ፍቄን የብሔራዊ ቴአትር ቤተኛ ከመሆኔ 1989 በፊት ነው የማውቀው፡፡ በሩቁ፡፡ በአድናቆት፡፡ በፍቅር፡፡ በጣም በፍቅር የምወደው እሱን ለመተካት የምመኘው ሰው ነበር፡፡ ያኔ፡፡


ድምፁ ፣ እርጋታው ፣ የመድረክ አጠቃቀም ብቃቱ ፣በሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ ድራማ ከነጀማነሽ ሰሎሞን ጋ ሲሠራ የነበረው የአተዋወን ብቃት ፤ እሑድ ምሽትና በድጋሚ ሰኞ ጠዋት ከመጽሐፍት ዓለም ፕሮግራም ላይ ይተርካቸው የነበሩ መጽሐፍት የገጸ-ባሕሪያቱ ድምፁጽግርማ ሞገሱ ለፍቄ ልዩ ቦታ እንድሰጠው አድርጎኛል፡፡
በሚተውንባቸው ቴአትሮች አብዛኛውን ጊዜ የንጉሥ ገጸ-ባሕሪ አልያም መሪ ተዋናይ ሆኖ መጫወቱ ብዙዎች እንዲያውቁት ሆኗል፡ ፡ ከአንድም አራት ዐሥርት ዓመታት ተሻግሮ ዕውቅናው ያልደበዘዘ ክብሩ ያልቀዘቀዘ ፤ ሁሌም ደረጃውን እንደጠበቀ ያለ ተዋናይ ነበር፡፡

ፈርጥ መጽሔት ሰኔ 1994 ላይ የወቅቱ ተሸላሚዎችን ታሪክና ብቃት በመጥቀስ ለአንባቢያን አቅርቧቸው ነበር፡፡ እኛም ፍቃዱ ተ/ማርያምን ከምንጫችን በጥቂቱ እነሆ፡፡

Top 5 Dating Sites With Only The Prettiest Profiles

የ1994 የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት በተዋንያን ዘርፍ ተሸላሚው ፍቃዱ ተ/ማርያም የተወለደው ጥቅምት 1 ቀን 1948 ነበር ፡፡ ይህ ዓመት ብሔራዊ ቴአትር የተከፈተበት ዓመት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ዛሬ የ62 ዓመት (ላስረጀው ከበደኝ) አንጋፋ ተዋናይ አዲስ አበባ፣ አራት ኪሎ ፣ባሻ ወልዴ ችሎት ፣ጅሩ ሰፈር ነው የተወለደው፡፡ ዛሬ ሰፈሩ ለልማት ፈርሶ ወይ አልለማ ወይ አልኖሩበት በቆርቆሮ ታጥሮ የውሻ መፈንጪያ ሆኗል፡፡

የተማረው ፦ ኢዮቤልዮ ቤተመንግሥት ፣ዑራኤል ት/ቤት ፣ ኮከበ ጽባህ ፣ ዳግማዊ ምኒልክ ነው፡፡ በ1976 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር ጥበባት ክፍል ይሰጥ የነበረውን ልዩ የቴአትር ትምህርት ለሁለት ዓመት ተኩል ተከታትሏል፡፡ ከ10 ዓመታት በፊትም በማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

በልጅነቱ ለፊልም ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ አራት ኪሎ ወወክማም ይሳተፍ ነበር፡፡ አንድ ቀን ትሩፋት ወ/የስን ያገኛትና አድናቆቱን ገልጾ ቴአትር መሥራት እንደሚወድ ይነገራታል፡፡ እሷም ሀገር ፍቅር የቴአትር ዕድገት ክበብ መሥራች ከሆኑት ከአቶ ተስፋዬ አበበ ጋ አገናኘችው፡፡ (ይሄ ማለት 1965 ነው) እዚያ ዝነኞቹን እነ ወጋየሁ ንጋቱ ፣ደበበ እሸቱን ፣ተክሌ ደስታን ሲራክ ታደሰን ፣ዓለሙ ገ/አብ ፣ዓለም ፀሐይ ወዳጆን ያገኛቸዋል፡፡ እነዚህን የዘመኑን ዝነኞች ማግኘት ምን ዓይነት የደስታ ስሜት እንደሚሰማ አማተር የጥበብ ሰው በደንብ ያውቀዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ ፍቄ ማዘጋጃ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ተቀጠረ፡፡ መቼ እንደሆነ ባላውቅም (1980ዎቹ ውስጥ ይመስለኛል) ወደ ብሔራዊ ቴአትር ተዘዋወረ፡፡

በፕሮፌሽናል መድረክ የመጀመሪያ ሥራው ባለካባና ባለዳባ የመንግሥቱ ለማ ድርሰትን ነበር፡፡ ይህንን ድርሰት ከረጅም ዓመታት በኋላም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ በብቃት ሲጫወተው ተመልክቻለሁ፡፡

በ1968 በአያልነህ ሙላት ተደርሶ በአባተ መኩሪያ የተዘጋጀውን “እሳት ሲነድ” ቴአትርን ገና በ20 ዓመቱ በመሪ ተዋናይነት ለመጫወት በቃ፡፡ ፍቃዱ ባለፉት ድፍን 44 የቴአትር ዓመቱ በበርካታ ቴአትሮች ፣የቴሌቪዥን ድራማዎች ፣ የመጽሐፍት ትረካዎች ፣ ፊልሞች የሬዲዮ ድራማዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከተሳተፈባቸው ቴአትሮች ጥቂቱ ፦

