“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአድሎ የተፈተነው የሸቀጦች አቅርቦት

ሰዓቷ ደርሶ ሸቀጦቹን የምትሸጠው ሴት በቦታዋ ላይ እንደደረሰች ‹‹የመጣው ሸቀጥ አነስተኛ ስለሆነ አብዛኛው ለመንግሥት ሠራተኛ ብቻ ነው የሚሰጠው›› በማለት አስቀድማ ተናገረች፡፡ በዚህም ነዋሪው ቅር የተሰኘ ቢሆንም መለወጥ የሚችለው ነገር ባለመኖሩ ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛው ሸቀጦቹን በወቅቱ ሳያገኝ ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ አሁን አሁንማ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ሻጮችና ውክልና የተሰጣቸው ሱቆች ለመንግሥት ሠራተኞች ነው ቅድሚያ የሚሰጠው በሚል ምክንያት ዘይትም ሆነ ሌሎች ሸቀጦች እያሉ ለነዋሪው ሳይሸጡ ማስቀመጥ የየቀን ክንውን እየሆነ ነው፡፡

በአንጻሩ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የፌዴራል ቢሮዎችን ከአለ በጅምላ እንዲሁም በከተማዋ ክፍለ ከተሞችና በወረዳ ቢሮዎች የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞችን ደግሞ በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ የሸማች ማህበራት ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም በፌዴራልና በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች አገልግሎቱን እንዲያገኙ መሥሪያ ቤቶቹ የሠራተኞቹን ስም ዝርዝር ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመላክ እንዲመዘገቡ እየተደረገ ነው፡፡ የተዘረጋው አሰራርም የተመዘገቡ ሠራተኞች በሚፈልጉት መጠን በየጊዜው አገልግሎቱን በመሥሪያ ቤታቸው እንዲያገኙ የሚያስችል አገልግሎት እንደጀመሩ ይታወቃል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛው ከአቅራቢያው በሚገኝ ሸማች ማህበራት ሸቀጦች እንዲገዛ ሲደረግ የአካባቢውን ነዋሪ ሳይጎዳ ቢሆንም በተግባር የታየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ለማረጋጋት በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች ቢሆንም መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ አለመሆኑም ይነገራል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወርቅነሽ ገብሬ እንደሚናገሩት፤ በአዲስ አበባ የሚታየውን የሸቀጦች ዋጋ መጨመርና ብሎም የሸቀጦች መጥፋትን ለመቆጣጠር ሸማች ህብረት ማህበራት እንዲመሰረቱ ተደርጓል፡፡ ማህበራቱ የተመሰረቱት በህብረተሰቡ እንደመሆኑ ቅድሚያ ማገልገል ያለባቸው ህብረተሰቡን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት አካባቢ ግን ለህብረተሰቡ ሸቀጦችን ከመስጠት ይልቅ ለመንግሥት ሠራተኛው የማድላት ሁኔታዎች መኖራቸውን ወይዘሮዋ ይናገራሉ፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኛው ከአቅራቢያው ከሚገኘው ሸማች ማህበር ሸቀጥ የመግዛት መብት አለው በሚል ቅድሚያ የሚገዛ በመሆኑ ደግሞ ህብረተሰቡን እየተጎዳ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

በአድሎ የተፈተነው የሸቀጦች አቅርቦት
እየተስተዋሉ ያሉት ችግሮች መፍታት ካልተቻለ በቀጣይ ነዋሪው ከሸማች ማህበራት ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንደሚያሳጣውም ነው ወይዘሮ ወርቅነሽ ስጋታቸውን የሚገልጹት፡፡ በመሆኑም በሸማች ማህበራት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችና ውክልና ተሰጥቷቸው የሚሸጡ ሱቆችም ለነዋሪው ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አቶ መቆያ ተሾመ፣ በየካ ክፍለከተማ ሾላ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የሸማች ማህበራት ለመንግሥት ሠራተኛው በመተዋወቅ ብቻ እንደሚሸጡ የተናገሩ ሲሆን፤ በተለይ በወረዳዎችና በክፍለ ከተሞች አካባቢ እንደሚስተዋል ያመለክታሉ፡፡ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በህብረተሰቡ እንደ መመስረታቸው ሸቀጦች ሲመጡ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለነዋሪው መሆን እንደነበረበት ይናገራሉ፡፡ 
በከተማዋ በሚስተዋለው የሸቀጦች ዋጋ ንረት ምክንያትም፣ ከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኛው ከአቅራቢያው ተጠቃሚ ይሁን ሲባል የአካባቢውን ነዋሪ በሚጎዳ መልክ መሠራት የለበትም ይላሉ፡፡ ውክልና ተሰጥቷቸው በየአካባቢው ሸቀጦችን ለህብረተሰቡ የሚሸጡ ሱቆች አገልግሎት አሰጣጣቸው መፈተሽ እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አሰበ መኮንን እንደሚለው፤ በወረዳ አካባቢ የሚገኙ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ህብረተሰቡን ለማገልገል የተከፈቱ ቢሆንም ለመንግሥት ሠራተኛው የማድላት ሁኔታዎች አሉ፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው በሚኖርበት አካባቢና በመሥሪያ ቤቱ ሁለት ጊዜ ሸቀጦችን እየገዛ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህም ነዋሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን እያጡ ነው፡፡
በክፍለከተማና በወረዳዎች አካባቢ የሚገኙ ሸማች ማህበራት አሰራራቸውን ማስተካከልና መፈተሸ አለባቸው የሚለው ወጣት አሰበ፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች አካባቢ የሚታዩ ክፍተቶችም ሊታረሙ እንደሚገባ ይገልፃል፡፡ በአዲስ አበባ የሚታየውን የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ለማረጋጋት የታሰቡት ሸማች ማህበራትም ቅድሚያ ለነዋሪው የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግብይት ተሳታፊነትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ እንደሚሉት፤ በየወረዳው የሚገኘው የመንግሥት ሠራተኛ ውስን ነው፡፡ የሚመጣው ኮታ ለመንግሥት ሠራተኛውም ለነዋሪውም እኩል ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚነሳው ቅሬታም ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ለመንግሥት ሠራተኛው እንደማንኛውም ነዋሪ ነው እየተሰጠው ያለው፡፡
በየአስራ አምስት ቀኑ ለመንግሥት ሠራተኛውና ለህብረተሰቡ እኩል እንዲከፋፈሉ እንደሚደረግ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ የመንግሥት ሠራተኛው ሙሉቀን በሥራ ላይ የሚያሳልፍ በመሆኑ አስፈላጊ ምርት እንዲገዛ አቅራቢያው ካለው ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት እንዲወስድ የማድረግ ሥራ መጀመሩን ያመለክታሉ፡፡
ሸማች ህብረት ሥራ ማህበሩ ምርት ሲያመጣ በቀጥታ ለሱቆች የሚያከፋፍል ሲሆን፤ ህብረተሰቡ በአካባቢው ከሚገኘው ሱቅ በመሄድ ምርቶችን እየገዛ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ በአሁን ወቅትም የምርት መቆራረጥ፣ በወቅቱ አለመምጣትና ስርጭቱ ቀጥተኛ ያለመሆን ነገሮችን ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን በመግለጽም፤ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ በመፈተሽ ማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ይጠቁማሉ፡፡

ዜና ሐተታ መርድ ክፍሉ   addiszemen

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የትግራይ ክልል ባቀረበው ፍላጎት መሠረት የአፈር ማዳበሪያ መቶ በመቶ እንዲቀርብ መደረጉ ተገለጸ
0Shares
0