“Our true nationality is mankind.”H.G.

መከላከያ ጸጥታ እንዲያስከበር ታዘዘ፤ አብዲ ተነስቶ አዲስ መሪ ተሰየመ፤ ቤተክርስቲያን አወገዘች

ከሰውነት ደረጃ በወረደ መልኩ በውክልና በሶማሌ ክልል እየተካሄደ ያለውን አስነዋሪ ድርጊት እንዲስቆምና እንዲቆጣጠር የመከላከያ ሰራዊት በይፋ ትዕዛዝ ተሰጠው። አብዲ ኢሌ የሚባለው ቦዘኔ ተነስቶ በምትኩ የክልሉ ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ በሆኑት አቶ  አህመድ አብዲ ሞሃመድ ተሰይመዋል። ቤተክርስቲያን  ብክልሉ የተፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት አወገዘች።

መከላከያ መግባትና ሰላም ማስከበር፣ እንዲሁም የንጹሃንን ህይወት መታደጉ እግባብ እንዳልሆነና ህገ መንግስትን መናድ እንደሆነ በመግከጽ የትግራይ ክልል ቢቃወምም አብዲ በስተመጨረሻ ተወግዷል። ዛጎል አብዲ ትናት በቁጥጥር ስር ሆኖ አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎችን መስጠቱን መዝገቡ ይታወሳል። 

Image result for abdi iley and meles zenawi

ከትግራይ ክልል ጎን ለጎን የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር በተመሳሳይ አብዲ ኢሌን በመደገፍ መገለጫ አውጥቶ ነበር። በሶማሌ ክልል ቶርቸር፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስራት፣ ስቃይ ሲደርስባቸው የነበሩና እየተሰቃዩ ያሉት የኦብነግ አባላትና ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ሆኖ ሳለ ግንባሩ አብዲ ኢሌን ደግፎ መግለጫ ማውጣጡ አንጋጋሪ ሆኗል።

ፋና መከላከያ መታዘዙንና ቤትክርስቲያን ድርጊቱን ተቃውማ ያወጣችውን መግለጫ ተንተርሶ የሚከተለውን ዘግቧል።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ፥ የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የፀጥታ ሃይሉ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም የማስከበር ስራውን እንዲሰራ መታዘዙን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ፀጥታ የማስከበር ስራ እንደሚጀምር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል። ኃላፊ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ በነዋሪዎች ሲነሳ መቆየቱን ነው ያስታወቁት።

በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በታየው የፍቅርና የመደመር ሂደት ውስጥ እኛም እንካተት በሚል ጥያቄ ያነሱ የህዝብ ተወካዮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ በክልሉ መንግስት ጥቂት አመራሮች ሲደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።

“ስልጣን ልቀቅ ተብያለሁ፤ ስልጣኔን ከምለቅ ብሞት ይሻለኛል” በሚል ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበርም ነው ያነሱት። ያለ ክልሉ ነዋሪዎች ፈቃድና ይሁንታ “ክልሉን አስገነጥላለሁ” በማለት ከፍተኛ ውዥንብር በመፍጠር ኢ-ህገመንግስታዊ እና ሀላፊ ሚኒስትር አስነዋሪ ብለው የገለፁት ድርጊት ሲፈፀም ቆይቷል ብለዋል።

የሀገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ለመጣል እንዲሁም አካባቢው እንዳይረጋጋ የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን የማሰራጨት ተግባር ሲፈፀም ነበርም ብለዋል አቶ አህመድ። ስልጣኔን እነጠቃለሁ በሚል የክልሉ ልዩ ሀይልን ላልተቋቋመለት ዓላማ በማዋል መንገዶች ሲዘጉ ነበር በማለት ለአብነትም ከሀረር ጅግጅጋ እና ወደ ጅቡቲ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተው እንደነበር አንስተዋል።

በክልሉ በተለይም በጅግጅጋ ለተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የሰው ህይወት፣ የሀይማኖትና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል።

ዛሬ ላይ የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ በክልሉ የፀጥታ እና ህግን የማስከበር ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በደረሰው ጥፋት እጃቸው ያለበት ሰዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና የደረሰው ጥፋት ልክም ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ሀላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልፀዋል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጸመውን ድርጊት አወገዘች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ በክልሉ በተፈጸመው ድርጊት ሳቢያ የሰው ህይዎት በመጥፋቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ሰባት አብያተ ክርስትያናት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው የካህናት ህይዎት ማለፉንም ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም የሰላማዊ ሰዎች ህይዎት ማለፉንና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፥ በሁኔታው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

አሁን ላይ አብረው በኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባም ጠይቀዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም የተፈጠረው ችግር እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን እንደ ወትሮው ሁሉ ድጋፏን ታደርጋለች ብለዋል። ለተቸገሩ ወገኖችም ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመው፥ ህይዎታቸውን ላጡ ወገኖችም በሁሉም አድባራትና ገዳማት ፍትሃት ይደረጋልም ነው ያሉት።

ከዚህም በተጨማሪም ነገ የሚጀምረው የፍልሰታ ጾም በሁሉም አድባራት እና ገዳማት በምህላ እና በጸሎት እንደሚታሰብም አንስተዋል።

በዙፋን ካሳሁን እና በካሳዬ ወልዴ – ፋና ብሮድካስቲንግ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0