ግደይ ግደይ አለኝ ፦ መንግሥቱ ለማ
መቃብር ቆፋሪውና ሬሳ ሣጥን ሻጩ ፦ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ቤቱ ፦ ሥዩም ተፈራ
ሠርግና ዋዜማ ፦ ሥዩም ወልዴ
የጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኅን መልእክተ ወዛደር መቅድም
ኦቴሎ
ቴዎድሮስ የከርሞ ሰው
ታርቲዩፍ (ሞልየር)
ማክቤዝ
ሐምሌት
የሊስትሮ ኦፔራ ፦ አባተ መኩሪያ
ኤዲፐስ ንጉሥ ፦ዶ/ር ኃይሉ አርአያ
ዋዜማ (በጣም የወደድኩለት) ቴዎድሮስ
ተሰማና ጫንያለው ወ/ጊዮርጊስ
ንጉሥ አርማህ ፦ መልካሙ ዘሪሁን ይጠቀሳሉ፡፡

ከሠራቸው ቴአትሮች ከግማሽ በላዩን አይቼለታለሁ፡፡ በወቅቱ ፍቃዱ ቴአትር ሠርቶ አለማየት ያስተዛዝብ ነበር (1980-1999) ፍቄ የሠራቸውን ቴአትሮች እንደሚያስታውስም ሲናገር፦
“ጠለቅ ብሎ የገባሕን ነገር አትረሳውም፡፡ የጸጋዬ ገ/መድኅን የከርሞ ሰውን ፣ የመንግሥቱ ለማ “ባለካባና ባለዳባን” አልረሳቸውም፡፡ እንደገና ይሠሩ ቢባል ትንሽ ንባብ ይበቃኛል፡፡ ቃለ ተውኔቶች የማልረሳበት ምክንያት ፍቅር ነው፡፡ ፍቅሩ ስላለኝ ሁልጊዜ ውስጤ ይኖራሉ፡፡

“የከርሞ ሰው” የራሳችን ታሪክ ነው፡፡ ሰፈሩ ቁጭራ ነው፡፡ አሜሪካን ድረስ ሠርተነዋል፡፡ በቀለ ተፈራ አዘጋጅቶት እኔ ፣ሱራፌልና ሥዩም ሆነን እዚህ ሠርተነዋል፡፡ ተውኔቱ አልቆ ሰዓት ስንመለከት እስከ አራት ሰዓት እንጫወተው ነበር፡፡ በኋላ ሲታይ ለካ ሦስታችንም እንወደዋለን፡፡ በቃ ስንታመምበት ፣ስንታሽበት እንውላለን፡፡ የምር የምር ነበር የምንጫወተው”

ፍቃዱ በ45 የቴአትር ዓመቱ (ከ1965 እስከዛሬ) ስለጻፈው ተውኔት ወይም ስላዘጋጀው ቴአትር የሰማሁት ነገር የለም፡፡ እንደ ባልደረቦቹ ገለጻ ፍቃዱ ቴአትር የማያዘጋጀው እጅግ ትሁት በመሆኑ ፤ በቴአትር ዝግጅት ወቅት ደግሞ መጎሻሸም ስለማይታጣ ያንን በመሸሽ ነው፡፡

ፍቄ ለሚዲያም እንደ ሌሎቹ አክተሮች ቅርብ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ ለቃለ መጠይቅ ፈልገውት ያልተቀበላቸው ጋዜጠኞች በአንድ ወቅት የተሳሳተ ነገር በመጻፋቸው መቆጣቱንና ቁጣውንም “አንበሳው አገሳ” በሚል በሳምንቱ መጻፋቸውን አስታውሳለሁ፡፡
ሽልማት ፦ የፍቄ ትልቁ ሽልማት ሥራዎቹን ያዩ ሁሉ ያለ ልዩነት እሱን መውደዳቸው ነው፣ሌላው የሥነጥበባትና መገናኛ ብዙኃን የወቅቱ ተሸላሚ መሆኑ ፣ በአንድ ወቅት በሠራው ፊልም የመኪና ተሸላሚ መሆኑ…..
“የፍቃዱ ትልቅ ሀብቱ ድምፁ ነው። የማይሰለች ድምፅ አለው ፡፡ ይህን ጣፋጭ ድምፁን አዳራሽ ውስጥ ፊት እና ኋላ የተቀመጠ ሰው እኩል ይሰማዋል ፡፡አይጮህም፡፡….እያንዳንዱ የሚናገረው ቃል ይሰማል፡፡ በዚህ ላይ በጣም ዲሲፒሊንድ ነው፡፡ ችግር አጋጥሞት ልምምድ ላይ የሚያረፍድ ከሆነ ደውሎ ይናገራል፡፡ ሥራው ላይ በጣም ሲሪየስ ነው፡፡”
ማንያዘዋል እንደሻው፡፡
“ለሕዝቡ ሊሰጥ የሚገባውን ነገር በሙሉ ይሰጣል፡፡ ቴዎድሮስ ቴአትር በጣም ብዙ ለሆኑ ተመልካቾች ሜዳ ላይ ተሠርቷል፡፡ በእንዲህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በአግባቡ ይሠራ ነበር፡፡”

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *