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያስጠነቀቁት። 

የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ከሸኙ በሁዋላ በደቂቃዎች ልዩነት በቀጥታ ባስተላለፉት የምስጋና መልዕክት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ጉዳዮች ላይ አጠንክረው ተናገረዋል። በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ድንበሮች ላይ በርካታ ዜጎች በተደጋጋሚ ህይወታቸው ማለፉን፣ በደቡብና ቦታውን በስም ሳይጠሩ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲሉ በገለጹዋቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት ህገ መንግስታዊ አደራውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲወጣ አዘዋል።

ሃዘን በተሞላበት ስሜት ትዕዛዝ ያስተላለፉት ዶክተር አብይ ከትዕዛዙ ጎን ለጎን ይህ በጥቂት ሰዎች ክብሪትና ቤንዚን አቀባይነት የሚከናወነው ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቆም ደም የጠማቸው አካላት መጠቀሚያ የሚሆኑ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ መክረዋል። ዘክረዋል። ለምነዋል። ሁሌም እንደሚሉት ይህ አካሄድ ስለማይጠቅም የሚጠቅመንን የሰላምና የፍቅር መንገድ መከተል እንደሚያዋጣ ወትውተዋል።

የከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ድል ብስራት ለ”ሕዝባቸው” ካሰሙና “ሕዝባቸውን” በምስጋና ካከበሩ በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከፋፍሎ ማጣላት የኖርንበት ነው። አልጠቀመንም” ሲሉ ይህ አብሮ ለዘመናት የኖረን ህዝብ እሳትና ቤንዚን እያቀበሉ የሚያጋድሉትን ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ለምነዋል። ስለማይጠም ” ተውት” ሲሉም ተማጽነዋል። ” ለመግደል አንደመርም” ሲሉ በሜሊኒየም አዳራሽ የተናገሩት ዶክተር አብይ ይህ ክፉ አካሄድ እንዲቆም መማጸን የጀመሩት ወደ ሃላፊነት ከመጡ ማግስት ጀምሮ መሆኑ አይዘነጋም። 

ከዚህ ሁሉ ውትወታ በሁዋላ የመከላከያ ሰራዊት አገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ሲያዙ የተለመደው ፈገግታ አይታይባቸውም ነበር። ያም ሆኖ የመከላከያ ሰራዊት ንጹሃን ሳይሞቱና ሳይቆስሉ፣ እጅግ ሙያዊ ጥበብ በተሞላበት፣ በስልትና በማስተዋል የምረጋጋቱን ስራ እንዲሰራ አብዝተው አሳስበዋል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በተደጋጋሚ እየወሰደ ያለው ጥቃት፣ በመተማ አቅጣጫ የሰሜን ሱዳን ወታደሮች የሚከፍቱት ግጭት፣ በጌዲዮ ህዝብ ላይ የደረሰው መፈናቀል፣ በሲዳማ የተከሰተው ከፍተኛ የርስ በርስ ግጭት ቀና አሳቢ ዜጎችን ያሳዘነ፣ ያስኮረፈና እልህ ውስጥ የከተተ ክስተት ሲሆን፣ አብዛኞች የህግ የበላይነት እንዲከበር ጥያቄ ያቀረቡበት ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው ያነሱት የውጭ ምንዛሬ ጉዳይን ነው። በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ ስለሚገባ በግል ቤታቸው የውጭ ምንዛሬ ያከማቹ በቀጥታ ወደ ባንኮች በመሄድ እንዲመነዝሩ መክረዋል። ” አልተነገረንም እንዳትሉ” ሲሉ እንዳስታወቁት አሁን ዋጋው እየረከሰ ያለው ዶላር ይበልጥ እንደሚረክስ በማሰብ ወደ ባንክ እንዲሄዱና እንዲመነዝሩ ዶላሩ ላላቸው ሲመክሩ አይይዘውም ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ያላቸውም በተመሳሳይ ብራቸውን ወደ ባንክ እንዲያዘዋውሩ መክረዋል።

በቅርቡ ይህንን የገንዘብ ክምችት የሚያጠራ ኦፕሬሽን እንደሚካሄድ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚስትር አብይ፣ ክፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይዘው ወደ ባንክ የሚመጡ ክፍሎችን ባንኮች ያለምንም ማንገራገር እንዲያስተናግዷቸው አዘዋል። ይጀመራል ስላሉት ኦፕሬሽን ግን ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።

ጠቅላይ ሚኒስሩ እግረ መንገዳቸውን መሐሙድ አህመድንና አሊ ቢራን ህመማቸውን ችለው ላበረከቱት ኢላማውን የመታ ድንቅ ስራ  ስም ጠርተው ከልብ አመስግነዋል። አያይዘውም አርቲስቶች ሙያቸውንና ታዋቂነታቸውን ተጠቅመው ወደ ፍቅርና ሰላም የሚወስድ ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ መክረዋል። በውቅቱ በቀጥታ ስርጭት እንደታየው አንዳንድ መዘላበድና ትርጉም የሌለው ከዝግጅቱ ጋር የማይሄዱ ሃሳቦች ከአንዳንድ አርቲስቶች መሰማቱ በርካቶችን ያበሳጨና ዓላማውን የሳተ መሆኑንን ለመገንዘብ ተችሏል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካው መስክ ከፍተኛ የተባለ ስምምነት ማድረጋቸውን ያስታወቁት ዶክተር አብይ፣ ሁለቱ አገራት በጸጥታ ጉዳይ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። 

ባልተለመደ ሁኔታ ደስታቸውን ሲገልጹ የታዩት ኢሳያስ በአማርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር አሁን የተጀመረውን ፍቅርና ሰላም ማንም አይቀለብሰውም ሲሉ መናገራቸው የተጀመረው የሰላም ንግግር ከድርድር አልፎ አንዱ ሌላውን የመጠበቅና የመንከባከብ ደረጃ የደረሰ መሆኑን አመላክች እንደሆነ ነው። 

በሃዋሳ ባደረጉት ንግግር ” አንተ ምራን፤ መሪያችን ነህ” እስከማለት የደረሱት ወዲ አፉወርቂ አድሮ ይፋ የሚሆን የሁለቱንም አገር ህዝብ የሚያስተሳስር ስምምነቶችን ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

ይህ የዓለም ታላላቅ አገራትን አድናቆት የሳበና ያስደነቀ፣ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ የሚደረግለት ታሪካዊ የሰላም መንገድ የጎናጸፈርው የደስታ ስሜት የሚያንገበግባቸው ክፍሎች ይህን አንጸባራቂ ድል ለማንቋሸሽ ሲሞክሩ ይታያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ክብሪትና ቤንዚን በማቅረብ አገሪቱ እንድትተራመስ እየሰሩ ነው። አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ” በጀት የሚመድቡ ክፍሎች” ናቸው። 

በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ ልብ ውስጥ የነገሱት፣ ምስላቸው በያንዳንዱ ቤት የተሰቀል፣ ህዝብ በልቡ ብቻ ሳይሆን በደረቱ ላይ ከፍ ያደረጋቸው፣ በቢሮውና በመኪኖቹ ውስጥ የማይለያቸው፣ ንግግሮቻቸውን ደጋግሞ እየሰማ ያከበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን ህዝብ ” ሕዝቤ” ሲሉ ደጋግመው በመጥራት እምነታቸውን በየቀኑ እያጸኑ ነው። ለዚህም ይመስላል ከጀመሩት እንቅስቃሴ አንጻር፣ ከማይወዷቸው ክፍሎች ክፋት ብዛት ዜጎች የሚሰጉላቸው። የሚጸልዩላቸው። በህብረት ሆነው በጾም ጸሎት የሚያነቡላቸው። ይህንን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ” አንድ አብይ ቢሞት መቶ ሚሊዮን አብዮች አሉ” ሲሉ ህዝባቸው እንዳይሰጋ ለማጽናናት የሞከሩት። 

” የለውጥ አራማጅ ይሞታል እንጂ፣ ለውጥና የለውጥ ሃሳብ” አይሞትም ሲል የተሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋግመው እንዳሉት ህዝብ ከስሜት በመራቅ ከተራ ጥላቻና የጅምላ ፍረጃ ተላቆ ሁሌም የተጀመረዉ ለውጥ እንዳይጨናገፍ መትጋት ይገባዋል። 

 
 
 
 
 

0Shares
0