ኢትዮጵያን ለማዳን፤ እንደ ሐገርና ሕዝብ እንዳንጠፋ እንደመር!

እውነትን ስፈልግ ነበር:: እውነትን አልተደበቀችም:: እውነትን የደበቋት እኔው ነበርኩ:: የጠፋብኝ እውነት አልነበረም:: የጠፋብኝ እውነትን የማረጋግጥበት ማስረጃ ነበር:: እውነትንና እውነተኛ ማስረጃ በልቤ ውስጥ አገኘሁ:: ማስረጃዬም ጠ/ሚ አቢይ አህመድና ፕ/ት ለማ መገርሣ እንዲሁም ቡድናቸው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው:: ይህ ገባኝ:: እነርሱ ለኢትዮጲያና ለኢትዮጵያውያን ጥቅም የቆሙ ኢትዮጵያውያን ካልሆኑ እኔም ኢትዮጵያዊ አይደለሁም::

“ፈጣሪ ሚሊዮን ፋኖሶችን ይዞ በሚሊዮን ሰዎች መካከል ቢቆም ሊያዩት የሚችሉት እውነትን በልባቸው ባኖሩ ጥቂቶች ብቻ ነው:: እውነት የምትታየው በውስጣቸው እውነትን በያዙ ሰዎች ነው:: በልቡ ውስጥ እውነትን ያልያዘ ሁሌም እውነትን ለማየት ይታወራል”
(ሱዚ ቃሲም)

“If the Creator stood before a million men with the light of a million lamps, only a few would truly see him because truth is already alive in their hearts. Truth can only be seen by those with truth in them. He who does not have Truth in his heart, will always be blind to her.”

[‘Rise Up and Salute the Sun’, Suzy Kassem]

” በአገሩ ላይ ማንም ኢትዮጵያዊ መጤ አይደለም። አገሩ ነው:: የትም ይሁን የት፣ ሁላችንም የተለያየ ስም፣ የተለያየ መልክ ሊኖረን ይችላል።ነገር ግን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን!”
(ፕ/ት ለማ መገርሣ)

“ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት ስትልኩ ከፊደል ጋር ኢትዮጵያዊነትን አስተምሩ”
(ጠ/ሚ አቢይ አህመድ)

ይህን አባባላቸውን አሁን አምኛለሁ:: እውነት ለኔ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው:: ይህ ቡድን ዴሞክራሲያዊ አይደለም:: ኢትዮጵያዊ ግን ነው:: ለኢትዮጵያ መኖርና ዴሞክራሲያዊ መሆን፤ ኢትዮጵያ ላይ ካንጃበበው የመበታተን አደጋን የምንቀለብሰውና ልንሞክረው የሚገባን ብቸኛ መንገድ ነው:: ኢትዮጵያን ለማፍረስና ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ብለው ከሚሰሩ አፍራሽ ሃይሎች መዳኛ መንገድ ነው:: እኔ ከዚህ ቡድን ጋር በይፋና በምክንያታዊነት ተደምሬያለሁ::

ኢትዮጵያዊነቴንና ኢትዮጵያን ለመቀነስ ከተሰለፉ ሃይሎች ለመከላከል ‘መደመር’ ብቸኛ ምርጫም እንደሆነ አምኛለሁ:: የኢትዮጵያንና ህዝቧን ህልውና አደጋ ከመውደቁ በፊት መፍትሄው ይህን ቡድን በመደገፍ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት እንዲያሻግረን መታገል መርጣለሁ:: ‘መደመር’ የመርህ አንድነት እንጂ የሃሣብ ውህደት እንዳልሆነ እረዳለሁ:: ‘መደመር’ አምልኮ ሣይሆን አንድነት ነው:: አንድነት ለጋራ ግብ እንጂ ውህደትም አይደለም::

በብሔረተኝነትም ይሁን በአንድነት ድርጅቶች የተሰለፉና የኢትዮጵያን መፈረካከስ የማይፈልጉ ሁሉ ከመደመርና መብትና ነፃነትን በድምሩ ውስጥ ለማግኘት ከመታገል ውጭ ምርጫም የለም:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት(እ.አአ.1939-1945) ኮሚኒዝምና ካፒታሊዝም ፋሺዝምንና ናዚዝምን ድል የነሱት ልዩነታቸውን አቻችለው አብረው በመደመራቸው ነው:: መደመራቸው ሃይል ስለሆናቸው ነው። ይህ ሃገርኛ ብሂል አለን “ድር ቢያብር አንበሣ ያስር (when spiders unite, they tie down lion)”.

ኢትዮጵያ ከውልደቷ ጀምሮ ነፃ የሆነች ሐገር ናት:: የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከውልደቱ አንስቶ የነፃነትን ፍሬ እንኳን ለመብላት ለማሽተት አልቻለም:: ይህ የሆነው በጨቋኝ ስርዐትና መንግስታት ጫና ብቻ ሣይሆን እራሣቸውን ነፃ ሳያወጡ ነፃ ሊያወጧት በሚሞክሩ ልጆቿ መናቆርና አለመግባባትም ነው:: ልጆቿ አንድ በሚያደርጋቸው የጋራ የወንድማማችነት እሴት ላይ ሣይሆን ባላቸው የተለያየ ስምና መጠሪያ ብዛት የሚለካና ከጊዜና ከሁኔታዎች መለዋወጥ ጋር የማይቀየር የፓለቲካ አስተሳሰብ ይዘው እርስ በርስ መናቆርን በመምረጣቸው ለጠላቶችና ጨቋኝ መንግስታት ከፋፍለህ ግዛ ፓሊሲ ተጋላጭ በመሆናቸው ነው:: ከእውነታ ይልቅ የታሪክ እስረኛ ስለሆኑ ነው:: አይምሮ-ወለድ ፅንሠ-ሃሣባዊ ግንዛቤያቸውን ከእውነታ ጋር ማዛመድ በመቸገራቸው ነው:: ባጭሩ የግል: የቡድን: የፆታና ሃይማኖትእኩልነት የሚረጋገጥበትንና የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዐት በመፍትሄነት ለመቀበል በማመንታታቸው ነው:: መብትና ነፃነት የራቃችው በእኩይ ገዢዎች ጠንካራ መዳፍ ብቻ ሣይሆን ለነፃነታቸው በአንድነት መቆምና በጋራ መታገል ዳገት ሆኖባቸው ነው:: ፅንፈኛና የማይታረቁ ቅራኔዎችን እየመዘዙ ለልዩነት ምክንያት በማድረግ ነው:: ከድርድር ይልቅ ፍጥጫን፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ናፋቂ እየሆኑ ነው:: የቁጥር አናሳ አግላይ አፓርታይዳዊ ወይም በብዝሃን ቁጥር ላይ የሚዘወር ‘የብዝሃን አምባገነንነትን’ በመከጀላቸው ነው:: ምንነታቸውን የማይጋፋ በማንነታቸው የሚኮሩበትን ቡሲቪክ ብሔረተኝነት ላይ ለሚቀነቀን ዴሞክራሲያዊ ስርዐት እጅ መስጠት ባለመፈለጋቸው ነው:: ይህ አፍራሽ የአስተሳሰብ ዝንባሌ መቀጨት አለበት::

ኢትዮጵያና ህዝቧ የሚለሙትም ይሁን የሚጠፍት በልጆቿ ነው:: ኢትዮጵያና ልጆቿ የሚድኑት በኢትዮጵያዊነት ነው:: ፓለቲካ በጊዜ ይቀየራል:: ሐገርና ህዝብ ዘላለማዊ ናቸው::

ኢትዮጵያን በማፍረስ የህልም ሐገርን አንሠራም:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሞከር ይህን ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆነን ህዝብ በእርስ በርስ ጦርነት መማገድ ነው:: የህዝብ ዕልቂትን መፍቀድ ነው:: አንድነት እንዳለ ሁሉ ልዩነትም አለ:: ፍፁም አንድ የሆነ ሕዝብና ሐገርም የለም:: ልዩነትን ውበት አንድነትን ጥንካሬ ማድረግ የሚቻለው ለሁሉም እኩልነት ማረጋገጫና በሕዝብ፣ ለሕዝብና ከሕዝብ በተመረጠ መንግስት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት በመገንባትና ፍትሕና ነፃነትን በማስፈን ነው::

‘በዜግነት ላይ የተገነባ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት’

ኢትዮጵያን ‘በመደመር’ ካላዳንናት በመቀነስ እንበትናታለን!

የቀናሾችን ሤራ የምናመክነው በኢትዮጵያዊነት መደመርን ስንመርጥና ኢትዮጵያዊ ሃይል መሆን ስንችል ነው!

ኢትዮጵያውያን የቋንቋና የስም እንጂ የዘር ልዩነት የለንም!

በመደመር የፍትሕና የእኩልነት እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እንታገል!

ይህን የሩድያርድ ኪፕሊንግ አባባል እናስታውስ።

“የመንጋው ጥንካሬ የተኩላው መኖር፤ የተኩላውም ጥንካሬ የመንጋው መኖር ነው (The strength of the pack is the wolf, The strength of the wolf is the pack)”.

ይህ ማለት ለኢትዮጵያውያን ጥንካሬ ምክንያት የኢትዮጵያ መኖር፤ ለኢትዮጵያ ጥንካሬ ምክንያትም ለኢትዮጵያውያን መኖር ነው።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *